Friday, January 29, 2016

ዕረፍተ ድንግል



በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(ከመጽሐፈ ገጹ የተወሰደ)
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 20 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ይዞ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እመቤታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የሔደው የዕረፍቷ ጊዜ መድረሱን ለማብሠር ነበር፡፡ የድል ምልክት የሆነውን ፍሬው የተንዠረገገ የቴምር ፍሬ የሚያፈራውን ዘንባባ ይዞ ለሁለተኛ ጊዜ እርሷ ወዳለችበት ይዞ ገብቶ ደስ ይበልሽ ሲላት አሁንም እየሰገዳና እጅ እየነሣ ነበር፡፡ ጌታችን እንዳዘዘውም "ልጅሽና ጌታሽ እናቴ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ጊዜው ደርሷል ብሏል፡፡ ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ቅድስት ሆይ ስለዚህም ለሁለተኛ ጊዜ ይህን መልካም የምሥራች እነግረሽ ዘንድ ላከኝ፡፡ ብፅዕት ሆይ በምድር የሚኖሩትን ሁሉ በደስታ እንደሞላሻቸው አሁን ደግሞ በዕረፍትሽና በዕርገትሽ ምክንያት የሰማይ ኃይላት በደስታ ይሞሉ ዘንድ በሰማይ ያሉ ነፍሳትም ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በክብር ያበሩ ዘንድ ምክንያት ትሆኛለሽ፡፡ ደስተኛይቱ ፍስሕት የሚል ማዕረግ ለዘላለም ተስጥቶሻልና ስታዝኝና ስታለቅሽ በኖርሽው መጠን ደስ ይበልሽ፡፡ ጸሎቶችሽና አስተብቁዖቶችሽ በሙሉ በልጅሽ ፊት ወደ ሰማይ ዐርገዋል፤ ስለዚህም ይህን ዓለም ትተሽው ወደ ሰማይ ትሔጅና ፍጻሜ በሌለው የዘላለም ሕይወት ከልጅሽ ጋር ትኖሪ ዘንድ አዝዟል" ብሎ ዘንባባውንም በእጇ ሰጣት፡፡

Friday, January 22, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተረጐመው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ!


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 13 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
     በ388 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም መግቢያ ላይ ተጀምሮ፥ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የተጠናቀቀው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የኦሪት ዘፍጥረት የትርጓሜ መጽሐፍ የመጀመሪያ ቅጹ በገበያ ላይ ዋለ፡፡ ይህ ከሐዋርያት ዘመን አንሥቶ በተመሠረተውና በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እንደ ታነፀ በሚነገረው ፓላዪያ (The Palaia) በተባለ በታላቁ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው ትምህርት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን እጅግ የጠለቀ ፍቅርና የሰው ልጅም ምን ያህል ክቡር ፍጥረት እንደ ኾነ የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡

Saturday, January 9, 2016

ስግደት (ክፍል 1)


በዲ/ ሕሊና በለጠ ዘኆኅተ ብርሃን


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2008 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 በፍጹም ልብ በፍጹም ነፍስ በፍጹም ኃይል (ዘዳ.65) የሚወደድ የሆነውን አምላካችን እግዚአብሔርን ስናመልከው ሥጋችንንም፣ ነፍሳችንንም፣ መንፈሳችንንም አስተባብረን መሆን አለበት፡፡ መጻሕፍትን በማንበብ፣ ለብዎትን /ማስተዋልን/ በመጠቀም፣ ዕውቀትን ገንዘብ በማድረግ፣ ነቢብን /ንግግርን/ በማስገዛት፣ ሀልዎትን /መኖርን/ በመሠዋትና በመሳሰሉት እግዚአብሔርን ማምለክ ባሕርያተ ነፍስን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡ ጾም/ከሥጋ ፍላጎት መከልከል/ እና ስግደትን የመሳሰሉት ደግሞ በሥጋ እግዚአብሔርን የምናመልክባቸው፣ ሥጋችንን የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ (ይህ ማለት ግን ስግደት ለሥጋውያን ብቻ የተገባ ነው ማለት አይደለም፤መላእክቱ ሁሉ ስገዱለት”/መዝ.977/ እንዳለ መላእክትም የሚሰግዱ ናቸውና፡፡) ፍቅር፣ ቸርነት፣ ምኅረት፣ መመጽወት እና የመሳሰሉት የመንፈስ ሥራዎች ደግሞ ወደ ፍጹምነት የሚወስዱን የሥጋን ድካምና የነፍስን ሐልዮት የምንቀድስባቸው እንዲሁም መንፈሳችንን ለአምልኮተ እግዚአብሔር የምናስገዛባቸው መንገዶች ናቸው፡፡

FeedBurner FeedCount