Wednesday, August 1, 2012

የቅዱሳን ሕይወት!


መግቢያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም ወደዚህ ምድር ከመምጣቱ በፊት እኛ የሰው ልጆች የምናውቀው ሞትን ብቻ ነበረ። ሞት ለእኛ እጅግ የቀረበና ከእያንዳንዳችንም ሆነ ከመላው የሰው ዘር በላይ እጅግ ኃይለኛ ነበረ።  ምድር የሞት እስር ቤት እኛ የሰው ልጆች ደግሞ ረዳት የሌለን የሞት ባሪያዎች ነበርን። ነገር ግን ሰው በሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ተገለጠ ተስፋ የሌለን መዋቲያን፣ የሞት ባሮች ለነበርን የዘላለም ሕይወት ተገለጠልን” ( ዮሐ. *) ይህንንም የዘላለም ሕይወት  በዓይናችን አየነው፤ ተመለከትነው፤ በእጃችንም ዳሰስነው ( ዮሐ. *) እኛ ክርስቲያኖችም ይህንን የዘላለም ሕይወት ለሁሉም ገለጥነው (መሰከርነው)( ዮሐ. *) ከክርስቶስ ጋር በኅብረት ስለመኖርም በዚህ ምድር እያለን እንኳን ዘላለማዊ ሕይወትን መኖር ጀመርን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት እንደሆነ አወቅን፤ እርሱም የመጣው ለዚህ ነበርና። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የታመነና እውነተኛ ፍቅር ማለት ይህ  ነው፡፡በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልናእንዲል (፩ዮሐ. *) ስለዚህልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም”(፩ዮሐ. *፲፪)

ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ወሰን የሌለው ነው። ምክንያቱም የዘላለምን ሕይወት  ለማግኘት ሁሉም ሰውበቀላሉሊኖረው ከሚችለው በእርሱ ማመንና መታመን በቀር ሌላ መስፈርት አይፈለግብንምና።በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና”(ዮሐ. *፲፮)እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለውእንዲል (ዮሐ. *፵፯) የእኛ እውነተኛ ሕይወት የሚጀምረው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት ነው። እምነት፣ ቀስ በቀስ ሊያነጻን፣ ሊያድሰንና አማልክት ዘበጸጋ ሊያደርገን ለሚችል ለኢየሱስ ክርስቶስ  በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ልባችንና በፍጹም ኃይላችን በቁርጥ ሐሳብ ራሳችንን ለእርሱ እንድንሰጥ ያደርገናል። ሕይወታችን ሕይወት የሚሆነው በክርስቶስ ስንኖር ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒው የሆነ ነገር በሙሉ ሞት ይባላል። ሞት ኃጢአት፣ ኃጢአት ደግሞ ሕይወት ከሆነውና የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር መለየት ነው።

 ለመሆኑ ክርስቲያኖች ምንድን ናቸው? ክርስቲያኖች ለባሴ ክርስቶስ (ክርስቶስን የለበሱ) ዘላለማዊ ሕይወትን የያዙ ማለት ናቸው። ቅዱሳን ደግሞ ዘላለማዊ በሆነ በክርስቶስ ከፍተኛ የቅድስና ደረጃ ላይ የደረሱ፣ ሞት የማይሠለጥንባቸው ፍጹማን ክርስቲያኖች ናቸው። ሁለንተናዊ ሕይወታቸው በክርስቶስ የሆነ ነው። ቅዱሳን በክርስቶስ በመኖር እርሱ የሠራቸውን ሥራዎች መሥራት ይችላሉ - “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊልጵ. *፲፫)እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋልእንዲል (ዮሐ. ፲፬*፲፪)
ለምሳሌ የሐዋርያት ሥራማለት ሐዋርያት በክርስቶስ ኃይል የሠሯቸው የክርስቶስ ሥራዎች ማለት ነው።  የቅዱሳን ሕይወት ማለት ደግሞ የሐዋርያት ሥራ ቀጣይ ክፍል ማለት ነው። ልክ እንደ ሐዋርያት ሁሉ በቅዱሳን ሕይወት ውስጥም አንድ ዓይነት ወንጌል፣ አንድ ዓይነት ሕይወት፣ አንድ እውነት፣ አንድ ዓይነት ጽድቅ፣ አንድ ዓይነት ፍቅር፣ አንድ ዓይነት እምነት፣ አንድ ዓይነት ዘላለማዊነት፣ አንድ ዓይነት ሰማያዊ ኃይል፣ አንድ አምላክ፣ አንድ ጌታ እናገኛለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለምም ያው ስለሆነ (ዕብ. ፲፫*) በየዘመናቱ እስከ ዕለተ ምጽአት ለሚነሱ ቅዱሳን አንድ ይነት ኃይል ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈልን በሐዋርያት ሥራ  አብነት የቅዱሳንን የሕይወት ተጋድሎ መጻፍ፣ ማንበብና መከተል  መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። በዚህ መሠረት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ቀጥሎ ከተሡት ቅዱሳን ጀምሮ ያሉትን አበውና እማት ሕይወት በመጻፍና በማስተማር የቅዱስ ሉቃስን ሥራ እየፈጸመች ትገኛለች።

 በቤተክርስቲያናችን የቅዱሳንን የሕይወት ተጋድሎ በስፋት ከትቦ የሚገኘው መጽሐፍ ስንክሳር ይባላል። ይህ መጽሐፍ በዓመት ውስጥ ባሉት ቀናት ታስበው የሚውሉትን ቅዱሳን ዜና ገድል በቅደም ተከተል የያዘና በሚገባ የተዋቀረ ስለሆነ ለማንበብ እጅግ የተመቸ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህንን መጽሐፍ እንድታነቡት ተጋብዛችኋል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

ይቀጥላል!
    
  

FeedBurner FeedCount