Thursday, February 12, 2015

ቅዱሳት መጻሕፍት ስለማንበብ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ የካቲት 5 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እስኪ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መጽሐፍ ቅዱስን ላለማንበብ ምክንያት ይደረድሩ ለነበሩ ሰዎች ይሰጣቸው የነበረውን ተግሣፅ ከዚኽም ከዚያም ያሰባሰብኩትን አንድ ላይ አድርጌ ላካፍላችኁና ራሳችንን እንመርምርበት፡-
·        መጽሐፍ ቅዱስ የለንም የሚሉ ነበሩ፡፡ ይኽም በጣም ውድ ስለኾነ ነው፡፡ 4ኛው ... አንድን ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት የአንድ ዓመት ደመወዝ ነበርና፡፡ ሊቁ ግንይኽ ምክንያት አይኾንም፡፡ ብያንስ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉው ባይኖራችኁም ከወንጌል አንዱን ብቻ መግዛት ትችላላችኁ፤ ርሱንም ዘወትር ማንበብ ትችላላችኁይላቸው ነበር፡፡ይኽን ማድረግ ባትችሉ እንኳን ዘወትር ወደዚኽ ጕባኤ በመምጣት በነጻ መማር ትችላላችኁ፡፡ ብያንስ ወደ ቅዳሴው ኑ፡፡ እዚያ የሚነበበውንና የሚተረጐመውን በሥርዓት አዳምጡ፡፡ ወዮ! እዚኽ ስትመጡ ትቁነጠነጣላችኁ፤ ሙቀቱ ብርዱ ትላላችኁ፡፡ ወደ ገበያ ቦታ፣ ወደ ተውኔት፣ ወደ ስታድዬም ስትሔዱ ግን ምንም አይመስላችኁም፡፡ ዶፍ ዝናብ ቢዘንብባችኁ፣ ሙቀቱ አናትን የሚበሳ ቢኾን፣ በውኃ ጥም ብትያዙ ትቋቋማላችኁ፡፡ ታድያ ምን ዓይነት ይቅርታ ይኾን የሚደረግላችኁ?” ይላቸው ነበር፡፡

Thursday, February 5, 2015

በእንተ አትሕቶ ርእስ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቀረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 28 ቀን፣ 2007 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  እግዚአብሔርን የምትወዱት አንድም እግዚአብሔር የሚወዳችኁ ልጆቼ! ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ ምን ያኽል ጥቅም እንዳለው፥ በአንጻሩ ደግሞ ትዕቢትን ገንዘብ ማድረግ ምን ያኽል ጕዳት እንዳለው ታውቁ ዘንድ እወዳለኁ፡፡ ምንም ያኽል ምግባር ትሩፋት ቢኖረን፣ ብንጾም፣ አሥራት በኵራት ብናወጣ፣ ሌላም ብዙ የብዙ ብዙ ምግባራትን ብናደርግ ትሕትና ግን ከሌለን ከንቱ ነን ብዬ እነግራችኋለኁ፡፡ ምንም ያኽል ኃጥአን ሳለን ነገር ግን የተሰበረ ልቡና ካለን፥ በምግባር በትሩፋት አሸብርቀው ሳለ ትዕቢተኞች ከኾኑት ሰዎች ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጆች ነን ብዬ እነግራችኋለኁ፡፡ ከቀራጩ በላይ ማን ኃጢአተኛ ነበር? /ሉቃ.189-14/፡፡ ነገር ግን ይኽ ኃጢአተኛ ሰው ዓይኑን ወደ ሰማይ ቀና አድርጐ ሊያይ ባለመውደዱ፣ በምትመሰገንበት በቤተ መቅደስኅ መቆም የማይቻለኝ ኀጥእ ነኝ በማለቱ ከማይቀማው፣ ከማይበድለው፣ ከማያመነዝረው፣ በሳምንት ኹለት ጊዜ ከሚጾመው፣ ከገንዘቡ ኹሉ አሥራት ከሚያወጣው ፈሪሳዊው ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አገኘ፡፡ ይኽስ እንዴት ሊኾን ቻለ?

Sunday, January 25, 2015

ከሳምንታት በኋላ ይወጣል



ውድ የመቅረዝ ቤተ ሰቦች እንዴት አላችኁ? እጅግ የምንወዳቸው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስብከቶችና ተግሣጻት እነሆ በአንድ ላይ በዐቢይ ጾም ዋዜማ ልናገኛቸው ነው፡፡ 201 ገጽ ባለው በዚኽ መጽሐፍ ውስጥ 56 የተለያዩ የሊቁ ስብከቶችና ተግሣጻት ተካተዋል፡፡ አጠር አጠር ብለው የተዘጋጁ ሲኾኑ ረዣዥም ጽሑፎችን ለማንበብ ትዕግሥቱና ጊዜ ለሌላቸው እጅግ ተመራጭ ናቸው፡፡ ይጠቀሙበት፡፡ ይኽን መጽሐፍ ሲገዙ በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ እንደ ማለት ነው፡
1. ነፍስዎን በቃለ እግዚአብሔር ይመግባሉ፤
2. የመቅረዝ ዘተዋሕዶን አገልግሎት ከዚኽ የበለጠ እንዲሰፋ ይደግፋሉ፡፡ 

FeedBurner FeedCount