Wednesday, May 18, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፪


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 10 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች ሆይ! በክፍል አንድ ትምህርታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ተወለደባት ከተማ ስለ አንጾኪያ ጥቂት ተነጋግረናል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ወደ ሊቁ ልደትና እድገት እንቀጥል፤ መልካም ንባብ!
ከአንደበተ ርቱዕነቱ የተነሣ አፈወርቅ የተባለው ይህ ቅዱስ የተወለደው 347 .. ነው፡፡ 50 ዓመት የሚኾን ዕድሜውን የሚያሳልፈውም በዚህች በአንጾኪያ ከተማ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዕድሜ 330 .. ገደማ ከተወለዱት ከቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያና ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንደዚሁም 335 .. ከተወለደው ከቅዱስ ባስልዮስ ታናሽ ወንድም ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በዕድሜ ያንሳል፡፡ ከአባ ሆሮኒመስ ደግሞ ተቀራራቢ ዕድሜ አላቸው፡፡ በኋላ ከመንበሩ እንዲጋዝ ከሚያደርገው ከአሌክሳንድርያው ፓትሪያርክ ከቴዎፍሎስም ጋር ልደታቸው ተቀራራቢ ነው፤ ፓትሪያርክ ቴዎፍሎስ የሚወለደው 345 .. ላይ ነውና፡፡

Tuesday, May 17, 2016

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ክፍል ፩

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ግንቦት 9 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ተወዳጆች ሆይ! ግንቦት 12 የተወዳጁ አባታችን የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት እንደ መኾኑ ስለ ሊቁ ከዚህ በፊት ከምናውቀው በተጨማሪ አንዳንድ ነገሮችን እንድንነጋገር ወድጃለሁ፡፡ በዚሁ የመጀመሪያ ክፍልም ስለ ተወለደባትና ስላደገባት ከተማ ስለ አንጾኪያ የተወሰኑ ነጥቦችን እንነጋገራለን፡፡ መልካም ንባብ!
በአራተኛ ... አጋማሽ ላይ በሮማ ክፍለ ግዛት እጅግ በጣም ከሚታወቁት ከተሞች አንዷ አንጾኪያ ነች፡፡ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት አንጣክያ ተብላ በምትታወቀው የደቡብ ቱርክ ውስጥ የምትገኝ የሶሪያ ልሳነ ምድር ነች፡፡
ይህቺ ከተማ 300 ... የታላቁ እስክንድር ጀኔሮችሎች አንዱ በሚኾን በሴሉከስ ቀዳማዊ ኒካቶር በደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኝ ባሕሩ በሚፈስ ኦሮንቶስ በተባለ ወንዝ ዳር የተመሠረተች ናት፡፡ አጥሯ ግንብ ሲኾን 10 ኪሎ ሜትር ያህል ይረዝማል፡፡ በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 508 ሜትር ከፍታ ያለውና በደን የተሸፈነ ተራራ አላት፡፡ ዋናው መንገዷ በእብነ በረድ የተነጠፈ፣ በኹለቱም አቅጣጫ ኹለት ፎቅ ባላቸው ሕንፃዎች የደመቀ፣ ሌሊት ሌሊት በዘይት በሚሠሩ መብራቶች ያሸበረቀ ነው፡፡ ከተማይቱ እጅግ አስደናቂ በኾኑ ሕንፃዎች የተዋበች፣ በቂ የሚባል የውኃ ተደራሽነት ያላት፣ 18 የሚኾኑ የመዋኛ ሥፍራዎችና ቲአትር ቤቶች እንዲሁም የሰረገላ እሽቅድድም ቦታዎች የሚገኙባት ናት፡፡ ከከተማይቱ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 8 ኪሎ ሜትር ላይ ነፋሻማ ቦታ ላይ የተሠሩ ቪላ ቤቶች፣ አሁንም በጥቅም ላይ ያሉ ፏፏቴዎች፣ አፖሎ የተባለ ጣዖት ቤትና የኦሎምፒክ ውድድር በየጊዜው የሚካሔድበት ሥፍራ የሚገኙባት ከተማ ነች፡፡

Saturday, May 14, 2016

የትዳር አንድምታው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ መጽሐፍ በገበያ ውሏል

በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጎመውየትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮለአምስተኛ ጊዜ ታትሟል።
          በዚህ መጽሐፍ ውስጥ መልስ የሚያገኙባቸው ነጥቦች፡-
እግዚአብሔር በትዳር ውስጥ ያለውን ድንቅ ፈቃድ፤
ሚስት ለባሏ ትገዛየመባሉ ምክንያትና አተረጓጎም፤
የባልና የሚስት እኩልነትና አንድ አካል ስለ መኾናቸው የተሰጡ ድንቅ ማብራሪያዎች፤
ባልና ሚስት በየበኩላቸው ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ ምግባራት፤
ለትዳራቸው ስኬት የሚጠቅሙን ሰማያዊ ፍልስፍናዎችና መንፈሳዊ ጥበባት፤
ኢአማኒ የትዳር ጓደኛ ቢኖረን ምን እናደርግ ዘንድ እንደሚገባን፤
ስለ ባርነት ትርጉም፤
አሳፋሪና አስፈሪ ትእዛዛት ስላሏት ጨካኝ እመቤት ማንነት፤
ስለ ትክክለኛው ድንግናዊ ሕይወት፤
ትኩረት ስላልተቸራቸው ነገር ግን ለብዙዎች ትዳር መፍረስ ዋና ምክንያት ስለኾነውመከልከል

Wednesday, May 4, 2016

ባሎች ለሚስቶቻቸው ሊያሳዩአቸው የሚገባ ፍቅር

   ☞ (በመምህር ሽመልስ መርጊያ የተተረጎመችውና ከአራት ዓመት በኋላ ለአምስተኛ ጊዜ ታትማ ግንቦት አንድ ቀን በገበያ ከምትውለው - የትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ - መጽሐፍ የተቀነጨበ፣ ገጽ 17-19)

☞ … ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስትህ ለአንተ ትገዛልህ ዘንድ ትሻለህን? ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት አንተም እንዲሁ ለሚስትህ አድርግላት፡፡ ሕይወትህን ስለ ርሷ አሳልፈህ መስጠት ካለብህ ስለርሷ ሕይወትህን አሳልፈህ ስጥ፤ መከራም መቀበል ካለብህ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ፡፡
አንተ ይህን ብትፈጽመው ስንኳ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ካደረገላት ጋር ሲነጻጸር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንተ ይህን ያደረግኸው ከአንተ ጋር ፈጽማ ለተዛመደችህ ለአንዲት ሴት ነው፡፡ “But He for one who turned on Him and hated Him” “እርሱ ግን ከእርሱ ለተመለሰችውና ለጠላቸው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡” ርሱ ከርሱ የተመለሰችውንና የጠላችውን እንዲሁም ያቃለለችውን ገንዘቡ ሲያደርጋት በማስፈራራት፣ በማስገደድ ወይም ይህን በመሳሰሉ ነገሮች አልነበረም፤ ነገር ግን ኀዘን ባልተቀላቀለበት ፍጹም በሆነ ፍቅር በመሆን ነበር፡፡ አንተም ለሚስትህ እንዲሁ አድርግላት አዎን! ምናልባት ሚስትህ አንተን ልታመናጭቅህ፣ ልትንቅህ፣ ልታፌዝብህም ትችላለች፤ ቢሆንም ግን አንተ ለርሷ ካለህ አርቆ አሳቢነት ንጹሕ ፍቅርና ኀዘኔታ የተነሣ ልትታገሣት ይገባሃል፡፡
ከሰው ሁሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖርም ከእነዚህ የተሻሉ ነገሮች ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተለይም ለባልና ለሚስት፡፡ አንድ ሰው አገልጋይ ባሪያውን በማስፈራራት ለመግዛት ቢሞክር ለጥቂት ጊዜአት ሊገዛለት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባሪያ እንዲህ ዓይነት አገዛዝ ስለማይመቸው ከእርሱ ፈጥኖ ይሸሻል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የሕይወቱን አጋር፣ የልጆቹን እናት፣ የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ሚስቱን በፍቅርና በፍጹም አክብሮት እንጂ ልክ እንደ ባሪያ በፍርሃት ሰንሰለት በማሰር ወይም በማስጨነቅ ርሷን ሊገዛት መሞከር አይገባውም፤ ሚስት በባልዋ ምክንያት የምትሸበር ከሆነ አንድነታቸው ምን ዓይነት አንድነት ነው?

FeedBurner FeedCount