Saturday, July 22, 2017

ነገረ ሰብእ - ትምህርተ ሃይማኖት ክፍል 19(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባብያን! እንደ ምን ሰነበታችሁ? መቼስ መቅረዝ ዘተዋሕዶ የጡመራ መድረካችን ከስንፍናዬ የተነሣ ጨለምለም ካለች ወራት ተቆጥረዋል፡፡ እስኪ ደግሞ እግዚአብሔር እስከ ፈቀደልን ድረስ ዘይት እንጨምርባትና ታብራ፡፡ ለዛሬም የትምህርተ ሃይማኖት ትምህርታችን ቀጣይ ክፍል ስለ ኾነው ስለ “ሰው ልጅ” ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
የሰው ልጅ የሥነ ፍጥረት ኹሉ አክሊል ነው፡፡ ፍጥረታቱ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የተፈጠሩት ለሰው ነውና፡፡ በሰው ልጅና በሌሎች ፍጥረታት አፈጣጠር ላይም ልዩነት አለው፡፡ እግዚአብሔር መግቦቱ፣ ጠብቆቱ፣ ፍቅሩ ለፍጥረታት ኹሉ ቢኾንም የሰው ልጅ ግን ከፍጥረት ኹሉ በላይ ልዩ የኾነ ቦታ አለው፡፡
ምዕራበውያን “ዘመነ አብርሆት” ከሚሉት ጊዜ አንሥቶ ግን ትክክለኛው የሰው ትርጉሙ እየተዛባ መጥቷል፡፡ የሰው እውነተኛ ትርጉሙ በጭምብሎች ተሸፍኖ ዓለም ሰው እያለች የምትጠራው ጭምብሉን ኾኗል፡፡
ለምሳሌ በዚህ ዓለም ከነገረ ሰብእ የትምህርት ዘርፎች አንዱ የኾነው አርኪኦሎጂ ስለ ሰው ልጅ ባሕል፣ ተረፈ ዐፅም፣ አመጋገብ ሥርዓት እና የመሳሰሉትን ያጠናል፡፡ ሥነ ሕይወታዊ ነገረ ሰብእ (Biological Anthropology) ደግሞ ሰዎች የተለያዩ አከባቢዎችን እንዴት መልመድ እንደ ቻሉ፣ የአንድ በሽታና ሞት መነሻው ምን እንደ ኾነ፣ ባሕልና ሥነ ሕይወት የሰው ልጅን ሕይወት ከመቅረጽ አንጻር ምን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ስለሚመሳሰሉባቸውና ስለሚለያዩባቸው ነጥቦች ያጠናል፡፡ ማኅበረ ሰባዊ ነገረ ሰብእ (Social Anthropology) የተባለው ዘርፍም ሰዎች እንዴት በተለያዩ ቦታዎች እንደሚኖሩ፣ በዙሪያቸው ያለው ዓለምም እንዴት እንደሚገነዘቡት፣ ከጎረቤታቸው ጋር ስላላቸው መስተጋብር እና ስለመሳሰሉት ያጠናሉ፡፡ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ሌላው ዘርፍ (Linguistic Anthropology) ደግሞ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች እንዴት እንደሚግባቡ፣ ቋንቋ ከምናየው ጋር እንዴት የተሰናሰለ እንደ ኾነ ያጠናሉ፡፡
እንግዲህ ዓለም ስለ ሰው ያላት ዕውቀት እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የትምህርት መስኮች (Descriptive Anthropologies) የሚሰጧት መረጃ ነው፡፡ ይህ በራሱ ጥፋት ባይኾንም ነገር ግን ቁንጽል ነው፡፡
ሎጥን የምትመዝነው በሰዶም ሰዎች ነው፡፡ አብርሃምን የምትመለከተው በዑር ወይም በካራን ሰዎች መስፈርትነት ነው፡፡ አንድ ቅዱስ አትናቴዎስን የምታየው በአርዮሳዊው ዓለም የተንሸዋረረ ዓይን ነው፡፡
ዘመናዊነት (Modernity) ሰውን የሚመዝነው ከግላዊነቱ፣ በሥራ ከመጠመዱ፣ የዚህን ዓለም ኑሮን ከማሸነፉ፣ “አንተ እንደዚያ ታስባለህ፤ እኔ ግን እንደዚህ አስባለሁ” በማለት እውነታን እንደ እውነት ሳይኾን እንደ አንድ እይታ ከመመልከት እና ከመሳሰሉት አንጻር ነው፡፡
ዓለማዊነትም (Secularism) ዋና ማእከሉን የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት ላይ በማድረግ “ሰውን ሰው የሚያሰኘው ቁሳዊ ሀብቱና ንብረቱ ነው” የሚል ስብከቱን ይሰብካል፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ምድራዊ ሕይወት በቂ ምላሽ አይሰጥም በማለት የሰው መሠረታዊ ፍላጎቱ ምድራዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ አድርጎት ያርፋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩትን ዕቃ (ሮቦት) “ሰው” ብለው ለመጥራት እየተጣጣሩ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ዓለም ምን ያህል ከእውነታ ርቃ እንደ ኼደችና እኛም ምን ያህል በቀጥታም ይኾን በተዘዋዋሪ ነጽሮታችን እንደ ተዛባ የሚያመለክት ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም የሰው አማናዊ ትርጉሙ ከላይ የለበሰው ጭምብሉ ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ጥብቅ አንድነትና ኅብረት መኾኑን በማስገንዘብ ኦርቶዶክሳዊ መነጽርን ማሳየት ነው፡፡

Thursday, January 12, 2017

ይቅርታበቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር 4 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱአምላክ አሜን!
… ከሠራተኞችህ አንዱ ከአንተ መቶ ቅንጣት ወርቆችን ተበደረ እንበል፡፡ ሌላ ሰው ደግሞ ከዚህ ሠራተኛህ የተበደረው ጥቂት ብር ነበረው፡፡ ከዚህ ሠራተኛህ የተበደረው ያ ሰውም ወደ አንተ መጥቶ ቸርነትን እንድታደርግለት ለመነህ፡፡ አንተም ሠራተኛህን ጠርተህ፡- “የዚህን ሰው ዕዳ ተውለት፤ ከእኔ ከተበደርከው ዕዳህም እቀንስልሃለሁ” ብትለውና ይህ ሠራተኛህ ከዚያ በኋላ በዚያ ሰው ላይ ቢጨክንና ቢከፋ ይህን ሠራተኛ ከእጅህ ሊያድነው የሚችል ሰው አለን? እጅግ እንደ ነቀፈህ አድርገህ ቈጥረህ ብዙ ግርፋትን አትገርፈውምን? [እንዲህ ብታደርግ] እጅግ ፍትሐዊ ነው፡፡ እግዚአብሔርም የሚያደርገው እንደዚህ ነው፤ በዚያች ዕለተ ምጽአት ላይ እንዲህ ይልሃልና፡- “አንተ ክፉና ተንኰለኛ ባሪያ ያንን ሰው ይቅር ብትለው ይቅርታው የአንተ ነበርን? ለእርሱ እንድታደርግለት የታዘዝከው ከእኔ የተበደርከውን ነበር፡፡ ያልኩህ ‘ዕዳዉን ብትተውለት እኔም እተውልሃለሁ’ ነው፡፡ በእውነት እንዲህ ይህን ኹኔታ ጨምሬ ባልነግርህም እንኳን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ዕዳዉን ትተውለት ዘንድ በተገባህ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ወዳጅ ኾኜ ውለታን ጠየቅሁህ እንጂ እንደ ጌታ አላዘዝኩህም፡፡ የጠየቅሁህ የእኔ ከኾነው ነው፤ ይህን ካደረግህም እጅግ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን እንደምሰጥህ ቃል ገብቼልህ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ልትሻሻል አልቻልክም፡፡”

ህየንተ “ወልታ ጽድቅ” - እንተ ይእቲ ሐዳስ መጽሐፍ!በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 3 ቀን፣ 2009 ..)- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ባለመወድሱኩሉ ይሤኒ ለእመ አሠንይኮ – (አንተ) ለበጎ ካደረግኸው ሁሉም ለበጎ ይሆናልእንዲል ማኅበራዊ ሚዲያን (እስከ ተቻለን) ስለ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትም ሆነ ስለ ተቀረው አገራዊ ጉዳይ ለበጎ ዓላማ ለማዋል ሳንታትር የቀረን አይመስለኝም፡፡  ከታተርንባቸው አርእስተ ጉዳዮች ደቂቀ እስጢፋኖስንና ጥንተ አብሶን የተመለከቱ በእመቤታችን ዙሪያ እያጠነጠኑ ታሪክና ዶግማ የሚያጣቅሱ ረዘም ያሉ መጣጥፎ ይጠቀሳሉ፡፡ መረጥናቸው፡፡ አየናቸው፡፡ ከለስናቸው፡፡ በክለሳው የፍቁራን ወንድሞቼ ብርሃኑ አድማስ፣ የኄኖክ ኃይሌና የገብረ እግዚአብሔር ኪደ በቀና ልቡና የታጀበ ጥልቅ አስተያየት ታከለበት፤ ከእነርሱ በመጣ ጥቆማ መነሻነት መጣጥፎቹን በተጨማሪ ማጣቀሻ አዳበርናቸው፡፡ ዳበሩ፡፡ ተገጣጠሙ፡፡ ከግጥምጥሙወልታ ጽድቅየምትሰኝ ደንቧላ መጽሐፍ በሽልም ወጣች፤ ተወለደች! መወለዷ ጥሩ! ዜና ልደቷን ተሻግረን እስኪ የጽንሰቷን ነገር እንስማው

Saturday, July 23, 2016

ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ በ‹‹ያ! ትውልድ›› መካከል … ‹‹ሞትህ ደጅ አደረ››! ክፍል ሁለት…!

በአማን ነጸረ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 16 ቀን 2008 ዓ.ም.):- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

3. ሰቆቃወ ቴዎፍሎስ… ቅድመ-ሞት፣ ጊዜ-ሞት፣ ድኅረ-ሞት...ሞትህ ደጅ አደረ!
ከሞመቱ በፊት ስብዕናውን ለመግደል ተሞከረ፡፡ ሲሞት የፓትርርክነት ወግና ሥርዓቱ ቀርቶ ሞቱን ለሙት በሚገባ ክብር ሳያደርጉለት ቀሩ፡፡ ድኅረ-ሞት ታሪኩን ለማስተሀቀር ተሽቀዳደሙ፡፡ ሞቱን፣ እረፍቱን ከለከሉት፤ ሞቱን ደጅ አሳደሩበት፡፡ ሰቆቃውን አበዙበት፡፡ ስለሰቆቃው መዛግብት ካኖሩልን ልናወጋ ጀምረናል፡፡
3.1. ቅድመ-ሞት…የተሐድሶ ጉባኤ (የኮ/ል አጥናፉ የቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ)!
3.1.1. የ1966 ዓ.ም አብዮት እየጋመ፣ እየፋመ፣ እየተቀጣጠለ የንጉሡን ዙፋን በይፋ ለመገልበጥ 25 ቀናት ሲቀሩት ነሐሴ 11 ቀን 1966 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለኮ/ል አጥናፉ የሆነ ‹‹ጠቅላይ ቤተ ክሕነት እስከ አሁን በምትሠራበት ደንብና ሥርዓት ሥራዋን ስትቀጥል…ከጎን ሆኖ የሚሠራ›› በሚል ሽፋን ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥኝ ጊዜያዊ ጉባኤ›› ተቋቋመ(ድምጸ ተዋሕዶ ጋዜጣ፣ ሐምሌና ነሐሴ 1983 ዓ.ም፡ገ.7)፡፡ ይሕ ጉባኤ በቤተ ክህነት አካባቢ ‹‹የተሐድሶ ጉባኤ›› በሚል ሲታወቅ የጉባኤው አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ ደግሞ ‹‹የኮ/ል አጥናፉ የቤተ ክርስቲያን ኮሚቴ›› ይሉታል፡፡ በወቅቱ ሸዋ ክፍለ ሀገርን ወክለው የደርግ ሸንጎ(መማክርት ጉባኤ) አባል የነበሩት ፕ/ር ጌታቸው እንዴት የኮ/ል አጥናፉ ኮሚቴ አባል እንደሆኑና የኮሚቴውን አባላት ዝርዝር ሲገልጹ ‹‹…ኮ/ል አጥናፉ አባተ ጠርቶኝ ‹ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ወጥታ ራሷን የምትችለበትን መንገድ የሚፈልግ ኮሚቴ ልናቋቋም ነውና በአባልነት እንዲያገለግሉ እፈልጋለሁ› አለኝ፡፡ ንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ ገብረማርያም፣ አለቃ አያሌው ታምሩ፣ ቄስ ዳኛቸው ካሳሁን፣ ዶክተር ክንፈርግብ ዘለቀ፣ አቶ ፍቅረድንግል በየነ፣ አቶ መርስዔኀዘን አበበ፣ አቶ አእምሮ ወንድማገኘሁ፣ አቶ(በኋላ ሊቀ ማዕምራን) አበባው ይግዛው የኮሚቴው አባላት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ ኮሚቴው ሊቀ መንበር ሲመርጥ…ዶ/ር ክነፈርግብ ዘለቀ ተመረጠ›› ይላሉ(ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ፡ገ.202)፡፡ የኮሚቴው አባላት 9 ሰዎች ነበሩ ማለት ነው፡፡

FeedBurner FeedCount