Monday, December 28, 2015

ስለ በርለዓም ሰማዕት



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 18 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
    በርለዓም ሰማዕት በዲዮቅልጥያኖስ ጊዜ በአንጾኪያ የነበረ እጅግ ጥቡዕ ክርስቲያን ነው፡፡ መምለክያነ ጣዖት ለጣዖት ይሠዋ ዘንድ ባስገደዱት ጊዜ ያሳየው ጽናት እስከ ምን ድረስ እንደ ኾነ፣ የዲያብሎስ የማታለል ሥራ እንዴት በየጊዜው እንደሚቀያየር፣ ሊቁ ያስተምራቸው የነበሩት ምእመናንም ከዚህ ሰማዕት ምን ሊማሩ እንደሚገባቸው ሰማዕቱ ወዳረፈበት መቃብር ወስዶ ያስተማራቸው ነው፡፡ መታሰቢያዉም እ.ኤ.አ. ሕዳር 19 ነው፡፡
† † †

     (1) ዛሬ ንዑድ ክቡር የሚኾን በርለዓም ወደ ቅዱስ በዓሉ ጠርቶናል፡፡ ነገር ግን እንድናመሰግነው አይደለም፤ እንድንመስለው ነው እንጂ፡፡ ሲያመሰግን እንድንሰማውም አይደለም፤ የደረሰበትን ቅድስና ዐይተን እርሱን መስለን እዚያ የቅድስና ማዕርግ ላይ እንድንደርስ ነው እንጂ፡፡ የዚህ ዓለም ሰዎች ወደ ሥልጣን ሲወጡ ሌሎች ሰዎች ልክ እንደ እነርሱ ታላላቅ ኾነው ማየትን በፍጹም አይወዱም፤ ቅንአት ውስጣቸውን ይተናነቃቸዋል፡፡ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ግን እንደዚህ አይደለም፤ ፍጹም ተቃራኒ ነው እንጂ፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት ክብራቸውን ከምንም በላይ ከፍ ብሎ የሚያዩት ደቀ መዛሙርቶቻቸው እነርሱን አብነት አድርገው ከእነርሱ በላይ የተሻሉ ኾነው ሲመለከቱአቸው ነው፡፡ በመኾኑም አንድ ሰው ሰማዕታትን ማመስገን ቢፈልግ እነርሱን ሊመስል ይገቧል፡፡ አንድ ሰው የእምነት አትሌቶችን ማሞገስ ቢፈልግ እነርሱን መስሎ ምግባር ትሩፋትን ሊሠራ ይገቧል፡፡ ይህ ነገርም እነርሱ ካገኙት ሹመት ሽልማት በላይ ሰማዕታቱን ደስ ያሰኛቸዋል፡፡ በእርግጥም ያገኙትን ሹመት ሽልማት ከምንም በላይ የሚያጣጥሙትና የተሰጣቸው ክብር ምን ያህል ታላቅ እንደ ኾነ የሚገነዘቡት እኛ እነርሱን መስለን የሔድን እንደ ኾነ ነው፡፡ ይህንንም በማስመልከት ንዑድ ክቡር የሚኾን ጳውሎስ የተናገረውን አድምጡ፤ እንዲህ ያለውን፡- “እናንተ በጌታችን ጸንታችሁ ብትቆሙ አሁን እኛ በሕይወት እንኖራለን” /1ኛ ተሰ.3፥8/፡፡ ከዚህ በፊትም ብፁዕ ሙሴ እንዲህ ብሏል፡- “አሁንም ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር ትላቸው እንደ ኾነ ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ ደምስሰኝ” /ዘጸ.32፥32/፡፡ እንዲህ ማለቱ ነበር፡- “እነርሱ ከተጎዱ የእኔ ክብር ምንም አይደለም፤ የምእመናን ሙላት ማለት የአካል መገናኘትም ነውና፡፡ ታዲያ ራስ የሕይወት አክሊልን አግኝቶ እግር ቢቀጣ ምን ጥቅም አለው?”

Thursday, December 17, 2015

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ (2)


በሥርጉተ ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 07 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ሰማዕትነቱ


ቅዱስ አግናጥዮስ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ በነበረበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከዓላውያን የሮማ ነገሥታት ከፍተኛ መከራና ስቃይ ይደርስባት ነበር:: በድምጥያኖስ ዘመነ መንግሥት ከነበረው የመከራ ማዕበል በጾም እና በጸሎት፣ በብዙ መንፈሳዊ ተጋድሎ፥ በተለይም ምእመናን መከራውን ተሰቅቀው ከሃይማኖት እንዳይወጡ ተግቶ በማስተማር እንደ መልካም ካፒቴን ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን መርቶ አሻግሯል:: ቅዱስ አግናጥዮስ ከትሕትናው የተነሣ ስለ ራሱ ሕይወት እውነተኛ የክርስቶስ ፍቅር ላይ ገና አልደረስኩም፤ እውነተኛ የደቀ መዝሙርነት ፍጽምና ላይ አልደረስኩም እያለ ያዝን ነበር:: በመሆኑም ሰማዕትነት የበለጠ ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርብ በማመን ለሰማዕትነት ክብር እንዲበቃ በእጅጉ ይመኝ ነበር::

Friday, December 11, 2015

አዲስ መጽሐፍ በቅርብ ቀን


(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ 2 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ውድ የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባቢያን! እንደ ምን ሰነበታችሁ? ላለፉት አምስት ሳምንታት ገደማ በመቅረዝ ላይ አዲስ ጽሑፍ ሳልለጥፍ በመቆየቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እንዲህ የኾንኩበት ዋና ምክንያት ግን ላለፉት ስድስት ወራት ስተረጉመው የቆየሁትንና ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አያሌ መጻሕፍት አንዱ የኾነው የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያ ቅጽ መጽሐፍን የመጨረሻዉን ቅርጽ ለማስያዝ ብሎም ወደ ኅትመት ለማስገባት በነበረብኝ ጫና ምክንያት ነው፡፡ እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ በእኔ ዓቅም በብዙ ድካም የተተረጎመው ይህ አዲስ መጽሐፍ በቅርብ ጊዜ ወደ እናንተ ይደርሳል፡፡ ለማቆያ ያህልም ከመጽሐፉ መቅድም ከዚህ በታች አቅርቤላችኋለሁ፡-

Wednesday, November 4, 2015

የዓርብ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል 18
ዓርብ ዐረበ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን ተካተተ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓርብ ማለት መካተቻ መደምደሚያ ማለት ነው። ምዕራብ ስንል መግቢያ፣ መጥለቂያ (ለምሳሌ የፀሐይ መግቢያን ምዕራብ እንደምንለው) ማለት ሲኾን ዐረብ ሲባልም ተመሳሳይ ነው - ከኢየሩሳሌም ምዕራባዊ አቅጣጫ ያሉ ሀገራት የዐረብ ምድር ይባላሉና። ዐርብ የተባለበት ምክንያት በዕለተ እሑድ መፈጠር የጀመሩት ፍጥረታት ተፈጥረው ያበቁበት፣ የተካተቱበት ቀን ስለ ኾነ ነው፡፡
በዚህ ቀን እግዚአብሔር “ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ እንስሳትን ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ ታውጣ” ብሎ አዘዘ /ዘፍ.1፥24/፡፡ በዚሁም መሠረት ልክ እንደ ሐሙስ ፍጥረታት በእግራቸው የሚሔዱ፣ በልባቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ፍጥረታት ናቸው፡፡ የሐሙስና የዓርብ መኾናቸውን የምንለየውም በአኗኗራቸውና በግብራቸው ሲኾን የሐሙስ ፍጥረታት በባሕር፣ የዓርብ ፍጥረታትም በየብስ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ቀን በአራተኛ አዳምን ፈጥሯል። ይህንን በኋላ እንመለስበታለን፡፡
በሳይንሳዊ መንገድ ሔደን ምድር እነዚህን ፍጥረታት እንዴት ልታስገኛቸው ቻለች ብለን ብንጠይቅ መልስ የለውም፡፡ የተገኙት እግዚአብሔር ስላዘዘ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምድሪቱን አዘዛት፤ እርሷም አረገዘች፤ ወለደቻቸውም፡፡ ዛሬም ይህ እውነት እንደ ኾነ የምናይበት ኹናቴ አለ፡፡ ዝናብ ወደ ሰኔ አከባቢ መዝነብ ሲጀምር አስቀድመን ያላየናቸው ፍጥረታት ከምድር ወጥተው ሲበሩ፣ እንዲሁም እንደ እንቁራሪት ያሉ ፍጥረታት ወደ መኖር ሲመጡ እናያቸዋለን፡፡ አስቀድሞ ባልተጣለ ዕንቁላል የተለያዩ ዓይነት ትላትሎች ከጭቃ ውስጥ ሲፈጠሩ እናያቸዋለን፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ጥበብ ታያላችሁን?

Tuesday, October 27, 2015

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ (1)



በሥርጉተ ሥላሴ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፥ ቅዱስ አግናጥዮስ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ስለ ትሕትና ለማስተማር በመካከላቸው ያቆመው ሕፃን ነው፡፡ ከዚህም የተወለደበትን ዘመን መገመት ይቻላል (30-35 ዓ.ም.)፡፡ በጌታችን ደቀ መዛሙርት መካከል በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?” የሚል ክርክር በተነ ጊዜ፥ ጌታ ሕፃኑን ቅዱስ አግናጥዮስን አቅፎ በመሳም፡- ተመልሳችሁ ከየውሀት ጠባይዓዊ ደርሳችሁ እንደዚህ ሕፃን ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም አላቸው፥ “ሕፃንንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመው እንዲህም አለ፥ እውነት እላችኋለሁ ካልተመለሳችሁ እንደዚህም ሕፃን ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም . . . ” እንዲል /ማቴ.18፥2-5፣ አንድምታ ወንጌል/፡፡ ሰማይና ምድርን ፈጥረው በተሸከሙ እጆች፣ ሕዝብና አሕዛብን ለማዳን ግራ ቀኝ በተዘረጉ ቅዱሳት ክንዶች መታቀፍ ምንኛ መቀደስ ነው?! ቅዱስ አግናጥዮስ ጌታችን በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ሕፃን ብሎ እንደመሰለለት እንደዚያው እንደ ምሳሌው ሆኖ እስከ መጨረሻ ሕይወቱ በየውሀት ጠባይዓዊ የኖረ፣ ጌታ አቅፎ እንደ ተሸከመው እርሱም ጌታውን በልቡናው የተሸከመ ቅዱስ አባት ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ አግናጥዮስ ራሱን በተደጋጋሚ ቲኦፎረስ (Theophorus - እግዚአብሔርን በልቡናው የተሸከመ፣ ለባሴ እግዚአብሔር)ስቶፎረስ (Chritophorus - ክርስቶስን በልቡናው የተሸከመ፣ ለባሴ ክርስቶስ) እያለ ይጠራ ነበር፤ በጣም ደስ የሚሰኝበት ሙም ነበር፡፡ ለዚህም ነው በመጨረሻ ለተራቡ አናብስት ተጥሎ ሰማዕትነቱን በፈጸመበት ሰዓት አናብስት ሌላውን አካሉን በመላ ሲበሉ ልቡን መርጠው የተ፡፡

Monday, October 19, 2015

የሐሙስ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 9 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል 17
ሐሙስ የሚለው ሐመሰ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲኾን አምስት አደረገ ማለት ነው። ለሥነ ፍጥረት አምስተኛ ቀን ስለኾነ ሐሙስ ተብሏል።
በዚህ ቀን እግዚአብሔር፡- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾችን ታስገኝ” ብሎ አዘዘ /ዘፍ.1፥20-21/፡፡ በዚሁም መሠረት በእግራቸው የሚሔዱ፣ በልባቸው የሚሳቡና በክንፋቸው የሚበሩ ሦስት ወገን ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡ እነዚህ ፍጥረታት ተፈጥሮአቸው ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ - ማለትም ከመሬት፣ ከውኃ፣ ከእሳትና ከነፋስ - ሲኾን በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ ደመ ነፍስ ማለትም በደም ነፍስነት፣ በደም ኃይል የሚንቀሳቀሱ፣ ደማቸው ሲቆም ሕይወታቸውም አብሮ የሚቆም ማለት ነው፡፡ ይህም እስትንፋስ እያልን የምንጠራው ነው፡፡ ይህ እስትንፋስ - ማለትም ደመ ነፍስ - በሰውም ዘንድ አለ፡፡
እነዚህ በዚህ ዕለት የተፈጠሩት ፍጥረታት ካለ መኖር ወደ መኖር የመጡት እግዚአብሔር ስላዘዘ እንጂ ውኃው በራሱ ኃይል ያስገኛቸው አይደለም፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር ካልፈቀደና ካላዘዘ በስተቀር ምድር አንዲት ቡቃያስ እንኳን ማብቀል እንደማትችለው ማለት ነው፡፡ ምድር እነዚያን ቡቃያዎች ስታበቅል አስቀድሞ ተዘርቶባት አይደለም፡፡ ውኃይቱም እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸውን ፍጥረታት ያስገኘችው አስቀድሞ እነዚህን ፍጥረታት ሊያስገኝ የሚችል ንጥረ ነገር በውስጧ ስለያዘች ሳይኾን እንዲሁ እግዚአብሔር ስላዘዛቸውና እነዚህን ፍጥረታትንም የማስገኘት ዓቅም ስለ ሰጣቸው እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር፥ የእነዚህ ፍጥረታት ዋናው መገኛቸው ቃለ እግዚአብሔር ነው፤ ቃሉ ኃይልን የተመላና ሕይወትን የሚያስገኝ ቃል ነውና፡፡

Tuesday, October 13, 2015

የረቡዕ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥቅምት 2 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል ዐሥራ ስድስት
ቸሩ እግዚአብሔር በዚህ በአራተኛው ቀን ሦስት ፍጥረታትን ማለትም፡- ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጥሯል፡፡ የፀሐይ አፈጣጠር ከእሳትና ከነፋስ ሲኾን የጨረቃና የከዋክብት ደግሞ ከውኃና ከነፋስ ነው፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሳርያ ምናልባት ልንጠይቀው የምንችል ጥያቄ፡- “በመጀመሪያው ቀን ላይ ብርሃን ተፈጥሯል፡፡ ሌላ ብርሃን ታዲያ ለምን አስፈለገ?” በማለት ይጠይቅና እርሱ ራሱ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡- “አስቀድሞ የተፈጠረው የብርሃን ተፈጥሮ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ቀድሞ ለተፈጠረው ብርሃን መሣሪያ ትኾን ዘንድ ፀሐይ ተፈጠረች፡፡ ኩራዝ ማለት እሳት ማለት አይደለም፡፡ እሳት የማብራት ባሕርይ አለው፡፡ ኩራዝን የሠራነው ያ እሳት ሥርዓት ባለው መልኩ በጨለማ ላይ እንዲያበራልን ነው፡፡ እነዚህ የብርሃን አካላትም የተፈጠሩት ልክ እንደዚሁ አስቀድሞ የተፈጠረውን ብሩህና ጽሩይ ብርሃን መሣሪያ እንዲኾኑ ነው” /አክሲማሮስ፣ ክፍለ ትምህርት 6 ቍ. 2/፡፡

Sunday, October 11, 2015

ዕለት ዕለት ቃለ እግዚአብሔርን ለማያነቡ ሰዎች የተሰጠ ተግሣፅ



በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 30 ቀን፣ 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ቃለ እግዚአብሔር መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ ይህን መንፈሳዊ መሣሪያ እንዴት እንደምንጠቀምበትና እንደምንታጠቀው ካላወቅንበት ግን በእጃችን ስላለ ብቻ ምንም ሊጠቅመን አይችልም፡፡ ጠንካራ ጥሩርና ራስ ቍር፣ ጋሻና ሰይፍ አለ እንበል፡፡ አንድ ሰው መጥቶም እነዚህን ታጠቃቸው፡፡ ነገር ግን ጥሩሩን በእግሩ፣ ራስ ቍሩን በራሱ ላይ ሳይኾን በዓይኑ ላይ፣ ጋሻውን በደረቱ ላይ ሳይኾን በእግሩ ላይ አሰረው እንበል፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው እነዚህን መሣሪያዎች ስለ ታጠቀ ብቻ ጥቅም ያገኛልን? ይባስኑ የሚጎዳ አይደለምን? ይህ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሰው ተጠቃሚ ያልኾነው ግን ከመሣሪያው ድክመት አይደለም፤ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ሰውዬው ስለማያውቅ እንጂ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘንድም እንደዚህ ነው፡፡ ትእዛዙን በአግባቡ የማንጠቀምበት ከኾነ የቃሉ ኃይል ምንም ባይቀንስም እኛ ግን ምንም የምንጠቀመው ነገር አይኖርም፡፡

Thursday, October 8, 2015

ዘመነ ጽጌ



በዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 27 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ክኅሎቱ ከፍጡራን ኅሊና በላይ የሆነ የቅዱሳን አምላክ የመላው ዓለም ፈጣሪ "ይህን" የሚታየውንና "ያን" የማይታየውን ሁሉ መልካም አድርጎ ፈጥሮታል:: በዚህም ሁሉ ውስጥ ፍጥረታቱ ለመገኘታቸው ሦስት መንገዶች እና ሦስት አላማዎች ታይተዋል:: መንገድ ላልነው በኃልዮ(በማሰብ) የተፈጠሩ አሉ እንደመላእክት ያሉት ለዚህ ምሳሌ ሆነው ይቀርባሉ:: ደግሞም በነቢብ(በመናገር) የተፈጠሩ አሉ እንደ ብርሃን ያሉትን ለአብነት መጥቀስ የሚቻል ሲሆን በሦስተኛው መንገድ በገቢር (በሥራ) የሰውን ልጅ ብቻ ፈጥሮታል:: ለሦስት አላማ ያልነውን ስናይ ደግሞ፡-

Tuesday, October 6, 2015

የማክሰኞ ፍጥረታት



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 25 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ትምህርተ ሃይማኖት - ክፍል ዐሥራ አምስት
ሦስተኛይቱ ዕለት ዕለተ ሠሉስ ትባላለች፡፡ ሠሉስ ማለት ለፍጥረት ሦስተኛ ማለት ነው፡፡ በአማርኛ ማግሰኞ ትባላለች፤ የሰኞ ማግስት እንደ ማለት ነው፡፡ በተለምዶ ግን ማክሰኞ እንላለን፡፡ እኛም አንባብያንን ግራ ላለማጋባት በዚህ አካሔድ እንቀጥላለን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ሰኞ ላይ ውኃዉን ከሦስት ከፍሎ ምድርን ግን ከውኃ እንዳልለያት ተነጋግረን ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ማለትም ማክሰኞ ላይ ግን በዚህ ዓለም የነበረውን ውኃ ወደ አንድ ስፍራ እንዲሰበሰብ አድርጓል፡፡ ውኃው ሲሰበሰብም ምድር ተገልጣለች፡፡ ነገር ግን ተገለጠች እንጂ ቡቃያ አልነበረባትም፡፡ በመኾኑም በምሳር የሚቈረጡ (እንደ ዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወዘተ)፣ በማጭድ የሚታጨዱ፣ በጥፍር የሚለቀሙ (እንደ ሎሚ፣ እንደ ትርንጎ ያሉ) አዝርእትን፣ አትክልትንና ዕፅዋትን እንድታስገኝ አዘዛት፡፡ ምድርም የቃሉን ትእዛዝ አድምጣ እነዚህን ሦስት ፍጥረታትን አምጣ ወለደች /ዘፍ.1፡12-14/፡፡

Sunday, October 4, 2015

የዘመናችን አጥማቂ ነን ባዮች፡- የሐሳዊው መሲሕ መንገድ ጠራጊዎች

በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ክፍል ሁለት
1.   ተአምራት ማድረግ የምን ውጤት ነው? ተአምራት ማድረግ ከሁለት ነገሮች ሊመጣ ይችላል፡፡ ከመንፈሳዊ ብቃትና ከሰይጣን አሠራር፡፡ በክርስትና ሕይወቱ የበረታ ሰው መንፈሳዊ ብቃቱ በሕይወቱ በሚገለጡ ተአምራት ሊታወቅ ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የምናገኛቸው ቅዱሳን በገድል ተቀጥቅጠው፣ ሰማዕትነት ከፍለው፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሚገባ ተጉዘው ዲያብሎስን ድል ሲነሡት በሕይወታቸው ውስጥ ተአምራት ይገለጣሉ፡፡ ይህም ማለት ተአምራት የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ ነው ማለት ነው፡፡ የተአምራት ስጦታ እንዲሁ በድንገት አይገለጥም፡፡ በዚያ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እያደገ፣ እየተገለጠና እየተመሰከረለት በሚመጣ መንፈሳዊ ዕድገት ምክንያት እንጂ፡፡ ለዚህ ሁለት ምሳሌዎች እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ አራት ምዕራፍ ያለው መንፈሳዊ ዕድገቱ በየዘመናቱ ተገልጦልናል፡፡ በፍኖተ ደማስቆ መመለሱ(የሐዋ8) በአንጾኪያ በሱባኤ መኖሩ(የሐዋ13) ለአገልግሎት ተጠርቶ ከበርናባስ ጋር መውጣቱ እና ከአረማውያን፣ ከአይሁድና ከመናፍቃን ጋር ባደረገው ተጋድሎ የምናገኘው በትምህርትና በተአምራት የተገለጠ ሕይወቱ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ቀስ በቀስ እያደገ (ወየሐውር እም ኃይል ውስተ ኃይል እንዲል) የመጣ ነው፡፡

FeedBurner FeedCount