Pages

Wednesday, July 26, 2017

ሥራህን ሥራ፤ ሌሎችን እርዳ፤ የሚጠቅም ሰውም ኹን!

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ሌሎች ሰዎችን ከማያድን ክርስቲያን በላይ የከፋ ምንም የለም፡፡ አንተ ሰው! ድኻ ነኝ የምትለኝ ለምንድን ነው? ኹለት ዲናር የጣለችዋ ሴት ትፋረድባሃለች፡፡ ከምናምንቴ ቤተ ሰብ እንደ ተወለድክ የምትነግረኝስ ለምንድን ነው? ሐዋርያትም ምናምንቴዎች ነበሩ፤ ነገር ግን ታላላቅ መኾን ተችሏቸዋል፡፡ አለመማርህን ሰበብ አድርገህ አትንገረኝ፤ ሐዋርያትም ያልተማሩ ነበሩና፡፡
ባሪያ ብትኾንም እንኳ፣ ስደተኛ ብትኾንም እንኳ ሥራህን መሥራት ይቻልሃል፤ ሌሎችን መርዳት ይቻልሃል፤ ሰዎችን ማዳን ይቻልሃል፥ አናሲሞስም እንደ አንተ ዓይነት ሰው ነበርና (ፊልሞ.1፡10-11)፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ምን ወዳለ ማዕረግ ከፍ እንዳደረገውና ምን ብሎ እንደ ጠራው አድምጥ፡- “በእስራቴ ስለ ወለድሁት፡፡”

Tuesday, July 25, 2017

መቅረዝ ዘተዋሕዶ : ሰማዕታት

መቅረዝ ዘተዋሕዶ : ሰማዕታት: (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!         ሰማዕት የሚለው ቃል ስርወ ቃሉ “ሰምዐ” የሚል ሲኾን ይኸውም ሰማ፣ አደመጠ፣ አስተ...

Saturday, July 22, 2017

ነገረ ሰብእ - ትምህርተ ሃይማኖት ክፍል 19



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ 15 ቀን 2009 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ ዘተዋሕዶ አንባብያን! እንደ ምን ሰነበታችሁ? መቼስ መቅረዝ ዘተዋሕዶ የጡመራ መድረካችን ከስንፍናዬ የተነሣ ጨለምለም ካለች ወራት ተቆጥረዋል፡፡ እስኪ ደግሞ እግዚአብሔር እስከ ፈቀደልን ድረስ ዘይት እንጨምርባትና ታብራ፡፡ ለዛሬም የትምህርተ ሃይማኖት ትምህርታችን ቀጣይ ክፍል ስለ ኾነው ስለ “ሰው ልጅ” ይዤ ቀርቤያለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
የሰው ልጅ የሥነ ፍጥረት ኹሉ አክሊል ነው፡፡ ፍጥረታቱ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የተፈጠሩት ለሰው ነውና፡፡ በሰው ልጅና በሌሎች ፍጥረታት አፈጣጠር ላይም ልዩነት አለው፡፡ እግዚአብሔር መግቦቱ፣ ጠብቆቱ፣ ፍቅሩ ለፍጥረታት ኹሉ ቢኾንም የሰው ልጅ ግን ከፍጥረት ኹሉ በላይ ልዩ የኾነ ቦታ አለው፡፡
ምዕራበውያን “ዘመነ አብርሆት” ከሚሉት ጊዜ አንሥቶ ግን ትክክለኛው የሰው ትርጉሙ እየተዛባ መጥቷል፡፡ የሰው እውነተኛ ትርጉሙ በጭምብሎች ተሸፍኖ ዓለም ሰው እያለች የምትጠራው ጭምብሉን ኾኗል፡፡
ለምሳሌ በዚህ ዓለም ከነገረ ሰብእ የትምህርት ዘርፎች አንዱ የኾነው አርኪኦሎጂ ስለ ሰው ልጅ ባሕል፣ ተረፈ ዐፅም፣ አመጋገብ ሥርዓት እና የመሳሰሉትን ያጠናል፡፡ ሥነ ሕይወታዊ ነገረ ሰብእ (Biological Anthropology) ደግሞ ሰዎች የተለያዩ አከባቢዎችን እንዴት መልመድ እንደ ቻሉ፣ የአንድ በሽታና ሞት መነሻው ምን እንደ ኾነ፣ ባሕልና ሥነ ሕይወት የሰው ልጅን ሕይወት ከመቅረጽ አንጻር ምን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ስለሚመሳሰሉባቸውና ስለሚለያዩባቸው ነጥቦች ያጠናል፡፡ ማኅበረ ሰባዊ ነገረ ሰብእ (Social Anthropology) የተባለው ዘርፍም ሰዎች እንዴት በተለያዩ ቦታዎች እንደሚኖሩ፣ በዙሪያቸው ያለው ዓለምም እንዴት እንደሚገነዘቡት፣ ከጎረቤታቸው ጋር ስላላቸው መስተጋብር እና ስለመሳሰሉት ያጠናሉ፡፡ ቋንቋን መሠረት ያደረገ ሌላው ዘርፍ (Linguistic Anthropology) ደግሞ በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች እንዴት እንደሚግባቡ፣ ቋንቋ ከምናየው ጋር እንዴት የተሰናሰለ እንደ ኾነ ያጠናሉ፡፡
እንግዲህ ዓለም ስለ ሰው ያላት ዕውቀት እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የትምህርት መስኮች (Descriptive Anthropologies) የሚሰጧት መረጃ ነው፡፡ ይህ በራሱ ጥፋት ባይኾንም ነገር ግን ቁንጽል ነው፡፡
ሎጥን የምትመዝነው በሰዶም ሰዎች ነው፡፡ አብርሃምን የምትመለከተው በዑር ወይም በካራን ሰዎች መስፈርትነት ነው፡፡ አንድ ቅዱስ አትናቴዎስን የምታየው በአርዮሳዊው ዓለም የተንሸዋረረ ዓይን ነው፡፡
ዘመናዊነት (Modernity) ሰውን የሚመዝነው ከግላዊነቱ፣ በሥራ ከመጠመዱ፣ የዚህን ዓለም ኑሮን ከማሸነፉ፣ “አንተ እንደዚያ ታስባለህ፤ እኔ ግን እንደዚህ አስባለሁ” በማለት እውነታን እንደ እውነት ሳይኾን እንደ አንድ እይታ ከመመልከት እና ከመሳሰሉት አንጻር ነው፡፡
ዓለማዊነትም (Secularism) ዋና ማእከሉን የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት ላይ በማድረግ “ሰውን ሰው የሚያሰኘው ቁሳዊ ሀብቱና ንብረቱ ነው” የሚል ስብከቱን ይሰብካል፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ምድራዊ ሕይወት በቂ ምላሽ አይሰጥም በማለት የሰው መሠረታዊ ፍላጎቱ ምድራዊ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ አድርጎት ያርፋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩትን ዕቃ (ሮቦት) “ሰው” ብለው ለመጥራት እየተጣጣሩ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ዓለም ምን ያህል ከእውነታ ርቃ እንደ ኼደችና እኛም ምን ያህል በቀጥታም ይኾን በተዘዋዋሪ ነጽሮታችን እንደ ተዛባ የሚያመለክት ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም የሰው አማናዊ ትርጉሙ ከላይ የለበሰው ጭምብሉ ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ጥብቅ አንድነትና ኅብረት መኾኑን በማስገንዘብ ኦርቶዶክሳዊ መነጽርን ማሳየት ነው፡፡