Monday, May 21, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የአሥራ ሁለተኛው ሳምንት ጥናት!!

“ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ” /ቁ.12/፡፡ በዚያ የነበሩት ሰዎች ወንጌለ መንግሥት መስማት ነበረባቸውና፡፡ ነገር ግን ወንጌላዊው “ወንድሞቹ” እያላቸው ያሉት የማን ልጆች ናቸው? እንዲህ ተብለው እየተገለጹ ያሉት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ዝምድና ያላቸው ናቸው እንጂ የእርሷ ልጆች አይደሉም፡፡ ይኸውም አብርሃም ለሎጥ /ዘፍ.13፡8/፣ ላባ ለያዕቆብ /ዘፍ.29፡15/ ወንድሜ እንደተባባሉት ዓይነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን ደቀመዛሙርቱን ወንደሞቼ እያለ ይጠራቸው እንደነበር ተገልጧል /ማቴ.14፡46-50፣ Augustine, On the Gospel of St. John, Tracte 10:2-3/፡፡ አንድም ዮሴፍ ከሚስቱ የወለዳቸውና ከጌታ ጋር አብረው ያደጉ ናቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
 “የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ” /ቁ.13/፡፡ ይህ ፋሲካ ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ የተደረገ የመጀመረያው ፋሲካ ነው፡፡ ሁለተኛው በሉቃ.6፡1፣ ሦስተኛው በዮሐ.6፡4፣ የመጨረሻው ደግሞ በዮሐ.11፡55 ተገልጸዋል፡፡  የሚገርመው ነገር ከዚህ በፊት ይህ ፋሲካ “የእግዚአብሔር ፋሲካ” ተብሎ ይጠራ ነበር /ዘጸ.12፡11/፡፡ አሁን ግን አይሁዳውያኑ የራሳቸው የሆነ ሰው ሠራሽ ወግና ልማድ ስለጨመሩበት ያ የድሮ ስሙ ተለውጦ “የአይሁድ ፋሲካ” ተብሎ እናየዋለን፡፡ በነብዩ እንዲህ እንደተባለ፡- “በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች” /ኢሳ.1፡14፣ Origen Commentary on the Gospel of John, Book 10:80-81/፡፡
“በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ” /ቁ.14/፡፡ እነዚህ ሻጮች እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ ቤተ መቅደሱን የንግድ ቦታ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ልብ ከእግዚአብሔረ ጋር ሳይሆን ከሚሸጡት ንብረትና ከሚያገብስብሱት ገንዘብ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጌታ ለመገዛት ሳይሆን እርሱን ለመሸጥ የሚሰበሰቡ ናቸው፡፡ ለእነሱስ በዚያ በሚሠዋው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ቢገዙ ይሻላቸው ነበር /አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 “ጌታችንም የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ” /ቁ.15/፡፡ አስቀድመን እንደገለጥነው የእነዚህ አይሁዳውያን መሥዋዕት፣ በዓላት፣ ምናምቴን ጨምረው የሚያመጡት ቁርባን ደስ ስላላሰኘው ገለባብጦባቸዋል /ኢሳ.1፡11-15/፡፡ አንድ ነገር ግን ልብ በሉ! ጌታችን የገበያ ቦታውን ብቻ አልገለባበጠም፤ ይልቁንም መሥዋዕተ ኦሪቱም ጭምር እንጂ /Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 1.2:13-18/፡፡
“ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው” /ቁ.16/፡፡ ጌታችን ይህንን ሁሉ ሲያደርግ “የአባታችንን ቤት” ሳይሆን “የአባቴን ቤት” ሲል እንመለከተዋለን፡፡ ይኸውም አንዳንዶች እንደሚያናፍሱት የምንፍቅና ወሬ ሳይሆን እርሱ ዕሩይ ምስለ አብ በመለኰቱ (ከአባቱ ጋር የተካከለ መሆኑን) ያሳያል፡፡ “የአባቴን ቤት” የሚለውም አይሁድ አስቀድመው እግዚአብሔርን በአንድነቱ ብቻ ስለሚያውቁት ነው፡፡ አሁን ግን በባሕረ ዮርዳኖስ ግልጽ እንደሆነ በአንድነት በሦስትነት የሚመለክበት ቅዱስ ስፍራ ነው /ሉቃ.2፡49 St. Cyril of Jerusalem, Article 7:6/፡፡
 “ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ በመዝሙር 68፡10 ላይ እንደ ተጻፈ አሰቡ” /ቁ.17/።
ይህች ቅናት ጌታን እስከ መስቀል ድረስ ያደረሰች ቅናት ነች፡፡ ይህች ቅናት እርሱ ተዋርዶ እኛ የከበርንባት ቅናት ናት፡፡ ይህች ቅናት እርሱ ደሀ ሆኖ እኛ ባለጸጋ የሆንንባት ቅናት ናት፡፡ ወንድሞቼ! ዛሬ ይህች ቅናት ሁላችንም ልትበላን ያስፈልጋል! አኅቶቼ! ይህች ቅናት የአይሁድ ቅናት የመሰለች ክፉ ቅናት አይደለችም፡፡ ይህች ቅናት በውስጧ ተንኰል ያልተቀላቀለባት በንጹሕ ፍቅር የምትደረግ ቅናት ናት፡፡ ይህች ቅናት ዛሬ በተለይ አብዝታ ታስፈልገናለች፡፡ ፍቅር በቀዘቀዘበት ዘመን ይህች  ቅናት በቤታችን ታስፈልገናለች፤ መናፍቃን በበዙበት ዘመን ይህች ቅናት በቤተ ክርስቲያናችን ታስፈልገናለች፡፡
 ጌታ ዛሬም ይህች ቅናት ትበላዋለች፡፡ አማናዊው ቤተመቅደስ (ሰውነታችን) የነጋዴ ቤት፣ የክፋት ቤት፣ የሌቦች ቤት ሲሆን ጌታ ይህች ቅናት ትበላዋለች፡፡ ንጹሕ መሆን ሲገባን በተለያዩ ነገሮች ስንረክስ ዛሬም ያዝናል፡፡ ወደ ቤቱ እንመለስ፡፡ እግዚአብሔር ዛሬ በጅራፍ ሳይሆን በፍቅር ይጠራናል፡፡ እስክንከፍትለት ድረስም በበር ቆሟል፡፡ ወንድሞች እግዚአብሔርን “ማራናታ” እንበለው፡፡ ከዚያም ፈቃዳችንን ተመልክቶ እንዴት እንደሚያጠራን ራሱ ያውቅበታል፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ እኛን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!!!

Sunday, May 20, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የአሥራ አንደኛው ሳምንት ጥናት!!!


  (ከቻሉ በጸሎት ጀምረው በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት!)
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታችን ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ አሁን ግን እንዲህ የሚላት ምንም እንኳን ልጇ ወዳጇ ቢሆንም በአምላክነቱ ሰው የሚያዘው አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀን የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 22/፡፡ እመቤታችንም ይህንን ስለምታውቅ፡- “ልጄ ወዳጄ! አንተ ከጊዜና ከቦታ ቀመር ውጪ እንደሆንክ አውቃለሁ፤ ሁሉም በጊዜው ውብ አድርገህ የምትሠራ ኤልሻዳይ መሆንህንም አላጣውም፡፡ ልጄ ወዳጄ! አሁን የምለምንህ ወገኖቼን ከሐፍረት እንድትታደጋቸው እንጂ በአምላክነትህ ለማዘዝ አይደለም፤ ከባቴ አበሳ አምላክ መሆንህን አሳምሬ አውቃለሁና፡፡ ልጄ ሆይ! ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ሆነህ የመጣህ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እንደሆንክማ መልአኩ አክብሮ ከነገረኝ ቃል አውቃለሁ፤ በሕግ በአምልኮ ለሚቀርቡህ ግን ሰማዔ ጸሎት ነህና እባክህን ራራላቸው” ብላ በአራኅርኆ ማለደችው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም፡- “እናቴ ሆይ! አንቺ ሴት የምልሽ ኃይለ አርያማዊት እንዳልሆንሽ ለመግለጽ ነው፡፡ ይልቁንም አስቀድሞ በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ ተብሎ የተነገረልሽ የአዳም ልጅ መሆንሽን ለማስገንዘብ እንጂ ውኃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ካንቺ ጋር ምን ፀብ አለኝ” ብሎ መለሰላት፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ፡-  “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
“አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም እኔህን ጋኖች ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው” /ቁ.6-7/። ወንጌላዊው “አይሁድ የማንጻት ልማድ የሚያደርጉባቸው የድንጋይ ጋኖች በዚያ ነበሩ” የሚለን ያለምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ምክንያትን የሚፈልጉ ከሐድያን “ጠጁ አላለቀም ነበር፤ ቀርቶ የነበረውን አበርክቶ ሰጣቸው እንጂ” ብለው ምክንያት እንዳያገኙ ነው፡፡ ምክንያቱም በኦሪቱ ሕግ መሠረት ጋኖቹ ለማንጻት የሚጠቀሙባቸው ጋኖች ከሆኑ ለመጠጥ የሚሆን ወይን ጠጅ ፈጽሞ አይቀዳባቸውምና /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
 ቀጥሎም “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣ ግን አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ዶኪማስ ብሎ ጠራው። ሰው ሁሉ አስቀድሞ ሸሎውን፣ በርዳዳውን፣ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ ተራውን፣ መናኛውን ያጠጣል፡፡ አንተ ግን ሸሎውን፣ በርዳዳውን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው” /ቁ.8-10/። አንዳንድ ልበ ስሑታን “ሠርገኞቹ ሁሉም ሰክረው ስለ ነበር የወይኑን ጣዕም ሊያውቁ አይችሉም፤ ስለዚህ የጠጡት የተለወጠው መልካሙን ወይን ሳይሆን መናኛውን ነው” ብለው ለማጥላላት ይሞክራሉ፡፡ ወንጌላዊው ግን የእነዚህን ነቀፋ አስቀድሞ ስለሚያውቅ “መጀመርያ ሠርገኞቹ ሁሉ ቀመሱት” አላለንም፡፡ አስቀድሞ የቀመሰው ያልሰከረው ሊሰክርም የማይችለው አሳዳሪው ብቻ ነው፡፡ እንደውም ወንጌላዊው ትንሽ ቆየቶ፡- “ኢየሱስም ውኃውን የወይን ጠጅ ወደ አደረገባት ወደ ገሊላ ቃና ዳግመኛ መጣ” በማለት ወይኑ በተአምራት የተለወጠ መሆኑን ነግሮናል /ምዕ.4፡46፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡  
 “ኢየሱስ በሦስት ዓመት ከሚያገርገው ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ቁ.11/። አስተውላችሁ ከሆነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወይን ለማድረግ ሲጸልይ ወይም ሲለምን አንመለከተውም፡፡ ይልቁንም ሠራተኞቹ ለአሳዳሪው እንዲሰጡት ነገራቸው እንጂ እስኪ ልቅመሰው እንኳን አላለም፡፡ እኛ እንደምናውቀው ተራ ወይን ሳይሆን እጅግ መልካም የሆነ ወይን እንደሰጣቸው ያውቃልና፡፡ በዚህም ጌትነቱን ገለጠ፤ ከአባቱ ጋር ያለውን መተካከል አሳየ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም አመኑበት፡፡
ወንድሞቼ ሆይ! ዛሬም እግዚአብሔር እንደ ውኃ ጣዕም ያጣው ሕይወታችንን ወደ መልካም ወይንነት ፍጹም ሊለውጠው ይፈልጋል፡፡ እንግዲያስ እንደ ውኃ የቀዘቀዘው፣ የደከመው ማንነታችን ወደ እርሱ እናቅርበውና ፈቃዳችንን ተመልክቶ ወደ ወይን ይቀይርልናል፡፡ ከዚያ በኋላ በቃና እንደሆነው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የደስታ ምክንያት እንሆናለን፡፡ ይህን ሁሉ እንድናደርግ እንደ ነነዌ ሰዎችም እንድንለወጥ እግዚአብሔር ይርዳን!!!

የዮሐንስ ወንጌል የ10ኛው ሳምንት ጥናት!!


“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ”/ቁ.3/፡፡ ሰርጉ የሆነው የይሁዳ ዕጣ ከምትሆን ከኢየሩሳሌም ሳይሆን ነብዩ “የአሕዛብ ገሊላ” ባላት በቃና ነው /ኢሳ.9፡1/፡፡ ጌታ በዚያ መገኘቱ የአይሁድ ምኵራብ አማናዊውን ሙሽራ እንዳልተቀበለችው የአሕዛብ ቤተክርስቲያን ግን በደስታ እንደተቀበለችው ያሳያል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ Commentary on the Gospel of John 2:1/፡፡ ይህም የሆነው ከተጠመቀ በሦስተኛው ቀን ነው፡፡ የመጀመርያው ቀን እንድርያስና ዮሐንስን የጠራበት ቀን ሲሆን ሁለተኛው ቀን ደግሞ ፊሊጶስና ናትናኤልን የጠራበት ቀን ነው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:2:1/፡፡ አንድም ጌታ የጾመው 40 ቀንና 40 ሌሊት እንደ አንድ ቀን ተቆጥሮ ነው፡፡
“እመቤታችንም ቤተ ዘመድ ናትና በዚያ ነበረች፡፡ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ታደሙ” /ቁ.2/፡፡ “ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን እንግዲህ ሰው አይለየው” እንደ ተባለ ፈጣሪ በፍጥረት መጀመርያ በአዳምና በሔዋን የመሠረተውን የጥንቱን ሥርዓተ ጋብቻ በአዲሱ የምሕረት ኪዳን በኪዳነ መንፈስ ቅዱስም መጽናቱንና መቀደሱን ጌታ በመዋዕለ ሥጋዌው አንዴ ብቻ በተገኘበት በዚሁ ሠርግ አረጋግጦልናል /ቅዱስ ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ ክብር ይልቅ ስለ ሰዎች መልካምነት የሚገደው ነውና በዚያ ተገኘ፡፡ የባርያዎቹን መልክ ለመያዝ እንኳን ያላፈረ ጌታ በባሮቹ ሠርግ መገኘት አላሳፈረውም፤ እንኳንስ ከዚህ ቅዱስ ጋብቻ “ከኃጢአተኞች” ጋር እንኳን ሳያፍር ለመመገብ ተቀምጧል /ፊል.2፡7፣ማቴ.9፡13 ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ድርሳን 20፡1/፡፡
 ከዚያ በኋላ የወይን ጠጅ አለቀ፡፡ እመቤታችንም “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” /ቁ.3/፡፡ ይህንንም ያደረገችው ልጇ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ስለምታውቅ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚያች ቀን በፊት ሁሉንም በልቧ ትጠብቀው ነበር እንጂ “የአምላክ እናት ነኝ፤ እርሱም አምላክ ነው” እያለች ራሷን ከፍ ከፍ አታደርግም ነበር፡፡ በዚሁ ሰዓት ግን የሆነው ነገር አሳፋሪ ነውና ሁልንም ለሚችል ልጇ በቀስታ አናገረችው፡፡ ከራሷ ፍላጎት ይልቅ ስለ ምእመናን የምትጨነቅ እናት መሆኗንም ያመለክታል፡፡ ልመናዋም “ሊያደርግ ይችል ይሆናል” በሚልና ጥርጣሬ በተሞላበት አኳኋን ሳይሆን በእርግጠኝነት እንደሚያደርግላት በማመን ነበር፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነቱን ልብ ይፈልጋል /ቅ.ቄርሎስ ዘአሌክሳንድርያ/፡፡
ሌለው የምረዳው ነገር ደግሞ ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ራሱን ለሕዝቡ መግለጥ ስለ ነበረበት ይህ ተአምር የአስተርእዮ አካልም እንደ ነበር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የተገለጠው የእርሱ አምላክነት ብቻ ሳይሆን የእናቱ እመ አምላክነትንም ጭምር ነበር፡፡
“ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” /ቁ.4/፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስ ጌታ ኢየሱስ ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም “ይታዘዝላቸው ነበር” ይለናል /ሉቃ.2፡51/፡፡ እዚህ ቦታ ግን ለእመቤታችን እንዲህ የሚላት በአምላክነቱ አገብሮ ተአዝዞ እንደሌለበት ለማጠየቅ ነው፤ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ የሚሠራበት የራሱ ጊዜ አለውና፤ በቀትር የሚሠራውን በሠለስት አይሠራውም፤ በሠለስት የሚሠራውም በነግህ አይሠራውምና፡፡ ይህ ቢሆንም ግን “እመቤታችን ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ትላቸዋለች” /ቁ.5/፡፡ ልጇ ምን ያህል እንደሚያከብራት ደግሞም የጠየቀችውን እንደሚያደርግላት ታውቃለችና /ቅ.ቄርሎስ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ይቆየን!!

የዮሐንስ ወንጌል የ9ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.1፡44-ፍጻሜ)!!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምለካ አሜን!!
“በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ፥ ፊልጶስንም አገኘና ተከተለኝ አለው” /ቁ.44/፡፡
 ጌታ በወርቃማው ስብከቱ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “የሚፈልግ እርሱ ያገኛል” /ማቴ.7፡8/፡፡ እውነት ነው! ፊልጶስ የተዘጋጀና እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ስለ ነበረው እነ እንድርያስ ከመጥምቁ እንደተማሩት ከማንም ሳይማር ጌታ “ተከተለኝ” ስላለው ብቻ ተከትሎታል፡፡ ቀጥለን እንደምንመለከተውም ሲያነበው የነበረው ትንቢት ሲፈጸምለት ስላየ በጣምኑ ተደስቷል፡፡ በእርግጥም ጌታ ይህንኑ ልቡን አይቶ ተከተለኝ ብሎታል /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ Homily on John 20፡1/፡፡
ይህ ፊልጶስ አስቀድመው ዮሐንስ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ” ሲል ሰምተው ከተከተሉተ ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ (የዓሣ ከተማ) ነበረ /ቁ.45/። ፊሊጶስ እንደ ናትናኤል ባይሆንም ከነብያትና ከሙሴ መጻሕፍት በትንሽ በትንሹ ያነብ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በኦሪት የጻፈለትን ነቢያትም ስለ እርሱ ትንቢት የተናገሩለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል” የሚለው፡፡ እዚህ ጋር ናትናኤልም የሕግና የነብያትን መጻሕፍት ያውቅ እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ናትናኤል ግን መልሶ “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” ብሎታል /ቁ.47/፡፡ ለምን እንዲህ አለው? ስንልም ገሊላ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖር ማኅበረሰብ የሚኖርባት፣ ለሃይማኖታዊ ጉዳይ ብዙም ግድ የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩባት አከባቢ እንደሆነች እንመለከታለን፡፡ ስለዚህም በሌሎቹ የአይሁድ ሕዝብ ዘንድ የተናቁ ነበሩ፡፡ አይሁድ ለኒቆዲሞስ “ነብይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ” ማለታቸውም ይህንኑ ሐሳብ ያጠናክራል /ዮሐ.7፡52/፡፡ ፊልጶስ ናትናኤል ከሚለው ሐሳብ ተቃራኒ የሆነ ነገር ተደርጐ ስላየና ተከራክሮ ማስረዳት ባይቻለው “የእኔ ንግግር ካላሳመነህ ጌታ ራሱ ያሳምንህ ዘንድ መጥተህ እይና ተረዳ” አለው /ቴዎዶር ዘሜውፕሳስትያ Commentary on John 1:1:46/።
 ናትናኤልም አሁን የፊሊጶስን ንግግር ለማረጋገጥ መጣ፡፡ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፡- ክዳት ተንኰል የሌለበት በእውነት እስራኤላዊ እነሆ አለ” /ቁ.48/፡፡ የሚገርም ነው! ናትናኤል “ከገሊላ መልካም ነገር ይወጣልን?” በማለቱ እንደሰው አስተሳሰብ መወቀስ ሲገባው ተመሰገነ፤ በውዳሴ ከንቱ ሳይሆን በአውነት በጌታ አንደበት ተወደሰ፡፡ እንዴትስ አልተወቀሰም ስንልም የናትናኤል ንግግር ከተንኰል የመነጨ ሳይሆን የፊሊጶስ ንግግር ከነብያቱ ትንቢት ጋር የተጋጨ መስሎት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም ናትናኤል ከመጻሕፍት ሲያነብ ያገኘውና የተረዳው ክርስቶስ ከዳዊት ከተማ ከቤተልሔም እንጂ ከናዝሬት እንደማይመጣ ነውና /ሚክ.5፡2/፡፡ ስለዚህ ናትናኤል እንደዚያ ማለቱና ክርስቶስም “ተንኰል የሌለበት ማለቱ” ትክክል ነበር፡፡ መጻሕፍትን አንዳንዶች እንደሚያደርጉት በራሱ ፈቃድ ለመተርጐም አለመሞከሩ ደግሞ የበለጠ ቅንነቱን ያሳያል /ቅ.ኤፍሬም ሶርያዊ Commentary on Tatian’s Diatessaron 4:14/፡፡
 የናትናኤል ቅንነት የበለጠ ግልጽ የሚሆነው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጌታ “ተንኰል የሌለበት” ሲለው “ከወዴት ታውቀኛለህ?” ማለቱም ጭምር እንጂ። “ኢየሱስም መልሶ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው” በማለት የበለጠ ያምን ዘንድ የነበረበትን ቦታ ብቻ ሳይሆን ጊዜውም ጭምር ነገረው /ቁ.49፣ ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡ በምሥጢራዊ አነጋገር ግን “አባትህ አዳምና እናትህ ሔዋን በወደቁበት ዕጸ በለስ ስር ወድቀህ በኃጢአት ተጐሳቁለህ ሳለህ በመለኰታዊ ባሕርዬ አውቃሃለሁ፤ አይቻሃለሁ” ማለቱ ነበር /ቅ.አምብሮስ/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ ከዚሁ የበለስ ግልድም አላቅቆ ጸጋውን ያለብሰን ዘንድ እኛን የጠፋነውን ለመፈለግ መጥቷል /አውግስጢኖስ/፡፡
 ከዚህ በኋላ ክርስቶስ የልቡን ስለነገረው ምንም ሳይጠራጠር እምነት ጨመረና “መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለ፡፡ በዚህ ሰዓት ፊልጶስ እንደነገረው ከማመን፣ ከመረዳት፣ ከመደነቅ፤ በሐሴት ከሞመላትና ለክርስቶስ እጅ ከመስጠት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበረውም /ቁ.50/፡፡ “ኢየሱስም መልሶ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? በል በዚህ ብቻ አትደነቅ! ገና ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ /ቁ.51/። እኔ ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) ስላይደለሁ ገና ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት እኔን ለማገልገል ሲወጡና ሲወርዱ ታያለህ” በማለት አባቱ ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያየውን ራዕይ መፈጸሙን ይነግረው ነበር /ቁ.52/፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ እንደተናገረው ናትናኤል መላእክት ክርስቶስ ፈታኙን ድል ሲያደርግ /ማቴ.4፡11/፤ ሲሰቀል፣ ከሙታን ተለይቶ ሲነሣ፣ ሲያርግ መላእክት ሲያገለግሉት አይቷል፡፡ ናትናኤል ባያይም ይህ ክስተት በቤተልሔም ግርግምም “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰበእ ሃሌ ሉያ” ሲሉ ተመልክተናል፡፡
አስተውላችሁ ከሆነ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ከነገረው በኋላ ናትናኤል አንዲትም ቃል መልሶ አልተነፈሰም /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒከማሁ/፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ላላመኑት እንደ ናትናኤል “ረቢ አማን አንተ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር- መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚል ቀና ልብ ይስጥልን፤ እኛንም በተዋሕዶ ያጽናን አሜን!!!!!!

FeedBurner FeedCount