Monday, May 21, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የ16ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡13-21)!!

የዮሐንስ ወንጌል የ16ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡13-21)!!

by Gebregziabher Kide on Wednesday, March 14, 2012 at 5:14pm ·
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
“ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው /ቁ.13/። “ይህ አነጋገር ከኒቆዲሞስ ንግግር ጋር ምን ግንኝነት አለው” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ግንኝነትስ አለው፡፡ ምክንያቱም ኒቆዲሞስ ጌታችንን “ከእግዚአብሔር የተላከ መምህር” አድርጎ አስቦት ስለ ነበር ጌታ ኒቆዲሞስን “አንተ እንደምታውቃቸው ምድራውያን መምህራን አድርገህ አታስበኝ፤ ምክንያቱም ከእኔ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ደግሞም የወረደ የለም፡፡ በሌላ አገላለጽ እነዚህ መምህራን በዚህ ምድር ስታያቸው እዚህ ምድር ብቻ የሚታዩና ከሰማይ የሌሉ ናቸው፤ እኔ ግን እዚህ በግዙፍ ሥጋ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ብታየኝም ከአባቴ ጋራ በህልውና አንድ ነኝ፤ በሰማይም በምድርም ሙሉዕ ነኝ፤ ሰማያዊ ሀብትን ሰማያዊ ዕውቀትን ገንዘብ አድርጌ የመጣሁኝ እኔ ብቻ ነኝ” ሲለው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ታድያ እርሱ ሙሉዕ በኵለሄ በመለኰቱ ሳለ እንዴት ወረደና ወጣ ይባላል?” ይላሉ፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስላቸዋለን፡- እንዲህ እየተባለለት ያለው ወልድ በመለኰቱ ዙፋኑን ትቶ መውረዱን ለመግለጥ ሳይሆን በሥጋ ማርያም ገዝፎ መታየቱን፣ የባሮቹን መልክ ይዞ መምጣቱን ለማመልከት ነው፡፡ የሰው ልጅ ብሎ ራሱን ሲገልጥም እርሱ ሙሉ ሰውነትን ማለትም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሥጋንና ፍጹም ነፍስን ነስቶ መገለጡን ለማመልከት ነው /St. John Chrysostom on the Gospel of John, hom.27:1/፡፡
 አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ቅዱሳን ወደ ሰማይ ቢወጡም ዓለምን ለማዳን አልወረዱም፡፡ ስለዚህ እኛም መውጣት ከፈለግን ሠረገላም ይሁን አውሮፕላን ሳያስፈልገን እንወጣ ዘንድ እንዲያወጣን የወረደውን ጌታ እንመን፡፡ መውጣት ከፈለግን ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም እንዲል ብቻችንን መውጣት አንችልም፡፡ ዳግም ተወልደን የሙሽራው ብልቶች ከሆንን ግን ከእርሱ ጋር አንድ አካል ስለምንሆን መውጣቱ ቀላል ነው /Augustine, Sermon on the New Testament Lessons 41:7-8/፡፡
 “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ” መጥቷልና፡፡ የዚህ የዳግም ልደታችን ምንጭ አንድም የመውረዱ ምሥጢር መስቀል ነውና /ቁ.14-15/። እነዚህ ሁለቱም ምሥጢራት ማለትም የጥምቀቱና የመስቀሉ ምሥጢር ክርስቶስ ለምንጠላው እንኳን ድንቅ የሆነ ፍቅሩን ያሳየባቸው ምሥጢራት ናቸው፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ኃጢአት ሲያበዙ በመርዘኛ እባብ ተነድፈው ሙሴ በሰቀለው የነሐሱ እባብ ከሞት እንደተረፉ አሁንም በመርዘኛው እባብ (ኃጢአት ፍዳ ባለበት በዲያብሎስ) የተነደፍን ሁሉ በነሐሱ እባብ (ኃጢአት ፍዳ በሌለበት በንጹሐ ባሕርይ በጌታ ስቅለት) እንደምንድን እየተናገረ ነው፡፡ ልናስተውለው የሚገባ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እባብ የክፋት ምሳሌ ብትሆንም ጌታችን (ሎቱ ስብሐትና) በነሐሱ እባብ እየተመሰለ ያለው ክፉ ሆኖ ሳይሆን በፍቃዱ “በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ…ኃጢአትን በሥጋ ለመኰነን” ስለ መጣ ነው /ሮሜ.8፡3፣ St. Gregory of Nyssa, Vita Moysis, PG 44:415/፡፡
ምክንያቱም፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” /ቁ.16/። የዘላለምን ሕይወት የሚሰጠን እርሱ ዘላለማዊ ስለሆነ ነው፤ ትንሣኤ ሕይወትን የሚሰጠን እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ምንም አፈርና ጭቃ ብንሆንም እንዲሁ (ያለ ምክንያት) ወደደን፡፡ እኛን ለማዳንም አንድያ (የባሕርይ) ልጁን እንጂ ከባሮቹ አንዱን፣ ወይም መላእክትን፣ ወይም ሊቃነ መላእክትን አልላከልንም፡፡ ምንም ቸርነቱን ለመቀበል ያልተገባን ብንሆንም እንዲሁ ደሙን አፈሰሰልን /St. John Chrysostom. Ibid/፡፡
 “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና” /ቁ.17/። በሌላ አገላለጥ በሥጋዊው እጅ ለሌለው እጅ፣ እግር ለሌለው እግር፣ ዓይን ለሌለው ዓይን በመንፈሳዊው ቅሉ ደግም ተሐድገ ለኪ ኃጢአትኪ- ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል ተሐድገ ለከ ኃጢአትከ- ኃጢአትህ ተሰርዮልሀል ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ እያለ ሊያድነው ካሳ ሊከፍልለት እንጂ ቀድሞ በፈረደበት ፍርድ ሌላ ፍርድ ሊፈርድበት አልመጣም፡፡ ስለዚህ “በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” /ቁ.18/። ያላመነው ሁሉ ትንሣኤ ቢኖሮውም ትንሣኤ ለዘሐሳር ነው፡፡ አሁን ተፈርዶበታል ሲልም አስቀድሞ ለዚያ ተወስኗል ማለት ሳይሆን አስቀድሞ ባለማመኑ ያው ትንሣኤው ለፍርድ ነው ማለት ነው፡፡/ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ/፡፡
 “ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው” /ቁ.19/። “ይህ ማለት” ይላል ክርስቶስ “እኔ ዓለምን እፈርድበት ዘንደ መጥቼ ብሆን ኖሮ ሰዎች ላለማመናቸው ምክንያት ባገኙ ነበር፡፡ ነገር ግን አመጣጤ የሰው ልጅን በሙሉ ከጨለማ ወደ ብረሃን አወጣ ዘንድ ነው፡፡ ወደ ብርሃን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ማለትም በእኔ ያምኑ ዘንድ ፈቃደኞች ያልሆኑ ይፈረድባቸዋል፤ ስለ ተፈረደባቸውም ምክንያት የላቸውም” /St. John Chrysostom. Ibid/፡፡
“ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” /ቁ.20-21/።
 እንግዲያስ ወንድሞቼ ሆይ! ጨለማው እንዳይጋርደን ወደ ብርሃን ለመውጣት እንቻኰል፤ እንድን ዘንድ እንንቃ፤ ጊዜ ሳለልን እንነሣ፤ ቀን ሳለልን ብርሃኑም  ሲያበራልን እንንቃ፤ ቀኑም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወደ እርሱ ብንመጣ ኃጢአታችን ይቅርታ ይደረግለታል፡፡ ምንም ጽድቅ ሳይኖረን በባዶ ራሳችንን ከፍ ከፍ የምናደርግ ሁሉ ትርፉ በጨለማ መቅረት ነውና ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንውጣ፡፡
 ሰው የእግዚአብሔር ፈቃድ ፍጥረት ነው፡፡ ኃጢአት ደግሞ የእኛ ፈቃድ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ አኛ ያደረግነውን ትተን እግዚአብሔር ወዳደረገልን የፍቅር ሥራ እንውጣ፡፡ የእኛ ሥራ ሕጸጽ እንዳለበት ስናውቅ ሕጸጽ ወደሌለበት የእግዚአብሔር ሥራ እንፍጠን፡፡ ንስሐ የመልካም ነገር ጅማሬ ናት፡፡ ሰው በጨለማ ውስጥ መኖሩን ሲያውቅ (በኃጢአት ውስጥ ለማለት ነው) ይቅርታ እንደሚያስፈልገውም ያውቃል፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ ሰውን እንዲሁ በማፍቀር ሰው የሆነው ጌታ ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!!

የዮሐንስ ወንጌል የ15ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡6-12)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
“ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” /ቁ.5/። “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብሎ እንደ ኒቆዲሞስ የሚጠይቅና የሚጠራጠር ሰው ካለ እንዲህ ብለን መልሰን እንጠይቀዋለን፡-  አዳም ከሕቱም መሬት የተወለደው እንዴት ነው? አስቀድሞ አፈር ቆይቶ በኋላ እንዴት ብሎ የተለያየ የሰውነት አካል ያለው ሰው ሆነ? አፈር ብቻ የነበረው በኋላ እንዴት ብሎ አጥንት፣ ጅማት፣ የደም ቧንቧ… ሆነ? ወንድሞች ሆይ! በዘፍጥረት መጀመርያ እንደምናነበው አፈር አፈር ነው፡፡ እግዚአብሔር በእጁ ሲያበጃጀው ግን ሰው ሆነ፡፡ አሁንም ሰው በማኅፀነ ዮርዳኖስ ውስጥ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ሆኖ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ይህ መለኰታዊ አሠራር ስለሆነ ሰዋዊ አመክንዮ እንሰጥ ዘንድ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ የምናምን እንጂ የምንጠራጠር አንሁን /St. John Chrysostom Homily on the Gospel of John Hom.25/፡፡
በእርግጥም አንድ ሰው አዲስ ሕይወትን ለመጀመር አሮጌው ሕይወቱን መጣል አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አሮጌው ሰውነቱ መሞት አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በጥምቀት በኵል ነው /ሮሜ.6፡4-5፣ Basil the Great, On the Spirit 15:35/፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለገባልን የትንሣኤ ተስፋ ዐረቦን እንቀበላለን /2ቆሮ.1፡22/፡፡
“ለምንስ በውኃ አደረገው?” ልትሉ ትችላለችሁ፡፡ ስለ ብዙ ምክንያት፡- አንደኛ “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ” የሚለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ /ሕዝ.35፡25/፡፡ ሁለተኛ ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይፈሳል፤ ጥምቀትም ለሁሉ ነውና፡፡ ሦስተኛ ውኃ ያነጻል፤ ጥምቀትም ያነጻልና፡፡ አራተኛ ውኃ ለወሰደው ፍለጋ የለውም፤ በጥምቀት የተሰረየ ኃጢአትም በፍዳ አይመረመርምና፡፡ አምስተኛ ውኃ መልክ ያለመልማል፤ ጥምቀትም መልክአ ነፍስን ያለማልማልና፡፡ ስድስተኛ በውኃ የታጠበ ልብስ ኃይል ጽንዕ ግዘፍ እየነሣ ይሄዳል፤ ምእመናንም ተጠምቀው ገድል ትሩፋት እያከሉ ይሄዳሉና፡፡ ሰባተኛ “ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ” ተብላ ነበር፤ አሁን ግን ክርስቶስ ገብቶባታልና ሕያውና ለባዊት ነፍስ ያላቸው ሰዎች ይገኝባታልና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ /ዘፍ.1፡20፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ማቴ.3፡17/፡፡ እናም ስለ ሌላ ብዙ ምክንያት፡፡
 ጌታ ይቀጥላል፤ እንዲህም ይላል፡- “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” /ቁ.6/።  ይህም ማለት “ከግዙፍ ሥጋ የሚወለደው ግዙፍ ሥጋ ነው፤  ከረቂቅ መንፈስ ቅዱስ የምትወለድ ነፍስ ግን መንፈሳዊት ናት፡፡ ከሥጋ ብቻ ስንወለድ “አፈር ነህና” የሚለው ማንነታችን ይቀጥላል፤ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ስንወለድ ግን ከማይሞተው እግዚአብሔር የማንሞት መንፈሳውያን ሆነን እንወለዳለን” ማለት ነው /ዮሐ.1፡12፣ Gregory of Nyssa/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ውኃው አሁን አብራከ መንፈስ ቅዱስ ማኅፀነ ዮርዳኖስ ስለሆነ “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” እንጂ “ከውኃ የተወለደ ውኃ ነው” አይባለም፡፡
 ኒቆዲሞስ ግን ነገሩ ረቀቀበት፤ እየተደናገረም ይደነቃል፡፡ ስለዚህም ጌታ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ” ይሏል /ቁ.7/። የሚያየው ነገር ግን የማያስተውለው ምሳሌ በማምጣትም ያስረዷል፡- “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” /ቁ.8/። ይህ ነፋስ “ወደዚህ ሂድ፤ ወደዚህም አትሂድ” የሚለው ሳይኖር እርሱ ወደ ወደደው ብቻ ይሄዳል፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ስንወለድም እንዲህ ነው፡፡ አንድም እንደምንወለድ እናውቃለን፤ እንዴት እንደሚወልደን ግን አናውቅም፡፡ አንድም በበዓለ ኃምሳ እንደ ሆነው መንፈስ ቅዱስ ትንቢት ሲያናግር ምሥጢር ሲገልጥ ሱባዔ ሲያስቈጥር ልናስተውለው እንችላለን፤ እንዴት እንደሚያድር ማወቅ ግን አይቻለንም፤ በሰዋዊ አረዳድም ልንረዳው አይቻለንም /Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 2:3-7/፡፡ ከመንፈስ የሚወለዱትም ልደት እንዲህ ነው፡፡ ይህም ማለት ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው አንተ ከወዴት እንደመጣህና (ከማን እንደተወለድክና) ወዴትም እንደምትሄድ (ሌላ ሀገር እንዳለህ) አያውቅም /ፊል.3፡20፣ Augustine, Tractes on the Gospel of John 12:5/፡፡
 “ኒቆዲሞስም መልሶ፡- ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት የባሰ ግራ ይጋባል/ቁ.9/፡፡ “ጌታችንም መልሶ፡- አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ይሏል /ቁ.10/፡፡ ከእናንተ መካከል “ዳግም ልደትና የኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር መሆን ምን ያገናኘዋል?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ሔዋን ከአዳም አንዲት የጎድን አጥንት እንዴት ተፈጠረች? ኤልሳዕ የሰጠመውን ብረት እንዲሰፍ እንጨቱ ግን ያለ ባሕርዩ እንዴት እንዲሰጥም አደረገው? እስራኤል ባሕረ ኤርትራን እንዴት ተሻገሩ? ንዕማን በፈለገ ዮርዳኖስ ውኃ ተጠምቆ እንዴት ነጻ? /St. John Chrysostom Ibid/ በእርግጥም ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ሲሆን የሂሶጵ ቅጠል ምሥጢር፤ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ሆኖ ነገር ግን ማታ በውኃ ታጥቦ ንጹሕ ይሆናል የሚለውን የኦሪቱ ሥርዓት፤ ያዕቆብ በኵር ሳይሆን ብኵርናን እንዴት እንደተቀበለ፤ ማርያም እኅተ ሙሴ እንዴት ነጻች የሚለውን ሁሉ የአይሁድ መምህር ሲሆን ሊያውቀው ይገባ ነበር /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatians Diatessaron 14:13/፡፡ 
 ከዚህ በኋላ ግን ጌታ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” /ቁ.11-12/ በማለት (ክርስቶስ) የሚናገረው ነገር በሰው ሕሊና ስለማይደረስ በእምነት እንዲቀበለው ይነግሯል፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ በባሕርይ አምላክነቱ ከባሕርይ አባቱና ከባሕርይ ሕይወቱ ጋር የሚናረውን ሁሉ በትክክል ያውቋል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን እንኳንስ ሰማያዊው ልደት ምድራዊው ነፋስ እንኳ ከየት መጥቶ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም፤ ኒቆዲሞስ ብቻ ሳይሆን እኛም አናውቅም /St. Cyril of Alexandria, Commentary on John/፡፡
ወንድሞቼ! እንግዲያስ ይህን ሰማያዊ ምሥጢር የምናምን እንጂ የምንጠራጠር አንሁን፡፡ ታላቁ መምህራችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረን በላይ ሌላ ምድራዊ መምህር ለራሳችን የምናመጣ አንሁን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

የዮሐንስ ወንጌል የ14ኛውን ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡1-4)!!

 (ከቻሉ ጸልየው በትዕግሥትና በሰቂለ ሕሊና ሆነው ያንቡት)!!
“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ” /ቁ.1/። ብዙ የዘመኑ የስነ መለኰት ተማሪዎች ኒቆዲሞስን የማታው (Extension) ተማሪ ይሉታል፡፡ ይህ ሰው አስቀድሞ በኢየሩሳሌም የፋሲካ በዓል የጌታችንን ተአምራት አይተው ካመኑት የፈሪሳውያን ወገን አንዱ ነው /ዮሐ.2፡23/፡፡ ኒቆዲሞስ በአንድ ቦታ ስለ ክርስቶስ አይሁዳውያኑን፡- “ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” ብሎ ሲከራከራቸው እናገኘዋለን /ዮሐ.7፡51/፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጌታችን ስለ ሰው ልጆች ፍቅር በመስቀል ላይ ከተሠዋ በኋላ ቅዱስ ሥጋውን አውርዶ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆን ገንዞ በክብር ሲቀብረው እንመለከተዋለን /ዮሐ.19፡39/፡፡ አሁን ግን ጌታችንን ገና በትክክል ማን መሆኑን ስላልተረዳ አብልጦ ይማር ዘንድ በሌሊት መጣ፡፡ በሌሊት መምጣቱም አይሁዳውያኑን ፈርቶ ነው፡፡ አይሁዳውያኑ አስቀድመው “እርሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚመሰክር ቢኖር ከምኵራብ እንዲያወጡት ተስማምተው ነበርና” /ዮሐ.9፡22/፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ተቀብሎታል፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም የሚተርፍ ታላቅ ምሥጢርን አስተምሮታል /St. John Chrysostom, Homily on the Gospel of John 24/፡፡
 ኒቆዲሞስ “ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ” በማለትና ጌታ ያደረጋቸውን ተአምራት በማድነቅ ብቻ ድኅነት የሚገኝ መስሎት ነበር፡፡ ስለዚህም “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን” ይለል /St. Cyril of Alexandria, Commentary on the Gospel of John 2/፡፡
 ጌታችንም “ኒቆዲሞስ! መምህር ሆይ፣ ጌታ ሆይ በማለትህ ብቻ ድኅነትን እንደምታገኝ አድርገህ አታስብ፤ መዳንህን ወደምትፈጽምበት ሕይወት ለመግባት አስቀድመህ ዳግመኛ ልትወለድ ያስፈልገሀል፡፡  እውነት እነግረሃለሁ፥ አንተ ብቻ ሳትሆን ማንም ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ይሏል /ቁ.3/።  በሌላ አገላለጽ “ዳግመኛ ካለተወለድክ በቀር፣ ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ ካልታደስክ በቀር /ቲቶ.3፡5/ ስለ እኔ የምታስበው ሁሉ ሥጋዊና ደማዊ ነው፡፡ እኔ ግን አሁን አንተ እንደምታስበው ከዚህ በፊት ወደ እናንተ እንደላክሁላችሁ ነቢያትም መምህራንም አይደለሁም፡፡ ይልቁንም እነዚህ አንተ የምታውቃቸው ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩልኝ መሲሕ መሆኔን ልትረዳ አትችልም፡፡  ዳግመኛም ካልተወለድክ በቀር የልጅነትን ማኅተም ስለማይኖርህ ከእኔ ጋር በመንግሥተ ሰማያት ዕድል ተርታ አይኖርህም፤ መንፈስ ቅዱስ ካላደረብህ በቀር እኔ የባሕርይ አምላክ ነው ብለህ ልታምን አትችልም” ይሏል /1ቆሮ.12፡3፣ St. John Chrysostom, Ibid/፡፡
 አዎ! በሰሌዳ ላይ በተሠራ ሥዕል ከውጭ በመጣ ቆሻሻ ሲዝግና ሲበላሽ የእርሱ ምስል የሆነው ሰው ስለ ሥዕሉ ሲል ሰሌዳውን ይወለውለዋል፤ ይሰነግለዋል፡፡ ይህም ሥዕሉ ያለበትን እንጨት በመጣል ሳይሆን ከውጭ መጥቶ ሥዕሉን ያበላሸውን ቆሻሻ በማስወገድ ወደ ጥንት ሁኔታው ይመልሰው ዘንድ የሚቻለውን ያደርጋል፡፡ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር ቃልም በአርአያው ተሠርቶ የነበረውን ሰው ያድሰው ዘንድ ፣ በኃጢአቱ የጠፋውን ኃጢአቱን በማስተስረይ ይፈልገውና ያገኘው ዘንድ መጣ፡፡ ራሱ በወንጌል “እኔ የጠፋውን ልፈልግና ላድን መጥቻለሁ” እንዲል /ሉቃ.19፡10/፡፡ ስለዚህ ሰው እንደገና ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር “አፈር ነህና” የሚለው አሮጌ ማንነቱን ይዞ ይቀጥላል፡፡ ዳግመኛ መወለድ ማለትም እንደገና ከሴት መወለድ ማለት ሳይሆን ነፍስ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል እንደገና መፈጠሯንና መወለዷን የሚያመለክት ነው /St. Athanasius, On The Incarnation 14:1-2/፡፡
 በእርግጥም ከመንፈስ ቅዱስ አዲስ ልደትን፤ ከአዲሱ ልደታችንም አዲስ የተፈጠረውን ሰውነትን፤ አዲስ ሰውነት ስናገኝም ክርስቶስ እርሱ ማን መሆኑን በትክክል እናውቃለን /St. Gregory of Nazianzus, On the Holy Spirit, Theological oration 5:28/፡፡
ስለዚህም ጌታችን፡- “ኒቆዲሞስ ሆይ! እኔ ከእግዚአብሔር መምህር ሆኜ እንደተላክሁ ካወቅክ፤ ያደርኳቸው ተአምራትም ይህንን ካረጋገጡልህ አሁንም አንድ ነገር ይቀራሃል፡፡ ይኸውም ሰው ሟች ሆኖ ማለትም ዳግመኛ በማይበሰብስ ባሕርይ ሳይነሣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ አይችልም /1ቆሮ.15፡50/፡፡ ስለዚህ ከእኔ ጋር ልትነሣ ከወደድክ እኔ እንደምሞተው ሞት ልትሞት እንደምነሣውም ትንሣኤ ልትነሣ ያስፈልጋሃል፡፡ ይህንንም የምትፈጽመው በጥምቀት በኩል ነው፡፡ ዳግመኛ ወደ ሥላሴ ማኅፀን ልትገባ ያስፈልገሀል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ይህን የምትፈጽመው በጥምቀት ውኃ በኩል ነው፡፡ ይህ ወደ ሥላሴ ማኅፀን የምትገባበት ውኃ እንደ ድሮ አጠራርህ ውኃ አይምሰልህ፡፡ እዚህ ማኅፀን ውስጥ ስትገባ የሥላሴን እንጂ የውኃውን ስም የማትጠራውም ለዚሁ ነው፡፡ አንድ ሕፃን በእናቱ ሽል /ማኅፀን/ እንደሚፈጠረው ሁሉ አንተም በዚሁ ማኅፀን ዳግም ካልተፈጠርክ በቀር የእኔን ሞትና ትንሣኤ አትተባበርም” ይሏል /ሮሜ.6፡5፣ Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 2:3.3/፡፡
 ኒቆዲሞስ ግን ሰው ከአዳምና ከሔዋን ሲወለድ እንጂ ከቅድስት ሥላሴ፣ ከቤተ ክርስቲያን (በምሥጢረ ጥምቀት በኩል) የሚገኘውን ረቂቁን ልደት ምን እንደሆነ ስለማያውቅ ይደናገራል፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያውቀው ሞትን የሚወልዱ እንጂ ሕይወትን የሚወልዱ ወላጆችን አይደለም፤ ምድራዊውን እንጂ ሰማያዊውና ረቂቁን ልደት አያውቅም፤ ከወንድና ከሴት ፈቃድ የሚገኘውን ልደት እንጂ ከአብ፣ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚገኘውን ልደት አያውቅም /Augustine, Tractes on the Gospelof John, 11:6/፡፡
ስለዚህም “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” ይላል /ቁ.4/።
 የሚገርመው ዛሬም ብዙ ሰዎች እንደ ኒቆዲሞስ ተቸግረው ማየታችን ነው፡፡ “እንዴት ቅድመ ዓለም ከአብ ተወለደ ትሉናላችሁ”፤ “እንዴት እግዚአብሔር ሰው ይሆናል?” ፤ “እንዴት ሰው ውኃ ውስጥ ገብቶ ዳግም ይወለዳል?” በማለት ፍጥረታዊ አመክንዮ ለማምጣት ይጥራሉ፡፡ ጌታ ሰማያዊ ነገር ሲነግረው ኒቆዲሞስ ግን ምድራዊ ነገርን ያወራል፡፡ ዛሬም ሰማያዊዉን ምሥጢር የተረዳነውን ያህል ስንነግራቸው ምድራዊ ማረጋገጫ ይፈልጋሉ፡፡ በሕጻን አእምሮአቸውም “እንዴት ሆኖ” በማለት ራሳቸውን ያስጨንቃሉ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ለመሰሉ ሰዎች እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም” /1ቆሮ.2፡14/፡፡
 ወንድሞቼ! ሰማያዊውን ምሥጢር በምድራዊ አመክንዮ ለመረዳት አንሞክር፡፡  እግዚአብሔር “ይሆናል፤ ይደረጋል” ካለን “አሜን፤ ይሁን፤ ይደረግ” ብለን መረታት እንጂ ሽሽት አያስፈልገንም፡፡ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይህ አስተሳሰባችን እሾክ ይሆንብንና “ኢየሱስ ጌታ ነው፤ ክርስቶስ መምህር ሆኖ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣ እናውቃለን” እያልን ነገር ግን ወደ መንፈሳዊ መረዳት ሳንደርስ እንደተደናበርን እንቀራለን፡፡ የሚያስፈልገው ግን እምነት ብቻ ነው፡፡

የዮሐንስ ወንጌል የ13ኛው ሳምንት ጥናት (ዮሐ.2፡18-ፍጻሜ)!!

ወንጌላዊው “ስለዚህ አይሁድ መልሰው፡- ይህን ስለምታደርግ (የምንሸጠውን ስለምትገለባብጥ) ምን ምልክት ታሳየናለህ? አሉት” በማለት ይቀጥላል /ቁ.18/። የሚገርም ነው! አይሁድ በዚህ ንግግራቸው፡- “ቤቱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረጋችን አግባብነት አለው፤ አንተ ይህን ቤት የአባቴ የጸሎት ቤት ነው ስትል ግን (ሎቱ ስብሐት) ሕግን ባታውቅ ነው፡፡ ከምድራውያን ነገሥታት ከሌዋውያን ካህናት ሳትሆን ይህን ስለምታደርግስ ምን ምልክት ታሳየናለህ?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ አቤት! ሰው በኃጢአት ሲደነዝዝ ለክፋቱም ምልክትን ይሻል፡፡ ዛሬ አንዳንድ ሰነፎች፡- “አታጭሱ፤ አትቃሙ፤ አትጠጡ፤ በጾም ወራት ዓሣ አትብሉ… የሚል ጥቅስ የት አለ?” እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ጌታም እዝነ ልቡናቸው ስለታወረ ለጊዜው አልገባቸውም እንጂ እንዲህ በማለት ምልክትን ይሠጣቸው ነበር፡- “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” /ቁ.19/።
 “ሁሉም ላይገባቸው (ደቀ መዛሙርቱም ጭምር) ለምን እንዲህ ማለት አስፈለገው?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስላችኋለን፡- ጌታ እንዲህ የሚያደርገው እርሱ ሁሉንም አዋቂ መሆኑን እንዲገነዘቡ ነው /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን 23/፡፡ በእርግጥም ለጊዜው ግራ ቢገባቸውም (ደቀ መዛሙርቱ ተጠቅመው እነርሱ አልተጠቀሙበትም እንጂ) ከገደሉት በኋላ  ምን ማለቱ እንደሆነ ገብቶአቸዋል /ማቴ.26፡61፣ አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 10:251-52/፡፡
እዚህ ጋር ሌላ የምንረዳው ቁም ነገር አለ፡፡ ይኸውም አንዳንድ መንፍቃን እንደሚሳደቡት ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ አለመሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ቃሉ እንደሚያስረዳን ነፍሱን የማኖርም የማንሣትም ሥልጣን እንዳለው “በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” እያለ በግልጽ እየነገረን ነውና /ዮሐ.10፡18፣ Hilary of Poitiers, On The Trinity 9:12/፡፡
 አሁንም እነዚህ አይሁድ ጌታ በሚናገራቸው ነገር የባሰ ግራ ተጋብተው፡- “ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታንጸዋለህን?” በማለት ይጠይቁታል /ቁ.20/። በሰሎሞን የታነጸው ቤተ መቅደስ የመጀመርያው ቤተ መቅደስ በ20 ዓመት ያለቀ ነው፡፡ እስራኤላውያን ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው በዘሩባቤል ዘመነ መንግሥት የተሠራው ግን አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶባቸዋል /ዕዝራ.6፡15/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ሁሉም ባይገባቸውም ጌታ ማኅደር ስለሚባል ሰውነቱ እንጂ ስለዚያ ቤተ መቅደስ እየተናገረ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው እንኳን ወንጌሉን ጌታ ከተነሣ በኋላ ስለሚጽፈው የክርስቶስ ንግግር ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዳ፡- “እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” የሚለው /ቁ.21/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ጌታ ስለ ሰውነቱ እየተናገረ መሆኑን ለምን በግልጽ አልተናገረም?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም “ለጊዜው የሚነግራቸውን በቀላሉ ላይቀበሉት ስለሚችሉ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ተደናገሩት ለዚሁ ነው” ብለን እንመልስለታለን /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/።
ስለዚህ ጌታ “ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ያላቸው ማኅደር ስለሚባለው ሰውነቱ እንደ ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ማለትም ይነሣል ብለው የተናገሩትን ነብያትንና ኢየሱስ ራሱ አነሣዋለሁ ብሎ የተናገረውን ቃል አመኑ” /ቁ.22/። አዎ! አስቀድመን እንዳልነው፡- “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱትና አባቴ ያነሣዋል” ሳይሆን “እኔ አነሣዋለሁ” እንዳላቸው አሰቡ፡፡ አባቱ አስነሣው ቢባልም የሚጣላ ነገር አይደለም፡፡ እርሱና አብ አንድ ናቸውና፡፡ ስለዚህ እንደተናገረው ተነሣ፤ እነርሱም አመኑበት፤ ሕይወትም ሆናቸው /ሮሜ.1፡4፣ቅ.አምብሮስ Tractes on the Gospel of John 10:11/፡፡
ወንጌላዊው ይቀጥልና፡- “ኢየሱስ በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፥ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ” ይለናል /ቁ.23/፡፡ “የትኛውን ምልክት?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ በቤተመቅደስ የነበሩትን ሻጮች ማስወጣቱን እንደ ምልክት አይቶት ሳይሆን ሌላ ያደረጋቸው ነገር ግን በዚሁ መጽሐፍ ያልተጻፉ ተአምራት እንዳደረገ ያስገነዝበናል /አርጌንስ Commentary on the Gospel of John 10:319/፡፡
“ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር” /ቁ.24/። “ለምን?” ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፡፡ ጌታ እነዚህን ሰዎች ያልተማመነባቸው ከልባቸው አምነውበት ሳይሆን ባሳያቸው ተአምራት ለጊዜው በስሜት ተነድተው “አምነናል” እንዳሉ ያውቃልና፤ ልባቸው ብዙ አፈር የሌለበት ጥልቅ መሬትም እንደሌለው ጭንጫ እንደሆነ ያውቃልና /ማቴ.13፡5/፡፡
 አዎ! እርሱ ክርስቶስ ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡ “እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ” የሚያውቅ አምላክ ነው /ቁ.25፣ መዝ.32፡15/፤ ጠቢቡ እንዳለው “እርሱ ብቻ የሰውን ልብ ሐሳብ ያውቃል” /1ነገ.8፡39/፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ሰዎች፣ በፍጥረታቱ ልብ የሚመላሰውንና የሚታሰበው ምን እንደሆነ ለማወቅ ሌላ ምስክር አይፈልግም፤ ራሱ ፈጣሪ ነውና ይህንን ለማወቅ አባቱን መለመን አያስፈልገውም /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ ዝኒ ከማሁ/፡፡
ወንድሞቼ! ዛሬም “ክርስቶስ አምላክ አይደለም” የሚሉ ብዙ ልበ ስሑታን አሉና ይህን እውነት ልንመሰክርላቸው ያስፈልጋል፡፡ “የጾመው እሴተ ጾምን (የጾምን ዋጋ) የሚሰጥ ነው… የጸለየው ምልጃን የሚሰማ ነው… የተራበው የተራቡትን በቸርነቱ የሚያጠግብ ነው… የተጠማው የሕይወትን ውኃ የሚያድል ነው… የደከመው እርሱ ራሱ ሰንበት ነው… ያለቀሰው እርሱ ራሱ ያዘኑትንን ዕምባ የሚያብስ ነው…፡፡ ይህን ሁሉ ያደረገው ግን እኛንም እናተንም ከመውደዱ የተነሣ ነው፡፡ እርሱ ዝቅ ዝቅ አድርገን ልናየው የሚገባው ጌታ ሳይሆን ለእኛ ብሎ ደሀ የሆነ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለምም አባት ነው፡፡ ስለዚህ እርሱን ለማመን አትቸገሩ” ብለን እንመስክርላቸው፡፡
ይህን ሁሉ እንድናደርግ በቸርነቱም መንግሥቱ እንዲያወርሰን ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡

FeedBurner FeedCount