በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ጌታ ለተገፉት ምርኩዛቸው ለተጨነቁትም
ዕረፍት ነው፡፡ አዎ! ሳምራይቱ ሴት በጧት ውኃ ልትቀዳ አለመምጣቷ መለኰታዊ ዕቅድ ከመሆኑ በተጨማሪ ውኃ የሚቀዱት
ሴቶች በእርሷ ላይ የሚሳድሩት ተጽዕኖ እንዳለ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ አዋልደ ሰማርያ በማታገኝበት ሰዓት ብቻዋን
“ውኃ ልትቀዳ መጣች” /ቁ.7/። ይገርማል! ርብቃ ከይስሐቅ፣ ራሄል ከያዕቆብ እንዲሁም የካህኑ የዮቶር ልጅ ከሙሴ
ጋር የተገናኙት በውኃ ጉድጓድ ነበር፡፡ ይህች ሳምራይቱ ሴትም ከነፍሷ እጮኛ ከክርስቶስ ጋር የምትገናኘው በያዕቆብ
ጕድጓድ ነው፡፡ በዚሁ ሰዓት ነው እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ በሄዱ ጊዜ ውኃን በደመና እየቋጠረ
ምድርን የሚያረሰርሳት ጌታ እንደ ምስኪን “ውኃ አጠጪኝ” የሚላት /ቁ.8/። እንዴት ያለ ግሩም ንግግር፣
እንዴት ያለ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ ቃል ነው? ምክንያቱም የሴትዮዋን መሻት ይመለከት ዘንድ ውኃ አጠጪኝ ይላታልና፡፡
በእርግጥም ጌታችን ውኃ ተጠምቶ ነበር፡፡ የእምነት ውኃ! የሰው ልጆች የመዳን ውኃ! ስለዚህም “አንቺ ሴት!
እምነትሽን ተጠምቻለሁ፤ መዳንሽን ተርቤአለሁ” ይላታል /ቁ.34፣ አውግስጢኖስ- Sermon On New Testamen
Lessons, 49:3/፡፡
ሳማራይቱ ሴትም ጌታን በአለባበሱ አንድም በንግግሩ ብታውቀው “አንተ
አይሁዳዊ እኔም ሳምራዊት ስሆን እንዴት ውኃ አጠጭኝ ብለህ ትለምናለህ? አይሁድ ከሳምራውያን ጋር በሥርዓት
እንደማይተባበሩ አታውቅምን?” ትሏለች /ቁ.9/። ሴቲቱ ይህን የምትለው በቅንነት እንጂ በክፋት አልነበረም! “እኛ
ሳምራውያን ከእናንተ ከአይሁድ ጋር መነጋገር አንችልም” ሳይሆን በመገረም “አንተ አይሁዳዊ ስትሆን እኔም ሳምራዊት
ስሆን እንዴት ያንን የጥል ግድግዳን አፍርሰህ በፍቅር ልታነጋግረኝ ቻልክ?” ትሏለች /ቅ.ዮሐንስ
አፈወርቅ-Homilies On St. John,31:4/፡፡
የፍቅር ጌታም የሴትዮዋን ልብ በሳምራውያንና
በአይሁድ መካከል ካለው መለያየት ይልቅ ስለ ማየ ሕይወት እንድታሰላስል ያደርጋታል፡፡ ስለዚህም፡- “የእግዚአብሔርን
ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር”
ይላታል /ቁ.10/። እንዲህ ማለቱም ነበር፡-“ልጄ! አሁን ስለዚያ መለያየትና ጥል ሚነገርበት ሰዓት አብቅቷል፡፡
የሚያነጋገረሽ አምላክ ወልደ አምላክ፣ የሰው ልጆች ተስፋ፣ ኃይሉ ለአብ ወጸጋ ዘአሕዛብ እርሱ መሆኑን ብታውቂ
ሁለመናሽን ከኃጢአት እድፍ ትርቂበት ዘንድ አንቺው ራስሽ እንደ መዝሙረኛው ዳዊት “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ
አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች” እያልሽ በለመንሽው ነበር” ይላታል /መዝ.42፡1፣
St.Ambros-Of The Holy Spirit,1:16;175/፡፡
ሴቲቱም እንደ ግራ መጋባትም እንደ
መደነቅም ብላ፡- “ጌታ ሆይ! ቀድተህ ታጠጣኛለህ እንዳልል መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ ከያዝከው ውኃ
ታጠጣኛለህ እንዳልልም በእጅህ መንቀል አልያዝክም፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?” ትሏለች/ቁ.11/፡፡
አስቀድመን እንዳልነው የሴትዮዋ ንግግር እንደ አይሁድ በተንኰል የተለወሰ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው አሁንም
በአክብሮት “ጌታ ሆይ!” ስትለው የምናስተውለው፡፡ እንዴት ያለች ልበ ንጹሕ ሴት ነች? ቅንነቷ ምሁረ ኦሪት
ከተባለው ከኒቆዲሞስ በላይ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም ምሁረ ኦሪት ቢሆንም አንዳንድ የሚተገብራቸው ነገር ግን ምን
ማለት እንደሆኑ የማያስተውላቸው ነገሮች ነበሩ (ለምሳሌ፡- የማንጻት ውኃ እንዴት ያነጻ እንደ ነበር አያውቅም)፡፡
ይህች ሴት ግን “አባታችን ያዕቆብ እና ልጆቹ ከብቶቹም ውኃ የጠጡት ከዚህ ጕድጓድ ነው፡፡ ሌላ የተሻለ የውኃ
ጕድጓድ ቢኖራቸው ኖሮ ሁሉም ከዚህ ጕድጓድ ብቻ ባልቀዱ ነበር፡፡ አንተ ግን ሌላ ከዚህ የተሻለ ውኃ እሰጥሻለሁ
እያልከኝ ነው፡፡ እንግዲህ ከአባታችን ከያዕቆብ ካልበለጥክ በስተቀር ሌላ የተሻለ ውኃ እንዴት መስጠት ይቻልሃል?”
ትሏለች፡፡ ንግግሯ ከቅንነት የመነጨ መሆኑን የበለጠ የምናውቀው ደግሞ ጌታችን እንዲህ ሲላት፡- “ሌላ የተሻለ ውኃ
ካለህ እንዴት መጀመርያ አንተው ራስህ አትጠጣም” ማለት ትችል ነበር፡፡ የዋሕነቷ ግን እንዲህ እንድትል
አልፈቀደላትም /ቁ.12, St.John Chrysostom,Ibid/፡፡
ጌታችን ይቀጥላል፡፡ ሴትዮዋ እርሱ
ወደሚፈልገው አቅጣጫ እየመጣች ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ ጊዜ “አዎ! አንቺ እንዳልሽው እኔ ከያዕቆብ እበልጣለሁ”
አይላትም፡፡ ከዚሁ ይልቅ ጥበብ በተመላበት ንግግር፡- “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ የምሰጠው
ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈስ የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ ለዘላለም አይጠማም” ይላታል
/ቁ.13-14/። በዚህ ንግግሩ በያዕቆብ ውኃና እርሱ በሚሰጠው የሕይወት ውኃ ያለው ልዩነት ቀስ አድርጎ እየነገራት
ነበር፡፡ “በእኔ የሚያምን ሁል ጊዜ ከቶ አይጠማም፤ ጽምዓ ነፍስ አያገኘውም” እንዲል /ዮሐ.6፡35/፡፡ እንዲህ
ሲላትም እኔ ያስተማርኩትን ትምህርት እኔ በጥምቀት የሰጠሁትን ልጅነት የተቀበለ ሁሉ ዳግመኛ በነፍሱ አይጠማም
ማለቱ ነበር፡፡ እውነት ነው! ይህ ማየ ሕይወት በደስታ የሚጠጡት መለኰታዊ ውኃ ነው፤ ይህ ውኃ ዳግመኛ የሚያስጠማ
ውኃ አይደለም፤ ይህን ውኃ የሚጠጣ መጽሐፍ እንደሚል ዳግመኛ አይጠማም፤ ይህ ውኃ እንስራውን ካልሰበረ (ሰውነቱን
በኃጢአት ባላቆሸሸ) ሰው ጋር ለዘላለም ይኖራል /ኢሳ.12፡3፣ዮሐ.7፡38፣ ቅ.አምብሮስ, On the Holy
Spirit 1:16:181-182/፡፡
ዕጹብ ድንቅ ነው! ሴቲቱ በዚሁ የጌታ ንግግር ይህ ጥምን የሚቆርጥ
የሕይወት ውኃ ትጠጣ ዘንድ ጎመጀች፤ ስትመካበት የነበረው የአባቶቿ ጕድጓድም ናቀችውና፡-“ጌታ ሆይ! እንዳልጠማ
ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ” ትላለች /ቁ.15/። አስቀድሞ “ትለምኝኝ ነበር” ብሏት ነበር፤
ያላት አልቀረ ይሄው ተፈጸመ፡፡ አሁን የሴትዮዋን ሁናቴ በጽሞና አስታውሱ! ሰማያዊውን ውኃ ስትጐነጭ፤ እንስራዋን
ስትጥለው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ያዕቆብ ጕድጓድም ትዝ አይላትም፡፡ እንስራዋ የት እንደጣለቸው ትዝ አይላትም፡፡
ተወዳጆች! እምነቷ እንዴት እያደገ እንደሄደ ልብ በሉ፡፡ አስቀድማ ጌታዋን “አይሁዳዊ!” አለችው /ቁ.9/፤ ቀጥላ
“ጌታ ሆይ!” አለችው /ቁ.11/፤ ትንሽ ቆይታም ከያዕቆብ እንደሚበልጥ አስተዋለች /ቁ.12/፤ አሁን ደግሞ
የሕይወት ውኃ ምንጭ እርሱ መሆኑን ተገነዘበች /ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ዝኒከማሁ/፡፡
ወዮ! አባት ሆይ
የሳምራይቱን ሴት እንስራ ያስጣለ ፍቅርህ እንዴት ብርቱ ነው?! ጌታ ሆይ! ከደሀይቱና ከተጨነቀችው ሳምራይቱ ሴት
ጋር የተነጋገረ ትሕትናህ እንዴት ግሩም ነው?! አባት ሆይ! ዛሬም ነፍሳችን እንደ ዋልያ አንተን ተጠምታለችና
የሰጠኸንን ማየ ሕይወት (ክቡር ደምህ) በአግባቡ እንጠጣው ዘንድ እርዳን! በኃጢአታችን ምክንያት እንደ ሳምራይቱ
ሴት ያፈርን ብዙዎች ነንና በቸርነትህ ተቀበለን! ከወራጅ ውኃ ጋር የምንታገል ብዙዎች ነንና ከማየ ገነት ታጠጣን
ዘንድ እንማጸናሃለን! ፍቅርህ፣ ጥበብህ፣ ትሕትናህ ሳምራይቱን ሴት እንዳንበረከካት እኛንም ያቅፈን ዘንድ ፈቃድህ
ይሁን! ሳምራይቱ ሴት ቀስ በቀስ እምነቷ እየጨመረ እንደሄደ እኛም በእምነትና በምግባር እንድናድግ ክንድህ ትርዳን
አሜን ለይኩን ለይኩን!