Saturday, July 7, 2012

መጥምቁ ዮሐንስ እና አገልግሎቱ!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

   የታሪክ መዛግብት እንደሚናገሩት አንድ ንጉሥ ወደ አንድ አከባቢ ከመሄዱ በፊት መንገዱን ያዘጋጁ ዘንድ አስቀድሞ መልእክተኞችን ይልካል፡፡ የፍጥረታት ሁሉ ጌታ እና ንጉሥ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም እኛን ለማዳን ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት መንገዱን ይጠርጉ ዘንድ ብዙ ነቢያትን ልኳል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስም በበረሐ ተገድዶ ሳይሆን የጌታ ፍቅር አስገድዶት ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ እየጮኸ መልእክተኛ ሆኖ የመጣ ታላቅ ነቢይም ሐዋርያም ነው፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው፡- “እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈያለው /ማር.12-3/፡፡

    ወንጌላዊው ስለዚሁ የጌታ መልእክተኛ የተነገሩትን ሁለቱም ትንቢቶች እያነሣ ይናገራል /ሚል.31 ኢሳ.403/፡፡ ሚልክያስየጌታ መልእክተኛብሎ የጠራው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ሕዝቡን በንስሐ መንገድ እየጠረገ ስለ ነበረ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጌታን ለመጀመርያ ጊዜ ያየው በሥጋ ማርያም ሳይሆን በዐይነ እምነት ነበረ፡፡ ምንም እንኳን በእናቱ ማሕፀን ውስጥ የነበረ ቢሆንም ጌታውን በዐይነ እምነት ሲመለከተው ግን በደስታ ዘሏል /ሉቃ.144/፡፡

   ጠርጡለስ የተባለ የሁለተኛው ክፍለ ዘመን ምሁርመዝሙረኛው ዳዊት፡- ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ እንዳለ መጥምቁ ዮሐንስ መልእክተኛ ብቻ ሳይሆን መብራትም ነበረብሏል፡፡ በእርግጥም መስማትን ለሰሙት ወገኖች የሚያበራ ፋና ነበረ፡፡

   “ወንጌላዊውኢሳይያስም ዮሐንስንበምድረ በዳ የሚጮህ ድምጽብሎታል፡፡ እርሱ አዳኙን ክርስቶስ ለመግለጥ እንደ ተላከ የምሕረት መልአክ፣ እንደ አንበሳ በበረሐ እየጮኸ በኃጢአት የጠነከረውን ልባችንን ይሰብር ዘንድ የመጣ መልእክተኛ ነውና፡፡ ሰውነታችንን መልእክተኛ ለሆነለት ለእግዚአብሔር በግ ለክርስቶስ ማኅደር እንድንሆን ያዘጋጅ ዘንድ የመጣ ነብይ ነውና፡፡

   “ዓምደ ተዋሕዶየተባለው ታለቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስምመጥምቁ ዮሐንስ ከንጋቱ ኰከብ በፊት የነበረ ፀሐይይሏል፡፡ ምክንያቱም ዮሐንስ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ የሚያበራ ፋና ነበረና፡፡ በጨለማ ውስጥ ይመላለሱ ለነበሩት ሁሉ ወደ እውነተኛው ብርሃን ይደርሱ ዘንድ ያዘጋጅ ነበረና፡፡

   ዮሐንስ ያዘጋጀው የነበረው ጥርግያ የጌታን ወንጌል ነበረ፡፡ የትምህርቱ መሠረታዊ ዓላማም እያንዳንዱ ሰው የንስሐ ፍሬ እንዲያፈራ ማድረግ ነበር፡፡ የንስሐ ፍሬ ሲባልም የሠሩትን ኃጢአት መተው ብቻ ሳይሆን ፍሬም ጭምር ማፍራት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-በሰረቁበት እጅ አለመስረቅ ብቻ ሳይሆን በዚያ ወዶ መስጠት፣ በዘፈኑበት ከንፈር ዘፈንን መተው ብቻ ሳይሆን በዚያ መዘመር፣ አመንዝረን እንደ ሆነም ይኸን መተው ብቻ ሳይሆን ከሕጋዊ ሚስታችንም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜአት መቆጠብን የመሳሰለ ሁሉ ነው፡፡

    መጥምቁ ዮሐንስ በቃሉ ብቻ ሳይሆን በልብሱም ጭምር ይሰብክ ነበር፡፡ ምግባራችን እንደ ሞተ እንስሳ ቁርበት ጠፍር፣ ኃጢአታችንም እንደ ግመል ጠጉር ለበዛብን ለእኛ ክብር ይግባውና የእግዚአብሔር በግ እርሱ ክርስቶስ ይቆስልልን ዘንድ እንደ መጣ ይመሰክር ነበር፡፡

   እኛ ሁላችን ወደ ገዛ መንገዳችን ስናዘነብል፤ በከንቱም የማይበላውን በልተን ስንሞት እርሱ 30 ብር ተሸጦ እኛን ግን በማይተመን ዋጋ ገዝቶ ከዓለቱ ማር በልተን እንደሚያጠግበን ያውጅ ነበረ /መዝ.8116/፡፡

የመጥምቁ ረድኤትና በረከት አይለየን! የንስሐ ፍሬም እንድናፈራ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!

Friday, July 6, 2012

ሰው ከዚሁ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል- የዮሐንስ ወንጌል የ30ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.6፡41-52)!


   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  ቅዱስ ጳውሎስ በአንድ ወቅት ስለ አንዳንድ ሰዎች ሲናገር ለፊሊጵስዮስ ክርስቲያኖች፡- “ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ ክብራቸው በነውራቸው ነው” ብሏቸው ነበር/ፊሊ.3፡19/፡፡ ይህ የሐዋርያው ቃል በእነዚህ የአይሁድ ሰዎች በገሃድ ሲፈጸም እናስተውለዋለን፡፡ እንዴት ቢሉ እነዚህ ሰዎች ሆዳቸው ሲሞላና ሲጠግብ ጌታችንን “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው” ይሉታል፤ ሊያነግሡትም ይሻሉ /ቁ.14-15/፡፡ የዘላለምን ሕይወት ስለሚሰጠው ሰማያዊ መና፣ ዳግም ስለማያስጠማው ይልቁንም በደስታ ስለሚንቆረቆረው አርያማዊ ውኃ ሲነግራቸው ግን ያጕረመርማሉና፡፡ ከሥጋዊው መብል ይልቅ መንፈሳዊውን መብል እንዲሹ ሲጋበዙ፣ ስለ ትንሣኤ ሕይወት ሲነገሩ፣ አልዕሉ አልባቢክሙ- ልቡናችሁን በሥጋዊው መብል ከማባከን ወደ ሰማያዊው መብል አንሡ ሲባሉ ሊደነቁና ሊገረሙ ሲገባቸው መታወክ ጀመሩ፤ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩ /ቁ.41/፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ሲበሉና ሲጠግቡ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው” ብለው ይደነቃሉ፤ ጌታችን “ከሰማይ ወርጃለሁ” ሲላቸው ግን ሊሰሙት አልወደዱም፤ ይልቁንም አንጐራጐሩበት እንጂ፡፡ እርስ በእርሳቸውምአባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል?” ተባባሉበት እንጂ /ቁ.42/። በእርግጥም በሥጋዊ ዓይን ሁሉንም የሚመለከት ሰው ከክርስቶስ አንዳች ረብሕን አያገኝም፡፡ ጌታችን እንዴት ከሰማይ እንደወረደ መመርመር፣ በዘርዐ ብእሲ የተወለደ የዮሴፍ ልጅ ነው ብሎ ማሰብ፣ እንደላው ዘንድ እንዴት ሥጋዉን ሊሰጠን ይችላል ብሎ መታወክ ሥጋዊና ደማዊ አመክንዮዎችን የሚጠይቁ ናቸውና ምንም አያገኙም፡፡ ቀዳማዊ ልደቱ በእነርሱ ዘንድ የሚመረመር አይደለም፡፡ ይህን ባለማወቃቸውም አልተወቀሱበትም፡፡ ጌታችንም “እኔስ እናንተ እንደምትሉት የዮሴፍ ልጅ አይደለሁም” አላላቸውም፡፡ የዮሴፍ ልጅ ሆኖ ሳይሆን ውስጣቸው በሌላ ነገር ስለተመላ ስለ አስደናቂው ልደቱ ቢነግራቸውም ስለማይሰሙት እንጂ፡፡ ስለ ደኃራዊ ልደቱ ካላወቁስ ስለ ቀዳማዊ ልደቱ ያውቃሉ ተብሎ እንዴት ይታሰባል? ስለዚህ ያንጐራጐሩበትን ምክንያት ትቶ በሌላ ዘዴ ያቀርባቸው ዘንድ ወደደ /Saint John Chrysostom, Homilies on St. John, Hom.46:1./፡፡

   እንዲህ ነበር ያላቸው፡- “እርስ በእርሳችሁ የምታንጐራጉሩ አትሁኑ፡፡ አለማመናችሁ ሰማያዊው ልደቴን እንዳትመለከቱ ከልክሎአችኋልና፡፡ ስለዚህም የዮሴፍ ልጅ እንደሆንኩኝ ታስባላችሁ /ቁ.43/፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ የላከኝ አባቴ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ካልሰጠኝ በእኔ ማመን የባሕርይ ልጅነቴንም ማወቅ መረዳት የሚቻለው የለም /ቁ.44፣ Saint Cyril the Great/፡፡ እንዲህ ብዬ ስነግራችሁም ነጻ ፈቃድችሁን ተጋፍቶ አባቴ በእኔ እንድታምኑ ያደርጋችኋል ማለት አይደለም፤ ይልቁንም እናንተ ለማመን ፈቃደኞች ስትሆኑ ጸጋው በእጅጉ ይረዳችኋል ማለት እንጂ፡፡ አንድ ሰው ፈቃዱን ተጋፍቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ ይችላል፤ ከምሥዋዑ ፊት ሊቆም ይችላል፤ ሥጋዬንና ደሜንም ሊቀበል ይችላል፤ ሆኖም ግን ሐዋርያው “ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፤ በአፉም መስክሮ ይድናል” እንዳለ ፈቃዱን ይዞ ካልመጣ በቀር በእኔ ማመን ደግሞም መዳን የሚቻለው የለም /1ቆሮ.10፡10/፡፡ እኔ ጋር መቅረብ የሚቻለው በእግረ ሥጋ ሳይሆን በእግረ እምነት ነውና /Saint Augustine, Tractes on the Gospel of John, 26:2/፡፡

 “እናንተ እንደምታስቡት ሙሴም ቢሆን ሌላም ቢሆን አብን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ መላእክት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ ብዬ ስነግራችሁ እንኳ የሚያዩት ለእነርሱ በሚመጥናቸው መጠን እንጂ በባሕርይ አምላክነቱን አይደለም /ማቴ.18፡10/፡፡ እኔ ግን በባሕርይ ልጅነቴ አብን አይቼዋለሁ /ቁ.46፣ Saint John Chrysostom, ‘Divine Care’ translated by Aida Hanna, chapter 3 /፡፡


“ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” ተብሎ እንደተጻፈ አባቴ “ዝንቱ ውእቱ ወልድዬ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሰመርኩ- ልመለክበት የወወድሁት ለተዋሕዶ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲመሰክርልኝ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ በእኔም ያምናል /ቁ.45፣ ማቴ.3፡17/፡፡ ከእናንተ መካከል “አብ አንዳንዶችን በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ በአንተ እንዲያምኑ ካደረገ ሌሎችሳ እንዲያምኑ ለምን አያደርጋቸውም?” የሚል ቢኖር፡- “እነዚያ አብ ሊስባቸው ስላልወደደ ሳይሆን በፈቃዳቸው መምጣት ስላልወደዱ ነው፤ ፈቃደኞች ሆነው በእኔ አምነው አባቴም በረድኤቱ ስቦአቸው የሚመጡትን ግን በእኔ ይኖራሉ እኔም በእነርሱ፤ በመጨረሻው ቀን አስነሣቸዋለሁ፤ መንግሥተ ሰማያትም ይወርሳሉ” ብዬ በእውነት እነግራችኋለሁ፡፡ ኅብስተ ሕይወት እኔ ነኝና፡፡ አባቶቻችሁ መናውን በሉ፤ ሆኖም ግን ጊዜአዊ ችግራቸውን ፈታላቸው እንጂ በምድረ በዳ ከመሞት አላዳናቸውም፤ ዘላለማዊ ደኅንነትን አልሰጣቸውም /ቁ.49-50/፡፡ እኔ ከምሰጠው ከኅብስተ ሕይወት የሚበላ ሁሉ ግን በሥጋ ቢሞት በነፍስ እንዳይሞት ፈርሶ በስብሶም እንዳይቀር ይልቁንም ትንሣኤ ዘለክብር እንዲነሣ እነግራችኋለሁ፡፡ ስለዚህ አሁንም ደግሜ እነግራችኋለሁ ከሰማይ የወረደ ኅብስተ ሕይወት እኔ ነኝ፡፡ እኔ ከምሰጠው ከዚህ ኅብስተ ሕይወት የሚበላ ሰው የተያዘበት የባርነት ቀንበር ይሰበራል፤ የኃጢአት ሰንሰለቱ ይበጣጠሳል፤ ባሕረ እሳቱን ያሻገራል፤ ወደ ዘላለማዊው ሐሴት ይነጠቃል፤ ከሲዖል እስራት ለማምለጥም ሌላ ነገር አያስፈልገውም፡፡  ክፋቱ በደግነት ይተካል፤ ጥላቻው ለፍቅር ቦታውን ይለቃል፤ አድመኝነቱ ሥፍራውን ለአንድነት ያስረክባል፤ ሌሎችም የበጐነት ዓይነቶች ነፍሱንና ሥጋዉን ለመቈጣጠር ጓዛቸውን ጠቅልለው ይመጣሉ” /ቁ.51፣ Saint Cyril the Great, Commentary on the Gospel Of John 3፡6/፡፡

  አይሁድ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? አንዳንድ ጉርሻስ እንኳ ይደርሰናልን? ደግሞስ የዕሩቅ ብእሲ ሥጋ ቢበሉት ደሙን ቢጠጡት ደዌ ይሆናል እንጂ ሕይወት ይሆናልን?ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። እነርሱ የለመዱት ደመ በግዕ፣ ሥጋ በግዕ፣ ደመ ጠሊ፣ ሥጋ ጠሊ፣ ደመ ላህም፣ ሥጋ ላህም ነውና እንዲህ አሉ፡፡ ሆኖም ይህ ይሆን ዘንድ አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ነፍስና ሥጋን የሚቀድስ ሁለንተናንም ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻ ሰማያዊ መና ሰማያዊም ጽዋዕ ተሰጥቶናልና /St. Cyril Of Jerusalem, Mystagogical Lectures 4:4-6/፡፡

  አቤት! የሰይጣን የማታላያ መንገዱ እንዴት ብዙ ነው? አስቀድሞ የአይሁድን ልብ እንዳሳወረ ዛሬም ሰዎች ራሳቸው ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ክቡር ደሙ መቅረብ እንደሚገባቸው ፈጽመው እንዳያስቡት ያደርጋቸዋል፡፡ በክፋት ላይ ክፋት እያሠራ ከጸጋው እንዲርቁ ተራና መናኛ ምክንያትን ያቀርብላቸዋል፡፡ በቲሃ ወይን ጠጃቸው ከአፋቸው እንዳልተወገደ ሰካራሞች  ለራሳቸው የሚጠቅማቸው ነገር እንዲመለከቱ ዕድል አይሰጣቸውምና በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ /ኢዩ.1፡5/፡፡ እንግዲያውስ ሰይጣን በእኛ ላይ የጫነውን ቀንበር ሰብረን የታሰርንበትንም ማሰርያ በጥሰን እግዚአብሔርን በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ እናገልግለው፡፡ መጽሐፍ እንደሚል ለእግዚአብሔር በፍርሐት እንገዛ፤ በረዓድም ደስ ይበለን /መዝ.2፡11/፡፡ ራሳችንን በመቈጣጠር ከሥጋ ፈቃድና ፍላጐት በላይ ሆነን የተፈጠርን መሆናችንን እናሳይ፡፡ ሰማያዊውንና መለኰታዊውን ጸጋ እንቅረበው፡፡ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም በድፍረት ሳይሆን በእምነትና በፍርሐት እንቅረብ፡፡ የሰይጣንን ማታለል የምንመለከትበት ትክክለኛው መንገድ ይኼው ብቻ ነውና፡፡ “ከመለኰት ባሕርይ ተካፋዮች” ከሆንን ወደማይጠፋና የማይሞት የዘላለም ሕይወት እንሸጋገራለን /2ጴጥ.1፡4፣ ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ በዲ/ን ታደለ ፈንታው ገጽ 148/፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!




Thursday, July 5, 2012

ማንም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ- በቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ!


ከመጀመርያ ጀምሮ መልካም ነገርን መምረጥ ክፉ አይደለም፤ በመልካምነት አለመቀጠል ግን ብዙ ወቀሳን ያመጣል፡፡ የብዙ ሰዎች ክፉ መሆን በዚሁ የሚመደብ ነው፤ ብዙዎች ሕይወታቸውን በመልካም ጀምረው በኋላ ግን በክፋት መርዝ ተጠምቀው ሲሰክሩ ተመልክቻለሁና፡፡

 እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፡፡ ምንም እንኳን አሁን ወደ ክፋት ጥልቅ ወርዳችሁ ቢሆንም “ከዚሁ ተመልሰን መነሣት አይቻለንም፤ መለወጥም አይሆንልንም” በማለት ተስፋ የምትቈርጡ አትሁኑ፡፡ እናንተ ስትፈቅዱ እግዚአብሔርም ሲረዳችሁ ከክፋት ዐዘቅት መውጣት በእጅጉ ቀላል ነውና፡፡

 ከሁሉም በላይ አመንዝራ ተብላ በከተማው ዘንድ ትታወቅ የነበረችውን ሴት በመልካምነቷ እንዴት እንደምትወደስ አልሰማችሁምን? እየነገርኳችሁ ያለሁት በዮሐንስ ወንጌል ላይ ስለተጠቀሰችው ሴት አይደለም፡፡ በእኛ ዘመን ስላለችውና ፍኒሳ ከተባለችው ጋጠ ወጥ ከተማ ስለተገኘችው ሴት እንጂ፡፡ ይህች ሴት አስቀድማ በመካከላችን በአመንዝራነቷ ትታወቅ ነበር፡፡ በክብር ቦታ ሁሉ የመጀመርያን ስፍራ የምትይዝ ሴት ነበረች፤ ስሟ በሀገሩ ሁሉ የገነነ ነበር፤ በእኛ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሲልስያ እና በቀጰዶቅያም ጭምር እንጂ፡፡ ይህች ሴት ብዙ ከተሞችን አፍርሳለች፤ የብዙ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ንብረት በልታለች፡፡ ብዙዎችም “መተተኛ ናት” ይሏታል፤ ውበቷን ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ጭምር ትጠቀም ነበርና፡፡ ከዚሁ የተነሣ በአንዱ ቀን የንግሥቲቱን ልጅ እስከ ማማለል ደርሳለች፡፡ ጭካኔዋ የክፉ ክፉ ነበር፡፡

 ከዕለታት በአንዲቱ ቀን ግን ማመን እስኪያቅተኝ ድረስ ሆኖም ግን በዓይኔ ፍጹም ተለውጣ ራሷን በእግዚአብሔር የጸጋው ዙፋን ፊት ድፍት አድርጋ ስታለቅስ አየኋት፡፡ አሁን የቀድሞ ክፉ ሥራዎቿን ሁሉ እርግፍ አድርጋ ትታለች፤ በእርሷ ላይ ከነበሩት የአጋንንት ጭፍራ ተፋትታ አሁን የክርስቶስ ሙሽሪት ሆናለች፡፡

 በእውነት ከእርሷ የሚከፋ ሰው በዐይኔ አላየሁም፡፡ በኋላ ግን ራሷን ከእንደዚህ ዓይነቱ ክፉ ሥራ ከለከለች፡፡ ከዚህ በፊት ስትለብሳቸው የነበሩት የምንዝር ጌጦች ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ አሁን ግን እነዚህ ሁሉ በእርሷ ዘንድ ቦታ የላቸውም፡፡ እነዚህን ሁሉ አወላልቃ ጥላ ለእግዚአብሔር በሚገባ የማቅ ልብስ ለብሳ ራሷን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር አድርጋለች፡፡ ይህችን ሴት ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ለመመለስ የሀገሪቱ መኳንንት ከዙፋናቸው ወርደው ለምነዋት ነበር፤ ወታደሮች ትጥቃቸውን ታጥቀው በመምጣት አስፈራርተው ሊወስዷት ሞክረው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ወደ ቀድሞ ሕይወቷ ሊመልሷት አልተቻላቸውም፤ ከተቀበሏት ደናግላን በዓት ሊያስወጧት አልተቻላቸውም፡፡

 ይህች ሴት ከዚያ አስነዋሪ ሕይወቷ ተመልሳ ለቅዱስ ቁርባን በቅታለች፤ ለእግዚአብሔር ጸጋ የተገባ ሆና ተገኝታለች፤ ኃጢአቷን ሁሉ በጸጋው አጥባለች፤ ከተጠመቀች በኋላ ራሷን መግዛት ችላለች፡፡ ይህች ሴት የቀድሞ ሕይወቷን፣ ገላዋን ለብዙ ወዳጆቿ ያሳየችበትን ሕይወት “የእስር ቤት ሕይወት” ብላ ትጠራዋለች፡፡ በእውነት “ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ” የሚለው የከበረው የጌታ ቃል በእርሷ ሲፈጸም አየነው፤ መለወጥ ከፈለግን እኛን ማሰናከል የሚቻለው ኃይል እንደሌለ አወቅን ተረዳን፡፡

 እንግዲያስ ተወዳጆች ሆይ! ተስፋ በመቁረጥ በኃጢአት ዐዘቅት ሰምጠን የምንቀር አንሁን፡፡ ከእኛ መካከል በጽድቅ በረሀነት የሚኖር ማንም አይገኝ፡፡ ፊተኛ ነኝ የሚልም ከቶ አይኑር፤ ብዙ አመንዝሮች እርሱን አልፈዉት ሊሄዱ ይችላሉና፡፡ ማንምም ኋለኛ ነኝ ብሎ ተስፋ አይቁረጥ፤ ከልቡ ከተጸጸተና ከተመለሰ ፊተኛ መሆን ይቻለዋልና፡፡

 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላል፡- “ይህም ሁሉ ካደረገች በኋላ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተመለሰችም፡፡ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች” /ኤር.3፡7/፡፡ ወደ እግዚአብሔር ስንመለስ የቀድሞ ኃጢአታችንን አያስበውም፤ እግዚአብሔር እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለምና፡፡ በእውነት እርሱ በቀድሞ ኃጢአታችን የሚወቅሰን አይደለም፡፡ እርሱ እንደ ሰው አይደለምና፡- “እስከ አሁኑ ሰዓት ወዴት ነበርክ?” የሚለን አይደለም፡፡ ብቻ እኛ እንመለስ እንጂ እርሱ እንዲህ ያለ አምላክ አይደለም፡፡

ይህን እንደናደርግ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!   

Monday, July 2, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- ክፍል ሦስት!


      በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 በክፍል ሁለት ትምህርታችን ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ሥርዓት ከሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም የሚለይባቸውን ነጥቦች ማሳየት ጀምረን ነበር፡፡ የሚምር ነው፤ የታመነ ነው፤ በሰማያት ያለፈ ነው፤ በድካማችን የሚራራልን ነው ብለን አራት ነጥቦችን አይተናል፡፡ ለዛሬም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡ ቢችሉ አስቀድመው ይጸልዩ!
1. በመሐላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ መሐላ የማይለወጥ ነገርን ያመለክታል፡፡ አንድ ሰው ይህን አላደርግም እንዲህም አላደርግም ብሎ ከማለ የነገሩን ሓቅነት ያመለክታል፡፡ “ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጠው (ሎሌ በጌታው፣ ገረድ በእመቤቷ፣ ደቀ መዝሙር በመምህሩ፣ ልጅ በአባቱ) ይምላሉና ለማስረዳትም የሆነው መሓላ የሙግት (የክርክር የጸብ) ሁሉ ፍጻሜ ይሆናል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደማይለወጥ አብልጦ (አብዝቶ) ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ እግዚአብሔር ሊዋሽ (ሊፈርስ፣ ሊታበል) በማይቻል በሁለት  በማይለወጥ ነገር በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ በመሐላ (በሥጋዌው) በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን (ተስፋችንን አጽንተን ለያዝን ለእኛ ልቡናችን እንዳይነዋወጥ እንደ ወደብ የሚያጸናን ፍጹም ደስታ አለን)፤ እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ (እንደ መልከ ጼዴቅ ባለ ሹመት ተሹሞ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት የገባ የዘላለም አስታራቅያችን ፊተውራርያችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ነው” እንዲል /ዕብ.6፡16-19/፡፡ እንግዲያውስ ከሌዋውያን ክህነት በሚበልጥ ክህነት፣ እንደ መልከ ጼዴቅ ክህነት ዘላለማዊ በሆነ ክህነት የተሾመ ሊቀ ካህናት አለን፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ጥሪ የተመረጡ ቢሆኑም አገልግሎታቸው ጊዜአዊ ስለ ነበረ ያለ መሓላ የተሾሙ ነበሩና፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከኦሪት ለምትበልጥ ለወንጌል መምህር ለመንግሥተ ሰማይም አስታራቂ ሆኖአልና በመሓላ የተሾመ ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያውም ስለዚሁ ሲናገር እንዲህ አለ፡- “እነርሱም ያለ መሓላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፡- ጌታ፡- አንተ እንደ መልከጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሓላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሓላ ካህን እንዳልሆነ መጠን እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል /ዕብ.7፡20-22/፡፡ በዚህም ኦሪት ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስላልቻለች እንደተሻረች ወንጌል ግን ማዳን ስለቻለች፣ ሥርየተ ኃጢአትን ማሰጠት ስለቻለች ሕልፈት ሽረት እንደሌለባት አወቅን፤ ተረዳን፡፡ ካህኑም አገልግሎቱም እንደዚሁ፡፡ ለምን ቢሉ ያለ መሓላ ከተሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት ይልቅ በመሓላ የተሾመ ሊቀ ካህናት ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ይበልጣልና፡፡  
2. የማይለወጥ ክህነት ያለው ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የቀደሙት ሊቃነ ካህናት ያለ መሓላ ለተሠራችው ሕገ ኦሪት የተሾሙ ስለ ነበሩ አንድም መዋትያን ስለ ነበሩ ካህናት የሆኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በመሓላ ለተሠራችው ወንጌል የተሾመ ስለሆነ አንድም ሞትን በሞቱ ገድሎ ተነሥቶ በሕይወት የሚኖር ሥግው ቃል ስለሆነ ወራሽ የሌለው አንድ ነው፡፡ ክህነቱም (ኃጢአት የማሥተስረይ ችሎታውም) የባሕርዩ ስለ ሆነ በሞት (ሞት ሊያሸንፈው ስላልቻለ) አይለወጥም፡፡ የባሕርዩ የሆነውን ለእነዚያ በጸጋ ሰጥቷቸው ነበርና ሥጋ ለብሶ በክህነት ሲገለጥ ባሕርያዊ ሥልጣኑ የማይሻር ሆነ፡፡ ሐዋርያውም ይህን አስመልክቶ ሲናገር፡- “እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘለዓለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው አለን /ዕብ.7፡23-24/፡፡
3. ሞትን አሸንፎ በሕይወት የሚኖር ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና፡፡ ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” /ዕብ.7፡25/፡፡ ካቶሊክ ሳትታሰብ ፕሮቴስታንትም ሳትታለም ከ325 እስከ 389 ዓ.ም የነበረውና የቀጰዶቅያ አውራጃ ለምትሆን የቂሳርያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ይህን ሲተረጕመው እንዲህ ይላል፡- “ይህ ቃል የሚያመለክተን የጌታችን አስታራቂነቱን ነው፡፡…  ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል አንድ እግዚአብሔር አለና፣ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው  (ሰው ሆኖ ሰውና እግዚአብሔርን ያስታረቀ) ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም (ለሁሉ ቤዛ አድርጎ ራሱን አሳልፎ ለሞት ለሕማም የሰጠ) ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው /1ጢሞ.2፡5-6/፡፡ አሁንም ይህ ሥግው ቃል ከመቃብር በላይ ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ “በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን” እንላለን /1ኛ ዮሐ.2፡1/፡፡ ሆኖም ግን ይህን በአብ ፊት በመውደቅና በመነሣት የሚያደርገው አይደለም፤ በዕለተ ዐርብ በተቀበለው መከራ ባደረገው ተልእኮ እንጂ”  /On The Son, Theological Oration, 4(30):14/፡፡ ከ347 እስከ 407 ዓ.ም የነበረውና የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የሆነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንዲህ ይላል፡- “የቀደሙት ሊቀነ ካህናት መዋትያን ስለ ነበሩ ብዙ ናቸው፡፡ እርሱ ግን የማይሞት ሕያው ስለሆነ አንድ ነው፡፡ የማይሞትም ስለ ሆነ እርሱን አምነው የሚመጡትን ሁሉ ሊያድናቸው ይቻለዋል፡፡ እንደምንስ ያድናቸዋል? የሚል ሰው ካለም “በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ነው” ብለን እንመልስለታለን፡፡ በሃይማኖት በንስሐ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን የሚያድናቸው በዕለተ ዐርብ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያ በኋላም ጭምር እንጂ፡፡ በወደደበት ጊዜም ለመነላቸው፡፡ ሁል ጊዜ ይለምናል ብሎ የሚያስብስ ከቶ እንደምን ይኖራል? ጻድቃንስ እንኳ አንድ ጊዜ በለመኑት ልመና የሚሹትን የሚያገኙ አይደሉምን?… ሐዋርያውም ሁል ጊዜ ቁሞ የሚያገለግል እንዳያስመስሉት በማሰብ በመትጋት መሥዋዕት አንድ ጊዜ እንደሠዋ አስረዳ፡፡ አንድ ጊዜ ሰው እንደ ሆነ አንድ ጊዜ ተሾመ፤ አንድ ጊዜ እንደ ተሾመ አንድ ጊዜ አገለገለ፡፡ ሰው በሆነ ጊዜ የሰውነትን ሥራ በመሥራት ጸንቶ እንዳልኖረ ሁሉ ባገለገለ ጊዜም በማገልገል ጸንቶ አልኖረም፡፡ አሁን ቢያገለግል ኖሮ ሐዋርያው ቆመ እንጂ ተቀመጠ ባላለ ነበርና፡፡ መሥዋዕቱ ቁርጥ ልመናውን አንድ ጊዜ ወደ እዝነ አብ (በአብ ጀሮ) ወደ ገጸ አብ (በአብ ፊት) የደረሰች ስለሆነች እንደ ቀደሙት ሊቃነ ካህናት ሁል ጊዜ ሊያገለግል አያስፈልገውም” /Homily on the Epistle of Hebrews, Hom.13/፡፡ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትርጓሜም ተመሳሳይ ነው፡- “በዕለተ ዐርብ ባደረገው ተልእኮ እስከ ምጽአት ድረስ ሲያድንበት የሚኖር ስለ ሆነ በእርሱ አስታራቂነት ወደ እግዚአብሔር የቀረቡትን ማዳን ይቻለዋል” /የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከነ ትርጓሜው፣ ገጽ 434/፡፡ እንግዲያውስ ተወዳጆች ሆይ! “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል” የሚል ጥሬ ምንባቡን ብቻ በመያዝ እንዳይሳሳቱ ይጠንቀቁ፡፡ ይህ ማለት አስቀድመን እንደነገርንዎት የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ዐርብ የማስታረቅ አገልግሎት ከአዳም መፈጠር ጀምሮ እስከ ዕለተ ዐርብ ላሉት ሁሉ ብቻ ሳይሆን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በዚሁ የዕለተ ዐርቡ የማስታረቅ አገልግሎት እያመነ እንደሚድን ደሙም የማስታረቅ ችሎታ እንዳለው የሚገልጽ ነውና /ዮሐ.17፡20-21/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ የሠዋው መሥዋዕት እንደ ብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት መሥዋዕት ተረፈ ኃጢአት (ያልተደመሰሰ ኃጢአት) አስቀርቶበት አሁን ያንን ለማስተስረይ የሚወድቅ የሚነሣ አይደለምና፡፡ ጸሎቱና መሥዋዕቱ ምልአተ ኃጢአትን (ኃጢአትን ሁሉ) ለመደምሰስ አንድ ጊዜ ተፈጽሟልና /ዮሐ.19፡30/፡፡ ስለዚህ ይማልድልናል ስንል “የዕለተ ዐርቡ ቤዛነት፣ ካሣ፣ ሞት፣ ደም መፍሰስ አዲስና በየዕለቱ ንስሐ የሚገቡትን የሚያቀርብ የሚያድን ነው” ማለት መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡  ስለዚህም ነው ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች “ከእርሱ ውጪ ሌላ ሊቀ ካህን የለንም፤ ከቅዱስ ሥጋዉና ከክቡር ደሙ ውጪ ሌላ በየቀኑ የምናቀርበው መሥዋዕት የለንም” የምንለው፡፡ ክህነቱ የማይለወጥ፣ መሥዋዕቱም አንድ ጊዜ ቀርቦ በጊዜ ብዛት የማይበላሽ ሕያው አሁንም ትኵስ ነውና፡፡ ትኵስ መባሉም ነፍስ ስላለው ሳይሆን መለኰት የተዋሐደው ስለሆነ ነው፡፡
4. በእርሱ በኵል (እርሱን አምነው) ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድን የሚችል ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡- “የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል” /ዕብ.7፡25/፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጌታችን ራሱ እንዲህ ብሏል፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ እኔ የበጎች በር (ደጅ) ነኝ… በሩ እኔ ነኝ በእኔ የሚገባ (በእኔ ያመነ) ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም መሰማርያም ያገኛል (ክብረ ሥጋን ክብረ ነፍስን ያገኛል፤ መንግሥተ ሰማያትንም ይወርሳል)” /ዮሐ.10፡7፣9/፤ “እኔ መንገድና እውነት ነኝ (የሕይወትና የጽድቅ መንገዷ እኔ ነኝ) በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም (እኔን ልጅ ካላለ በቀር አብን አባት የሚለው የለም አንድም በእኔ የማያምን ከአብ ጋር መታረቅ አይችልም)” /ዮሐ.14፡6-7/፡፡ እውነት ነው! የሕይወት መሥመር ክርስቶስ ነውና ክርስቶስን አምኖ የሚኖር ሰው ሕይወትን ያገኛል፡፡ ማንም ይሁን ማን ክርስቶስን ካላመነ ቢጾምም ቢጸልይም ያለ ክርስቶስ ዋጋ የለውም፤ በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ዓለም በራሱ ሕይወት የለውም፤ በክርስቶስ ቤዛነት የማያምን በሌላ በምንም መንገድ አይድንም፡፡
5. ድካም የሌለበት ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ድካምን የሚለብሱ እንደነበረ መጽሐፍ የሚሰክረው የታወቀ የተረዳ እውነት ነው፡፡ ይህም በጣም የተገለጠ ድካም በታየባቸው በኤሊ ልጆች መረዳት እንችላለን፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉ የኤሊ ልጆች በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ሥጋ ለግል ጥቅማቸው በማዋል እግዚአብሔርን ያሳዝኑ ነበር፡፡ ይህም ሳይበቃቸው በመገናኛው ድንኳን ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ያመነዝሩ ነበር /1ሳሙ.2፡12-22/፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ጻድቅና ቅን፣ ነቀፋ የሌለበት እውነተኛ፣ ከኃጢአት ሁሉ ፈጽሞ የራቀ የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ ነው /ዕብ.7፡26/፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን ሲመሰክሩ እንዲህ ይላሉ፡- “በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም” /ኢሳ.53፡9/፤ “ኃጢአት ያላወቀው” /2ቆሮ.5፡21/፤ “እርሱ ኃጢአትን አላደረገም” /1ጴጥ.2፡22/፤ “በእርሱ ኃጢአት የለም” /1ዮሐ.3፡5/፡፡ ጌታችንም ራሱ እንዲህ ብሏል “ከእናንተ ስለ ኃጢአት (ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ) የሚከሰኝ ማን ነው?” /ዮሐ.8፡46/፡፡ ለሞት አሳልፈው የሰጡት ተቃዋሚዎቹም ሳይቀሩ ይህን መስክረዋል፡- “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” /ማቴ.27፡4/፤ “በዚህ ሰው አንድ በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” /ሉቃ.23፡4/፡፡  
6. ስለ ራሱ መሥዋዕት የማያሻው ነውር የለሽ ፍጹም ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ዕሩቅ ብእሲና እንደ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኞች ስለነበሩ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር በመሥዋዕት በጸሎት ከማስታረቃቸው በፊት ስለ ራሳቸው ቁርባን መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር /ዘሌ.9፡7፣ ዘሌ.16፡6፣ ዕብ.5፡3-4/፡፡ ሊቀካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስቀድመን እንደተናገርነው በባሕርይው ድካም የሌለበት ቅዱስ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለበት ንጹሕ፤ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ሳይጐድልበት የሚያድል ባዕለ ጸጋ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ ቡሩክ፤ ከኃጢአተኞችም የተለየና ነውር የሌለበት ፍጹም ስለሆነ “እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈለገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና” /ዕብ.7፡27/፡፡ 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር (ሳምንት ይቀጥላል)!

FeedBurner FeedCount