Sunday, August 12, 2012

ድንግል ሆይ! በኃጢአት በፍትወት የተጸነስሽ አይደለሽም!



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!


  እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግመሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸውብሎ ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙሩ ስለዘመረላት፤ ዳግመኛም ቅዱስ ያሬድማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ- ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች (በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና በቅድስና በድንግልና ታበራለች)” ብሎ ስለተናገረላት፤ ዳግመኛምእግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችን ሁሉ በእውነት ተመለከተ፤ ተነፈሰ አሻተተም፤ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ የአንቺ መዐዛ ወደደ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንቺ ላከብሎ ሊቁ አባ ሕርያቆስ ሰለተቀኘላት የእመብርሃን ነገረ ጽንሰቷን እንናገራለን፡፡

  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥርወ ሃይማኖት ከሚሆን ከአብርሃም ሥርወ መንግሥትም ከሚሆን ከዳዊት ወገን እንደ ተገኘች ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆን ምሥጢር በተናገረበት አንቀጽ፡- “እስመ አኮ እመላእክት ዘነሥኦ ለዘነሥኦ ዘእንበለ ዳዕሙ እምዘርአ አብርሃም- የነሣውን ባሕርይ ከአብርሃም ነሣው እንጂ ከመላእክት የነሣው አይደለምአለ /ዕብ.216/፡፡ በዚህ መሠረት ወላዲተ ቃል ቅድስት ድንግል ማርያም የአብርሃም ዘር መሆኗን አወቅን ተረዳን ማለት ነው፡፡ ልዑለ ቃል ኢሳይያስም፡- “ትወጽእ በትር እም ሥርወ እሴይ- ከእሴይ ሥር (ከእሴይ ነገድ) ብትር (እመቤታችን) ትወጣለች (ትወለዳለች) ወየዓርግ ጽጌ እምኔሃ- አበባም ከግንዱ ይወጣል (ከእርሷም ጌታ ይወለዳል)አለ /ኢሳ.111 ንባቡና ትርጓሜው በአንድምታ/፡፡  

  ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን የእመቤታችን ነገረ ጽንሰቷ እንደሚከተለው ነው፡-
 ቅድመ አያቶች የሚሆኑ ጴጥርቃና ቴክታ የሚባሉ ሰዎች በኢየሩሳሌም ተጋብተው ይኖሩ ነበር፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ቢሆኑም የሚወርሳቸው ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ጴጥርቃ ሚስቱ ቴክታን፡- “እኅቴ ቴክታ ሆይ! እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት፡፡ ቴክታም መልሳ፡- “ወንድሜ ሆይ! እግዚአብሔር ለእኔ ልጅ ቢነሳኝ አንተም እንደኔው ሆነህ ትቀራለህን? ይሰጥህ ይሆናልና ከሌላ ደርሰህ ውለድአለችው፡፡ እርሱም፡- “ይህስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃልአላት፡፡ በዚህ ጊዜ አዘኑ፡፡ ወዲያውም ራዕይ አዩ፡፡ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ ስድስተኛይቱም ጨረቃ ጨረቃይቱም ፀሐይን ስትወልድ አዩ፡፡

  ከዚህ በኋላ መፈክረ ሕልም (ሕልምን የሚተረጕም) ጋር ሄዱና ያዩትን ሁሉ ነገሩት፡፡ እርሱምእግዚአብሔር በምሕረቱ ጎብኝቷችኋልና ደግ ልጅ ትወልዳለችሁ፡፡ ሰባት እንስት ጥጆች መውለዳችሁ ሰባት ሴቶች ልጆችና የልጅ ልጆች መውለዳችሁ ነው፡፡ ስድስተኛይቱ ጨረቃም ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ነች፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም፤ እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ይሆናልአላቸው፡፡ እነርሱም ጊዜ ይተርጉመው ብለውት ሄዱ፡፡

 ከዚህ በኋላ ቴክታ ፀነሰች፤ ወለደችም፡፡ ስሟንምረከብኩ ስእለትዬ፤ ረከብኩ ተምኔትዬ-የተሳልኩትን አገኘሁ፤ የተመኘሁትን አገኘሁስትል ሄኤሜን አለቻት፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፣ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ቅድስት ሐናም አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡

 ኢያቄምና ሐና ኑሮአቸው በእግዚአብሔር ፊት ቅንና ግልጽ በሰውም ፊት የዋሃንና ስሕተት የማይታይባቸው ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡

 በዚህ ሁኔታ በሰውና በእግዚአብሔር የተመሰገኑ እነዚህ ደጋግ ሰዎች ልጅ ሳይኖራቸው ሃያ ዓመታት አለፉ፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እኛ ምን ያህል ታጋሾች እንሆን? ምን ያህል እግዚአብሔርን እንጠብቅ ይሆን? ምን ያህል እግዚአብሔርን እንለማመጥ ይሆን? እነዚህ ቅዱሳን ግን ሃያ ዓመታት ጠበቁ፡፡ ዝም ብሎ መጠበቅ አይደለም፡፡ በጸሎትና በልመና
እንጂ፡፡

  ከዕለታት በአንዱ ቀን ኢያቄም፡- “አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ አምላክ ሆይ! እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ አትናቀኝ ጸሎቴን ስማኝ፤ ፈቃዴን ፈጽምልኝ፤ ለዓይኔ ማረፍያ ለልቤ ተስፋ የሚሆን የተባረከ ወንድ ልጅ ስጠኝብሎ ሲለምን ዋለ፡፡ ሐናም በበኵሏ፡- “አቤቱ ጌታዬ የአባቶቼ የእስራኤል አምላክ! እኔ ባርያህ እለምንሃለሁ፤ ስማኝ ለዓይኔ ማረፍያ ለልቤም ተስፋ የምትሆን የተባረከች ሴት ልጅ የማሕጸኔን ፍሬ ስጠኝስትል ዋለች፡፡

  እንዲህም ብለው ሲጸልዩ ሲለምኑ ውለው ርግብ ከልጆቿ ጋር ስትጫወት አይታ ሐና፡- “አኔቱ ጌታዬ ለዚህች ግእዛን ለሌላት እስንስሳ ልጅ የሰጠህ አምላክ ምነው ለእኔ ልጅ ነሳኸኝ ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡  

   ስለዚህ ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው አብዝተው ለመኑ፡፡ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር አንጣፊ ጋራጅ ሆኖ ይኖራል እንጂ፡፡ ሴት ልጅም ብንወልድ እንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ትኑር እንጂብለውም ቃል ገብተው ተሳሉ፡፡

   ቅድስት ሐናና ቅዱስ ኢያቄምም ዕለቱን ራዕይ አይተው ነገር አግኝተው አደሩ፡፡ ኢያቄምሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ወፍ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየሁአላት፡፡ ወፍ የተባለው ጌታችን ሲሆን ነጭነቱም ንጹሐ ባሕርዩን የሚያሳይ ነው፡፡ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየሁ ማለቱም ጌታ የኢያቄምን (የሰውን) ባሕርይ ባሕርይ አድርጎ መውረዱን ነው፡፡ ሰባቱ ሰማያት የተባሉት የጌታችን የተለያዩ ባሕርያት ሲሆኑ እነርሱም ምልአቱ፣ ስፍሐቱ፣ ርቀቱ፣ ልዕልናው፣ ዕበዩ፣ መንግሥቱ እንደዚሁም እዘዙ ናቸው፡፡

 ሐናም እኔም አየሁ አለችው፡፡ ምን አየሽ ቢላት፡- “ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ወርዳ በጀሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁአለችው፡፡ ርግብ የተባለች እመቤታችን ስትሆን ነጭነቷም ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ ድንግልናዋ ነው፡፡በጀሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየሁማለቷ ደግሞ በመልአኩ ብሥራት እመቤታችንን መፅነሷን ነው፡፡ ይህም የሆነው ሐምሌ ሠላሳ ነው፡፡

 እነርሱም እንዲህ ያለ ራዕይ ካየን ነገር ካገኘን ብለው ዕለቱን ሩካቤ አልፈጸሙም፡፡ አስቀድመው ፈቃደ እግዚአብሔርን ጠየቁ እንጂ፡፡ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ በዓል ሲከበር ኢያቄም ከጐረቤቶቹ ጋር መባዕ ይዞ በዓሉን ለማክበር ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ በጊዜው የነበረው ሊቀ ካህናትም ይሳኮር (ሮቤል) ይባላል፡፡ ኢያቄም መሥዋዕት ይዞ መምጣቱን አይቶ ወደ እርሱ ሄደና፡- “ልጅ ሳይኖርህ (መኻን ስትሆን) እንዴት ወዲህ ትመጣለህ? መባንስ እንዴት ታቀርባለህ? እግዚአብሔር እኮ የመካኖች መባ አይቀበልምአለና ከለከለው፡፡ ኢያቄምም በከፍተኛ ሐፍረትና ሐዘን ተመለሰ፡፡ ሰዎች በራችን ይዘጋሉ፤ እግዚአብሔር ግን ይከፍትልናል፡፡ ሰዎችምን ያደክምሃል?” ይሉናል፤ እግዚአብሔር ግን ይደግፈናል፡፡

 ስለዚህ በዚህ ጊዜ ታላቅ ብርሃን የተጐናጸፈ የእግዚአብሔር መልአክ መጥቶ በኢያቄም ፊት ቆመ፡፡ እንዲህም አለው፡- ኢያቄም ሆይ! እኔን በማየት አትፍራ፤ አትጨነቅም፡፡ እኔ ጸሎትህ እንደተሰማ ምጽዋትህም ቅድመ እግዚአብሔር እንደደረሰ ልነግርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወዳንተ የተላክሁ የእግዚአብሔር መልአክ ነኝ፡፡ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ የብዙዎችን ማሕፀን ይዘጋል፤ ይከፍታልም፡፡ የጥንቷ እናትህ ሣራ እስከ ሰማንያ ዓመት ዕድሜዋ መካን ሁና በኋላ ግን የይስሐቅ እናት ሆነች፡፡ እንደዚሁም ራሔል የእግዚአብሔር ወዳጅ ሁና መካን ነበረች፤ በኋላ ደግሞ የዮሴፍ እናት ሆነች፡፡ የእግዚአብሔር የቅርብ ወዳጅ የነበሩት የሳምሶንና የሳሙኤል እናቶች መካን ነበሩ፤ በኋላ ግን የእነዚህ ታላላቅ ሰዎች እናቶች ሆኑ /መሳ.131-24 መሳ.120/፡፡ ስለዚህ ሚስትህ ሐና ሴት ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሟንም ማርያም ብለህ ትጠራታለህ፡፡ በእናትዋ ማሕፀን ውስጥ ሳለችም መንፈስ ቅዱስ ያድርባታል፡፡

 ዳግመኛም መልአኩ ወደ ሐና ሄደና እንዲህም አላት፡- ሐና ሆይ! ሌላ መንፈስ ያየሽ አይምሰልሽ! እኔ ጸሎትሽንና ምጽዋትሽን ከእግዚአብሔር ፊት የማቀርብ መልአክ ነኝና፡፡ አሁንም የመጣሁት ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትሆን ስሟም ማርያም የምትባል ልጅ የምትወልጂ መሆንሽን ልነግርሽ ነው በማለት አበሠራት፡፡ በዚህ እውነት፣ በብሥራተ መልአክ፣ በፈቃደ አምላክ እመ አምላክ እመቤታችን ከአባትዋ ከኢያቄም ከእናትዋም ከሐና ነሐሴ ሰባት ቀን 5484 ዓመተ ኵነኔ ሲፈጸም ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን 5485 ዓመተ ኵነኔ ሲፈጸም ተወለደች፡፡
  
   ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እም ሐና ወኢያቄም ዘተወለድኪ፡፡ ድንግል ሆይ! በኃጢአት በፍትወት የተጸነስሽ አይደለሽም፤ በሕግ በሆነ በሩካቤ ከሐናና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፡፡

   ድንግልናን ከእናትነት፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትንም ከድንግልና አስተባብረሽ የያዝሽ እመቤታችን ሆይ! ከገነት በተባረርን ጊዜ ተስፋችን የተፈጸመብሽ አንቺ ነሽና እናወድስሻለን፤ ብጽዕት ሆይ እንልሻለን፤ ቅድስት ሆይ እንልሻለን፡፡ ይኸውም አንደበታችን የሚችለውን ያህል መናገራችን እንጂ ምስጋናሽንስ የኪሩቤል አንደበትም ማድረስ አይቻለውም፤ የሱራፍኤል አንደበትም ተናግሮ አይፈጽመውም፡፡ ከወዳጅሽ ከልጅሽ ምሕረትንና ይቅርታን ለምኝልን፡፡ አሜን ለይኩን ለይኩን!!!!!!!!!!

ዋቢ
1.ቅዳሴ ማርያም አንድምታ
2.ነጭ ዕንቁ በአዳም ገላ
3.ትንቢተ ኢሳይያስ ንባቡና ትርጓሜው
4.ስንክሳር- የዲ/ መልአኩ እዘዘው ገጽ

FeedBurner FeedCount