Thursday, July 18, 2013

ፈቃደ እግዚአብሔር (ክፍል ሦስት)



በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ባለፉት ጊዜያት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዳንረዳ ያደረጉንን ሁለት ምክንያቶች ተመልክተን ነበር፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ከችግሮቹ ውስጥ ሦስቱን አቀርባለሁ፡፡ በሚቀጥለውና በመጨረሻው ክፍል ግን ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዴት እንደምንረዳ አይተን ጽሑፉ ይጠናቀቃል፡፡ መልካም ንባብ!

Wednesday, July 17, 2013

ውሉደ ብርሃን ትሆኑ ዘንድ በብርሃን እመኑ - የዮሐንስ ወንጌል የ፵፯ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.፲፪፡፴፬-፶)

በገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ውሸት በእልፍ የሚያማምሩ ሕብረ ቀለማት ብትቀባም ውሸትነቷ ከመታወቅ አታመልጥም፡፡ ያረጀና ያፈጀ ግድግዳም ምንም ያህል በሚያምር ቀለም ቢቀባም አዲስ መሆን አይችልም፡፡ የሚዋሽ ሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ ምንም ያህል ውሸቱን እውነት በሚመስሉ ውብ ቃላት ቢያሽሞነሙነውም ውሸታም መሆኑ በቀላሉ ይታወቃል፡፡ በአይሁድ ሕዝብ ዘንድ የምናስተውለውም ይኸንኑ ነው፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ ሁሉን (በአሚን) ወደ እኔ እስባለሁ” ሲላቸው /ቁ.፴፪/ እነርሱ ግን መልሰው፡-እኛስክርስቶስ (በመሲሑ) ሞት እንደሌለበት፣ ለዘለዓለምም እንደሚኖር በኦሪት ሰምተናል /መዝ.፻፱፡፬፣ ኢሳ.፬፡፮፣ ሕዝ.፴፯፡፳፮፣ ዳን.፯፡፲፫-፲፬/፤ አንተስ የሰው ልጅ ክርስቶስ ይሰቀል ዘንድ አለው እንደምን ትላላህ? ይህ የሰው ልጅ ክርስቶስስ ማን ነው?” ይሉታልና /ቁ.፴፬/። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን አንቀጽ በተረጐመበት ድርሳኑ እንዲህ ይላል፡- “ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች መሲሑ (ክርስቶስ) ለመዘኑ ኅልፈት ለመንግሥቱም ሽረት የሌለበት ዘለዓለማዊ መሆኑን ከተለያዩ መጻሕፍተ ብሉያት ቢያነቡም፣ እዚያው ዘለዓለማዊነቱን ባነበቡበት ቦታ ላይም ለሰው ልጆች ሲል ስለሚደርስበት መከራ መስቀልና ስለ ትንሣኤው ጨምረው አንብበዋል፡፡ ‘ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም’ /ኢሳ.፶፫፡፯/፤ ‘ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከመሰማርያህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ ተኛህ እንደ ሴት አንበሳም አንቀላፋህ እንደ አንበሳ ደቦልም የሚቀሰቅስህ የለም’ /ዘፍ.፵፱፡፱/ እና የመሳሰሉት ቃላት ደጋግመው አንብበዋቸዋል፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ (መሲሑ) አይደለም ለማለት ስለፈለጉ ብቻ ‘እኛስ በመሲሑ ሞት እንደሌለበት፣ ለዘለዓለምም እንደሚኖር በኦሪት ሰምተናል’ ይላሉ፡፡ የመሲሑ ሞት ዘለዓለማዊነቱን የሚጻረር አስመስለው ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ አንዱን ጫፍ ብቻ በመያዝም ወደ ስሕተት ይነጉዳሉ፡፡ ‘ከፍ ከፍ ያልሁ እንደሆነ’ ሲላቸው ‘እሞታለሁ እሰቀላለሁ’ ማለቱ እንደሆነ ስለገባቸው ‘አቤቱ ሆይ! ስለመሲሑ የምናውቀው አሁን እንደነገርንህ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ይሞታል ይሰቀላል የምትለው መሲሕ ፈጽመን አናውቀውም (አንተን አናውቅህም) ይሉታል” ይላል /St. John Chrysostom, Homily LXVIII/፡፡ ዓምደ ሃይማኖት የተባለው ቅዱስ ቄርሎስም “ከመጻሕፍት ጥቅስ በመጥቀስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረው ትምህርት ሐሰት ነው ለማለት ይጥሩ ነበር” ይላል /St. Cyril of Alexandria, Commentary on The Gospel of John, Book 8/፡፡

Thursday, November 15, 2012

…………. ገሊላ እትዊ …………..


በልዑል ገ/እግዚአብሔር

ደመና በወርኃ ጽጌ በበረሃ ሰፈፍ
ከገሊላ ወጥቶ በምስር ላይ ሲከንፍ
ዝናም ጣለለት ለዚያ በረሃ ግለቱ
የሐዲስ ኪዳን ምስራች አማናዊነቱ!
የሄሮድስ ጦር
ስልምልም ነው ከእሳት አይዋጋም
አዛይቱን
አዛኝቱን እመ መለኮትን አይጠጋም!
ሕጻን ከሰማይ የወረደ ድንቅ ቸር አድራጊ
ባለ እልፍ ሠራዊት ጋሸኛ ከእኩያት ተዋጊ
ብርሃን ያጣ የጨለማ መሬት ብርሃን ወጣለት
በድርሳን ቀለም ተቀልሞለት መዝገብ ተጻፈለት
የስደቱ አንድምታ ውሃ አፍስሷልና ላያደርቀው
ደመና በበጋ በግብጽ ታይቷልና ተአምር ነው!

Wednesday, November 7, 2012

ተጐጂው ማን ነው?


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
                      (ጥቅምት 29/2005 ዓ.ም፣ በገ/እግዚአብሔር ኪደ)
  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ካስተማራቸው ትምህርቶች አንዱ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ የሚረግሙአችሁን መርቁ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፤ ስለሚበድልዋችሁና ስለሚያሳድድዋችሁም ጸልዩ” የሚል ይገኝበታል /ማቴ.5፡43-44/፡፡
 ብዙዎቻችን ይህን ቃል ብናውቀውም ጠላቶቻችንን የምንወድበት፣ የምንመርቅበትና ስለ እነርሱ የምንጸልይበት ምክንያት ምን እንደሆነ ካለማስተዋላችን የተነሣ ይህን ለማድረግ እንቸገራለን፡፡ “ጌታ እንደዚያ እንድናደርግ ስላስተማረን ነው” በማለት እንደ ትእዛዝና ግዴታ ብቻ አድርገን የምንመለከተውም አንጠፋም፡፡
 ሆኖም ግን ከላይ የጠቀስነው የጌታችን ቃል እንዲህ የተባለበት የጠለቀ ምክንያት አለው፡፡ ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጥያቄአዊ በሆነ አመክንዮ እንዲህ በማለት ያብራራልናል፡-

FeedBurner FeedCount