Tuesday, December 17, 2013

ነቢዩ አሞጽ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፱ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“አሞጽ” ማለት “ሽክም፣ ጭነት” ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በዚኽ ስም የሚጠሩ ሦስት ሰዎች ያሉ ሲኾን እነርሱም የነቢዩ ኢሳይያስ አባት /ኢሳ.፩፡፩/፣ የምናሴ ልጅ ንጉሥ አሞጽ /፪ኛ ነገ.፳፩፡፲፰/ እንዲኹም ለዛሬ የምናየውና ከደቂቀ ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢዩ አሞጽ ናቸው፡፡
 የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት እንደሚያስረዳው የነቢዩ አሞጽ አባት ቴና ሲባል እናቱ ደግሞ ሜስታ ትባላለች፡፡ ነገዱም ከነገደ ስምዖን ወገን ነው፡፡

Sunday, December 15, 2013

ነቢዩ ሆሴዕ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፮ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
“ሆሴዕ” ማለት ከ፲፪ቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “መድኃኒት” ማለት ነው፡፡ መድኃኒት መባሉም እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ ባጭር ታጥቆ፥ ጋሻ ነጥቆ፥ ዘገር ነቅንቆ አማሌቃውያንን አጥፍቶ እስራኤልን አድኖ፥ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዉን ቆርሶ፥ ደሙን አፍስሶ፥ ፲፫ቱን ሕማማተ መስቀል ታግሦ፥ አጋንንትን ድል ነስቶ ነፍሳትን አድኖ አይደለም፤ አባት እናቱ በትንቢቱ በትምህርቱ እንዲያድን አውቀው “ሆሴዕ - መድኃኒት” ብለዉታል እንጂ፡፡ ስለዚኽ የስሙ ትርጓሜ ተልእኮውን የሚያስረዳ ነው ማለት ነው፡፡

Friday, December 13, 2013

ነቢዩ ዳንኤል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 “ዳንኤል” ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን የስሙም ትርጓሜ “እግዚአብሔር ፈራጅ ነው” ማለት ነው፡፡ ይኸውም ተልእኮውን የሚገልጥ ነው፡፡ አፍአዊ በኾነ ትርጓሜ (Literally) ስንመለከተው እግዚአብሔር በነቢዩ ዳንኤል አድሮ በአሕዛብ ላይ እንደሚፈርድ፤ በአሕዛብ ላይ ብቻ ሳይኾን የዋሐንን በሚከስሱ ሰዎች ላይ እንደሚፈርድ፤  አንድም እግዚአብሔር ጨቋኙን ንጉሥ አጥፍቶ ወደ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም ወገኖች ማለትም እስራኤልንና ይሁዳን ነፃ እንደሚያወጣቸው የሚያስረዳ ሲኾን፤ በምስጢራዊው መልኩ ግን የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዲያብሎስ ምርኮ የኼዱት ኹለቱም ወገኖች ማለትም ሕዝብም አሕዛብም ከኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶ የክብርን ሸማ እንደሚያለብሳቸው/ሰን የሚያመለከት ነው፡፡ 

Wednesday, December 11, 2013

ነገረ ማርያም - ክፍል ፫ (የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት)



በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት መምህር

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ታኅሳስ ፫ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ቅድስት ድንግል ማርያምም እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በእናት በአባቷ ቤት ውስጥ ኖራለች፤ ይኽነን በእናት በአባቷ ቤት የነበራትን አስተዳደግ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) በሚለው ጥንታዊዉ መጽሐፍ ሲገልጽ (ሕፃኗም ከቀን ወደ ቀን በኀይልና በብርታት እያደገች ኼደች፤ የስድስት ወር ልጅ በኾነች ጊዜ እናቷ መቆም ትችል እንደኾነ ለማየት መሬት ላይ አቆመቻት፤ ርሷም ሰባት ርምጃ ተራምዳ ወደእናቷ ዕቅፍ ውስጥ ገባች፤ እናቷም እንዲኽ አለቻትወደ ጌታ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስክወስድሽ ድረስ በራስች እንዳትራመጂ አለቻትና በመኝታ ቤቷ ውስጥ ውስጥ የቅድስና ስፍራ አበጀችላትአንድ ዓመት በኾናት ጊዜም ኢያቄም ታላቅ ግብዣ አድርጎ ካህናቱን፣ ጸሐፈትን፣ ታላቆችንና ሕዝብን ጠራ፤ ከዚያም ኢያቄም ልጁን ወደ ካህናቱ አቀረባት እነርሱምአባታችን እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ባርካት በትውልድ ኹሉ የሚጠራ ማብቂያ የሌለው ስምን ስጣት እያሉ ባረኳት፤ ሕዝቡም ኹሉይደረግ ይኹን ይጽና አሜንአሉ፤ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዳት ርሱምልዑል እግዚአብሔር ሆይ ይኽቺን ልጅ ተመልከት ለዘላለም በሚኖር በፍጹም በረከትም ባርካትበማለት ባረካት፤ ሐናም ይዛት ወደ ተቀደሰው የማደሪያዋ ክፍል በመውሰድ ጡትን ሰጠቻት…) ይላል፡፡

FeedBurner FeedCount