Saturday, April 25, 2015

ሰማዕታት

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ሰማዕት የሚለው ቃል ስርወ ቃሉ “ሰምዐ” የሚል ሲኾን ይኸውም ሰማ፣ አደመጠ፣ አስተዋለ፣ ተቀበለ፣ መሰከረ፣ ምስክር ኾነ፣ ያየውን የሰማውን ተናገረ፤ አየኹ ሰማኹ አለ ማለት ነው፡፡ በመኾኑም ሰማዕት ማለት የሚመሰክሩ፣ ሃይማኖታቸውን መስክረው በሰማዕትነት የሚሞቱ ማለት ነው፡፡ ለአንድ ሰማዒ ሲኾን ሲበዛ ሰማዕት ይኾናል፡፡
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሰማዕታት መዠመሪያ የሚባለው አቤል ነው፡፡ በአክአብና በኤልዛቤል ትእዛዝ በድንጋይ ተወግሮ በግፍ የተገደለው ናቡቴ፣ በይሁዳ ንጉሥ በምናሴ ትእዛዝ በእግሮቹና በራሱ መካከል በመጋዝ ተሰንጥቆ የሞተው ነቢዩ ኢሳይያስ፣ እንዲኹም በአይሁድ በድንጋይ ተወግሮ የተሠዋው ነቢዩ ኤርምያስም ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በዘመነ ሐዲስም ከሕፃናተ ቤተ ልሔም የዠመረው በእነ ካህኑ ዘካርያስ፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ቅዱስ ቂርቆስ፣ በአጠቃላይ በዲዮቅልጥያኖስና መክስምያኖስ የተጨፈጨፉት የሦስተኛውና የአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያም ሰማዕትነትና ክርስትና የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ አሕመድ፣ ሱስንዮስ፣ ፋሺስት ጣልያን፣ ደርግ፣ እንዲኹም በቅርቡ በአርሲ በምዕራብ ሐረርጌ በጅማ አጋሮ በአክራሪ ሙስሊሞች የተፈጸሙት ለዚኽ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ከዚኽ በመቀጠል ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “The Cult of the Saints - ፍኖተ ቅዱሳን” በተሰኘ መጽሐፍ በጊዜው ለነበሩ ምእመናን ስለ ተለያዩ ሰማዕታት ያስተማራቸውን ትምህርት ከአኹኑ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ጋር እያገናዘብኩ የተረጐምኩትን በአጭሩ አቅርቤላችኋለኁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡

Thursday, April 23, 2015

ሰው ሲሞትብን ምን እናድርግ?

በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 15 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ልጆቼ! ክርስቲያን ሲያርፍ አግባብ የሌለው ለቅሶ አይለቀስም፡፡ ታላቅ የኾነ ሥነ ሥርዓት እየተካሔደ ሳለ ለቅሶ አይለቀስም፡፡ እማልዳችኋለሁ! እስኪ ልጠይቃችሁና እናንተም መልሱልኝ! ኹላችንም በአንድ ቦታ ተሰብሰበን ሳለ የሀገራችን ንጉሥ ለአንዳችን የጥሪ ወረቀት ልከው ለእራት ግብዣ ጠሩን እንበል፡፡ ከእኛ መካከል ወደ ንጉሡ ተጠርቶ ስለ ሔደው ሰው የሚያለቅስ ማን ነው?

Wednesday, April 15, 2015

መንፈሳዊ ሕይወት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 8 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
(ይኽ ጽሑፍ ከዚኽ በፊት ተለጥፎ የነበረ ነው)
        በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ እሑድ ባለው ወራት ረቡዕንና ዓርብን ጨምሮ አይጦምም፤ የቀኖና ስግደትም አይሰገድም፡፡ ይኽም ሠለስቱ ምዕት በ325 ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ሲሰበሰቡ በሀያኛው ቀኖኗቸው የወሰኑት ቀኖና ነው /ሃይ.አበ.20፡26፣ The Oxford Dictionary of the Christian Church, pp 1250, 1738/፡፡ ይኽን ቀኖና ሲወስኑም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይኽ ወራት ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ያለውን ሕይወታችን የሚያሳይ ስለኾነ ነው እንጂ፡፡ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት ተብሎ የሚደረግ ጦምም ኾነ ስግደት የለም፡፡ ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ በዲያብሎስ ከመፈተን፣ ከእግዚአብሔር ውጪ የኾነ ሌላ ሐሳብን ከማሰብ ነጻ የሚወጣበት ወራት ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ፈቃዳችን ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር የተስማማ ነው፡፡ ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ከድካሙ ነጻ ስለሚኾን እግዚአብሔርን ለማመስገን ትጉኅ ነው፡፡ እንደ አኹኑ እንቅልፍ እንቅልፍ አይለውም፤ ዘወትር የቅዱሳን መላእክትን ምግብ ለመብላት ማለትም ለማመስገን የተዘጋጀ ነው እንጂ፡፡

Monday, April 13, 2015

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ዘጠኝ)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሚያዝያ 6 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
        ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን - በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
        አሰሮ ለሰይጣን - አግዐዞ ለአዳም
        ሰላም - እምእዜሰ
        ኮነ - ፍሰሐ ወሰላም
        ውድ የመቅረዝ አንባብያን! እንዴት አላችኁ? የትምህርተ ሃይማኖት ትምህርቱን እየተከታተላችኁ እንደኾነ ጽኑ እምነቴ ነው፡፡ እስከ አኹን ድረስ የትምህርተ ሃይማኖት መግቢያ፣ የሃይማኖት አዠማመርና እድገት፣ ከኹሉም በፊት አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ማወቅ ያለበት ብለን ነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ቅዱስ ትውፊት፣ ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አረዳድ፣ ስለ ዶግማና ቀኖና፤ ስለ እግዚአብሔር መኖርና ስለ ባሕርዩ ጠባያት እንዲኹም ስሙ ማን እንደኾነ ተማምረናል፡፡ ዛሬም ሥነ ፍጥረት ብለን እንቀጥላለን፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋልን ያድለን፡፡ አሜን!!!

FeedBurner FeedCount