Sunday, October 4, 2015

የዘመናችን አጥማቂ ነን ባዮች፡- የሐሳዊው መሲሕ መንገድ ጠራጊዎች

በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ክፍል ሁለት
1.   ተአምራት ማድረግ የምን ውጤት ነው? ተአምራት ማድረግ ከሁለት ነገሮች ሊመጣ ይችላል፡፡ ከመንፈሳዊ ብቃትና ከሰይጣን አሠራር፡፡ በክርስትና ሕይወቱ የበረታ ሰው መንፈሳዊ ብቃቱ በሕይወቱ በሚገለጡ ተአምራት ሊታወቅ ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የምናገኛቸው ቅዱሳን በገድል ተቀጥቅጠው፣ ሰማዕትነት ከፍለው፣ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በሚገባ ተጉዘው ዲያብሎስን ድል ሲነሡት በሕይወታቸው ውስጥ ተአምራት ይገለጣሉ፡፡ ይህም ማለት ተአምራት የመንፈሳዊ ብቃት መገለጫ ነው ማለት ነው፡፡ የተአምራት ስጦታ እንዲሁ በድንገት አይገለጥም፡፡ በዚያ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እያደገ፣ እየተገለጠና እየተመሰከረለት በሚመጣ መንፈሳዊ ዕድገት ምክንያት እንጂ፡፡ ለዚህ ሁለት ምሳሌዎች እናንሣ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስና አቡነ ተክለ ሃይማኖት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ አራት ምዕራፍ ያለው መንፈሳዊ ዕድገቱ በየዘመናቱ ተገልጦልናል፡፡ በፍኖተ ደማስቆ መመለሱ(የሐዋ8) በአንጾኪያ በሱባኤ መኖሩ(የሐዋ13) ለአገልግሎት ተጠርቶ ከበርናባስ ጋር መውጣቱ እና ከአረማውያን፣ ከአይሁድና ከመናፍቃን ጋር ባደረገው ተጋድሎ የምናገኘው በትምህርትና በተአምራት የተገለጠ ሕይወቱ ናቸው፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሕይወት ቀስ በቀስ እያደገ (ወየሐውር እም ኃይል ውስተ ኃይል እንዲል) የመጣ ነው፡፡

የዘመናችን አጥማቂ ነን ባዮች፡- የሐሳዊው መሲሕ መንገድ ጠራጊዎች



በዲ/ን ዳንኤል ክብረት
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ክፍል አንድ
በዚህ ዘመን በተደጋጋሚ ከሚነሡ መንፈሳውያን ጥቄዎች መካከል አንዱ የጥምቀትና አጥማቂዎች ጉዳይ ነው፡፡ ጥምቀት(የክርስትና ጥምቀትን አይመለከትም) በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ምእመናን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስ እንዲያገኙባቸው ከእግዚአብሔር ከተሰጡ ጸጋዎች አንዱ ነው፡፡(2 ነገሥት 5 ዮሐ. 5፣ዮሐ. 9)፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ውስጥ በልዩ ልዩ ገድላተ ቅዱሳን ላይ እንደምናነበው በጠበል ሕዝቡን ሲፈውስ ኖሯል፡፡ ሕዝብ ፈውስ የሚያገኝባቸው እንደ ሰሊሆምና እንደ ቤተ ሳይዳ የታወቁ የቃል ኪዳን ቦታዎችም ነበሩ፡፡
አሁን በያዝነው ዘመን አያሌአጥማቂ> የሚባሉ ሰዎች ተነሥተዋል፡፡ ክብራቸውን የሚገልጥ ማስታወቂያ ያስነግራሉ፣ መቁጠሪያ ይሸጣሉ፣ ቅባት ይቀባሉ፣ አዳራሽ ከፍተው ወይም ሕዝብ በሜዳ ሰብስበው እንፈውሳለን ይላሉ፤ ሰይጣን ተናገረ የሚባለውን በካሴት ቀድተው ይሸጣሉ፡፡ ከዚህ ቀጥዬ በማቀርባቸው አሥር ምክንያቶች እነዚህን ሐሳውያን መቀበል የለብንም ብዬ አምናለሁ፡፡

FeedBurner FeedCount