Tuesday, October 30, 2012

ጌታ ሆይ አምናለሁ -የዮሐንስ ወንጌል የ40ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.9)


       በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  በምዕራፍ 8 እንደተመለከትን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግራቸውን ነገር ከማመን ይልቅ አይሁድ “ጋኔን አለብህ” /8፡48/ ብለው በድንጋይ ሊወግሩት ሽተው ነበርና አንድም “አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” /8፡58/ ብሏቸው ነበርና ቁጣቸውን አብርዶ ቀዳማዊነቱን በገቢር (በሥራ) ያስረዳቸው ዘንድ ወደደ /መዝ.51፡4/፡፡ ስለዚህም ሲያልፍ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው (ሲለምን) አየ /ቁ.1/። ይህ ዐይነ ሰውር ሰው የዓይን ምልክት እንኳን አልነበረውም፡፡ እንዲሁ ልሙጥ ግንባር ነበረው እንጂ፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ሳይሆን ክርስቶስ አየው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ክርስቶስ ዕዉሩን በልዩ እይታ (በፍቅርና በሐዘኔታ) እንዳየው አስተዋሉ፤ ደነቃቸውም፡፡ አስቀድሞ መጻጉዑን ሲፈውሰው፡- “ዳግመኛ እንዳትበድል” ብሎት ስለነበረ /5፡14/ “ይህ ዕዉር ሆኖ የተወለደውም ዕዉርነቱ ከበደል የተነሣ ነው ማለት ነው” ብለው አሰቡ፡፡ አሳባቸው ግን ግራ አጋባቸው፡፡ ስለዚህም፡-  መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ነው ወይስ ወላጆቹ?” ብለው ጌታን ጠየቁት /ቁ.2/። ጌታችንም፡-እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው በራሱ ኃጢአት ይቀጣል እንጂ አባት ስለ ልጅ ልጅም ስለ አባት አይቀጣምና /ዘዳ.24፡16/፡፡ ታድያ እርሱ ነውን? ብትሉም አይደለም እላችኋለሁ፡፡ እንግዲያ ስለምን ዓይነ ስውር ሆነ? ብትሉም የእግዚአብሔር ሥራ (አስቀድሞ አዳምን ከምድር አፈር የፈጠርኩት ቀዳማዊ የምሆን እኔ መሆኔን) በእርሱ እንዲገለጥ ነው እላችኋለሁ /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatation’s Diatessaron, 28 /፡፡

Sunday, October 28, 2012

ምክረ አበው ቁጥር አራት


ልጆቼ! ሓኪሞች ብትሆኑ፣ መሀንዲሶች ብትሆኑ፣ የሽመና ሠራተኞች ብትሆኑ፣ መርከበኞችም ብትሆኑ መልካም ነው፡፡ ይህን ጥበብ መማራችሁም ጥሩ ነው፡፡ እኔ ግን ከዚህ የበለጠ ጥበብ አሳያችኋለሁ፡፡ በዚህ (በተማራችሁት ምድራዊ) ጥበባችሁም ሌላ ጥበብ ትማሩበት ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ ሰማያዊን ጥበብ! ከላይ በገልጽኩላችሁና እናንተ በተማራችሁት ጥበብ ተጠቅማችሁ ገንዘብ ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡ በዚህ ገንዘባችሁ ግን ድሆችን መርዳት ልመዱበት፡፡ ይህ የምነግራችሁን ጥበብ እንደ ቀላል የምታዩት አትሁኑ፡፡ መሀንዲሶች ብትሆኑ በምህንድስና ጥበባችሁና እውቀታችሁ በዚህ ምድር የሚያማምሩ ቪላ ቤቶችን ልትሠሩ ትችላላችሁ፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን
በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ የዘላለም ቤታችሁን ትሠራላችሁ፡፡ በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤታችሁ በጣም ብዙ ወጪ ብዙም ድካም ይጠይቃችኋል፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን ብዙ ልፋት የለውም፡፡ ወጪአችሁ መልካምና ፈቃደኛ መሆን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤት የተለያዩ ዓይነት ብረቶችና ማቅለጫዎች እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን ትጠቀማላችሁ፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋችሁም፡፡ የሚያስፈልጋችሁ ብሎን ወይንም ብረት ወይንም የከበረ ድንጋይ ሳይሆን መልካም ምግባራችሁና በጎ ፈቃዳችሁ ብቻ ነው፡፡

Friday, October 26, 2012

ቅዱስ እሰጢፋኖስ

               በዲ/ ሽመል መርጊያ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  
 በሐዋርያት ስብከት ቤተ ክርስቲያን ስትስፋፋ በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ተስበው ወደ ክርስትና እምነት የተመለሱ ከአይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች መሬታቸውንና ጥሪታቸውን በመሸጥ  ያላቸውን ሀብት አንድነት በማድረግ በኢየሩሳሌም የአንድነት ኑሮን ይኖሩ ነበር፡፡ በኅብረትም የሐዋርያት ትምህርትን በመስማትና  በጸሎት ይተጉ እንዲሁም ማዕድን በመባረክ በጋራ ይመገቡ ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስምአንድ ልብና አንዲት ነፍስ አላቸው በማለት (የሐዋ.432) ስለአንድነታቸው ፍጹምነት ይነግረናል፡፡

Tuesday, October 23, 2012

ሞትን መፍራት ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 
ጥያቄ፡- እሞታለሁ ብዬ ሳስብ በጣም እጨነቃለሁ፡፡ እናቴ እንደነገረችኝ ከሆነ ሞትን መፍራት የጀመርኩት ገና ከልጅነቴ ጀምሬ ነው፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ሳለሁ በጣም ከምቀርባቸው ጓደኞቼ መካከል ከአንዱ ጋር ተጣላሁና ሳልታረቀው በሳምንቱ ሞተ፡፡ በጊዜው በጣም ጸጸተኝ፡፡ ሞትን ባሰብኩ ቁጥር የሚታየኝ ያ ሳልታረቀው የሞተው ልጅ ነው፡፡ የመፍራቴ መጠንም በእድገቴ ልክ እየጨመረ ነው፡፡ ሌሊት ላይ ባንኜ “አሁን ብሞትስ?” ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ ንስሐ ብገባም ፍርሐቱ ሊለቀኝ አልቻለም፡፡ “ሰው ሞተ” ሲባልም በጣም እደነግጣለሁ፡፡ የምደነግጠውና የምፈራው ግን ሰውዬው ስለሞተ ሳይሆን “እኔም እኮ እሞታለሁ” ብዬ ነው፡፡ እባካችሁ በጣም ጨንቆኛልና ሞትን መፍራት ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?
                             እኅታችሁ ኤልሣቤጥ ነኝ ከአ.አ. 

ምላሽ፡-ውድ ጠያቂያችን! የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላምታ ባለሽበት ይድረስሽ፡፡ ለጠየቅሽን ጥያቄ የቻልነውን ያህል ለመርዳት መጻሕፍተ ሊቃውንትን አገላብጠን ያገኘነውን መልስ እነሆ ብለናል፡፡ እንደ ጠቋሚ ይረዳሻል ብለንም እናምናለን፡፡ ከቻልሽ አስቀድመሽ በጸሎት ጀምሪና በተመስጦ ሆነሽ አንቢው፡፡ መልካም ንባብ!

FeedBurner FeedCount