Tuesday, August 6, 2013

የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ- መግቢያ

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
                                                                                  
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- ውዳሴ፡- “ወደሰ” ከሚል ግስ የወጣ ሲኾን ትርጓሜውም ማወደስ፣ መወደስ፣ አወዳደስ፣ ውደሳ፣ ምስጋና… ማለት ነው፡፡ “ውዳሴ ማርያም”        ሲልም የማርያም ምስጋና ማለት ነው፡፡
  የውዳሴ ማርያም መጽሐፍ ጸሐፊ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ሲኾን መጽሐፉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በጣም የታወቀና የተወደደ የጸሎት መጽሐፍ ነው። ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ የሚያወድስ፣ ዘለአለማዊ ድንግልናዋን የሚያስተምር፣  በስነ ጽሑፋዊ ይዘቱም እጅግ ውብ የኾነ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ለማመስገን የተጻፈ ይኹን እንጂ በውስጡ እጅግ ረቂቅ የኾነ የስነ መለኮት ትምህርት (ለምሳሌ ስለ ምሥጢረ ሥላሴና ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ ) የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የቆሎ ተማሪዎች በቃል ትምህርቱ ዘርፍ ከየዘወትር ጸሎት ቀጥለው በንባብና በዜማ ይህን ውዳሴ ማርያም የተባለውን የትምህርት ክፍል ይማሩታል።
 ለጊዜው ይኸን እናቈየውና ወደ ተነሣንበት ዓላማ እንመለስ፡፡ በቀጥታ ወደ ትርጓሜው ከመግባታችን በፊትም ስለ ጸሐፊው ዜና መዋዕል በትንሹም ቢኾን በዚህ ክፍል ልናስቃኛችሁ ወድደናልና ተከታተሉን፡፡ መልካም ንባብ!

Monday, August 5, 2013

ፈቃደ እግዚአብሔር፤ ክፍል አራት (የመጨረሻው ክፍል)

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- የእግዚአብሔርን ፈቃድ በምን አውቃለሁ? የሚለው ጥያቄ በራሱ በእኛ ውስጥ የተለየ ምልክት መሻት መኖሩን ያመለክታል፡፡ ይህን ዐይነት ምልክትን የመሻት አካሔድ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ባለፈው ጊዜ በሦስተኛው ክፍል ጽሑፍ አይተን ነበር፡፡ ለቅዱሳን የሚደረገው መገለጥ ራሱ ቅዱሳን ራሳቸውን ክደው ሙሉ በሙሉ ማንነታቸውን ለእግዚአብሔር ስለሰጡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ማለትም መጻኢው ቀድሞ በእነርሱ የሚገለጸው የደረሱበትን መዓርግ ለማሳየት ነው እንጂ በእያንዳንዱ ነገር ላይ ምልክትን እየሻቱ ያም እየተደረገላቸው አይደለም፡፡ ታዲያ እኛ ኃጥአኑና ደካሞቹ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ይህን ጥያቄ ለመረዳት አስቀድመን ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር ሦስት መሠረታዊ ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡

Friday, July 26, 2013

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር ነውን? - ክፍል ፫ -

በገብረ እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡ ውድ ጠያቂያችን! እንደምን ሰነበቱ? ዳግም እንድንገናኝ፣ መንፈሳዊ ጭውውትም እንድናደርግ የፈቀደልን ለቸርነቱ ስፋት ለፍቅሩም ልኬት የሌለው ደግ ፈጣሪያችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይኹን፤ አሜን፡፡ እነሆ ለዛሬ ደግሞ ብዙ ስስ ልብ ያላቸው ወገኖች (በተለይም የይሖዋ ምሥክሮችና ሙስሊሞች) ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ፍጡር ነው” ለማለት ከሚጠቅስዋቸው ቃላተ መጻሕፍት ቀዳሚውን ይዘን ቀርበናል፡፡ እርሱም “እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ” /ምሳ.፰፡፳፪/ የሚለው ነው፡፡ እንኪያስ እኛም ከአማናዊው መርከብ እንሳፈርና ከሊቃውንቱ ጋር ሆነን የምሥጢሩን ጽዋዕ እንቅዳ፤ በጥርጣሬ ፀሐይ ደርቆ የተጠማው ልቦናችንም ከማየ ሕይወት እናጠጣው፡፡

Sunday, July 21, 2013

ማፈር ቀረ!!!

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐምሌ ፲፭ ቀን፣ ፳፻፭ ዓ.ም)፡- አንድ ምክርና ታሪክ አካፋይ የሆነኝ ወዳጄ ጋር ስለ ሙስና ስናወራ የድሮ ሙሰኞች ብያንስ ይሉኝታ ነበራቸው ሲል የተረከልኝ ታሪክ “በርግጥም” አሰኝቶኛል፡፡ እርሱ እንደነገረኝ ከሆነ አሁን በቅርቡ በደርግ ዘመን አንድ ትልቅ ሰው ሦስት ጊዜ ሎተሪ ደርሷቸው ነበር ይባላል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ሰውዬው ብርቱ ሙሰኛ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይሉኝታ ስለነበራቸው በማንአለብኝነት በሦስት ሺሕ ደመወዝ የአራት ሚልዮን ብር መኖሪያ ቤትና ባለ ስድስትና ምናምን ፎቅ እንደሚሠሩት እንደ አሁኖቹ አንዳንድ ሰዎች ዝም ብለው በድፍረት አይሠሩም ነበር፡፡ ሰውዬው በወዳጆቻቸው በኩል ሎተሪ የደረሰውን ሰው በብርቱ ጥንቃቄ አስፈልገው ራሱን ከማሳወቁ በፊት በትርፍ ይገዙትና እርሳቸው ደረሳቸው እየተባለ ዜና ይወጣላቸዋል፡፡ ለካስ ይህም ብልሃት ኖሯል፡፡ ታድያ እንደ ነገረኝ ከሆነ እስከ ሦስት ጊዜ ሎተሪ ደርሰዋቸዋል ይባላል፤ እኒያን ባለ ይሉኝታ ሰው፡፡ የረሱት ነገር ቢኖር ሦስት ጊዜ ትልልቅ ገንዘብ በሎተሪ የወጣላቸው አስብለው ስማቸውን በድንቃ ድንቅ የዓለም መዝገብ ማሰፈር ብቻ ይመስለኛል፡፡ ቢያደርጉት ኖሮ ብያንስ በዕድል ለምናምን ሰዎች ትልቅ ማስረጃም ይሆኑ ነበር፤ ግን አላደረጉትም ብሎኛል፡፡ ዛሬ ግን እንዲህ ያለ ይሉኝታ እንኳ ጠፍቷል፡፡ እንኳን በዓለሙ ሰዎች ዓለሙን ትተናል ከምንለውና ገቢያችን እንትን ከሆነው እንኳ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቤት ሠርቶ እንኳን ሊታፈር ደግሶ ማስመረቅ ከተለመደ ሰንብቷል፡፡ ነገሩ ድሮ እንኳን ሰው ሰይጣኑም አፋራም ነበር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ዛርና ጥንቆላ እንደዛሬው በባሕታውያንና በአጥማቂ ወይም በመሳሰለው ስም ይነግድ እንደነበር አልሰማሁም፡፡ እዚያው በየሠፈራቸው አንዴ ገብስማ ዶሮ ሌላ ጊዜም ሌላ እያሉ ይሠሩ ነበር እንጂ እንዲህ እንደ ዛሬው ለይቶላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ቦታዎች ላይ ሳይቀር ገብተው በቃሁ ነቃሁ አይሉም ነበር፡፡ ታድያ ብዙ ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ከሀገር ፍቅር ቲያትር የሰማሁት ብለው በአንድ መድረክ ላይ ሲናገሩት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያሰማኝ “ማፈር ቀረ፤ መሽኮርመም ቀረ” ትዝ ይለኛል፡፡ በርግጥም ነገሩን ሁሉ ለሚያስተውል ነውርም፣ ማፈርም፣ ይሉኝታም ተሰብስበው ገደል የገቡና ቃላቱ ብቻ የተረፉ ይመስላሉ፡፡

FeedBurner FeedCount