Pages

Monday, May 21, 2012

የዮሐንስ ወንጌል የ15ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.3፡6-12)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
“ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” /ቁ.5/። “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብሎ እንደ ኒቆዲሞስ የሚጠይቅና የሚጠራጠር ሰው ካለ እንዲህ ብለን መልሰን እንጠይቀዋለን፡-  አዳም ከሕቱም መሬት የተወለደው እንዴት ነው? አስቀድሞ አፈር ቆይቶ በኋላ እንዴት ብሎ የተለያየ የሰውነት አካል ያለው ሰው ሆነ? አፈር ብቻ የነበረው በኋላ እንዴት ብሎ አጥንት፣ ጅማት፣ የደም ቧንቧ… ሆነ? ወንድሞች ሆይ! በዘፍጥረት መጀመርያ እንደምናነበው አፈር አፈር ነው፡፡ እግዚአብሔር በእጁ ሲያበጃጀው ግን ሰው ሆነ፡፡ አሁንም ሰው በማኅፀነ ዮርዳኖስ ውስጥ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ሆኖ ይፈጠራል፡፡ ነገር ግን ይህ መለኰታዊ አሠራር ስለሆነ ሰዋዊ አመክንዮ እንሰጥ ዘንድ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ የምናምን እንጂ የምንጠራጠር አንሁን /St. John Chrysostom Homily on the Gospel of John Hom.25/፡፡
በእርግጥም አንድ ሰው አዲስ ሕይወትን ለመጀመር አሮጌው ሕይወቱን መጣል አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አሮጌው ሰውነቱ መሞት አለበት፡፡ ይህም የሚሆነው በጥምቀት በኵል ነው /ሮሜ.6፡4-5፣ Basil the Great, On the Spirit 15:35/፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለገባልን የትንሣኤ ተስፋ ዐረቦን እንቀበላለን /2ቆሮ.1፡22/፡፡
“ለምንስ በውኃ አደረገው?” ልትሉ ትችላለችሁ፡፡ ስለ ብዙ ምክንያት፡- አንደኛ “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ” የሚለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ /ሕዝ.35፡25/፡፡ ሁለተኛ ውኃ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ይፈሳል፤ ጥምቀትም ለሁሉ ነውና፡፡ ሦስተኛ ውኃ ያነጻል፤ ጥምቀትም ያነጻልና፡፡ አራተኛ ውኃ ለወሰደው ፍለጋ የለውም፤ በጥምቀት የተሰረየ ኃጢአትም በፍዳ አይመረመርምና፡፡ አምስተኛ ውኃ መልክ ያለመልማል፤ ጥምቀትም መልክአ ነፍስን ያለማልማልና፡፡ ስድስተኛ በውኃ የታጠበ ልብስ ኃይል ጽንዕ ግዘፍ እየነሣ ይሄዳል፤ ምእመናንም ተጠምቀው ገድል ትሩፋት እያከሉ ይሄዳሉና፡፡ ሰባተኛ “ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ” ተብላ ነበር፤ አሁን ግን ክርስቶስ ገብቶባታልና ሕያውና ለባዊት ነፍስ ያላቸው ሰዎች ይገኝባታልና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ /ዘፍ.1፡20፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ ማቴ.3፡17/፡፡ እናም ስለ ሌላ ብዙ ምክንያት፡፡
 ጌታ ይቀጥላል፤ እንዲህም ይላል፡- “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው” /ቁ.6/።  ይህም ማለት “ከግዙፍ ሥጋ የሚወለደው ግዙፍ ሥጋ ነው፤  ከረቂቅ መንፈስ ቅዱስ የምትወለድ ነፍስ ግን መንፈሳዊት ናት፡፡ ከሥጋ ብቻ ስንወለድ “አፈር ነህና” የሚለው ማንነታችን ይቀጥላል፤ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ስንወለድ ግን ከማይሞተው እግዚአብሔር የማንሞት መንፈሳውያን ሆነን እንወለዳለን” ማለት ነው /ዮሐ.1፡12፣ Gregory of Nyssa/፡፡ አስቀድመን እንዳልነው ውኃው አሁን አብራከ መንፈስ ቅዱስ ማኅፀነ ዮርዳኖስ ስለሆነ “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” እንጂ “ከውኃ የተወለደ ውኃ ነው” አይባለም፡፡
 ኒቆዲሞስ ግን ነገሩ ረቀቀበት፤ እየተደናገረም ይደነቃል፡፡ ስለዚህም ጌታ “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ” ይሏል /ቁ.7/። የሚያየው ነገር ግን የማያስተውለው ምሳሌ በማምጣትም ያስረዷል፡- “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” /ቁ.8/። ይህ ነፋስ “ወደዚህ ሂድ፤ ወደዚህም አትሂድ” የሚለው ሳይኖር እርሱ ወደ ወደደው ብቻ ይሄዳል፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ስንወለድም እንዲህ ነው፡፡ አንድም እንደምንወለድ እናውቃለን፤ እንዴት እንደሚወልደን ግን አናውቅም፡፡ አንድም በበዓለ ኃምሳ እንደ ሆነው መንፈስ ቅዱስ ትንቢት ሲያናግር ምሥጢር ሲገልጥ ሱባዔ ሲያስቈጥር ልናስተውለው እንችላለን፤ እንዴት እንደሚያድር ማወቅ ግን አይቻለንም፤ በሰዋዊ አረዳድም ልንረዳው አይቻለንም /Theodore of Mopsuestia, Commentary on John 2:3-7/፡፡ ከመንፈስ የሚወለዱትም ልደት እንዲህ ነው፡፡ ይህም ማለት ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው አንተ ከወዴት እንደመጣህና (ከማን እንደተወለድክና) ወዴትም እንደምትሄድ (ሌላ ሀገር እንዳለህ) አያውቅም /ፊል.3፡20፣ Augustine, Tractes on the Gospel of John 12:5/፡፡
 “ኒቆዲሞስም መልሶ፡- ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” በማለት የባሰ ግራ ይጋባል/ቁ.9/፡፡ “ጌታችንም መልሶ፡- አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” ይሏል /ቁ.10/፡፡ ከእናንተ መካከል “ዳግም ልደትና የኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር መሆን ምን ያገናኘዋል?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ሔዋን ከአዳም አንዲት የጎድን አጥንት እንዴት ተፈጠረች? ኤልሳዕ የሰጠመውን ብረት እንዲሰፍ እንጨቱ ግን ያለ ባሕርዩ እንዴት እንዲሰጥም አደረገው? እስራኤል ባሕረ ኤርትራን እንዴት ተሻገሩ? ንዕማን በፈለገ ዮርዳኖስ ውኃ ተጠምቆ እንዴት ነጻ? /St. John Chrysostom Ibid/ በእርግጥም ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ሲሆን የሂሶጵ ቅጠል ምሥጢር፤ እስከ ማታ ድረስ የረከሰ ሆኖ ነገር ግን ማታ በውኃ ታጥቦ ንጹሕ ይሆናል የሚለውን የኦሪቱ ሥርዓት፤ ያዕቆብ በኵር ሳይሆን ብኵርናን እንዴት እንደተቀበለ፤ ማርያም እኅተ ሙሴ እንዴት ነጻች የሚለውን ሁሉ የአይሁድ መምህር ሲሆን ሊያውቀው ይገባ ነበር /St. Ephrem the Syrian, Commentary on Tatians Diatessaron 14:13/፡፡ 
 ከዚህ በኋላ ግን ጌታ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” /ቁ.11-12/ በማለት (ክርስቶስ) የሚናገረው ነገር በሰው ሕሊና ስለማይደረስ በእምነት እንዲቀበለው ይነግሯል፡፡ በእርግጥም ክርስቶስ በባሕርይ አምላክነቱ ከባሕርይ አባቱና ከባሕርይ ሕይወቱ ጋር የሚናረውን ሁሉ በትክክል ያውቋል፡፡ ኒቆዲሞስ ግን እንኳንስ ሰማያዊው ልደት ምድራዊው ነፋስ እንኳ ከየት መጥቶ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም፤ ኒቆዲሞስ ብቻ ሳይሆን እኛም አናውቅም /St. Cyril of Alexandria, Commentary on John/፡፡
ወንድሞቼ! እንግዲያስ ይህን ሰማያዊ ምሥጢር የምናምን እንጂ የምንጠራጠር አንሁን፡፡ ታላቁ መምህራችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረን በላይ ሌላ ምድራዊ መምህር ለራሳችን የምናመጣ አንሁን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

No comments:

Post a Comment