Pages

Wednesday, May 2, 2012

ልትድን ትወዳለህን?- የዮሐንስ ወንጌል የ23ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡1-9)!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!! ሰላመ እግዚአብሔር ይብዛላችሁ ወንድም እኅቶቼ!

  የ23ኛ ሳምንት ጥናታችን እነሆ! “ከዚህ በኋላ፣ በቅፍርናሆም የነበረው የገብረ ንጉሡን ልጅ በገሊላ ሆኖ ከፈወሰ በኋላ፣ በቃና ሁለተኛ የሆነውን ምልክት ካሳየ በኋላ አሁን ደግሞ የአይሁድ በዓል ነበረና ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ” /ቁ.1/። ብዙ ሊቃውንት ይህ በዓል የአይሁድ ፋሲካ ነበረ ይላሉ፡፡ በዓለ ኃምሳ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ጌታችን በተደጋጋሚ ወደ በዓላቶቻቸው የሚሄደው ብዙ ሰዎች ለገቢረ በዓል ስለሚወጡና በዚያም ብዙዎችን በወንጌል መረብ ለማጥመድ ነው፡፡ እናም ጌታ ወደ በዓላቸው ሲወጣ “በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ወደ ምትባል፤ አምስት መመላለሻም” ወደ ነበረባት አንዲት መጠመቂያ ገባ /ቁ.2/። ቤተ ሳይዳ ማለት ቤተ ሳህል- የምሕረት ቤት ማለት ነው፡፡ እግዚእበሔር አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚሰጠው መዳን፣ በአማናዊው ጥምቀት ለሚገኘው ሥርየተ ኃጢአት ምሳሌና ጥላ ይሆን ዘንድ በዚህች መጠመቂያ ድውያነ ሥጋ ይፈወሱባት ወደ ነበረችው መጠመቅያ ገባ/St.John Chrysostom Homily On the Gospel of John,Hom .36፡1/፡፡ ወንጌላዊው “መጠመቅያዋ አምስት መመላለሻ ነበሩባት” ብሎ እንደነገረን አስቀድመን እንዳልነው እስራኤል ዘሥጋ በአምስቱ መጻሕፍተ ኦሪት ኃጢአታቸውን በዝርዝር አዩ፤ ተመለከቱ እንጂ ፍጹም የሆነ ምሕረትን አላገኙም ነበር፡፡ ስለዚህም “ኃይልህን ከአርያም ላክልን፤ ከደዌአችንም ፈውሰን” ብለው እንዲለማመጡ የተሰጠች ነበረች /Augustine, Sermon on NT Lessons 75:2/፡፡

 “በዚህች ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጠውም በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር”/ቁ.3-4/፡፡ መልአኩ ውኃውን ሲያናውጠው ካለባቸው ማንኛውም ዓይነት ደዌ ሥጋ ይፈወሱ ከነበረ የመላእክት ጌታ የሆነው ወልድ ሲገለጥ ደግሞ ከደዌ ዘሥጋ ብቻ ሳይሆን ከነፍሳቸው ደዌም ሥርየተ ኃጢአትን እንደሚያገኙ የሚያሳይ ነበር፡፡ እነዚህ አይሁድ ግን ይህን መዳን ቸል በማለት ጌታ ሊያድናቸው ስላልቻለ ሳይሆን መዳን ስላልፈለጉ ብቻ ኃጢአታቸውን በዝርዝር እያዩ በዚያው ቀሩ፡፡ ይባስ ብለውም ደሙ በእኛና በልጆቻችን ይሁን ብለው ማሉ /ቅ.ዮሐንስ አፈ.ዝኒከማሁ/፡፡ ጌታችን በዚህች መጠመቅያ የነበሩትን ሁሉም ሰዎች ከማዳን ይልቅ ሁሉም የሚያውቁት፣“ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ” ሊያድንላቸው ወደደ/ቁ.5/፡፡ ይህን የሚያደርገውም ሁሉም አድነን እንዲሉትና ወደው ፈቅደው ከሚማቅቁበት በሽታ ይፈወሱ ዘንድ ነው /አውግስጢኖስ ዝኒ ከማሁ/፡፡ እናም ሰው ወዳጁ ጌታ ይህ ሰው በደዌ ዳኛ ባልጋ ቁራኛ እንደተያዘ ለብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ ወደ አልጋው ቀረበ፡፡ አቤት ፍቀር! በዘባነ ኪሩብ የሚቀመጠው እርሱ “አንድ ቀን እድን ይሆናል” ብሎ ተስፋ ወደሚያደርገው ታማሚ ጠጋ አለና ፈውስ በሆነው ቃሉ፡- “ልጄ! ልትድን ትወዳለህን? አለው። እንዴት ያለ ትሕትና ነው? እንዴት ያለ ፍቅር ነው? በሽተኛ ምን እንደሚፈልግ ግልጽ ቢሆንም አስፈቅዶ ይፈውሰው ዘንድ “ልትድን ትወዳለህን? ተስፋህ ፍጻሜ እንዲያገኝ ትፈልጋለህን? ብፈውስህ ትፈቅዳለህን?” ይሏል /ቁ.6/፡፡ ወንድሞቼ አንድን ነገር ፈልገን ለአንዲት ሳምንት እንኳን ሳንጸልይና ሳንታገሥ እግዚአብሔርን የምናማርር ስንቶች እንሆን? ይህ መጻጉዕ ግን እንዲህ አላለም፡፡ ጌታ ሲጠይቀው እንኳን፡- “የታመመ ሰው ምን እንደሚፈልግ አጥተኸው ነው እንዲህ የምትጠይቀኝ?” ብሎ አይቆጣም፡፡ ከዚያ ይልቅ በፍጹም ትዕግሥት፡-“ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” /ቁ.7/፡፡ ድውዩ ይህንን የሚለው ጌታችን የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ ቢያየው ነጥቆ ይጥለኛል ባይሆን እንኳን ከሚከተሉት አንዱ ያዝልኛል ብሎ ነው፡፡ በሌላ አገላለጥ አምላክ መሆኑን ስላልተረዳ ነው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ478/። ከዚህ በኋላ ውኃውን መልአክም አልመጣም፤ ውኃውም አልተንቀሳቀሰም፡፡ ይልቁንም የመላእክት ጌታ፡- “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው /ቁ.8/። “ሰውዬውም ወዲያው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ” /ቁ.9/። እንዴት ግሩም ነው! እንኳንስ ለ38 ዓመት ለ38 ሰዓት ታሞ የተኛ ሰው ፊዚዮቴራፒ ሳያሠራለት እንደልቡ አይንቀሳቀስም፡፡ ይህ መጻጉዕ የነበረ ሰውዬ ግን ለ38 ዓመት የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤተዎቹ ሄደ፡፡ ወዮ! አባታችን ሆይ!እኛም እንደ ቤተሳይዳዎቹ ታማሚዎች በደዌ ነፍስ ተይዘን የምሰቃይ ነበርን፡፡ ሰው አጥተን ለ5500 ዘመናት በደዌ ዳኛ በሲዖል ቁራኝነት ተይዘን ነበር፡፡ ነገር ግን የዓለም ሁሉ መድኅን የሆነው አንድያ ልጅህን ልከህ ከዚሁ እስራት ፈታኸን፡፡ ታድያ ለዚሁ ፍቅርህ ተመስገን ከማለት ውጪ ምን እንላለን? ቅዱስ አባት ሆይ! ዛሬም ይህን መድኃኒት የሆነው ድምጽህን ከመስማት ልባችን እንዳይጠነክር እርዳው፡፡ “አሜን ይሁልንልን” ብለንም ከተኛንበት የስንፍናና ያለማመን አልጋ እንድንነሣ ወደ አማናዊው ሰንበት (ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት) በጽናት እንድንጓዝ እርዳን፡፡ መዳናችን እንድንፈጽም አበርታን፡፡ አሜን!! ሰላም ወሰናይ!!

No comments:

Post a Comment