Pages

Friday, May 18, 2012

=+=ድንግል ማርያም በቅ/ገብርኤል ሠላምታ (ክፍል ሁለት)=+=በመምህር ቃለአብ ካሳዬ=+=


ያለፈው ክፍል
ድንግል ማርያም በቅ/ገብርኤል ሠላምታ (ክፍል 1)

አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ

            ይህን የመልአኩን ቃል ቅ.ኤልሣቤጥም ሳትጨምር ሳትቀንስ ደግመዋለች (ሉቃ 1.47)። የድንግል ማርያም ከሴቶች ሁሉ ተለይቶ መባረክ በቅ.ገብርኤልና በቅ.ኤልሳቤጥ መመስከሩ ይህ እውነት በሠማይና በምድር የጸና መሆኑን ያሳያል። ገብርኤል ከሰማይ ኤልሳቤጥ ከምድር ለሆኑት ወኪል ናቸውና።

     አንዳንዶች ከሴቶች መካከል ማለት “እንደሴቶች ሁሉ” ወይም “ከእነርሱ እንደ አንዱ” ማለት ነው። ከዚህ ውጭ “ ተለይታ” የሚል ሐረግ ባለመኖሩ ከአማኞች ጋር የምትቆጠር አንድ ተራ ግለሰብ ናት ብለዋል። ታድያ እንደሌሎች ሴቶች ከሆነች ሌሎች ሴቶች ይህን ብሥራት ለምን አንደ እርሷ አልተቀበሉም?

  ከሴቶች ተለይታ የመባረኳ ምስጢር:-

  • ሌሎች ሴቶቸ ቢወልዱ፣ ፃደቃን ሰማዕታትን ነው ፣እርሷ ግን የወለደችው የእነርሱን ጌታ ነው።
  • ሌሎች ድንግል ቢሆኑ እስከጊዜው ነው፣ኋላ ተፈትሆ/ድንግልናን ማጣት/አለባቸው። እርሷ ግን በጊዜው ሁሉ ድንግል ናት።
             በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንዲህ የሚል ጽሑፍ አለ:-“እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው በፀሎት ይተጉ ነበር።” (ሐዋ 1፡14) ጸሐፊው ሐዋርያው ሉቃስ የኢየሱስ እናት እንደሌሎች ሴቶች ብትሆን “ ከሴቶች ጋር” ይል አልነበረምን? ከሴቶችተለይታ የተባረከች በመሆኗ ግን “ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት” ብሎ ለይቶ ፃፈ።

አርሷም ባየቸው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠቸና ይህ አንዴት ያለ ሠላምታ ነው ብላ አሰበች ድንጋጤ የህሊና ፤ ፍርሃት የልቦና፣ ረዓድ የጉልበት ነው። ድንግል ማርያም የደነገጠችው ከመልአኩ ንግግር የተነሳ በመሆኑ“ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና” የሚል ቃል እናነባለን። የተነገረን ቃል ሁሉ እንደወረደ መቀበል ከቶ መንፈሳዊነት አይደለም። ይልቁንም“ይገባኛል ወይ?”   ማለት ይገባናል። በደነገጡበት ሰዓት ማሰብ ከባድ ቢሆንም ድንግል ማረያም ግን “ ……ብላ አሰበች” ይላል። ድንጋጤ የህሊና ነዉና በህሊናዋ ጠየቀች ማለት ነዉ።  እንግዲያውስ ድንጋጤዋ ከእምነት ማነስ ሳይሆን “እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ከሚል ጥልቅ መገረም ነው። የሚገባትን የክብር ሰላምታ ቆም ብላ ከመረመረችው፣ የማይገባቸውን ምስጋና  ሳይመረምሩ ለሚቀበሉ፣ በአሚና ዝማሬ በደብተራ ቅኔ ለሚኮፈሱ ይህ ተግሣጽ  ነው።!

 መልአኩም እንዲህ አላት፡- ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አግኝተሻልና አትፍሪ!

ፍርሃት አርቆ መናገር ለመልአክ አዲስ ባለመሆኑ ሲሆን ዋናው ግን ነደ እሳትን ብሩህ መለኮትን ትሸከሚያለሽና አትፍሪ ሲላት ነው።

እነሆም ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጂያለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ !

ጸንሳ ወንድ ልጅ መውለዷ ቀድሞም በትንቢት በሰፊው ተጠቁሟል። (ት.ኢሳ.7፡14) (ት.ኢሳ 9/6)። መልአኩ ግን የዚህ ወንድ ልጅ ስሙ ኢየሱስ መሆኑን ነገራት። ኢየሱስ ማለት “መድሃኒት” ማለት ነው። መድሃኒትነቱ ለ^ጢአትም፣ ለሞትም ነው! ይህን ስም ተሸክሞ ታምሞ  የማይታከም፣ ሞቶ የማይነሳ ማንም የለም!

   ኢየሱስ የሚለው ክቡር ስሙ
  •  ከስም ሁሉ በላይ የሆነ (ፊሊ 2፡10)
  • ከሰማይ በታች እንድንድንበት ዘንድ የተሠጠ ( ሐዋ4፡12)
  • ጉልበት ሁሉ የሚሰግድለት (ፊሊ 2፡10)
  • ምላስ ሁሉ የሚመሰክርለት (ፊሊ2፡11)
  • ተጠርቶ የሚለመን (ዮሐ14፡14)
  • የ^ጢአት ሥርየት የሆነ (ሐዋ2.38) (ሐዋ3፡16)
  •  ብዙ መከራ የሚጠራ (ማቴ 5፡11)
  • ዘወትር የምናጌጥበት (ራዕ7:5)
  • እንዲሁም የሚያጸድቀን ነው (ሮሜ 10፡13)
እርሱም ታላቅ ይሆናል! የልዑል ልጅ ይባላል።

አርሱም ታላቅ ይሆናል:- እርሱ ቀድሞም ታላቅ ነው! ተንቆ የነበረው የእኛን ማንነት ሲዋሐድ ያገኘነውን ክብር ለመግለጽ ግን ታላቅ ይሆናል አለ!
የልዑል ልጅ ይባላል:- እርሱ ቀድሞም የልዑል ልጅ ነው፣ እርሱ የሰው ልጅ ሲሆን፣እኛም የልዑል ልጆች መሆናቸንን አረጋገጠልን። እርሱ እኛ ጋር ሲሆን እኛም እርሱ ጋር ሆነናልና ከራሱ ጋር ይጠራናል!

ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋነ ይሰጠዋል!

 የዳዊትን ዙፋን የማይሻ ፣የእሳት ዙፋን ጥሎ የመጣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ማለት አብ ክርቶስን የዳዊትን ሥጋ ያዋሕደዋል ማለት ነው። ክርሰቶስ በዳዊት ሥጋ የዳዊት ልጅ ነውና። አብ በማዋሐድ ፣ ወልድ በመዋሐድ፣ መንፈስ ቅዱስ በማጽናት በድንግል ማርያም ረቂቅ ሥራ ተፈጽሟል። መዝ (88)
በያዕቆብ ቤትም ለዘለዓለም ይነግሳል

       ያዕቆብ አስራኤል ተብሏል (ዘፍ 32:22)። ኢየሱስ ክርስቶስ በእስራኤል
       ዘሥጋ ለጊዜው በትንቢት፣ በእስራኤል ዘነፍስ  (በክርስቲያኖች) ላይ ግን በፍቅር    
       ለዘለዓለም ነግሷል።
      ለመንግሰቱም መጨረሻ የለውም

ይህ ቃል አሰቀድሞ በነቢዩ በዳንኤል “በወገኖችና አሕዛብ ላይ ልዩ ቋንቋም  የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግስትም ተሰጠው፣ ግዛቱም የማያልፍ የዘለዓለም ግዛት ነው። መንግስቱም የማይጠፋ ነው”። ተብሎ ተነግሯል (ት.ዳን 7፡13-14)

ማርያምም መልአኩን ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው።

በአካልም በአሳብም ወንድ የማታውቅ መሆኗን የሚያሳይ የከበረ ቃል ነው።እኔ አንዱንም ሳላሰብ አንተ ብዙ ነገረ አልከኝ፣ ምድር ያለ ዘር፣ ሴት ያለወንድ ዘር እንዴት ይሆናል? አለችው “ እንዴት?” ስትል መልአኩ እንደካህኑ ዘካርያስ አልገሠፃትም! ምክንያቱም:-

    1ኛ. ካህኑ ዘካርያስ ካረጀሁ በኋላ እንዴት አወልዳለሁ? ቢል ካረጀ በኋላ የወለደ
      አባቱ አብርሃም ነበረና ማመን ይገባው ነበር። ድንግል ማርያም ግን
      በድንግልና ወልዶ የታየ ምሳሌ የሌላት ከመሆኑም ባሻገር ይህ ነገር
      ከመልአኩ ዕውቀት በላይ በመሆኑ ነው።
     2ኛ. መልአኩ በፊቱ ቆሞ  የሚያገለግለውን ጌታ እርሷ ወልዳው ያገለግላታልና በማዕረግ ጉዳይ ያከብራታል (ሉቃ 1፡19)  (ሉቃ2፡51)።

  “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ^ይል ይጸልልሻል፣ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፣ እነሆ ዘመድሽ ኤልሣቤጥ እርሷ  ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ጸንሣለች። ለእርስዋ መካን ትባል ለነበረችው ይህ ሰደስተኛ ወር ነው።”

የመልአኩ መልእክት ለኤልሣቤጥ ባለፈ ሠዓት፣ በስተርጅናዋ ለማሀፀኗ ልጅን የሰጠ አንቺንም በድንግልና ሳለሽ ለማህጸንሽ ልጅ ይሰጣል የሚል ነው። የቅ.ኤልሳቤጥ በስተርጅና የድንግል ማርያም በድንግልና የመውለድ ጸጋ የሆነው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና

     ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና:-

የመልአኩ ማሳረጊያ ቃል፣ ማሸነፊያ ብርታት የሆነው ይህ ቃል ነው። ሰው የሚቻለውን ይችላል። አግዚአብሔር የማይቻለውን ይችላል። ሰው እግዚአብሔር አሰችሎት ይችላል። እግዚአብሔር ግን ማንም ሳያስችለው ይችላል!
ማርያምም እነሆኝ የጌታ ባርያ እንደቃልህ ይሁንልኝ
የጌታ ባርያ ነኝ የሚል ፈቃዱን በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚለውጥ ነው። እንደቃሌ ሳይሆን እንደቃልህ፣ እንደወሰድሁት ሳይሆን እንደሰጠኸኝ፣ እንደአሳቤ ሳይሆን እንደ ፈቃደህ፣ እኔ ላድርግ ሳይሆን ይሁንልኝ፣ እንደመሰለኝ ሳይሆን እንደወሰንከው፣ ስማኝ ሳይሆን ልስማህን የሚያስቀድም ነው!
                                                                                                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment