Pages

Wednesday, May 23, 2012

ከሁሉ በታች ቁጫጭ ስንሆን ከሁሉም በላይ አደረገን=+=



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደሚነግረን አሁን ካሣው ተከፍሏል፤ አናቅጸ ሲዖል ተሰባብሯል፣ የሰው ልጅም እንደ ድሮ በዕዳ በቁራኝነት ከመያዝ ነጻ ወጥቷል፤ ጌታችንም ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ እንዴት ያለ ፍቅር ነው?
 ተነሥቶም ለአርባ ቀናት ያህል ደቀመዛሙርቱን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምሥጢር ሲነግራቸውና ሲያስረዳቸው ቆየ /ሐዋ.1፡3/፤ [ይህ ትምህርት ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን መጽሐፈ ኪዳን ይባላል!] “ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡ በአባቴ ቤት ብዙ መኖርያ አለ፡፡ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበረ፡፡ ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና” እያለ ከዚህ በፊት የነገራቸውን እየደገመ የደቀመዛሙርቱን ልብ ሰማያዊውን ሕይወት እንዲናፍቅ ያደርገው ነበረ /ዮሐ.14፡1/፡፡ ሆኖም ግን እየተገለጠላቸው እንጂ ከዚህ በፊት ሲያደርገው እንደነበረ ቀንና ሌሊት ሁሉ ከእነርሱ ጋር በመዋልና በማደር አልነበረም፡፡ አሁን ስለ እኛ ብሎ ዝቅ ያለበት ያ ደካማ ማንነቱ የለምና፤ አሁን ያ የለበሠው ባሕርያችን በአዲስ መንፈሳዊ አካል ተነሥቷልና፡፡ 

 
  ጌታችን በነዚህ አርባ ቀናት እየታያቸው ከእነርሱ ጋር ሲበላና ሲጠጣ ነበር /ዮሐ.21፡10/፡፡ ከትንሣኤ በኋላ መራብና መጠማት ኖሮ አይደለም፤ ሥጋውን በመቃብር ትቶት እንዳልተነሣ ከዚህ በላይ ደግሞ ከተዋሕዶ በኋላ መለያየት እንደሌለ ሲያስረዳቸው እንጂ፡፡ መብላት ብቻ ሳይሆን ያ የከበርነበት ከድንግል የነሣው ባሕሪያችን ይዞት እንደተነሣ እንዲያውቁ በዚያም የትንሣኤን ክብር እንዲረዱ እንዲዳስሱት አንዳንድ ያላመኑትም ጣታቸውን በተወጋው ጐኑ እንዲያገቡ ይፈቅድላቸው ነበር /ዮሐ.20፡27/፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁሉ ካዩ በኋላ፣ የክርስቶስን ትንሣኤ ካዩ በኋላ፣ ትንሣኤውን ብቻ ሳይሆን የትንሣኤም ክብር ከተገነዘቡ በኋላ፣ የተገለጠውን የዘላለሙን ሕይወት ካስተዋሉ በኋላ ጮክ ብለው፡- “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን” እያሉ መሰከሩልን /1ዮሐ.1፡1/፤ መከራውን መሳተፍም ምን ያህል ክብር እንደሚያጐናጽፍ ነገሩን /ሮሜ.8፡17፣ 1ጴጥ.1፡11/፡፡
 አስቀድመን እንዳልነው ያን ሁሉ ካስተማራቸው በኋላ፣ ከእርሱ የሰሙትን ወንጌል ለዓለም እንዲመሰክሩ ከነገራቸው በኋላ “እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ የርቀት (ቀ-ጠብቆ ይነበብ!) ያይደለ የርኅቀት ደመና ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፡፡”
 አምላክ በዕልልታ፤ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ፤ በይባቤ በመላእክት ቅዳሴ በብርሃን በሥልጣን ዐረገ /መዝ.46፡5/፡፡ ሲያርግም እንደ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ሳይሆን መዝሙረኛው እንዳለው “ሰረገላውን ደመና የሚያደርግ እግዚአብሔር በዕልልታ አረገ” /መዝ.104፡3/፡፡ የሚደንቅ ነው! አሁን የመሬት ስበት በክርስቶስ ላይ ሥልጣን የለውም፤ የመለኰት የሆነ ሁሉ ለሥጋ ሆኗልና፡፡ ይህም የሆነው በደብረ ዘይት ተራራ ነበረ /ሐዋ.1፡12/፡፡ በዚህ ተራራ ጌታችን ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ተናገረ፤ ስለ ዓለም መጨረሻም አስተማረ /ማር.13፡3/፤ ከዚሁ ተራራ ግርጌ ባለው በጌቴሴማኒ በአይሁድ ጭፍሮች ተያዘ /ማቴ.16፡30/፤ እንደተናገርነውም ከዚሁ ተራራ በመለኰቱ ሳይሆን በባሕርያችን ዐረገ፡፡
 ወንድሞቼ በዚህ ዕርገት ያገኘነውን ክብር እናስተውል፡፡ ይህ “አፈር ነህና” ተብሎ ተፈርዶበት የነበረው ባሕርያችን አሁን በውዳችን በክርስቶስ እንዴት እንደ ከበረ ልብ እንበል፡፡ ይህ ባሕርያችን ከሰማያት መሆን ብቻ አልበቃውም፤ በመላእክት ቦታም አልተወሰነም፡፡ ከመላእክት በላይ ሆኖ ከሱራፍኤል በላይ ተቀመጠ እንጂ፡፡ ወንድሞቼ ይህ ሥጋ ከሊቃነ መላእክት በላይ መሆን ብቻ አልበቃውም፤ ወደ ላይ መውጣት ብቻ አልበቃውም፤ ወደ መንግሥት ዙፋን ወጥቶ እስከ መቀመጥ ደረሰ እንጂ፤ በአብ ዕሪና በአብ ትክክል ሆነ እንጂ፡፡
 በሰማይና በምድር መካከል ያለውን የርህቀት መጠን ስንት ነው? እስኪ ከበርባሮስ ጀምራችሁ ሥፈሩ፤ አስተውሉም፡፡ በገሃነምና በምድር መካከል ያለው ርህቀት ስንት ነው? ዳግመኛም ከምድር እስከ ጠፈር ያለውን ርህቀት ሥፈሩ፤ አስተውሉም፡፡ ከዚህ እስከ ሁለተኛው ሰማይ ያለው ርህቀት መጠን፣ ከሁለተኛው እስከ ሦስተኛው ሰማይ ያለውን የርህቀት መጠን፣ በሰማያውያን መላእክትና  በአርያም ባሉ መላእክት መንበረ መንግሥት መካከል ያለው የርህቀት መጠን ስንት ነው?
 እግዚአብሔር የእኛን ባሕርይ ከዚህን ከፍተኛ ያህል የርህቀት መጠን በላይ አውጥቶ አኖረው፡፡ ቀድሞ ሰውን ካወረደበት ቦታ በታች (መሬት ከመሆን የሚያንሥ) ምንም ምን የለም፤ ዛሬም ሰውን ካወጣበት በላይ (አምላክ ከመሆን የሚበልጥ) ምንም ምን የለም፡፡
 
ቀድሞ ትቢያ ነበርን፤ ከማይናገሩ ከእንስሳት ይልቅ እውቀትን አጥተን ነበርን


/ኢሳ.1፡3/፤ ፍቅር የሆነው ጌታችን ግን ከየት አንሥቶ ወዴት እንዳወጣን እንወቅ እንረዳ፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ቸርነት ወዴት አለ? ከዓሣ ይልቅ አይሰማ የነበረ፣ ለአጋንንትም መዘባበቻ የነበረ ሰውን እስከዚህ መዓርግ ከፍ ከፍ ማድረግስ እንደምን ያለ ፍቅር ነው?
 ለማይመረመር ለዚህ ክብር አንክሮ ይገባል! ከሁሉ በታች ቁጫጭ ስንሆን ከሁሉም በላይ አደረገን! ስንቶቻችን ለዚህ የተገባን እንሆን?
 ለዚህ ሕይወት የተገባን እንደንሆን ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳየነው ዳግም እንዲሁ ሲመጣ ከሚያከብራቸው ብሩካኑ ጋር ይደምረን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!!

No comments:

Post a Comment