Pages
▼
Wednesday, May 2, 2012
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ…!!
እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር ሁሉ ከእኛ ሊሰርቅ የሚፈልግ አንድ ጠላት አለን፡፡ የዚህ ጠላት ጦር ግን በዓይን የሚታይና በእጅ የሚዳሰስ አይደለም፡፡
ጠላታችን እርሱ ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ በዓይናችን ልናየው አንችልም፡፡ ማየት አንችልም ማለት ግን ሀልዎት የለውም ማለት አይደለም፡፡ ይህ ጥንተ ጠላታችን እኛን ከእግዚአብሔር ከመለየት በላይ የሚያስደስተው ነገር የለም፡፡
ሰይጣን በጣም ተንኰለኛ ነው፤ እኛን ከፈጣሪያችን ለመለየት የማይጠቀምበት ዘዴ የማይፈነቅለውም ድንጋይ የለም፡፡
ስለዚህ እርሱን ለመዋጋት ሁሌ መዘጋጀት አለባችሁ እንጂ “እንዲህማ ከሆነ” ብላችሁ ሰይጣንን ልትፈሩት አይገባም፡፡ ይህንን ለማደረግም እንደ ወታደር ትጥቃችሁን ሁሉ ልትታጠቁ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በዚህ ወርሐ ጾም! ጠላታችሁ መንፈስ ቢሆንም እግዚአብሔር ይህን ጠላት ድል የምታደርጉበት መንፈሳዊ ጦር ይሰጣችኋል፡፡
ስለዚህ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፡፡
ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ጠበቅ አድርጉት፡፡ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር ይወዳችኋል፤ ስለ ኃጢአታችሁ ብሎ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ያፈቅራችኋል! አሁንም ይህ ፍቅርና እውነት የሆነው እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ይህን እውነት ጠበቅ አድርጋችሁ ታጠቁት፤ እንዲህ ስታደርጉም በብርታትና በኃይል ሰይጣንን ድል ታደርጉታላችሁ፡፡
ልባችሁ ይጽና!!
የጽድቅ ጥሩርንም ልበሱ፡፡ ሁል ጊዜ መልካም የሆነውን ብቻ አድርጉ፡፡ እንዲህ ስታደርጉ ሰይጣን ወደ እናንተ ለመምጣት ወደ ልባችሁም ሾልኮ ለመግባት ዕድል አያገኝም፡፡ እንዲህ ስታደርጉ ሰይጣን እናንተን መጣል ስለማይችል ተደላድላችሁ ትቆማላችሁ፡፡
ቀጥላችሁም እግሮቻችሁ በሰላም ወንጌል በመዘጋጀት ይጫሙ፡፡ ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ይህንን ወንጌል ወደዚህ ቦታና ሰው አድርስ ሲላችሁ ለመሄድ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፡፡
በሁሉም ላይ ጨምራችሁም የሚምበለበሉትን የሰይጣንን ፍላጻዎች ሁሉ ታጠፉ ዘንድ የእምነትን ጋሻ አንሡ፡፡
ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነውና በርቱ! እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋልና ጽኑ! ብቻ እምነታችሁ ሁሉ በእርሱ ይሁን እንጂ ሰይጣን በእናንተ ላይ አንዳች አያደርግም፡፡
የመዳንን ራስ ቁር ያዙ፡፡ አሁን መዳናችሁን ወደ ምትፈጽሙበት የሕይወት ልምምድ ገብታችኋል፤ የእግዚአብሔር የልጅነትን ሥልጣን አግኝታችኋል፤ የሰይጣን ኃይሉ መክኗል፤ ሞትም ድል መንሳቱ ቀርቷል፡፡ ስለዚህ እናንተን ከእግዚአብሔር ለይቶ ሊወስድ የሚችል አካል የለምና ባላችሁበት ጽኑ፡፡
በመጨረሻ የመንፈስን ሰይፍ ያዙ፡፡ አዎ! እግዚአብሔር የሰይጣንን ውሸትና ክስ ድል የምናደርግበት መሣርያ ሰጥቶናል፡፡ የተሰጠን መሣርያም ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሰይጣንን ሐሳብ ሁሉ ከንቱ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ በዚሁ በጾም ወራት ጌታችን ጠላትን በቃሉ ወደ መሬት ሲጥለው እንደነበር እናንተም በእግዚአብሔር ቃል ሰይፍ ቆራርጡት፡፡ ሁል ጊዜ ይህን ሰይፍ ለመታጠቅ ቸል አትበሉ፡፡
አሁን እናንተ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፡፡ ከእጁም ማንም ሊነጥቃችሁ አይችልም፡፡ ብቻ እናንተ ይህን የሰይጣን ፍላጻ ልታጠፉበት የምትችሉበትን የእምነት ጋሻ አንሡ፡፡
ሁል ጊዜ እውነት እውነቱን ብቻ ተናገሩ፡፡ መልካም የሆነውንም አድርጉ፡፡
እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ቸርነት ደግሞም በምን ዓይነት ፍቅር እንደወደዳችሁ ለመናገር ቸል አትበሉ፡፡ ይህን የፍቅር ጽዋ ሌሎች እንዲቀምሱት ጋብዝዋቸው፡፡ እናንተም አሁን ካላችሁበት በላይ ጨምራችሁ አጣጥሙት፡፡
እምነታችሁ ሁሉ በእርሱ ጣሉት፡፡ እግዚአብሔር ስለናንተ ብሎ እስከምን ድረስ እንደደረሰ ሁል ጊዜ ከማሰብ አትቆጠቡ፡፡ ሊይዛችሁ ደግሞም እንዳትወድቁ ቀና ሊያደርጋችሁ ሲፈልግ እጃችሁን ከመስጠት አትቦዝኑ፡፡
ስለዚህ ሰይጣንን እግዚአብሔር በሰጣችሁ ሰይፍ (በቃሉ) ለመቆራረጥ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፡፡
ሰይጣን እግዚአብሔር የሰጣችሁን ነገር ለመንጠቅ በዙርያሁ ይዞራል- ነገር ግን አንዳች ስንኳ አትጨነቁ- እግዚአብሔር አሁንም አብሯችሁ ነው! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል!!
እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነውና በርቱ! የተዋሕዶ ልጆች ትጉ! በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ታመሙት፣ ስለ ተሰደዱት፣ ስለታሰሩት፣ ስለ ዝናብ፣ ስለ አዝርእት… ጸልዩ!
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል!!
No comments:
Post a Comment