Pages

Wednesday, May 16, 2012

የዮሐንስ ወንጌል (የመጀመርያ ሳምንት ጥናት)!!

በአዳራሽ ገብቶ ወደ እልፍኝ ማለፍ፣ እርካብ ተረግጦ ወደ ኮርቻ መውጣት እንደሚመች ሁሉ እኛም ለዛሬ መቅድሙን ተምረን ከቀጣይ ሳምንት በኋላ ወደ ወንጌሉ እንሄዳለን፡፡ የጸሐፊው ዜና መዋእል በአጭሩ፡-
የዮሐንስ ወንጌል ጸሐፊ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ነው /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ/፡፡ ዮሐንስ ማለት “ጸጋ እግዚአብሔር” ማለት ነው፡፡ አባቱ ዘብዴዎስ የሚባል የሲዶና ሀገር ገሊላዊ ሲሆን ዓሣ አጥማጅ ሳለ ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ሰዎችን እንደ ዓሣ በወንጌል መረብ ከዚሁ ዓለም ባሕር ለማጥመድ ተጠራ /ማቴ.4፡21/፡፡ እናቱም ማርያም ባውፍልያ ትባላለች /ማቴ.28፡1/፡፡ ወንድሙ ያዕቆብ በ44 ዓ.ም በሄሮድስ ዘአግሪጳ ተገደለ /ሐዋ.12፡1-2/፡፡ ብዙ ቅጽል ስሞችም አሉት፡- የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በመግለጡና ለጌታችን ባለው ቅንዓት ባሳየውም የኃይል ሥራ “ወልደ ነጐድጓድ” /ማር.3፡17/፣ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ስለሚናገር “ታዖሎጐስ- ነባቤ መለኰት”፣ ኃላፍያትንና መጻእያትን ስለሚናገር “አቡቀለምሲስ-ረአየ ኅቡአት- ባለ ራዕይ”፣ እንዲሁም የጌታን ጸዋትወ መከራ አይቶ ፊቱ በኃዘን ተቋጥሮ ይኖር ስለ ነበር “ቁጹረ ገጽ- ፊቱ በኃዘን የተቋጠረ” ይባላል፡፡ ጌታ ግርማ-መንግሥቱን ሲገልጥ /ማቴ.17፡1/፣ የኢያኢሮስን ልጅ ሲያነሣ /ማር.5፡37/፣ በጌቴሴማኒ የአታክልት ቦታ ሲጸልይ /ማቴ.26፡37/፣ ስለ ኢየሩሳሌም መጥፋት ትንቢት ሲናገር /ማር.13፡3/ ዮሐንስ አብሮ ስለ ነበር “የምሥጢር ልጅ”ም ይባላል፡፡ ጌታ ሲጠራው የ25 ዓመት ወጣት ነበር /ቅዱስ ሄሬኔዎስ/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “Pillars of the Church- አዕማደ ቤተ ክርስቲያን” ብሎ ከሚጠራቸው ሐዋርያት አንዱ ዮሐንስ ነው /ገላ.2፡9/፡፡ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በተለየ አኳኋንም ጌታን ይወደው ስለ ነበር ሁሌ ከእቅፍ አይለይም ነበር፡፡ በዚህም የጌታ ወዳጅ-ፍቁረ እግዚእ ተብሏል /ዮሐ.13፡23/፡፡ ጌታን እስከ መስቀል ድረስ የተከተለ እቸኛ ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታም ዮሐንስ ካሳየው ፍቅር ከ100 ዕጥፍ በላይ እናቱን እናት አድረጐ ሰጠው /ቅዱስ አውግስጢኖስ/፡፡ ምንኛ የታደለ ሐዋርያ ነው? /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/፡፡ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን በዮሐንስ ሃይማኖት እስከ መስቀል ድረስ ለምንሄድ ምእመናንንም ሁሉ ጌታ እመቤታችንን እናት አድርጐ ሰጥቶናል /ዮሐ.19፡20-27/፡፡ ዮሐንስ ከጌታ ትንሣኤ በኋላ ወንጌልን በታናሽ ኤስያ (ልዩ ስሙ ኤፌሶን) ያስተምር ነበር፡፡ ትምህርቶቹም ፍቅርን አብዝተው ይሰብካሉ /ቅዱስ ጀሮም/፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በአንድ ቀን፡- “አባታችን ሁል ጊዜ አንድ ዓይነት ትምህርት (ስለ ፍቅር) የምታስተምረን ለምንድነው?” ሲሉት “እርሷ የጌታ ትእዛዝ ናት፤ እርሷን ከጠበቃችሁ ይበቃችኋል” ይላቸው ነበር /ዮሐ.15፡12/፡፡ በሽምግልናው ጊዜ እንኳን እንደ ወጣት ለስብከተ ወንጌል አብዝቶ ይፋጠን ነበር /አውሳብየስ ዘቂሳርያ፣ ቀለሜንጦስ ዘአሌክሳንድርያ/፡፡ በጊዜው በነበረው ጨካኙ የሮም ቄሣር በድምጥያኖስ ወደ ፍጥሞ ደሴት ተሰደደ፡፡ በዚያም የራዕይን መጽሐፍ ጻፈ፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ዮሐንስ ተሰውሯል እንጂ አልሞተም፤ ነገር ግን ጌታ ሲመጣ ይሞታል /ዮሐ.21፡22-23/፡፡ወንጌሉ የተጻፈበት ቋንቋ፣ ቦታና ጊዜ፡-
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ከፍጥሞ ደሴት ከግዞት ሲመለስ በኤፌሶን በ96 ዓ.ም አከባቢ በዮኖናውያን ቋንቋ ጽፎታል /ቅዱስ ሄሬኔዎስ ዘልዮን/፡፡ምክንያተ ጽሒፍ- መጽሐፉ የተጻፈበት ዋና ዓላማ በአጭሩ፡-
v ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ እንደ ሆነ እናምን ዘንድ፥ አምነንም በስሙ ሕይወት ይሆንልን ዘንድ መጽሐፉ ተጽፎአል /ዮሐ.20፡31/፡፡
v በጊዜው ለነበሩ ኢስጦኢኮች ተብለው ለሚጠሩ የግሪክ ፈላስፎች መልስ ለመስጠት ተጽፏል፡፡ በሌላ አገላለጽ ለዕቅበተ-እምነት (Apology)፡፡ ፈላስፎቹ:- “ነፍስን፣ መላእክትን እና ሌሎች ረቂቃን ፍጥረታትን የፈጠረ Logos-ቃል የሚባል ደግ አምላክ አለ፡፡ ደግሞም ግዙፉን ዓለም እና የሰውን ሥጋ የፈጠረ ሌላ ክፉ አምላክ አለ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በደጉ አምላክ የተፈጠረችውንና በሰው ውስጥ ያለችውንና ነፍስ ነጻ ለማውጣት የተላከ “ፍንጣሪ-Ion” ነው፡፡ ሥጋ የክፉ አምላክ ፍጥረት ስለሆነም እርሱ ሥጋ አልለበሰም” ብለው ስለሚያስተምሩ ዮሐንስ “ወልደ እግዚአብሔር በመጀመሪያው Logos- ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ነበረ፥ ቃልም ራሱ እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው ከዘላለም ጀምሮ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። እናንተ የደጉ አምላክ ፍጥረትና የክፉ አምላክ ፍጥረት የምትሉት (የሚታየውም የማይታየውም) ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፥ ከተፈጠረውም አንድስ እንኳ ያለ እርሱ ቃልነት የተፈጠረ የለም” እያለ ይቀጥልና “ያ ቀዳማዊ Logos-ቃልም በመምሰል ሳይሆን በኩነት ሥጋን ተዋሕዶ በእኛ አደረ፤ አማኑኤል ሆነ” እያለ አስፍቶና አምልቶ በጥልቀት የሎጐስን እውነተኛ ትርጓሜ ጽፎላቸዋል፡፡
v በሌሎች ወንጌላውያን ያልተዳሰሰው ጥልቅ ነገረ-መለኰትን (Theology) ለማስተማር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጽፎታል /አውሳብዮስ ዘቂሳርያ፣ ቅዱስ ጀሮም/፡፡
v ሰማየ ሰማያትን ሰንጥቀን ወጥተን፤ ሱራፍኤል፣ አለቆችንና ሥልጣናትን አልፈን ወደ ዘባነ-ኪሩብ እንድንወጣና ባለ ግርማውን ንጉሥ እንገናኝ ዘንድ ይህን ጻፈልን (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡
v ሐዋርያው “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ነው” እንዳለ /ፊል.3፡20/ ወደዚያ ወደ እውነተኛው ቤታችን ይመራን ዘንድ ይህን ጽፎልናል (ቅዱስ አምብሮስ)፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment