Pages

Friday, June 8, 2012

ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ- የዮሐንስ ወንጌል የ26ኛ ሳምንት ጥናት (ዮሐ.5፡30-ፍጻሜ)!


     በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 አንድ ምንም እውቀቱና ልምዱ የሌለው ሰው ዝም ብሎ መሬት ስለ ቆፈረ ብቻ ወርቅ አያገኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ ምንም ረብሕና ጥቅም የሌለውን ድካም ያተርፋል እንጂ፡፡ ባስ ካለም የቆፈረው ጉድጓድ ተደርምሶበት ሕይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚነበብና እንዴት መረዳት እንዳለበት ያለወቀ ሰውም ይህን ሰው ይመስላል፡፡ ይህንን የምንለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ቀጥለን የምንመለከተው ቃል በቀላሉ ሊረዱት የማይችሉና ሰም ለበስ ወርቅ ስለሆነ እንጂ፡፡ ጌታችን “እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።  እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም” ስላለ ብቻ እንዲሁ ጥሬ ንባቡን በመያዝ ብዙ ሰዎች ይደናበራሉ /ቁ.30-31/፤ እውነት የሆነው “ክርስቶስ ስለ ራሱ የመሰከረው ምስክርነት እውነት አይደለም” ለማለት ይደፍራሉ፡፡ ሆኖም ግን ጌታችን ይህንን ሲል እነርሱ እንደሚሉት ማለቱ አልነበረም፡፡ አይሁድ “እግዚአብሔር አባቴ ነው፤ ከአባቴ ጋር የተስተካከልኩ ነኝ፤ አባቴ እስከ ዛሬ እንደሚሠራ እኔም በአንድ ፈቃዲት በአንዲት ሥልጣን እንዲህ አደርጋለሁ” ቢላቸው “አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም፡፡ ስለዚህም አናምንህም” /ዮሐ.8፡13/ ስለሚሉትና ሊገድሉት ስለሚፈልጉ፡- “እኔ ምንም ምን ከራሴ ብቻ አንቅቼ አላስተምርም፤ በህልውና እንደሰማሁ የሰማሁትን አስተምራለሁ እንጂ፡፡ ትምህርቴም እውነት ነው፤ የእኔ ፈቃድ ከአባቴ ፈቃድ ልዩ ሆኖ የእኔ ፈቃድ ብቻ ሊደረግ አልወድም፤ ወልድ ያልወደደው አብም አይወደውም” ነው የሚላቸው /ወንጌል ቅዱስ አንድምታ ገጽ 481/፡፡

   ሰው ወዳጁ ጌታ ንግግሩን በዚህ አያቆምም፤ ይልቁንም እንዲህ ብሎ ይቀጥላል እንጂ፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ፣ አብ ልኮ ያዋሐደኝ አምላክ ነኝ ብላችሁ እናንተ ግን ትሳደባለህ ትሉኛላችሁ፡፡ ሆኖም እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ፣ የአምላክነትን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ምስክርነቴንም አትቀበሉ፤ ባደርገው ግን እኔን እንኳ ባታምኑ አብ በእኔ ህልው እንደሆነ እኔም በአብ ህልው እንደሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ”/ዮሐ.10፡36/፤ አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው እኔም ለምወዳቸው ለሚያምኑብኝ ሕይወትን የመስጠት ኃይልና ሥልጣን እንዳለኝ እመኑ፡፡ አንተ ስለራስህ የምትመሰክረው ምስክርነት አንቀበልም ብትሉ እንኳን አብ ስለ እኔ የሚመሰክረውን ለመቀበል አትቸገሩ፤ የማደርገውን ሥራ አይታችሁ እመኑ፡፡ እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችሁ አልነበረምን? እርሱስ፡-እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔረ በግ ብሎ እውነት ነግሯችሁ አልነበረምን? /ዮሐ.1፡29/:: እንግዲያውስ ዮሐንስ የመሰከረላችሁ ምስክርነት እመኑ፡፡ ስለ ራስህ ምን ትላለህ? ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ምን ትላለህ? ብላችሁ ጠይቁትና እመኑ፡፡ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ እኔስ  ከሰው ምስክር አልቀበልም፡፡ እናንተ ትወዱት ስለ ነበረ እንደ ነብይም ታዩት ስለ ነበረ የእርሱን ትምህርት አድምጣችሁ በእኔ ታምኑ ዘንድ ትምህርቱን አስታወስኳችሁ እንጂ አምላክነቴን ለማረጋገጥስ የማደርገው ተአምራት ራሱ በቂ ነው /ቁ.34፣ Saint John Chrysostom  Homilies on ST. John, 41/፡፡

   “ዮሐንስ በተደነባበራችሁበት የጨለማ ዘመን የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፡፡ የፋና ጥቅሙም አማናዊው ፀሐይ እኔ እስክመጣ ድረስ እንጂ ከዚያ ወዲያ የሚሻው የለም፡፡ እናንተጥቂት ዘመን ማለትም መንፈቅ በትምህርቱ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ /ቁ.35፣ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ/።
   “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፡፡ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ እናንተን የማፍቀሬ ሥራ ምስክሬ ነው! አባቴ ገንዘብ ያደረገልኝ ተአምራት ምስክሬ ነው! አብ ስለ እኔ ሥጋዌ ያስነገረውን ትንቢት ባትቀበሉትም ምስክሬ ነው! የላከኝ አብ በፈለገ ዮርዳኖስ ስጠመቅ፡- ለተዋሕዶ የመረጥኩት በእርሱ ህልው ሆኜ ልመለክበት የወደድኩት ልጄ ይህ ነው ያለውም ምስክሬ ነው /ማቴ.3፡17፣ ቁ.37/! አሁንም እነግራችኋለሁ፤ ምስክሬ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ መጻሕፍትም ምስክሮቼ ናቸው! ሆኖም ግን መዝሙረኛው ዳዊት፡- አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ /መዝ.119፡11/ ያለውን ቃል የምታፈርሱ ስለሆናችሁ በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም /ቁ.38/፤ አብ በላከው በእኔ አላመናችሁም። እናንተ በመጻሕፍት ንባባቸው ብቻ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ስለሚመስላችሁ እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ ሆኖም ግን እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” /ቁ.39፣ Saint Gregory of Nyssa. The Song of Songs; translated by Dr. George Nawar, Sermon 6 /፡፡

   “ሕይወት ደኅንነት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም። ለፀሐይ ብርሃን የሻማ መብራት ምንም አይጨምርላትም፤ የእናንተ መዳንም በእኔ ላይ የሚጨምረው ክብር የለም፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አስረዳኋችሁ። እግዚአብሔርን ብትወዱት ኖሮ እናንተን ከማፍቀሩ የተነሣ የላከኝን እኔን ባመናችሁብኝ ነበርና!” /ቁ.40-42፣ Saint John Chrysostom, Ibid/፡፡

   እኔ በአባቴ ስም በአባቴ ምስክርነት መጥቼ ካልተቀበላችሁኝ ሐሳዌ መሲሕ ራሱ ባወጣው ስም ሲመጣ ትቀበሉታላችሁ፤ ታምኑበታላችሁም” /ቁ.43፣ Father John of Damascus Exposition of the Christian Faith, Book 4, Ch. 36/

 “እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ስለ ውዳሴ ከንቱ ብላችሁ ከአንዱ ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት በእኔ ልታምኑ ትችላላችሁ? ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔረ መሆኔን እንዴት ልታውቁና ልታስተውሉ ትችላላችሁ? /ቁ.44፣ ኤር.9፡24፣ Saint Jerome Letter 22:27/፡፡

  “እነግራችኋለሁ! ሰንበትን አልሻርኩም፣ የሌለኝን አምላክነትም ለራሴ አልጨመርኩም ብዬ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፡፡ የሚከሳችሁ የሚያሳጣችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው። ሙሴ የነገራችሁን የሰንበት አከባበር ብትጠብቁትና አከባበሩን ብታምኑትስ እኔም አንዳልሻርኩት በተረዳችሁ ባወቃችሁ ነበር /ቁ.45፣ ማቴ.12፡11/፤ አንድም እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነብይ ያስነሣላችኋል እርሱን ስሙት ብሎ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና የምነግራችሁን በሰማችሁ ነበር” /ቁ.46፣ ዘዳ.18፡15/።

  “ነገር ግን ሙሴ ስለ እኔ የጻፈውን፣ ነብያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው የተናገሩትን ካላመናችሁና ካልተቀበላችሁ እኔ “እግዚአብሔር አባቴ ነው” ብል እንዴት ታምናላችሁ?  አንድ ምንም እውቀቱና ልምዱ የሌለው ሰው ዝም ብሎ መሬት ስለ ቆፈረ ብቻ ወርቅ አያገኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ ምንም ረብሕና ጥቅም የሌለውን ድካም ያተርፋል እንጂ፡፡ ባስ ካለም የቆፈረው ጉድጓድ ተደርምሶበት ሕይወቱን ሊያጣ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚነበብና እንዴት መረዳት እንዳለበት ያለወቀ ሰውም እናንተን ይመስላል፡፡ ትንቢተ ነብያትን መጻሕፍተ ሙሴን ተሸክማችሁ ብትዞሩም ከጥሬ ንባቡ ውጪ ምሥጢሩን ስለ እኔ የሚናገረውን ካላስተዋላችሁ እንዴት በእኔ ታምናላችሁ?”/Saint John Chrysostom, Ibid/፡፡

  በእርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንደምሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው” ብሎ እንደተናገረ ልናስተውል ይገባል /ዮሐ.8፡14/፤ ለሳምራይቱ ሴት “የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ” ያለ እርሱ ነው /ዮሐ.426/፤ ዓይነ ሥዉር ለነበረውም “ከአንተ ጋር የሚናገረው እርሱ ነው” ብሎ ስለ ራሱ የመሰከረ እውነት የእውነትም አባት ነው /ዮሐ.9፡37/፡፡  

  ወዮ አባት ሆይ!ትሕትናህ እንዴት ግሩም ነው? ቃልህ እንዴት ጣፋጭ ነው? ሊወግሩህና ሊገድሉህ ሲመጡ ስለ እነርሱ መዳን ብለህ በፍቅር ማስረዳትህ እንዴት ድንቅ ነው? ንጉሣችን ሆይ! እውነቱን በእጃችን ተሸክመን በልባችን ከመካድ ጠብቀን! ምስክርነትህ እውነት እንደሆነ በልባችን አምነን፣ በአፋችን መስክረን በሕይወታችንም በእውነት ኖረን መንግሥትህን እንድንወርስ የማትቆረቁር እጅህ ትደግፈን! አፍቃርያችን ሆይ! የበደለኛ መንገድ የጠመመች ናት፤ የንጹሕ ሥራ ግን የቀናች ነትና በፊትህ የቀናን አድርገን! አንተ የመድኃኒታችን አምላክ ነህና በእውነትህ ምራን፤ አስተምረንም፡፡ አሜን አሜን አሜን!!


የዮሐንስ ወንጌል የ20ኛ ሳምንት ጥናት
የዮሐንስ ወንጌል የ21ኛ ሳምንት ጥናት

የዮሐንስ ወንጌል የ22ኛ ሳምንት ጥናት

የዮሐንስ ወንጌል የ24ኛ ሳምንት ጥናት

የዮሐንስ ወንጌል የ25ኛ ሳምንት ጥናት

No comments:

Post a Comment