Pages

Monday, June 25, 2012

የሃይማኖታችን ሊቀ ካህናት- ክፍል ሁለት!!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
    በክፍል አንድ ትምህርታችን ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ስለ ሊቀ ካህናት በስፋትና በጥልቀት የጻፈልን የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እንደሆነ፤ የዚህ ምክንያትም ምን እንደሆነ እና  ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን ትምህርት አብዝታ እንደምታስተምር ከአዋልድ መጻሕፍቶቿ ጠቅሰን ነበር ያቆምነው፡፡ ለዛሬ ደግሞ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ሥርዓት ከሰዎች ተመርጠው ከሚሾሙት የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ፍጹም የሚለይባቸውን ነጥቦች ማሳየት እንጀምራለን፡፡ አንባብያን ትምህርቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እያመሳከሩ ቢያነቡት የበለጠ ይጠቀማሉ፡፡

1. የሚምር ሊቀ ካህናት ነው፡፡ መጽሐፍ ይህን ሲመሰክር፡- “የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡ ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን መምሰል ተገባው” ይላል /ዕብ.2፡16-17/፡፡ አዎ! የዘመናት ጌታ እንደ ሰዎች ዘመን ተቈጠረለት፤ በልደት በሕማም በሞት ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፡፡ ባሕርያችንን የተዋሐደው ሌላ ምንም ምን ምክንያት የለውም፡፡ እኛን ከማፍቀሩ የተነሣ ዘመድ ሊሆነን አንድም እኛን ይቅር ለማለት ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ እንጂ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡- “ተመለከተን፤ እነሆም ጠላቶቹ ሆነን ተገኘን፡፡ ወደ እርሱ ያቀርበን ዘንድ የሚችል ኪዳንም ቢሆን መሥዋዕትም ቢሆን ፈጽሞ አልነበረንም፡፡ ስለዚህም አዘነልን፤ ራራልን፡፡ ከመላእክትም ይሁን ከኃይላት ወገን ሊቀ ካህናት አልሾመልንም፤ እርሱ አንዱ ወደዚህ ዓለም ወርዶ ባሕርያችንን ባሕርይ አድርጐ የሚምር ሊቀ ካህናት (አስታራቂ) ሆነን እንጂ” /ሃይማኖተ አበው 62፡13/፡፡ ይህም በመዋዕለ ሥጋዌው ተመልክተነዋል፡፡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሲፈርዱባቸው የነበሩ ሰዎች፣ “Public Sinners” ብለው ከማኅበረሰቡ ያገለሉዋቸውን ሰዎች አዛኙ ሊቀ ካህናችን ሲያገኛቸው ግን “እኔም አልፈርድብሽም”፤ “ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል” ይላቸዋል /ዮሐ.8፡11፣ ሉቃ.7፡48/፡፡ ስለዚህ ሊቀ ካህናችን መሓሪ ነው፡፡

2. የታመነ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ የነበሩ ሊቃነ ካህናት ይጐድላቸው ከነበረው ነገር አንዱ ታማኝነት ነበር፡፡ ለምሳሌ አሮንን ብንመለከት በእግዚአብሔር ፊት ታማኝነት ይጐድለው ነበር፡፡ መጽሐፍ ይህን ሲመሰክር፡- “እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው” ይላል  /ዘኅ.20፡12/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የእኛን ኃጢአት ለማሥተስረይ ነውርን ንቆ መከራውን አቃሎ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ ሐፍረተ መስቀልን ይሁንብኝ ብሎ የተቀበለ ታማኝ ሊቀ ካህናት ነው /ዕብ.12፡2/፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ይህን ሲያብራራው፡- “በእውነት የአብርሃምን ባሕርይ ነሣ እንጂ የነሣው የመላእክትን አይደለም።  ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።  መከራ የሚቀበሉትን ሕዙናነ ልብ ይረዳቸው ዘንድ እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ተቀበለ። ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረና” ይላል /Discourses against Arians, 2:8/፡፡

3. በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት የሚገቡት ወደ ምድራዊት ድንኳን ነበር፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በሰማያት ያለፈ (ውሳጤ መንጦላዕት የገባ) ትልቅ ሊቀ ካህናት ነው፡፡ ኢያሱ ወልደ ነዌ ሊቀ ካህናቱና ሌዋውያን ካህናቱ ከፊት ቀድመው ታቦቱ ሕጉን ተሸክመው ባይቀድሙ ኖሮ ሕዝቡን ፈለገ ዮርዳኖስን አሻግሮ ዕረፍተ ፍልስጥኤምን ባላወረሳቸው ነበር /ኢያሱ.3፡13/፡፡ ታላቁ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ደግ አስታራቂ ይሆነን ዘንድ ወደ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትም ይዞን ለመግባት እንደ እነዚያ (የብሉይ ኪዳን ሊቃነ ካህናት) ታቦት ሕጉን መሸከም አላስፈለገውም፡፡ እንደ ባሕርይ አምላክነቱ ወደ ገጸ አብ፣ ወደ እዝነ አብ አቀረበን እንጂ /ዕብ.4፡14/፡፡

4. በድካማችን የሚራራልን ሊቀ ካህናት ነው፡፡ የዘመነ ብሉይ ሊቃነ ካህናት ለሚስቱት ሰዎች የሚራሩላቸው ራሳቸው ደግሞ በስንፍናቸው ኃጢአት ስለሚሠሩ ነው፤ የሰውን ድካም በራሳቸው ድካም ስለሚረዱት ነው /ዕብ.5፡2-3/፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ግን ሰዎች ናቸውና ስሕተት የሠራው ሰው ኃጢአቱን ካልነገራቸው በቀር ምን ምን በደል እንደሠራ ማወቅ አይቻላቸውም፡፡ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ደክመን ለሠራነው ኃጢአት የባሕርይ አምላክ እንደመሆኑ ምን ምን ድካም እንዳለብንም ስለሚያውቅ ይራራልናል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እነዚህን ሁሉ ሰው ሆኖ በገቢር አይቶአቸዋል፡፡ የእኛን ስደት ተሰዶ አይቶታል፤ የእኛ መሰደብ ተሰድቦ አይቶታል፤ የእኛ መወቀስ ተወቅሶ አይቶታል፤ የልጆቹ መገረፍ ተገርፎ ብቻ ሳይሆን ተሰቅሎ አይቶታል፡፡ “ስለዚህ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም” /ዕብ.4፡15/፡፡

       ይቆየን! (ሳምንት ይቀጥላል!)

3 comments: