Pages

Thursday, July 12, 2012

.......ብርሃናተ ዓለም......





ማነው በሁለት እግሩ ዓለምን የዞረ
ጽፎ ተናግሮ ዘክሮ ወንጌል የነገረ?
ይህች አለት ናት የቤቴ መሠረት
በሷ ቤቴን ሰራሁ ኮኩሐ ሐይማኖት

አባቴ ዼጥሮስ ...
እስኪንገረኝ...
የቱ ይበልጣል?
መረብ በባህሩ መወርወር
ወንጌል ለዓለሙ መናገር ?
ዓሣን ....ማደን
ሕዝብን ማዳን?
የቱ ይበልጣል አባቴ ...?
በጀልባ መዋሉ
ጌታን ማገልገሉ?

ተወው ዼጥሮስ ...
ለካ እኔ ሞኙ
ያልገባኝ ምስጢሩ
የበለጠውን በተግባር ነግረኸኝ
ዓለምን ተፍተህ ሞተህ አሳየኸኝ

ወዮ!......ወዮ!...
ወዮልሽ ሮም!
የኒሮን ዓለም
የቄሳሮች ሃገር
የግፍ ድንበር
የደም ባህር

ወዮልሽ ሮም ...
የዼጥሮስ ስቅለት ክስ ይሁንብሽ
የቅዱሱ ችንካር ምስክር ይጥራብሽ
በእጇ ያለ ወርቅ
............ሮም አልደመቀችበት


አውራዎቹን አርድዕቱን
............................አላገኘችበት


ምን አረገ ወልደ ዮና ...?

የባህሪ አምላክ ... አምላክ
ወልደ አብ ወልደ አምላክ
መሰከረ እንጂ
እውነት ተናገረ ...
በልጁ እመኑ
በአባቱ እመኑ
በህይወቱ እመኑ
.................ስላለ


በሞተ ሬሳ ላይ
.................ቃሉን ዘርቶ

........................ኮትኩቶ

ነፍስ ስላበቀለ
እሸት ስለፈለፈለ

ምን አረገ ኬፋ ...?
"ነስሑ... ነስሑ እስመ ቀርበት

ለእግዚአብሔር መንግስቱ "
የቀማ ... ይመልስ
የበደለ ........ ይካስ
የረከሰ ...... ይቀደስ
ስላለ...
ለታወረ ሥጋ ተስፋን ስለሰጠ
ነፍስ ዘላለማዊትን ስላቆጠቆጠ

! ............ ሮም
ወዮ የደም ዓለም
ለሰይፍሽ...
ነበልባል ሰይፍ አለ
ለመስቀልሽ...
የእሳት አውታር አለ

የየዋሁ እንባ ይታበሳል
የቅዱሱ ደም ይታፈሳል
ያንቺ ግርፋት ክብር ሾመው
መታሰሩ ....... ፈቺ አረገው
መጠማቱ ...ጥጋብ ሰጠው
መሰቀሉ ... አክሊል ሆነው

ተዘከረነ ብርሃነ ዓለም
ረዐይኬ.... አባግዕ
ረዐይኬ... መሐስዕ
ረዐይኬ.... አባግዕ

ዼጥሮስ ሆይ ...
በደምህ የበቀልን
ልጆችህን አትርሳን
ተዘከረነ ... በጸሎተከ ... ቅድስት!



... ... ማነው...
ሦስተኛ ሰማይ ላይ የወጣው?
እግሩን ምድር ተክሎ
...........በተመስጦ ሰማይ የወጣ

በምዕራፍ በጫማ ማይለካውን
....አርያምን ወደ ምድር ያመጣ


እኔ ሳውል እያለ አውቀዋለሁ
ክርስቲያን ሲያስገድል አይቼዋለሁ
ታዲያ...
ይሄ ክብር ከየት ነው...
ታሪኩን የቀየረው ማነው?

በደማስቆ ታምር አየ አሉ ...
ነጎድጓድ ሲነጉድ
መሬት ሲናድ
ተሳዳጁ አናገረው አሉኝ
........................ጻፉልኝ

'አታሳደኝ.....

ዳግም አትግደለኝ !
ቤቴን አታፍርስ
.................ቤቴን ስራ

ልጆቼን አትግደል
..............ልጅን አፍራ

እሳት አትለኩስ
ቃሌን አድርስ

ይብእሰከ ረጊፅ ውስተ ቀኖት '

ተሳዳጅ ...
ስሙን ለወጠው
ዻውሎስ አለው

ከእንግዲህ ምርጥ እቃ
ለሦስተኛ ሰማይ የሚበቃ
አሁን ተገለጠ
ማንነቱ ታወቀ
ለካ ሳውል አይደለ
ዻውሎስ ..... ተባለ

አባት ሆይ ...
ምን አስተማርክ
ምን .... ተናገርክ?
በከመ ነገሩነ አበዊነ ...
በወንጌል አላፈረ
.........ለጣኦት አልዘከረ

ከዝሙት እንዲሸሽ
...........ለሕዝብ ተናገረ


ፍቅር ቋንቋ ነው...
ቋንቋ መግባቢያ ነው
ፍቅር መግባቢያ...
ፍቅር እግዚአብሔር ነው

የመንፈስ ፍሬ... ዘላለማዊነት
የሥጋ ፍሬ ...........ዓለማዊነት
ተናገረ ..... መሰከረ
ተአቀቡኬ እምሀሳውያን
ደሞ ከሚቅለሰለሱት
ርግብ ከሚመስሉት
በልባቸው ተንኮል ካረገዙ
በግብራቸው ሞትን ከመረዙ
ተጠበቁ
ተራራቁ
ሲለው ሰማሁት
ሲጽፈው አየሁት

ወይ አንቺ ሮማ
የደም ከተማ
ርግማኔን ሳልጨርስ
..........ርግማን ጨመርሁልሽ

እሳቱን ስመኘው
.................ዲኑን አከልሁልሽ

ፀረ ቅዱሳን መከራ ንጹሐን
ሃገረ ንቅዘት ብሄረ ሀጥኣን

ወዮ ሮም ወዮ ኔሮን !
ከነትጥቅሽ ገደል ግቢ
በስቃይ ጀዲድ ተሰብሰቢ
አንቺ ርጉም ...
ቅዱስ ምን አረገሽ ?
ሰረቀሽ....? አጠፋሽ...?

ሰዶም ይቅለላት
.................እሳት የፈላባት

ገሞራ ይሻላት
................ዲን የዘነመባት

እሷ በራሷ ላይ ...
...........አበሰች

ሀጢያት ሰራች
ያንቺ ግን ...
ኅሩያኑ ቅዱሳን ላይ...
ግፍ መከራ አጸናሽባቸው
ሰቀልሻቸው መተርሻቸው
እግዚኦ እግዚኦ ተበቀል በቀለነ
አርእየነ ጥፍአቶሙ ለፀርነ
እድሜ ይስጠኝ አይሻለሁ
...........እንባዬን አብሳለሁ


አሱስ ሩጫውን ጨርሷል
የክብር አክሊሉን ጭኗል

ብቻ...
የዻውሎስ ደም ቢፈስ
አጸደቀ ለምላማት ነፍስ
እሱስ...
ግርፋቱ ክብር ሾመው
መታሰሩ ፈቺ አረገው
መጠማቱ ጥጋብ ሰጠው
መቀላቱ አክሊል ሆነው

አባት ሆይ...
በደምህ የበቀልን
ልጆችህን አትርሳን
ተዘከረነ ... በጸሎተከ ... ቅድስት


መምህሮቼ ዼጥሮስ ዻውሎስ...
የዘራችሁት ቃል
.................በልቤ ያብብልኝ

የሞታችሁት ሞት
................ነፍሴን ያኑርልኝ


ፀጋ ዘአብ ህይወተ ወልድ ሱታፌ ዘመንፈስቅዱስ
ተውሂቦሙ ለብርሃናተ ዓለም ጼጥሮስ ወዻውሎስ
.............ተዘከሩነ............

............=//=............

(ልዑል ገ/እግዚአብሔር- ሐምሌ05/2004..)

1 comment:

  1. Betam Betam KHY Egziabher tsegawin yabzailih bereketachew ayileyen!

    ReplyDelete