Pages

Thursday, July 19, 2012

ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ- በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ!


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 በእውነት ፀዋትወ መከራ የለባትምና መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት፡፡ ብካይ፣ ልቅሶ፣ ሐዘን፣ በልብ መቆርቆር፣ መዋረድ፤ ነፍስን የሚያሳዝናት፣ የሚያስደነግጣት፣ ፍርሐት የለባትምና በእውነት መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት /ኢሳ.35፡10/፡፡ በፊትህ ወዝ መብላት መጠጣት፤ እሾህም አመኬላም የለባትምና በእውነት መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት /ዘፍ.3፡18-19/፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ “በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል እርሱም ገዢሽ ይሆናል” የሚል የለባትምና በእውነት መንግሥተ ሰማያት ዕረፍት ናት /ዘፍ.3፡16/፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ዕረፍተ ሥጋ ዕረፍተ ነፍስ፣ ተድላ ሥጋ ተድላ ነፍስ፣ በጎነት፣ የዋህነት፣ ቅንነት፣ ፍቅር አለ፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ምቀኝነትና መፎካከር የለም፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ሕማመ ሥጋ ሕማመ ነፍስ፣ ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ የለም፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ብርሃን እንጂ ጨለማ፣ መዓልት እንጂ ሌሊት የለም፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ደም ግባት ማሸብረቅ አለ፡፡ በመንግሥተ ሰማይ ለዘለዓለም የማያልፈውን በጎ በጎውን ክብር ማግኘት ነው እንጂ መሻት፣ መሰልቸት፣ መራብ፣ ቁንጣን የለም፡፡

 የመንግሥተ ሰማይን ነገር ምሳሌ መስዬ ልነግራችሁ ትወዳላችሁን? አዎን ትሉኝ እንደሆነ የሚቻለኝን ያህል መስዬ እናገራለሁ እንጂ ስለ መንግሥተ ሰማያትስ ፍጹም ምሳሌ መስሎ መናገር አይቻልም፡፡ እነሆ ሰማይን የሚጋርደው ደመና የሚሸፍነውም ጉም ሳይኖር በፀሐይ በከዋክብት አጊጦ ሲያሸበርቅ እናየዋለን፡፡ መንግሥተ ሰማይም እንዲህ ነው፡፡ የደም ግባቱን ማሸብረቅ ስንመለከት ብንዘገይ ሰማይ እንደምንመላለስባት ምድር እናደርገዋለን፡፡ ነገር ግን የመንግሥተ ሰማይ ምሳሌ በዚህ በሰማይ ምሳሌ ፀንቶ የሚኖር አይደለም፡፡ በማሸብረቅ ላይ ማሸብረቅ በደም ግባት ላይ ደም ግባት ሲጨመርለት ይኖራል እንጂ፡፡ በጭቃ በጨፈቃ ከተሠራ ቤት ይልቅ በወርቅ በዕንቁ የተሠራ ቤት እንደሚበልጥ ሁሉ ሰማይ እንደምትመላለስባት ምድር ካደረግኸው በኋላ ደግሞ ከዚያ ካየኸው ሰማይ በላይ ሌላ ሰማይ አለ፡፡ አሁንም ከዚያ በላይ ካየኸው ሰማይ በላይ ግዘፍ የሌላቸው ላኗኗራቸውም ኅልፈት የሌለባቸው መላእክት ሊቃነ መላእክት እንዲሁም ሌሎች ሕልቆ መሳፍርት ኃይላት አሉ፡፡ አሁንም ከፍ እያልክ ስትሄድ መንበረ ጸባዖትን ታገኛለህ፡፡ ዓቢይ ልዑል የሚሆን እግዚአብሔርም አለ፡፡

  ነገር ግን አስቀድመን እንደተናገርን የእኛ ቋንቋ እጅግ ደካማ ከመሆኑ የተነሣ የመንግሥተ ሰማይን ነገር ምሳሌ መስሎ መናገር አይቻልም፡፡ ይህን ለመናገር አስቀድሞ በዚያ መኖርና የተለማመዱትን ልምድ ማካፈልን ይጠይቃልና፡፡ ስለዚህ እንደሚቻለን አድርገን መንግሥተ ሰማያት የምናውቅበትን ምሳሌ መስለን መናገር ይገባናል እንጂ የመንግሥተ ሰማይን ነገር ምሳሌ መስሎ መናገር አይቻልም፡፡ እስኪ ንገሩኝ! ተድላ ደስታ ባለባት በገነት ሰባት ዓመት በነበረ ጊዜ የአዳም የደስታው ብዛት ምን ያህል ነበረ? ሰማይ ከምድር እንደሚበልጥ ሁሉ መንግሥተ ሰማይም ከዚህ (ከገነት ደስታ) ትበልጣለች፡፡

   እስኪ አሁንም ሌላ ምሳሌ መስለን እንናገር፡፡ አንድ በአራቱ ማዕዘን የነገሠ ንጉሥ የሚዋጋው የሚያሳዝነው ሽፍታ ሳይኖርበት በክብር፣ በማዕረግ፣ በመፈራት፣ በመወደድ ሲኖር ያን ጊዜ በልቡ የሚወጣው የሚወርደው የደስታው መጠን ምን ያህል ይመስላችኋል? በመንግሥተ ሰማያትም እንዲህ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም እንደሚገባ መስዬ አልተናገርኩምና ሌላ ምሳሌ ፈልጌ መናገር ይገባኛል፡፡

  ወዳጄ ሆይ መስዬ የምናገረውን ነገር በዓይነ ልቡና አስተውል! አንድ የሚነግሥ የንጉሥ ልጅ በእናቱ ማኅፀን ሳለ ምንም እንደማያውቅና ከተወለደ በኋላ ግን እንደሚነግሥ እንደሚገዛ ሁሉ የአሁኑ ጊዜና የመንግሥተ ሰማይ ሥርዓትም እንዲህ ነው፡፡ እነሆ ታሥሮ በመከራ በኃዘን የሚኖር ሰው፣ ልዩ ልዩ የሚሆን ፅኑ መከራ የተፈራረቀበት ሰው በኋላ ከመከራ አውጥተው ከእስራት ፈትተው አንግሠዉት የነገሠ ሰው ደስ እንደሚለው የመንግሥተ ሰማይ ተድላ ደስታም እንዲህ ነው፡፡

  ሆኖም ግን እስከ አሁን ድረስ የተካከለ ምሳሌ መስዬ ማስረዳት አልተቻለኝም፡፡ አንድ ሁሉንም ነገር (ንግሥናም ቢሆን) በዚህ ዓለም ያገኘ ሰው በመጀመርያይቱ ዕለት፣ አዋጅ በነገሩለት ቀን፣ ሹመት ያዳብር ባሉት ዕለት፣ እጅ መንሻ ባገቡለት ጊዜ መጠን በመጠን ደስታው እየበዛለት ይሄዳል፡፡ ሆኖም ግን ይህም የመንግሥተ ሰማይን ነገር በሚገባ የሚያስረዳ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰው ያገኘው ሁሉ ኃላፊ ጠፊ ስለሆነ እየለመደው እየሰለቸው ይሄዳልና፡፡ መንግሥተ ሰማያት ግን ፍቅሯ በልቦና ፀንቶ ይኖራል እንጂ በመሰጠቷ አትፈጸምም፤ አትለወጥም፤ አትሰለችም፡፡ ኅልፈት፣ መለወጥ፣ ፍጻሜ በሌለባት በመንግሥተ ሰማያት ያለ ጣዕም፣ ተድላ፣ መዓዛ ብርሃንን ያገኘች የነፍስማ አኗኗርዋ እንደምን ይሆን? የማታልፍ፣ ሐዘን ሁሉ ፀዋትወ መከራ የሌለባት፣ ከነውር ከነቀፋ ከመቆርቆር ንጽሕት የምትሆን፣ ደስታን ፍጹም ተድላን የተመላች፣ በትሩፋት ሥራ የሚገኘውን ክብር ልዕልናን የተመላች መንግሥተ ሰማያት እየፀናች ትሄዳለች እንጂ ፍጻሜ መለወጥ የለባትም፡፡

 ከምንኖርባት ከተማ ወጣ ባልን ጊዜ የነገሥታትና የመኳንንትን ድንኳናቸው ብናይ፣ ልዩ ልዩ የሚሆን የጦር ዕቃቸውን ብናይ፣ ጋሻ ጦራቸው ሲያሸበርቅ ብንመለከት ፈጽመን እናደንቃለን፤ ደስም ይለናል፡፡ አይቻለንም እንጂ ቢቻለንና ንጉሡ በወርቅ የተሠራ የጦር ዕቃውን ይዞ በፈረስ ሆኖ በመካከላቸው ሲሄድ ብናየው የነገሥን ያህል ይሰማናል፡፡ የማታላፍ በልዕልናም ያለች የቅዱሳን ማኅደር መንግሥተ ሰማያትን ባየን ጊዜ ’ማ እንደምን እንሆን ይሆን? “በዘለዓለም ማደርያቸው ይቀበልዋችኋል” ተብሎ እንደተነገረ /ሉቃ.16፡9/ ከለበሱት ብረት ወይም ነሐስ ሳይሆን ዓይነ ሥጋ ማየት ከማይቻለው ፍጹም ክብራቸው የተነሣ የእያንዳንዳቸው የጻድቃን መልክ ከፀሐይ ብርሃን ይልቅ ሲያሸበርቅ ስናየው ‘ማ እንደምን እንሆን ይሆን? ይህ ለሰዎች የሚሰጥ ክብር ነው፡፡ የመላእክትን፣ የሊቃነ መላእክትን፣ የኪሩቤልን፣ የሱራፌልን፣ የመናብርትን፣ የአጋእዝትን፣ የሥልጣናትን፣ የኃይላትን መልካቸው ግን ከመናገር የራቀ ነው፡፡

 “ዓይን ያላየችው ጀሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” ተብሎ እንደተነገረ /1ቆሮ.2፡9/ ስለ መንግሥተ ሰማያት መናገር የሚቻለው ‘ማ ማን ነው? በእውነቱ ይህችን መንግሥተ ሰማያት ከመውረስ ከተከለከሉት ሰዎች በላይ ወራዶች የሉም፤ ይህችን መንግሥተ ሰማያት ከሚወርሱ ሰዎች በላይም ንዑዳን ክቡራን የሉም፡፡ እንግዲያውስ ወንድሞች ሆይ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ንዑዳን ክቡራን ከሚሆኑ ሰዎች የምንቆጠር እንሁን፡፡ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ /ዕብ.4፡11/፡፡

  ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር የክብር ክብር፣ ጌትነት ገንዘቡ በሚሆን በፈጣርያችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰጭነት የማታልፍ መንግሥተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ ክቡራን ንዑዳን ከሚሆኑ ቅዱሳን ጋርም እንድንቆጠር ያድርገን አሜን፡፡   

2 comments:

  1. Kale hiwotin yasemalin. yagelgilot zemenihin fetari yarzimilin. yekidusan bereketachew yideribih amen. melkam yehone melikt new enameseginalen.

    ReplyDelete
  2. ቅዱስ ቡሩክ ሁን ገብረ እግዚአብሔር እንደ ስምህ ደምቀህ ኑር

    ReplyDelete