Pages

Sunday, October 28, 2012

ምክረ አበው ቁጥር አራት


ልጆቼ! ሓኪሞች ብትሆኑ፣ መሀንዲሶች ብትሆኑ፣ የሽመና ሠራተኞች ብትሆኑ፣ መርከበኞችም ብትሆኑ መልካም ነው፡፡ ይህን ጥበብ መማራችሁም ጥሩ ነው፡፡ እኔ ግን ከዚህ የበለጠ ጥበብ አሳያችኋለሁ፡፡ በዚህ (በተማራችሁት ምድራዊ) ጥበባችሁም ሌላ ጥበብ ትማሩበት ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡ ሰማያዊን ጥበብ! ከላይ በገልጽኩላችሁና እናንተ በተማራችሁት ጥበብ ተጠቅማችሁ ገንዘብ ማግኘታችሁ አይቀርም፡፡ በዚህ ገንዘባችሁ ግን ድሆችን መርዳት ልመዱበት፡፡ ይህ የምነግራችሁን ጥበብ እንደ ቀላል የምታዩት አትሁኑ፡፡ መሀንዲሶች ብትሆኑ በምህንድስና ጥበባችሁና እውቀታችሁ በዚህ ምድር የሚያማምሩ ቪላ ቤቶችን ልትሠሩ ትችላላችሁ፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን
በመንግሥተ ሰማያት ውስጥ የዘላለም ቤታችሁን ትሠራላችሁ፡፡ በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤታችሁ በጣም ብዙ ወጪ ብዙም ድካም ይጠይቃችኋል፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን ብዙ ልፋት የለውም፡፡ ወጪአችሁ መልካምና ፈቃደኛ መሆን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምድር ለምትሠሩት ቤት የተለያዩ ዓይነት ብረቶችና ማቅለጫዎች እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን ትጠቀማላችሁ፡፡ በምነግራችሁ ጥበብ ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋችሁም፡፡ የሚያስፈልጋችሁ ብሎን ወይንም ብረት ወይንም የከበረ ድንጋይ ሳይሆን መልካም ምግባራችሁና በጎ ፈቃዳችሁ ብቻ ነው፡፡

እንደውም እኔ እነዚህ የተማራችኋቸው ጥበቦች ጥበብ ብዬ ለመጥራት በጣም እቸገራለሁ፡፡ ለምን ብትሉኝ ከምነግራችሁ ጥበብ ጋር ሳወዳድራቸው በጣም ስለሚያንሱብኝ አያያዛቸው ላላወቀበት ሰውም ብዙ ጉዳት ስለሚያመጡ፡፡ እስኪ አስተውሉት! አንድ ሰው በዚህ ምድር ባገኘው ጥበብና ገንዘብ ተጠቅሞ ድሆችን መርዳት ሲገባው አላግባብ ሲበላ ሲጠጣ በኋላ ግን በስኳር፣ በሪህ፣ በቁርጥማት፣ በራስ ምታት፣ በልብና በኩላሊት በሽታ የሚሰቃይ ከሆነ ይህ ጥበብ እለው ዘንድ እንዴት እደፍራለሁ? እንግዲያውስ ጥበባችሁ ጥበብ ይሁንላችሁ፡፡ ጥበባችሁ ለሥጋችሁም ለነፍሳችሁም የሚጠቅም እንጂ በዚህ ዓለምም ይሁን በሚመጣው ዓለም የሚጎዳችሁ አይሁን፡፡ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

1 comment:

  1. “ልጆቼ! እግዚአብሔር የምንናገርበትን አንደበት፣ የምንሠራበትን እጅና እግር፣ የምናስብበት አእምሮ፣ የምናስተውልበትም ልቡና የሰጠን ወንድሞቻችንን እየረዳን የራሳችንን መዳን እንድንፈጽምበት እንደሆነ የምታስተውሉ ሁኑ፡፡ አንደበት የተሰጠን እንድንዘምርበት ወይንም በቅዳሴ ጊዜ እንድናመሰግንበት ብቻ ሳይሆን እንድናስተምርበትና እንድንገስጽበትም ጭምር ነው፡፡ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ጌታችንን እንመስለዋለን፡፡ በተቃራኒው የምንሄድ ከሆነ ግን ዲያብሎስን እንመስለዋለን፡፡ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ በመሰከረ ጊዜ ብጹዕ ነህ ተባለ፤ የአብ የሆነውንም እርሱ ስለተናገረው አብን መሰለው፡፡ መስቀሉን በተቃወመ ጊዜ ግን ሰይጣንን መሰለው፡፡ እንግዲያውስ በመታዘዝ እንናገርና ቃላቶቻችን የክርስቶስ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በንግግራችን ክርስቶስን የምንመስለው “ጣቢታ ሆይ ተነሽ” ወይንም “አልአዛር አልአዛር ተነሥና ተመላለስ” ስንል ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ በበለጠ በንግግራችን ክርስቶስን የምንመስለው የሚሰድቡንን ስንመርቅ፣ የሚያሳዱድንን ስንባርክ ነው፡፡ አንደበታችን በአግባቡ ስንገለገልበት የእግዚአብሔር እግር ይሆናል፡፡ ጠቃሚ ምክርን ስንለግስበት የክርስቶስ አንደበት ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሆነውን ብቻ ስንናገርበት አንደበታችን የክርስቶስ አንደበት ይሆናል፡፡ አንደበታችን የክርስቶስ አንደበት ሲሆን፣ አፋችን የአብ አፍ ሲሆን /ኤር.15፡19/ ሰውነታችንም የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ሲሆን ከማየት በላይ ምን የሚተካከለው ክብር አለ? አንደበታችን በወርቅ ብናሠራው ከዚያም በላይ ውድ በሆኑ የከበሩ ዕንቁዎች ብናስለብጠው በትሕትና ቃላት ከማስዋብ በላይ አናስጌጠውም፡፡ አለመሳደብን የምታውቅ ምላስ የሚተካከላት ማን ነው? ልጆቼ! እንግዲያውስ የሚሰድባችሁን ሰው መመረቅ ካልቻላችሁ ብያንስ ብያንስ ዝም በሉና ይህን ለማድረግ ተጣጣሩ፤ እግዚአብሔርም መሻታችሁን አይቶ ከላይ የገለጥነውን ዐይነት አንደበት ይሰጣችኋል፡፡ ይህን እንዴት አድርጌ እችላለሁ ብላችሁም ፍጹም የምትቸገሩ አትሁኑ፡፡ እግዚአብሔር ሰው ወዳጅ ስለሆነ ከመልካም ባሕርይው ይህን መልካም ነገር ይሰጣችሁ ዘንድ የታመነ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ታገኙ ዘንድ የዓቅማችሁን ያህል ተጣጣሩ፡፡ ከዚያም ሰይጣን ፊታችሁን እንኳን ለማየት ይንቀጠቀጣል፡፡ ክርስቶስን መስላችሁ ስትገኙ ዲያብሎስ ወደናንተ ለመቅረብ ዓቅም አያገኝም፡፡ እናንተ ውስጥ የንጉሡ (የእግዚአብሔር) መልክ ስለሚመለከት በእጅጉ ይፈራችኋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የቆሰለበትን መሣርያ እናንተ ውስጥ ስለሚመለከት በእጅጉ ይርዳል፡፡ ይህ መሣርያም በገዳመ ቆሮንቶስ ድል የሆነበት የክርስቶስ ትሕትናውና ጨዋ ንግግሩ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስን መስሎ የሚመጣባችሁ ሰው ክርስቶስን መስላችሁ ቅረቡት፡፡ ትንቢትን ከምትናገር አንደበት በትሕትና የምትናገር አንደበት ትበልጣለች፡፡ ትንቢት መናገር ስጦታ ነው፤ በትሕትና መናገር ግን ከእኛ ነው፡፡ ስለዚህ አንደበታችሁ መልካሙን ብቻ ትናገር ዘንድ ነፍሳችሁን አስተምሯት፡፡” ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

    ReplyDelete