Pages

Tuesday, October 23, 2012

ሞትን መፍራት ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
 
ጥያቄ፡- እሞታለሁ ብዬ ሳስብ በጣም እጨነቃለሁ፡፡ እናቴ እንደነገረችኝ ከሆነ ሞትን መፍራት የጀመርኩት ገና ከልጅነቴ ጀምሬ ነው፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ሳለሁ በጣም ከምቀርባቸው ጓደኞቼ መካከል ከአንዱ ጋር ተጣላሁና ሳልታረቀው በሳምንቱ ሞተ፡፡ በጊዜው በጣም ጸጸተኝ፡፡ ሞትን ባሰብኩ ቁጥር የሚታየኝ ያ ሳልታረቀው የሞተው ልጅ ነው፡፡ የመፍራቴ መጠንም በእድገቴ ልክ እየጨመረ ነው፡፡ ሌሊት ላይ ባንኜ “አሁን ብሞትስ?” ብዬ እጨነቃለሁ፡፡ ንስሐ ብገባም ፍርሐቱ ሊለቀኝ አልቻለም፡፡ “ሰው ሞተ” ሲባልም በጣም እደነግጣለሁ፡፡ የምደነግጠውና የምፈራው ግን ሰውዬው ስለሞተ ሳይሆን “እኔም እኮ እሞታለሁ” ብዬ ነው፡፡ እባካችሁ በጣም ጨንቆኛልና ሞትን መፍራት ማቆም የሚቻለው እንዴት ነው?
                             እኅታችሁ ኤልሣቤጥ ነኝ ከአ.አ. 

ምላሽ፡-ውድ ጠያቂያችን! የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላምታ ባለሽበት ይድረስሽ፡፡ ለጠየቅሽን ጥያቄ የቻልነውን ያህል ለመርዳት መጻሕፍተ ሊቃውንትን አገላብጠን ያገኘነውን መልስ እነሆ ብለናል፡፡ እንደ ጠቋሚ ይረዳሻል ብለንም እናምናለን፡፡ ከቻልሽ አስቀድመሽ በጸሎት ጀምሪና በተመስጦ ሆነሽ አንቢው፡፡ መልካም ንባብ!


  የሞት ፍርሐት (Thanatophobia) በዓለም ላይ የብዙ ሚልዮን ሰዎችን ሕይወት ከሚያሰቃዩ የፍርሐት ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ የችግሩ መንሥኤም ከሰው ወደ ሰው ይለያያል፡፡ የምንወደው ሰው ከአጠገባችን በሞት ሲለይ፣ ከፊት ለፊታችን በአሰቃቂ አደጋ የሚሞቱ ሰዎችን ስንመለከት፣ በሕፃንነታችን ጊዜ የሞት አስፈሪነትን የሚገልጹ ታሪኮች አዘውትረን የምንሰማ ከነበረ (ባለሙያዎች የልጆቻችን ሞግዚቶች ላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል የሚሉት ስለዚሁ እንደሆነ ልብ ይሏል)፣ የምናነባቸው መጻሕፍት ወይንም የምናያቸው ትዕይንቶች (ፊልሞች) ለዚሁ ፍርሐታችን ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ ሁሉ በጣም የከፋው ግን የእምነት ማነሥ  ለዚሁ ይዳርጋል፡፡ ላለማመናችን የራሳችን ፈቃድ እንደተጠበቀ ሆኖ ርኩሳን መናፍስት ይህን ሊያደርጉ እንደሚችሉም የታወቀ ነው፡፡
 በዚህ ፍርሐት የሚሰቃዩ ሰዎች ከፍርሐቱ በተጨማሪ ሌሎች የሚስተዋሉባቸው ምልክቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ “አሁንኑ ብሞትስ” ብሎ መጨነቅ፣ የሞቱ ሰዎችን ሲያዩ “በቃ! አሁን የእኔ ተራ ነው” ብሎ ቁጭ ብሎ ማደር (እንቅልፍ ማጣት)፣ ባስ ሲልም (የሞተን ሰው ላለማየት ወይንም ሲለቀስለት ላለመስማት ከመሄድ ስለሚቆጠቡ) ከማኅበራዊ ኑሮ መነጠል… ወዘተረፈ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የአፍ መድረቅና የልብ ምት መጨመር ሊስተዋል ይችላል፡፡
  ወደ መፍትሔው ስንመጣ በጣም ብዙ መንገዶችን መዘርዘር ይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም ከጽሑፉ ውስንነት (Scope) አንጻር በዋና ዋና ነጥቦች በማተኮር ከዚህ ችግር እንዴት ልትወጪ እንደምንችዪ መጠቆሙ ተገቢ ይሆናል፡፡
1. መቀበል፡- ውድ እኅታችን! ከሌሊት በኋላ ቀን፣ ከጨለማ በኋላ ብርሃን፣ ከክረምት በኋላ በጋ፣ ከዚህ ዓለም መኖር በኋላም “ሞት” ይመጣ ዘንድ ግድ የተፈጥሮ ሂደት እንደሆነ መቀበሉ ያስፈልጋል /ዕብ.9፡27/፡፡ ከዚህ ሂደት ማምለጥ የሚችል ማንም ፍጡር የለም፡፡ እዚህ ምድር እስካለሽ ድረስ የሚመጣውን የተፈጥሮ ሂደት መለወጥ ስለማትችዪ ዕድሜሽ በጨመረ ቁጥር ወደዚያች ቀን እየቀረብሽ እንደሆነ አስረጂ አያስፈልግሽም፡፡ ስለዚህ ከመደንገጥ ይልቅ መቀበሉ አማራጭ የሌለው እውነት ነው፡፡
2. ማመን፡- ሆኖም ግን ከሞትም በኋላ ትንሣኤ የማይቀር መሆኑ እንደ ቃሉ ማመን ይጠበቅብሻል፡፡ በዚህ ዓለም የምንሠራው ቤት በዕድሜ ብዛት፣ በመሬት መንቀጥቀጥ እንዲሁም ዛሬ ከየአቅጣጫው በምናያቸውና በምንሰማቸው በተለያዩ የአደጋ ዓይነቶች ይፈርሳል፡፡ የምንተክላቸው የወይን ዘለላዎች፣ የምንሠራቸው ማንኛውም ዓይነት ሥራዎች ከፍሬአቸው ለመቋደስ ብዙ ጊዜ እንጠብቃለን፡፡ በመንግሥተ ሰማያት ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ታድያ ወደዚያ መሄድ የማይናፍቅ ማን ነው? ወደዚያ የሚያሻግረውን ሞትስ የሚፈራ ማን ነው? ይህች የምንኖርባት ምድር ክርስቲያኖች ለምንሆን (ለእኛ) የእንግድነት ሀገራችን አይደለችምን? ታድያ በእንግድነት ሀገረ መኖር የሚናፍቅ ማን ነው? በጊዜአዊ መጠለያ (ካምፕ) ውስጥ ብርድና ሙቀት እየተፈራረቀበት መኖርን የሚፈቅድ ማን ነው? እንግዲያውስ ከዚህ ጊዜአዊ መጠለያችን የምንለይባት ቀን እንደ ልደት ቀናችን ልንናፍቃት የተገባ ነው፡፡ አዎ! በዘወትር ጸሎታችን “መንግሥትህ ትምጣ” ብለን የምንጠራትን መንግሥቱ መውረስን ስለምንናፍቅ እንጂ ስለምንፈራ አይደለም፡፡ እስኪ አንድ ቀላል አመክንዮ (Logic) እናምጣ! በስደት ሀገር እየኖረ ወደ እናት ሀገሩ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን የማይሻ ማን ነው? ወደ ሀገሩ ተመልሶ እናቱን፣ አባቱን፣ እኅቶቹን፣ ወንድሞቹን፣ ወዳጆቹንና አብሮ አደጎቹን ለማግኘት የማይቻኮል ማን ነው? መንግሥተ ሰማያት ግን ከኢትዮጵያ በላይ የሆነች የዘላለም ሀገራችን ናት፡፡ ታድያ የእመብርሃን እቅፍ የማይናፍቀው ማን ነው? እንደ አልአዛር ከደጉ አብርሃም ጉያ ውስጥ መሸጎጥ የማይናፍቀው ማን ነው? ቅዱሳን አባቶቻችንና ቅዱሳት እናቶቻችንን ማግኘት የማይናፍቀው ማን ነው? እዚያ የሚጠብቁን ቤተ ሰቦቻችን እልፍ አእላፍ አይደሉምን? ታድያ እዚህ ብቻችንን መኖር ስለምን እንወዳለን? ልጇ ከስደት ሀገር ተመልሶ ማየትን የማትናፍቅ ኢትዮጵያዊት እናት ማን ናት? ከስደት ሀገር ተመልሶለት የልጁን ፊት ማየት የማይጓጓ ኢትዮጵያዊ አባት ማን ነው? ከእናትም በላይ እናት የሆነችው እመብርሃን በንስሐ ታጥበን ከእቅፏ እንድንገኝላት የምትወድ አይደለችምን? ታድያ እርሷ እንዲህ እየናፈቀችን እኛ “ሞትን ስለምንፈራ አንመጣም” ልንላት ይገባልን? ወደ እናት መሄድስ እንደምን ያስፈራል? ወንድምን ማግኘት እንደምን ያስጨንቃል? እኅትን ማግኘት እንደምን እንቅልፍ ያሳጣል? ክቡራን ንዑዳን ከሚሆኑ ከሐዋርያት ጋር፣ ቅዱሳን ከሚሆኑ ከማኅበረ ነቢያት ጋር፣ እልፍ አእላፍ ከሚሆኑ ሰማዕታት ጋር፣ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ ሳያቋርጡ ከሚያመሰግኑ ሠራዊተ መላእክት ጋር፣ ዓለምን ከእነ ምኞቷ ሰቅለው ከሙሽራው ጋር ከገቡት ልባሞቹ ደናግላን ጋር፣ ከደጋጎቹ ሊቃውንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ጋር መኖር የማይሻ ማን ነው?
3. ማስተዋል፡- እንግዲያውስ እኅታችን ሆይ! ሞትን እፈራለሁ” ማለት እግዚአብሔርን መቃወም እንደሆነም በደንብ ማስተዋል ይኖርብሻል፡፡ ምክንያቱም “ሞትን እፈራለሁና አልሙት” ማለት “እግዚአብሔር ሆይ! ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ አልሻም፤ ከአንተ ጋር ከመሆን ይልቅም (ለእኔ) በዚህ ዓለም ያለው ደስታ ይሻለኛል” እንደማለት ነውና፡፡ ከፀሐይ ብርሃን (ከእግዚአብሔር) ይልቅ ሻማን (የምናያትን ፀሐይ) እንደመናፈቅ ነውና፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን ዕረፍት ትቶ “በላብህ ወጥተህ ወርደህ ብላ” የሚለውን የፍርድ ትእዛዝ እንደመቀበል ነውና፡፡ ስለዚህ በተራ ቁጥር ሦስት ላይ እንደተናገርን እኛ ከምንወዳቸው እነርሱም ከሚወዱን ቤተሰቦቻችን ተለይተን እንዳንሞት እንጂ ወደዚያ ዕረፍት የሚያሻግረንን የክርስቲያኖች ሞት የምትፈሪ አትሁኚ፡፡ ይህን እንድንፈራ የሚያደርገን በዚህ ዓለም ምኞት ተጠላልፈን ወድቀን በወዲያኛውም ዓለም እስከየሌለውን ስቃይን እንድንሰቃይ የሚወድ የጥንተ ጠላታችን ምክር እንደሆነ ልታውቂ ይገባል፡፡ እንደ ኢዮብ እየፈተነ እግዚአብሔርን እንድናማርር የሚፈልግ የክፉው ድምጽ እንደሆነ ልታስተውዪ ይገባል፡፡ ዕድሜአችን ሲጨምር፣ ዐይነ ሥዉር ስንሆን፣ የብዙ ብዙ ደዌ ዘሥጋ ተጠቂዎች ሆነን፣ ሰዎች እስኪሰለቹን ድረስ እዚህ ምድር ቆይተን እንድናማርር እና በኢዮብ ሚስት አድሮ እንዳደረገው እግዚአብሔርን እንድንሰድ ዘወትር የሚጐተጉተን የክፉው ሹክታ እንደሆነ ልትገነዘቢ ይገባል፡፡ እምነተ ጐደለዎች ሆነን በዚህ ዓለም ትንሣኤ ሙታን እንደሌላቸው እንሥሳት ያለ እምነት እንድንመላለስ የዲያብሎስ ደስታ ነው፡፡ በእምነት የሚኖር ሰው ግን ወደ ክርስቶስ መሄድን አይፈራም፡፡ ከዚህ ዓለም አሠራር ተላቆ መሄድን አያስደነግጠውም፡፡ እስኪ መጽሐፍ ቅዱስሽን ግለጪና የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለትን ግለጪ፡፡ ታሪኩ እንዲገባሽ ከቁጥር 22 ጀምረሽ ቃሉን አንቢው፡፡ ታሪኩ የአረጋዊው ስምዖን ታሪክ ነው፡፡ ከቁጥር 29 ላይ ስትደርሺ ስምዖን እንዲህ ይላል፡- ጌታ ሆይ አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን ታሰናብተዋለህ፡፡ ልሙት እያለ ነው፡፡ ለምን? ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፡፡ እኅታችን ሆይ! ክርስቶስ እንዲህ የሚናፈቅ እንጂ የሚፈራ አይደለም፡፡ ከክርስቶስ ጋር ስንሆን ስጋት የለም፤ ጭንቀት የለም፤ ፍርሐት የለም፤ ማዕበል የለም፤ ጦርነት የለም፤ ረሀብ የለም፤ መጠማት የለም፤ ደከመኝ የለም፤ ሰለቸኝ የለም /ኢሳ.3510/፡፡
ውድ እኅታችን ሆይ! በዚህ ዓለም ካሉ ከክፋት መናፍስት ጋር በየጊዜው ከመዋጋት ይልቅ በክርስቶስ ዐርፎ በሰላም መኖር አይበልጥምን? ከክፋት መናፍስት ጋር በተዋጋን ቁጥርስ አንዳንዴ በቁጣ፣ ሌላም ጊዜ በስድብ የምንፈተን አይደለምን? አንዱን አሸነፍን ስንልስ ሌላው ተሰውሮ የሚመጣ አይደለምን? ነፍሳችንስ በየደቂቃው ስደቱ የሚበረታባት አይደለምን? ከዲያብሎስ ጦር ለማምለጥስ ብዙ የምትለፋ አይደለችምን? እንዲህ ስንገፋ፡- “ዓለም ደስ ይሏል፡፡እንዲህም ስለሆነ፡- “ታዝናችሁተባልን /ዮሐ.1620/፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ስለማንዘልቅ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል አለን፡፡ ታድያ ከዚህ ሐዘን መውጣት የማይናፍቅ ማን ነው? ያንን ደስታ ለማግኘት ሞትን ረግጦ ለመሻገር የማይቻኮል ማን ነው? ከሐዘን መውጣትስ ያስጨንቃልን? ጌታችን ሲቀጥል እንዲህ ይላል፡- እንደገና አያችኋለሁ፤ ልባችሁ ደስ ይሏል፡፡ ደስታችሁም የሚወስድባችሁ የለም /ዮሐ.1622/፡፡ እኅታችን ሆይ! ይህን ተስፋ የሰጠን እኮ እንዲሁ ሰው አይደለም፡፡ ተስፋውን የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያው እንደተናገረው ሞታችንጥቅም ነው” /ፊል.121/፡፡ የእኛ መሞት የአሕዛብ ዓይነት ሞት ስላይደለ ጥቅም ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደነርሱ በዚህ ምድር ሥጋ ለብሰን የምንመላለስ ብንሆንም ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ የተወለድን ስለሆንን እንዲሁ ሥጋውያን አይደለንም፡፡ ዳግም ከማይጠፋው ዘር የተወለድን ስለሆንን ሞት በእኛ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ አባቶቻችንሞት ሆይ! ድል መንሣትህ ወዴት አለ?” የተሳለቁበት ይህ ቢገባቸው እንጂ ያለምክንያት አይደለም /1ቆሮ.1555/፡፡ ስለዚህ ሞታችን ጥቅም እንጂ ጉዳት፣ ደስታ እንጂ ሐዘን እንዳልሆነ ልታስተውዪ ይገባል፡፡
4.መቃወም፡-እንግዲያውስ ይህን የሚያስስብሽ ሰይጣን እንደሆነ በማስተዋል ሐዋርያው እንደነገረሽበእምነት ጸንተሽተቃወሚው /1ጴጥ.59/፡፡ እምነትሽን ለመሸርሸር የሚሯሯጠው ሰይጣን እንደሆነ በማወቅ ሰልፉን ለእግዚአብሔር አሳልፈሽ ስጪው /1ሳሙ.1447/፡፡ እግዚአብሔርም በአንቺ ከአንቺ ጋር ሆኖ ዲያብሎስን ድል ያደርጓል፡፡ እኅታችን ሆይ! እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር እንደነበረ ከአንቺ ጋርም ነውና አትፍሪ፡፡ በዚሁ የውጊያ ዐውድማ ብቻሽን አይደለሽምና አትደንግጪ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአንቺ ጋር ነውና አትጨነቂ፡፡ እኅታችን ሆይ! የምትኖሪው ከክርስቶስ ጋር እንጂ ብቻሽን አይደለሽም /ገላ.220/፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚራዱሽ ቅዱሳን መላእክት በዙርያሽ አሉ /ዕብ.114/፡፡ ስለዚህ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታሽ ሆነሽ ዲያብሎስን ተቃወሚው፤ ከአንቺም ይሸሻል /ያዕ.47/፡፡ ሰይጣን እንዲሁ በቀላሉ የማይርቅ መንቻካ ነውና በጾምና በጸሎት ተዋጊው /ማር.929/፡፡ ምክንያትን እየፈጠረ ሊያስደነግጥሽ ቢሞክርም ከዳዊት ጋር ሆነሽእግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?” በዪው /መዝ.261/፡፡ የዲያብሎስ ደባዎች ለማክሸፍ ዓይነተኛ መሣርያ ምክርና ንስሐ ነውና ደጋግሞ ይህን ሐሳብ ቢያመጣብሽም ደጋግመሽ ከንስሐ አባትሽ ጋር በመመካከር ኃይሉን አክሽፊበት፡፡ ወደ ሥጋውና ደሙ በመቅረብ ኃይሉን አምክኚበት፡፡ እንደተናገርን ከዚህ ዓለም እስካልተለየን ድረስ የሰይጣን ፍላጻው ብዙ ነውና በትዕግሥት ሆነሽ ተዋጊው፡፡ ይርቅሽ ዘንድም በዚሁ ርእስ አጥብቀሽ ፀልዪ፡፡
    ለተጨነቁት ማረፍያቸው የሚሆን እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ይሁን፡፡ አሜን!!


9 comments:

  1. [englizegna newe melse, be'amaregna bihoneme ye'ehetachene Teyaqei :)]

    As Orthodox Christians we have no reason to be depressed at the thought of death. This is not to say that we should have no fear of death - this feeling is natural since death introduces us to the unknown. Furthermore, a certain fear of death is very healthy spiritually, as the Holy Fathers teach us, and should lead to repentance and inward vigilance. In the Holy Scriptures we read: "In all you do, remember the end of your life, and then you will never sin" (Sirach 7:36).

    -> In my opinion, you should advise her not to let the fear of death hold her under its dominion, or else the evil one plays on her fear of death, furthering sin and death in rebellion to God's will.
    _______________________________

    The fear of death comes not only from the advent of the unknown, but also in knowing that death is a point when all opportunity for repentance and struggle is over; the time of reckoning is at hand.

    Share this story with the sister:

    + When St Sisoës lay upon his deathbed, the disciples surrounding the Elder saw that his face shone like the sun. They asked the dying man what he saw. Abba Sisoës replied that he saw St Anthony, the Prophets, and the Apostles. His face increased in brightness, and he spoke with someone. The monks asked, "With whom are you speaking, Father?" He said that angels had come for his soul, and he was entreating them to give him a little more time for repentance. The monks said, "You have no need for repentance, Father" St Sisoës said with great humility, "I do not think that I have even begun to repent."

    -> Even the ancient desert father, St. Sisoes, as he lay dying, prayed to live longer, saying that he needed more time to repent; that truly, he did not know whether he had yet begun to repent. If these were the thoughts of a holy man, how much more should we sinners struggle to prepare ourselves to meet the Just Judge Who, sonner or later, awaits us all?

    [Credits to Dr. George Kalousek, http://roca.org/OA/40/40f.htm]

    ReplyDelete
  2. Tilahun Yazie said on FB:- First you have to know that most fear death.secondly,you need to know much about the meaning and purpose of life.In order to do so,it is better to consult with spiritual teachers.Because you may need broad explanation.For the time being let me suggest u one book.Please read a book called `Tegsats`,which is ancient Ethiopian commentary on Hebrew by John Chrysostom.He will tell you about Death and some basic attitudes Christians needs to have towards death.

    ReplyDelete
  3. እነዚህን ጥቅሶች አስቢባቸው


    መዝሙር 23:4 በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።

    ኢሳያስ 41:10 እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።

    1ኛ ተሰሎንቄ 4:14 ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና።

    ዩሃ 11:25 ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።

    መዝ 116:15 የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።

    መዝ 3-4 የሞት ጣር ያዘኝ፥ የሲኦልም ሕማም አገኘኝ፤ ጭንቀትንና መከራን አገኘሁ።የእግዚአብሔርንም ስም ጠራሁ። አቤቱ፥ ነፍሴን አድናት።

    << ሃጥያቱ ይቅር የተባለለት ሰው ምስጉን ነው::>>

    ReplyDelete
  4. ሞትን መፍራትና በዚህ ምድር በሕይወት ለመቆየት መሻት ጤናማነት ነው፡፡ ስለዚህ በምንም መንገድ ከሞት ፍርሃት መሸሽ አይቻለንም፡፡ ይህ ጤናማ እንደሆነ ይገልጥልን ዘንድ ጌታችን “አባት ሆይ ይህች ፅዋ ከእኔ ትለፍ” ብሎ መጸለዩን እንመለከታለን፡፡ የዚህ መልእክቱ እንዲህም እንደሆነ ቅዱስ አፍርሃት ይገልጻል፡፡ ባል ከሚስቱ መለየትን እንደማይወድ እንዲሁ ነፍስም ከሥጋዋ መለየትን አትወድም፡፡ ምንም ከጌታ ጋር መኖር ከሁሉ የሚሻል ቢሆንም በመጨረሻዋ ሰዓት ሞት ነፍስን ማስፈራቱዋ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ከሞት ፍርሃት ማንም ቢሆን ሊረቅ አይችልም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ ጤናማ ፍርሃት የሚለው ይህንን ነው፡፡

    ReplyDelete
  5. Memhr tnsh mabrarya btchemrln. Mknyatum yeehtachn frhat enklf yemikeleklat, smu betenesa meten yemiasdenegtat kehone endet tenama libal ychlal?

    ReplyDelete
  6. በፍልሰታ የሚነገር አንድ ታሪክ አለ።
    አንድ ዲያቆን ነበር እንደተቀበለው የእግዚአብሔር ፀጋ አያገለግልም (ሰነፍ ነበር) ስንፍናው ብቻ አልነበረም ሌሎች ኃጢአቶችም ይፈፅም ነበር ካለ ዝሙት በስተቀር። ታድያ የፍልሰታ ፆም ሲደርስ ግን እንደማንኛውም አገልጋይ ከዛም በበለጠ ታጥቆ ያገለግላል ይላካል። ስንፍና የሚባል ነገር አይታይበትም -- በፍልሰታ ጾም። ልጁ ግን አንዲት የማይረሳትና የማያስታጉላት ፀሎት ነበረችው -- "እመቤቴ ሆይ ስንፍናዬን ታውቅያለሽ ስለዚህ ንስሐ ሳልገባ ከነኃጢአቴ እልዳልሞት አደራ አደራ አደራ።" ይላት ነበር ሞቱን ሲያስበው አስቸናቂ ነበርና። ጾሙ እንዳለቀ ደግሞ ማንም አይዘውም። ወደ ነበረው ህይወት ይመለሳል። አንድ ጊዜ ወደ ሌላ አገር ሲሄድ ሽፍቶች ያገኙታል። ለሞት እስኪደርስ ድረስ ይደበድቡታል ግን አይሞትም ቢሉት ቢሉት አልሆን ስላቸው ቆመው "ምን አይነት ተአምር ነው ?!" እያሉ ሲያደንቁ ለሞት በደረሰች እስትንፋስ "አትድከሙ እመቤቴን ንስሐ ሳልገባ እንዳልሞት አደራ ስላልኳት ነው።ከቻላችሁስ ካህን ጥሩልኝ ንስሐ ገብችሄ ልሙት" ይላቸውና ደንቁዋቸው ወደ አቅራቢያ ቦታ ሄደው ካህን አስመጥተው ንስሐውን ተቀብሎ በሰላም ዐረፈ።
    ----------
    አሁን ንስሐ ብንገባም በምን ሁኔታ ሆነን እንደምንሞት ስለማናውቅ ሁሌ ስለሞታችን ነገር ማሰብና መፍራት ተገቢ ነው። "ነገ የሚሆነውን አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ" እንደተባለ። በኃጢአት ዕዳ ተይዘን እንዳንሞት በእውነት መፀለይና መፍራት ግድ ይለናል። ወንድማችን Kinfe Gabriel እንዳለው አባቶች ንፁሃን ሳሉ ስለሞታቸው ከተጨነቁ እኛማ እንዴት አብዝተን እንድንጨነቅ አይገባንም?
    አንድ ንጹህ አባት ደግሞ (በልጅነቱ ነው ይባላል) ወደ ቤተ መቅደስ እየሮጠ መጣ። ጳጳሱም ከመንፈስ ቅዱስ እንደተላከ (የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ) እንዳለው አውቆ አልከለከለውም። ፊቱ ወደ ህዝቡ አዞረና እንዲህ አለ;
    "እኔ በህይወቴ ሶስት ነገሮች ያስፈሩኛል
    1 - ነፍሴ ከሥጋዬ ስትለይ
    2 - ነፍሴ በፍርድ አደባባይ ስትቆም
    3 - ከእውነተኛው ዳኛ ፍርድ ስትወጣ መስማት
    ብሎ ወደ ቦታው ተመለሰ። ሕዝቡም አለቀሰ።
    ይህ ህጻን (አባት) እንዲህ ካለ እንዴት እኛ ከዛ በላይ አንልም?
    በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት ጸጋዎች (እውነተኛ ትሕትና፣ እምባ፣ ስለሞት እያሰቡ መፍራት ወዘተ) በቀላሉ የሚገኙ አይደሉምና ባናጣቸው መልካም ነው። ስለዚህ እንድሁ ትቀጥል።
    እንዲህ የምንፈራ ከሆነ ኃጢአት አንሰራም፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከፊታችን ስለምናደርገው። ንጹህ ህይወት ይኖረናል፣ ኃጢአት ብንሰራም እግሮቻችን ለንስሐ ይፈትናሉ። ሃብተ አንብዕ (የማንባት ጸጋ) የሚገኘው ከዚሁ ነው።
    ብዙ መንፈሳዊ ሀብቶች ሊያሰጠን ስለሚችል ቢቀጥል መልካም ነው።

    ማስጠንቀቂያ: ፍርሃቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ ሰይጣን ሊጠቀምበት ስለሚችል ግን ብልህ (ጠቢብ) መሆን ያስፈልጋል። አባቶቻችን ይህን ፍርሃት ገንዘብ ማድረጋቸው ለመንፈሳዊ ህይወታቸው እድገት ተጠቅመውበታል። ከኃጢአት እንዲርቁ አድሮጓቸዋል። ስለዚህ ከኃጢአት እያራቀን ወይም ኃጢአት ስንሰራም ለንስሐ እንድንፈጥን እያደረገን ከሆነ አሁንም መልካም ነው። ነገር ግን ተስፋ በማስቆረጥ በእግዚአብሔር ላይ እምነት እንዳይኖረን ለጽድቅ ሥራ እንዳንሰራ የሚያደርገን ከሆነ ግን መጠንቀቅና ብልህ መሆን ያስፈልጋል።
    ጥያቄው እንቅልፍ የሚያሳጣ ሆኖ አልተሰማኝም --- ስለሞት ሲያስቡና ሲሰሙ ከሆነ አሁንም እንደተባለው ጤናማ ነው ብዬ አስባለሁ።
    የአባቶቻችን ጸጋ ለኛም ያድለን። አሜን !

    ReplyDelete
  7. Kewyytachu hulet aynet frhat astewlalehu! Andegnawna Kinfe Gabriel, Shimels endihum Zerabruk yegeletachut tenama sihon huletegnaw gn yeehtachn aynetuna tenama yalhone frhat.

    ReplyDelete
  8. እግዜአብሔር ፍርሀትሽን ከቀኙ ያርግልሽ። በጾሎት በርች : ቁልፎ የሔው ነው።

    ReplyDelete
  9. ቃለ ህይወት ያሰማልን ።

    ReplyDelete