Pages

Sunday, November 4, 2012

ስለ አንድ የበግ ግልገል (ለሕፃናት)


           ወላጆች ይህን ትምህርት ለልጆችዎ ፕሪንት በማድረግ ወስደው ያንቡላቸው? 
 
ልጆች እንደምን ከረማችሁ? ትምህርትስ እንዴት ነው? ሰንበት ትምህርት ቤትስ ትሄዳላችሁ? ጎበዞች! ለዛሬ ደግሞ አንድ ቆንጆ ምክር ይዤላችሁ ስለመጣሁ በጽሞና ተከታተሉኝ፡፡ እሺ? ጎበዞች!
 ብዙ በጎች የነበሩት አንድ ሰው ነበረ፡፡ እህ… አላችሁ? ታድያ ይህ ሰው በጎቹን ሲጠብቅ በጣም ተጠንቅቆ ነው፡፡ የለመለመ ሳር ይመግባቸዋል፤ የጠራ ውኃ ያጠጣቸዋል፤ ወደ ተራራ ላይ ቢወጡ በጥንቃቄ ያወርዳቸዋል፤ የደከሙ ካሉ ደግሞ ይሸከማቸዋል፡፡ ወደ ማሳ ውስጥ እየገቡ ሳር ሲለቃቅሙ ደግሞ ባጠገባቸው ተቀምጦ ዋሽንት ይነፋላቸዋል፡፡ በጎቹም ዋሽንቱን እየሰሙ እጅግ ደስ ይላቸዋል፡፡

 ሲመሽም እንዳይበርዳቸው ወዳዘጋጀላቸው መልካሙ ጉረኖዋቸው አግብቶ ያጉራቸዋል፡፡ አውሬም እንዳያስደነግጣቸው ውሾች በስተውጭ ሆነው ይጮሁላቸዋል፡፡ ከአንዱ ግልገል በግ በቀር ሁሉም ጠባቂያቸውን ይወዱታል፡፡ ያ አንዱ ግልገል ግን ጠባቂውን አይወደውም ነበርና ማታ ማታ ወደ ጉረኖው መግባት አይፈልግም ነበር፡፡ አንድ ቀንም ወደ እናቱ ቀረበና፡- “እማዬ! እኛ ማታ ማታ የሚዘጋብን ለምንድነው? እነሆ ውሾቹ ሳይዘጋባቸው በደኅና ያድራሉ፤ አሁንም ማታ እናንተ ስትገቡ እኔ ተደብቄ ልቅርና በጨረቃ ብርሃን ከወዲያና ወዲህ እየሮጥሁ ልደር?” አላት፡፡ 

 እናቲቱም፡- “ልጄ ሆይ! አርፈህ ተቀመጥ፡፡ ጠባቂያችን እጅግ መልካም ሰው ነው፡፡ እርሱ እንዳዘዘን ውለን ብንገባ ይሻለናል፡፡ እምቢ ያልህ እንደሆነ ግን በራስህ ላይ ጥፋትን ታመጣለህ” አለችው፡፡
 ግልገሉም ይህን በሰማ ጊዜ፡- “እናቴ ሆይ! መልካም ምክር አልመከርሽኝም፡፡ እኔስ ያሰብሁትን ሳላደርገው አልቀርም” አላት፡፡

 ከዚህ በኋላ ጠባቂያቸው ማታ በጎቹን ሁሉ ነድቶ ወደ ቤት ሲመለስ ያ ግልገል ወደ ጉረኖው የገባ መስሎ በአጥር ተደብቆ ቀረ፡፡ ጠባቂውም ግልገሉ ቀድሞ የገባ መስሎት አጉሮባቸው ወደ ቤቱ ገባ፡፡
 ጊዜው ሲጨልምና በጎቹ ሁሉ ለጥ ብለው ሲተኙም ግልገሉ ከተደበቀበት ስፍራ እየሮጠ ወጣና ወደ ዱር ተመለሰ፡፡ በዚያም ወዲያና ወዲህ እየሮጠ ሲጫወት አንድ ተኩላ አይቶት ኑሮ በድንገት ደረሰበት፡፡ ግልገሉም ወደ ጉረኖው ለመሮጥ አሰበ፡፡ ሆኖም ሩቅ ስለነበረ የማይሆንለት ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ ተኩላው ታቅፎ ወስዶ ወደ ጕድጓዱ ውስጥ አግብቶ ገነጣጥሎ በላው፡፡

  አያሳዝንም ልጆች?! የአባትና የእናታቸውን ምክር የማይሰሙ ልጆችም እንዲህ ይሆናሉ፡፡ እናንተ ግን የወላጆቻችሁን ምክር ስሙ፡፡ እሺ ልጆች?

 በሉ በሌላ ጊዜ ሌላ ምክር ይዤላችሁ እስክመጣ ድረስ ደኅና ሰንብቱ እሺ! ደኅና ሁኑ፡፡
           (ምንጭ፡-ወዳጄ ልቤና ሌሎችም፣ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ)  

ለወላጆች
ፕሪንት ለማድረግ ከታች ያለውን Print/PDF የሚለውን ቁልፍ ይጫኑ!
ስለትብብርዎ እናመሰግናለን! 

No comments:

Post a Comment