Pages

Friday, July 19, 2013

ፈቃደ እግዚአብሔር- (ክፍል ሁለት)

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ በድጋሜ የተለጠፈ)፡- ባለፈው ዕትም ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመቀበል እንዳንችል ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንደኛውንና ‹‹ ክፉው ከእግዚአብሔር አይደለም›› የምንለውን የተሳሳተ ሀሳባችንን ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር ተመልክተን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ሁለተኛውን ብቻ እንመለከታለን፡፡

2) ‹‹ ክፉ›› የትኛው ነው?
ሁለተኛውና ከፈቃደ እግዚአብሔር በቀላሉ የሚለየን ነገር ደግሞ ‹‹ ክፉ›› ስለምንለው ነገር ያለን ግንዛቤ ነው፡፡ ለመሆኑ ክፉ ልንለው የሚገባው የትኛውን ነው? ክፉ ሰዎችስ እነማን ናቸው? ይህም ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና ከእግዚአብሔር እንዳያጣላን ልናስብበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በቅዱሳት መጻሕፍት ተደጋግሞ እንደተገለጸው ክፉ በሚሏቸው ሰዎችም ሆነ ድርጊቶች ብዙ የእምነት ልዩነት ይታያል፡፡ ለምሳሌ እሥራኤል በቀቲሎተ አምላክ የተሰማሙት ሰዎች  ጌታን ክፉ አድርገው ሰለሳሉላቸውና እነርሱም ስለተቀበሉት ነው፡፡ በዘመነ ቅዱስ ዳዊት ጊዜም እሥራኤል ከደገኛው ንጉሣቸው ከዳዊት ይልቅ ሸንጋዩን አቤሴሎምን ለመከተል የበቁት የማታለል ሥራውን የደግነት አድርገው ስለ ቆጠሩት ነው፡፡ ከእነዚህ ታሪኮች በቀላሉ ለመረዳት እንደምንችለው ‹‹ ክፉ›› የሚመስሉን ሰዎች ክፉ ላይሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖሩን ነው፡፡ ይህን በማድረጋችን ቢያንስ ከሁለት ታላላቅ ኃጣውእ ልንጠበቅ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ አትፍረዱ...›› ከሚለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትእዛዙ ከተላለፈበት ምክንያት ማለትም ጻድቁን ኃጥእ ኃጥኡንም ጻድቅ ከማለት እንድናለን፡፡ ‹‹ኀጥኡን የሚያጸድቅና በጻድቁ ላይ የሚፈርድ፥ ሁለቱ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው›› /ምሳ 1715/ ተብሎ ተጽፏልና፡፡  በዚህም ክፉ ያልሆነውን ክፉ በጎ ያልሆነውንም በጎ ከማለትና ከእግዚአብሔርም ፈቃድ ከመውጣት እንድናለን፡፡
ሌላውና መሠረታዊው ነገር ደግሞ በእኛ ላይ የሚደርሱትና ክፉ የሚመስሉን ነገሮች በርግጥ ክፉ ናቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ሕማምን፣ ረሃብንና ችግርን፣ ድርቅንና ስደትን፣ መታሠርንና መገፋትን፣ መደኸየትን፣ ከነበረን ክብር ማነስን፤ ... በተለምዶ ወይም ብዙ ጊዜ ክፉ አድርገን እንቆጥራቸዋለን፡፡ በርግጥ እነዚህና የመሳሰሉት ነገሮች ክፉ ናቸውን? አሁንም በእኛ ዘንድ ክፉ ተደርገው ሊቆጠሩ ቢችሉም በእግዚአብሔር ዘንድስ ክፉ ሊሆኑ ይችሉ ይሆንን? በርግጥ በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፍ ላይ እንዳየነው እግዚአብሔር ‹‹ ክፉ ነገሮችን የማመጣ እኔ ነኝ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ንግግሩ በእኛ ስሜት ለመናገር ነው እንጂ በእርሱ ዘንድ ክፉ ሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነዚያን ሁሉ ነገሮች በእኛ ላይ የሚያመጣው ከነፍስ ቁሳላችን ለመፈወስና  ከሚመጣብንም ከባድ ቅጣት ለማዳን ነው እንጂ ለመጉዳት አይደለም፡፡ለጊዜው ለእኛ ጉዳት ሆነው ቢሰሙንም ለእግዚአብሔር ግን አንደኛ ፍርዱ ትክክል ስለሆነና ስለማያዳላ የሚገባንን እንጂ ከሚገባን በላይ ስለማያመጣ እየጎዳን አይደለም፡፡ ሁለተኛም እንደተገለጸው እኛን ከስሕተቶቻችን ለመመለስ የሚያደርጋቸው ስለሆኑ የሚያስተምርባቸው እንጂ ለማማረር ያመጣቸው አይደሉምና ክፉ አይደሉም፡፡
በአንድ ወቅት በአንድ ገዳም የነበረ አባት ታምሞ በተኛ ጊዜ ከሌላው አባት የተላከለት መልእክት ፈቃደ እግዚአብሔርን የተረዱት ሀሳባቸው ምን እንደሆነ የሚያሳይ ድንቅ ነገር ነው፡፡ ያልታመመው አባት ለታመመው  ‹‹ ታምመህ በመተኛትህ ጤነኛ ብሆን ኖሮ ይህን ይህን እሠራ ነበር እያልክ አታስብ፡፡ ጤነኛ ሆነህ እግዚአብሔር እንድትሠራው ያልፈቀደልህን ከምትሠራ ታምመህ ፈቃዱን ብትፈጽም ይሻልሃልና፡፡ መታመመህ ፈቃዱ ከሆነ ቶሎ መዳንና መነሣት አለብኝ ማለትም አይገባህም፡፡ መታመምህ ፈቃዱ ሆኗልና›› በማለት ልኮለት ነበር፡፡ በርግጥም በእኛ ዘመን ብዙ ሰው ከእግዚአብሔር እየተለየ ወደ ባዕድ አምልኮዎችና ጠንቋዮች ወደ አታላይና ነጋዴ አጥማቂዎች ወይም በጥምቀት ሰብብ ብዙ ጥፋት ወደሚሠሩ አስመሳዮች እስከመሔድ የሚደርሰው መታመምን፣ ማጣትን፣ መዋረድን፣ መሻርን፣ በሰው ዘንድ ያለንን ክብር ማጣትንና የመሳሰሉትን እንደ ክፉ ብቻ  ተገላቢጦሹን ደግሞ እንደ በጎ ብቻ የመውሰድ አባዜ ስላለብን ነው፡፡ ከእነዚህ ስንላቀቅም ደስተኞችና እግዚአብሔርን አገልጋዮች የምንሆንም ይመስለናል፡፡ በእውነተኛው የክርስትና ሕይወት ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ማለት ለነፍሳችን ጥቅም ሊያገለግሉ የሚችሉትንና ምንአልባትም ሥጋችንን ግን ሊቆነጥጡ የሚችሉትን ጭምር በደስታ መቀበልን ያጠቃልላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ለእኛ መልካም እንዲሆንልን የተሰጡ ናቸውና፡፡ ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ከብዙ የስቃይ ዘመናት በኋላ  ከብሮና ተሹሞ ሳለ ልብሱን ገፍፈው ራቁቱን የሸጡት ወንድሞቹ ባገኙትና በድርጊታቸው አፍረውና ተሳቅቀው ባያቸው ጊዜ፦ ‹‹ ወደ እኔ ቅረቡ፤ ... ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና ››  /ዘፍ 45 4- 5/ በማለት የመለሰላቸው ክፉ የሚመስለን ሁሉ ክፉ እንዳልሆነ ያምን ስለነበረነና በተገግበባረርመም ስላረጋገጠ ነው፡፡
 ብዙዎቻችን ክፉ የምንለውና የሚመስለን ቢርቅ ደስተኞች የምንሆን ይመስለናል፡፡
ሁል ጊዜም ደስተኛ ሆኖ መኖር የሚፈልግ አንድ ሰው እንዲሁ መስሎት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር እንዲያደርግለትና ይህን እንዴት እንዲያስተምረውም አብዝቶ ይጸልይ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እግዚአብሔር ተገለጸና ደስተኛ መሆን የሚችልበትን ነገር መማር ይችል ዘንድ ወደ አንድ ገዳም መራው፡፡ ወደ ቦታው ሲደርስ ያስተምርሃል የተባለውን ሰው ተቀምጦ ሲለምን አገኘው፡፡ እንደ ደረሰም ወደ ለማኙ ጠጋ ብሎ ‹‹ መልካም ቀን ይሆንልህ ወንድሜ እንደምን ዋልክ?›› በማለት ሰላምታ ይሰጠዋል፡፡ ሰውየውም ‹‹ ስለመልካም ምኞትህ አመሰግናለሁ፤ ነገር ግን ክፉ ቀን የሚባልም አላውቅም፤ አላጋጠመኝምም›› ይለዋል፡፡ ከዚያ መመላለስ ቀጠሉ፡፡ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር ደስተኛ ሕይወትን በርግጠኝነት ሰጥቶሃላ›› ሲለው፤ ያም አባት  ‹‹ እውነት ነው፤ ደስተኛ ያልሆንኩበት ጊዜ የለም፡፡ ይህን ስል ዝም ብየ ተራ ነገር እየተናገርሁም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ምንም ምን የምበላው ባጣሁ ጊዜም ስለማጣቴ እግዚአብሔርን  አመሰግናለሁ፤ በዘነበ ወይም በረዶ በወረደ ጊዜም እንዲሁ አምላኬን አከብራለሁ፤ ሰዎች በሰደቡኝ፣ ባሳደዱኝ፣ ወይም ባመናጨቁኝ ጊዜም ለእግዚአብሔር ክብር እሰጣለሁ፡፡  ያልተደሰትኩበት ጊዜ የለም የምለውም በርግጥም ደስተኛ ስለሆንኩ ነው ይህም የሆነው እኔ የምፈልገው ባይሆንም እግዚአብሔር የፈቀደው እንዲሆን በሕይወቴ ስለተለማመድኩ ነው፡፡ መራራም ሆነ ጣፋጭ፤ ምንም ነገር ይግጠመኝ ለእኔ መልካም መሆኑን አምኜ ሁሉንም ከእጁ በደስታ እቀበላለሁ፡፡ ስለዚህም የማይወሰድ ደስታ ተሰጠኝ›› ሲል መለሰለት፡፡ ሊማር የመጣውም ሰው ‹‹ ይህን ሁሉ ያደርግልህ ዘንድ ፈጣሪን (እግዚአብሔርን) የት አገኘኸው?›› አለው፡፡ አባትም  ‹‹ ራሴን(ትኩረቴን) ከፍጥረታት  ስለይና ፈቃዴን ወደ ፈቃዱ ሳነሣ አገኘሁት›› አለው፡፡ በመልሱ እየተገረመ ያለው ይህ ሰው በመደነቅ ‹‹ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?›› ሲል ጥያቄውን ቀጠለ፡፡ አባትም በልበ ሙሉነት ‹‹ እኔ ንጉሥ ነኝ›› ሲል መለሰለት፡፡ ‹‹ግዛትህ የት ነው?›› ሲል እንደገና  እየተገረመ ጠየቀው፡፡ ‹‹ፈቲው ለእውቀት፣ እውቀትም ለፈጣሪ በሚገዙበትና ሁሉም ነገር በሥርዓት በሚኖርበት ከተማ በነፍሴ ላይ ነው›› ሲል መለሰ፡፡ በመጨረሻ  ፍጹምነት ላይ እንደደረሰ ስለተረዳ ‹‹ ወደዚህ ፍጹምነት እንዴት ልትደረስ ቻልከ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ አባትም ‹‹ በዝምታ፤ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገርን ባዘወተርኩ ጊዜ ከሰዎች ጋር በዝምታ መኖርን ተለማመድኩ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ደግሞ ነፍስን በሰላም የመጠበቂያ መንገድ መሆኑን ተረድቻለሁ›› በማለት መለሰለት፡፡ በዚህ ምልልስም ሰው ክፉ የሚመስሉን ነገሮች ሁሉ ክፉ አለመሆናቸውንና ከእኛ አስተሳሰብ ወይም የእምነት ጉደለት የተነሣ እንጂ ጎጂ የሚመስሉን ሁሉ ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ አውቆ የእውነተኛ ደስታ ምንጩም ይህን ተቀብሎ መኖር መሆኑን ተረድቶ ተመለሰ፡፡
 በርግጥም እኛ ደካሞች ነን፡፡ ‹‹ እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፥ ጌታ ግን ያስብልኛል›› /መዝ 40 17/ ተብሎ እንደተጻፈው እግዚአብሔር ግን ያስብልናል፤ ስለዚህም የሚጠቅመንን ነገር ያደርጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ልጁ አቤሴሎም ጦርነት በከፈተበትና በመንግሥቱ ላይ በተነሣበት ጊዜ ሸሽቶ ወደ ደብረ ዘይት ሲሻገር ሳሚ ወልደ ጌራ መንገድ ላይ ጠብቆ ሰደበው፡፡ ‹‹... በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፤ እግዚአብሔርም መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፡፡  እነሆም፥ አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል ... ››  እያለ ሲራገም ከንጉሡ ጋር የነበረው አቢሳ ‹‹  ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቍረጠው ›› ሲል ንጉሡን ጠየቀ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ግን ‹‹ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? አለ›› / 2 ሳሙ16 8 - 10 / ይላል፡፡ በርግጥ ንጉሡ ዳዊት እግዚአብሔር ለሳሚ ተገልጾ ሒድና ስደበው እንደማይል ያውቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ከፉና ውርደት የመሰለው ነገር ለእርሱ ጠቃሚ እንደሆነ ኃጢአቱን የሚያስተሠርይለት መሆኑንና እግዚአብሔር የእርሱን ትሕትናውንም እንደሚፈልገው ስለገባው መዋረዱን በደስታ ተቀበለው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሳሚ ተገልጦ አነጋግሮ አልላከውም፤ በሳሚ ተሳዳቢነትና በስሕተቱም ተሳታፊ አይደለም ማለት ነገሩን እግዚአብሔር ያልፈቀደው አያሰኘውምና ፡፡ በሠራዊቱ አባላት ዘንድ እንደ መደፈርና ከፉ የተወሰደው ስድብና ርግማን በዳዊት ኅሊና ለመልካም ነበረ፡፡ በርግጥም ለመልካም ሆነለት ፡፡ እንደ እምነትህ() ይደረግልህ() ማለት ይኸው ነውና፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን የሚገጥሙን መዋረድ የሚመስሉን፤ ስድቦች፤ ርግማኖች፣ መከራዎች፤ እስራትና ግርፋቶችም ለአንድ ክርስቲያን ክፉ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲያውም የድኅነት፣ የክብር፣ የጸጋና የዘላለማዊ ደስታ በሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‹‹ ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ›› /ሐዋ 541/ ተብሎ እንደተጻፈው ሐዋርያት በተገረፉ ጊዜ የተደሰቱት ክፉ የሚመስለን ሁሉ ክፉ ባይሆን ነው፡፡ እግዚአብሔርም ከመገረፍ ማዳን የማይችል ሆኖ ሳይሆን ሐዋርያቱ እንዳሉት ነገሩን መናቅ የተገባን ብለው ስለቆጠሩት ነው የተደሰቱት፡፡ አሁን በእኛ ዘመን ካለ ክርሲቲያን የማያጉረመርም ማን አለ? አንዲትን መከራ እንኳ ለመቀበልስ የሚፈቅድ ማን ነው? ለመሆኑ በእኛ ዘመን እግዚአብሔር የሚወዳቸው ብለን የምንናገርላቸው ሰዎች እነማን ናቸው? በሀብት ያልተምነሸነሸ፣ በኑሮው የማይቀማጠልን ሰው እግዚአብሔር ረዳህ እነለዋለንን? ለመሆኑ ከታመሙት ወይም ከታሠሩት ወይም ይህን የመሰለ ነገር ከሚቀበሉት እግዚአብሔር የሚወዳቸው ያሉ ይመስለን ይሆን? በርግጥ ይህ ሁሉ የገጠማቸው ጻድቅና ፍርድ ወይም መከራ የመማይገባቸው ናቸው ማለት አይደለም፡፡ መከራዎቹና ፈተናዎቹ በሠራናቸው ስሕተቶች ያለ ስሕተታችንም ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡ በሁለቱም መንገዶች ላለነው ክፉዎች አይሆኑም፡፡ በርግጥም ለምንቀበለው መከራ የሚያበቃ ኅጢአትና በደል ፈጽመንም ከሆነ መከራው ለንስሐ፤ ለሥርየትና ለድኅነት ይሆንልናል፡፡ ባልፈጸምነውም ከሆነ ለክብርና ለጸጋ ይሆንልናል፡፡ ሁለቱንም ማግኘት የሚቻለው ግን ስሕተት ያልሠራው እንደ ዮሴፍ እንደ ዳዊት ለበጎ አድርጎ ሲቀበለው የበደልነው ደግሞ እንደ ፈያታዊ ዘየማን  ለእኛስ በጥፋታችን ነው ይገባናል ማለት ስንችል ነው፡፡ የማንቀበለው ከሆነ በግራ እንደተሰቀለው ሽፍታ መከራውንም ኩነኔውንም እንቀበላለን እንጂ ስለጠላነው ብቻ አይቀርልንም፡፡  አሁን አሁን እኮ ሌላው ቀርቶ ሰዎችን እግዚአብሔር ባረካቸው የሚባልላቸው በመኪና ላይ መኪና፣ በቤት ላይ ቤት፣ በሀብት ላይ ሀብት ሲያገኙ እየሆነ ብቻ ነው፡፡ በርግጥ እንዲህ ዓይነት ነገሮችም ከመባረክ የተነሣ ሊገኙ ይችላሉ፤ ከአሁን በፊትም በዚህ የተባረኩ ነበሩ፤ አሁንም የሚባረክላቸው ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ምድራዊ ሀብትና ሹመት የበረከት መለኪያ ተደርገው ማስተማሪያዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡  እኛም በመንፈሳዊ ዕውቀትም ሆነ ሕይወት ወርደን ወርደን  እዚህ ደረጃ የደረስነው ‹‹ ከፉ›› የሚመስሉን ነገሮች ውስጥ መልካም ነገር መኖሩን እየተቀበሉ ከመኖር ስለወጣንና ፈቃደ እግዚአብሔርንም በተሳሳተ መንገድ የምንተረጉም ስለሆነ ነው፡፡
(ይቆየን፤ ይቀጥላል፡፡)
*** © ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን ብራሃኑ አድማስ የምጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡


No comments:

Post a Comment