Pages

Monday, August 5, 2013

ፈቃደ እግዚአብሔር፤ ክፍል አራት (የመጨረሻው ክፍል)

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ሐምሌ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም.)፡- የእግዚአብሔርን ፈቃድ በምን አውቃለሁ? የሚለው ጥያቄ በራሱ በእኛ ውስጥ የተለየ ምልክት መሻት መኖሩን ያመለክታል፡፡ ይህን ዐይነት ምልክትን የመሻት አካሔድ ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ባለፈው ጊዜ በሦስተኛው ክፍል ጽሑፍ አይተን ነበር፡፡ ለቅዱሳን የሚደረገው መገለጥ ራሱ ቅዱሳን ራሳቸውን ክደው ሙሉ በሙሉ ማንነታቸውን ለእግዚአብሔር ስለሰጡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ማለትም መጻኢው ቀድሞ በእነርሱ የሚገለጸው የደረሱበትን መዓርግ ለማሳየት ነው እንጂ በእያንዳንዱ ነገር ላይ ምልክትን እየሻቱ ያም እየተደረገላቸው አይደለም፡፡ ታዲያ እኛ ኃጥአኑና ደካሞቹ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ይህን ጥያቄ ለመረዳት አስቀድመን ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር ሦስት መሠረታዊ ነጥቦችን እንመለከታለን፡፡


) የእግዚአብሔር ፈቃድ በራሱ ሁለት ዓይነት ነው፡፡

 የመጀመሪያውና ዋናው እግዚአብሔር ለፍጥረቱ በአጠቃላይ ሊታይ የሚችለውና ስለሁላችን ያለው ፈቃድ ነው፡፡ ይህንንም ‹‹ ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው ›› / ዮሐ 6 ፤ 40/ ሲል በወንጌል ገልጾልናል፡፡ ከነገረ ድኅነት ጋር ባናያይዘውም እግዚአብሔር በዓለም ያለው ፈቃድ የሁላችንም ደኅንነት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን የፐርሻውያን ትልቅ ከተማ ወደነበረችው ወደ ነነዌ ነቢዩ ዮናስን ከላከው በትምህርቱ አምነውና ጾመው ከዳኑ በኋላ ነቢዩ ዮናስ ሲቆጣ በመጀመሪያ እግዚአብሔር አንዲት ቅል አብቅሎ መጠለያ በመስጠትና በማስጠለል ደስ አሰኘው፡፡ ነገር ግን ወዲያውኑ በማድረቅ ደግሞ አበሳጨው፡፡ ዮናስም በሐዘንና በንዴት ሆኖ እግዚአብሔር ለምን ይህን እንደሚያደርግ ሲጠይቀው ‹‹ እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን? አለው›› /ዮና 4፤11/ ተብሎ እንደተጻፈው እግዚአብሔር በሕግ በአምልኮ ለማይኖሩ ሕዝቦች እንኳ ፈቃዱ ሁልጊዜም መዳናቸው ብቻ ነው፡፡ ቢቻልና የእግዚአብሔር መንግሥት ቢሰበክላቸው በነፍሳቸውም ቢድኑ ደስ ይለዋል፤ ካልሆነ ከመቅሰፍትና ከጥፋት ቢድኑም ደስ ይለዋል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ለየትኞቹም ሰዎች ያለው ፈቃድ መዳናቸው መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ላይ እግዚአብሔር ያደርገው ዘንድ ዮናስ ይፈልገው የነበረው ከእግዚአብሔር ፈቃድ ምን ያህል የራቀ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

ሁለተኛው ፈቃዱም ለእያንዳንዳችን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ያለው ፈቃዱ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ድኅነታችንን የሚያስቀድም ነው፡፡ ድኅነታችን የሚያስቀድም ነው የሚባለውም መከራ፣ ስደት፤ እስራና ሞትም ጭምር እንኳ እንዲመጣ ፈቃዱ ቢሆን በእኛ በሚደርሰው የሚደሰት ሆኖ ሳይሆን ከዚያ ነፍሳችን ልታጭደው የሚገባውን ምሕረትና ይቅርታ ወይም ማስተዋል በማሰብ ነው፡፡ ‹‹ አካዝያስም ወደ ኢዮራም በመምጣቱ ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረ ›› /2ኛ ዜና 22 ፤ 7/ ወይም ‹‹ የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረና›› / 2ኛ ዜና 25 ፤ 20/ ተብሎ እንደተጻፈው እግዚአብሔር ሰዎችን ለመቅጣትም ሆነ ለማጥፋት ፈቃዱ የሚሆንበት ጊዜ አለው፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ቀደም ብለን ባየነው አጠቃላዩንና ዋናውን የእግዚአብሔር ፈቃድ በመቃወም የሚሠሩትን አስወግዶ አብዛኞቹን ለማዳን ፈቃዱ ስለሚሆን ነው፡፡በታሪክ እንደ ታየው እንደ ዘመነ ኖኅ ሰዎች የጎሰቆለውን ሁሉ አስወግዶ አዲስ ትውልድ ያስነሣል፤ እሥራኤልንም ብትንትናቸውን አውጥቶ ለሁለት ሺሕ ዘመን ያለ ሀገር ያኖራቸው እነርሱን ለመበቀልና በጥፋታቸውም ስለሚደሰት ብቻ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ እንዲህ ያደረጋቸው ‹‹ ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን›› ብለው በራሰቸው ላይ ፈርደው ወድደው ፈቅደው መከራውን ራሳቸው ስለጠሩት ነው፡፡ ዳግመኛም እነርሱ ከዚያች ምድር ባይርቁ ኖሮ የክርስትና ተአምራት የተፈጸመባቸውን ቦታዎች ሁሉ አጥፍተው ሐዋርያትንም ገድለው ክርስትናን ሐሰት ለማስመሰል ይጥሩ ነበር፡፡ ቅዱስ ያዕቆብን አስገድለው እስጢፋኖስን ወግረው ገድለው ቅዱስ ጴጥሮስን ሊጨምሩ ሲሉ መልአኩ በሌሊት አጠፋው /ሐዋ 12/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስንም ሳንገድል አንበላም ብለው ተማምለው ሳሉ እርሱ የሮም ዜግነት ስለነበረው ገዢው ፈርቶ ወደ ሮማ ላከውና በጥበበ እግዚአብሔር ተረፈ፡፡ ሌሎች ብዙዎችንም ገድለዋል፡፡ ስለዚህም ጌታ እርሱ ባወቀ በራሳቸው ላይ የፈረዱትን ፍርድ ተቀብሎ አጠፋቸው፤ በታተናቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ያውና እስከዛሬ ድረስ ተአምራቱ የተፈጸመባቸው ቦታዎች እየተጎበኙ ዓለምም ላይ ክርስትና እንዲሠፋ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖአል፡፡ ስለዚህ መሰደዳቸውና መጥፋታቸው ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎም ከኢየሩሳሌም እስከ ሰፔንና ፖርቱጋል ከሰሜን አውሮፓ እስከ ሰሜን አፈሪካ ድረስ ተንሠራፍቶ የነበረው የሮም ግዛትም እንዲህ እንዲሆን እግዚአብሔር የፈቀደው በጊዜው ክርስትናን ለማስፋት እንዲያገለግል ነበር፡፡ ስለዚህ በተናጠል ለእያንዳንዳችን ያለው ፈቃዱም ምንም ዓይነት ቢሆን ለሰው ልጅና ለዓለማችን ጥቅም ካለው ፈቃዱ የማይቃረንና ሁልጊዜም ፍጹም መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

ለ) የእግዚአብሔር ፈቃድ አይለዋወጥም፡፡

ለእግዚአብሔር ለባሕርዩ ለውጥ አይስማማውም፡፡ የሚለወጥ አምላክ አይደለም፡፡ /ሚል 3፤ 6/ ከዚህ ባሕርዩ የተነሣም ፈቃዱ አይለወጥም፡፡ ምክንያቱም ካለማወቅ ወደ ማወቅ የሚያደርሰውና ፈቃዱን ሊያስለውጠው የሚችል ምንም የለምና፡፡ ፍርዱ የተለወጠ ቢመስል እንኳ ፈቃዱ የሚለወጥ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቀደም ብለን በገለጽነው በነነዌ ሰዎች ታሪክ ውስጥ ነቢዩ ዮናስን ‹‹ ነነዌ እስከ ሦስት ቀን ትገለበጣለች›› እያለ እንዲያስተምር ልኮታል፡፡ ነገር ግን ቶሎ በምሕረት አይቷቸዋል፡፡ ይህ የሆነው ፈቃዱ ጥንቱንም መዳናቸው ስለነበረ ነው እንጂ የሚሆነውን ሳያውቅ ከወሰነ በኋላ እንደሚጸጸት ግለሰብ የሆነ አይደለም፡፡ የንጉሥ ሕዝቅያስን ትሞታለህ ካለው በኋላ ዕድሜውን በ 15 ዓመት ጨምሮለታል፡፡ ይህ እንዲሆን ቀድሞ ፈቃዱ ነበረ፤ ነገር ግን ይምረውና ዕድሜ ይጨምረው ዘንድ እውነተኛ ንስሐ መግባት እንዲችል ነበር ‹‹ ትሞታለህ እንጂ አትድንም›› ሲል የላከበት፡፡ በርግጥ እንዲሞት ብቻ ቢፈልግ ኖሮ ሳይልክበት ይገድለው ነበርና፡፡ ስለዚህ እነዚህን የመሰሉና  ለእግዚአብሔር ተጸጸተ ተብሎ እንኳን ብናነብ የውሳኔ ለውጥ የሚመስሉን ነገሮች ሁሉ ጥንቱን እንዲያ እንዲሆን ለመርዳት የተደረጉ በመሆናቸው የፈቃድ ለውጥ የሚባሉ አይደሉም፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነውም እንዲያውም ዋናውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ድኅነትን  ቀዳሚ ያደረገ መሆኑን የሚያረጋጡ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለዕብራውያን ሰዎች በላከው መልእክት ‹‹ ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤ ›› / ዕብ 6፥17-18/ ሲል ያረጋገጠልን ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ በሕዝቅያስ፣ በነነዌ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር የተላከባቸው መልእክት ሞት ሊያመጣ የሚችል ኃጢአት መሥራታቸውን አውቀውና ንስሐ ገብተው እንዲድኑ  ፈቃዱ ስለነበረ እንጂ ፈቃዱ ተለዋዋጭ ስለሆነ አይደለም፡፡ ነገሮች እንዲለዋወጡ መፍቀዱ የራሱ ፈቃድ መለዋወጥ አይደለምና፡፡

ሐ) ስለነገ ማወቅ ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት አይደለም፡፡

ብዙዎቻችን ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ አድረገን የምንወስደው ስለነገ ሕይዎታችን ቀድሞ ቢያሳውቀን ብለን የምናስበውን ነገር ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሚገለጽላቸው ሰዎች ነቢያት ይባላሉ፡፡ አንድን ነገር ከመደረጉ በፊት እግዚአብሔር ነገሩን አስቀድሞ ገልጾላቸዋልና፡፡ ምንም እንኳ ነቢያት ፈቃደ እግዚአብሔርን ቢያውቁም የሚሆነውን ማወቅ ግን ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ለምሳሌ ነገሩ ለመደረጉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆንም  ቀድሞ ማወቅ ቀድሞ ማወቅ ብቻ እንጂ ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ ሊሆን አይችልም፡፡ በርግጥ ቀድሞ ማወቅ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ አስተዋጽኦ የለውም ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ቀድመው አውቀውም ፈቃደ እግዚአብሔርን ረስተው ወይም ጠልተው የሚጠፉ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ይሁዳ የእግዚአብሔርን የሥጋዌ ዓላማ ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ራሱን ለማዳን ግን አልቻለም፡፡ እንዲያውም ጌታን አሳልፎ የሚሰጥ ባይወለድ ይሻለው ነበር ሲባል ሁሉ ነበረ፤ ይህን ሁሉ ማወቁ ግን ራሱን ከፈቃደ እግዚአብሔር ጋር አንድ እንዲያደርግ አልረዳውም፡፡ ለጌታችን ሞቱ በፈቃዱ የተደረገ ቢሆንም ይሁዳ አሳልፎ የሰጠው ሊቃነ ካህናትም የሰቀሉት ዓለሙን ያድን ብለው ስላልሆነ ከፈቃደ እግዚአብሔር በተቃራኒው እንዳሉ ለመረዳት አያዳግትም ፡፡ ስለዚህ መጻኢውን ማወቅ ሁሉ ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅና በዚያም መኖር ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ይህ የሚሆነውም ስለ ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ጭምር ነው፡፡ የመጀመሪያው የሚሆነው ነገር ሁሉ አስቀድሞ ሊታወቅ ቢችልም የተወሰነበትና እንዲሆን እግዚአብሔር አድራጊውን የሚያስገድድበት ስላልሆነ ነው፡፡ ይህም ቀደም ብለን ባየናቸው ክፍሎች ውስጥ ተደጋግሞ እንደተገለጸው እግዚአብሔር የክፉዎችን ክፋት ባይወድም ያሰቡትን ከማድረግ ወይም ነጻ ፈቃዳቸውን ከማድረግ አይከልክላቸውም፡፡ ስለዚህ ነገሩ የሚፈጸም መሆኑን ቀድሞ ቢገልጸው ደርጊቱ መፈጸሙን ይወድዳል ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ተጎጂ የምንለው አካል የእግዚአብሔር ፈቃዱ ነው ብሎ ተቀብሎ ከዚያ በረከትን ማጨድ ይችላል፡፡ሁለተኛው ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለው ውሕደት የሚመሠረተው እኛ ትእዛዙን ለመፈጸም በምናደርገው ፈቃደኝነት ላይ እንጂ መጻኢውን ለማወቅ በምናደርገው ሩጫ ላይ ስላልሆነ ነው፡፡

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር እንዴት እንችላለን?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ካስተማራቸው መሠረታዊ ትምህርቶች ውስጥ በፈቃደ እግዚአብሔር መኖር ምን እንደሆነ ያስተማረው አንዱ ነው፡፡ ‹‹ ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ፡፡ ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው፡፡ እርሱም መልሶ፦ አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ፡፡ ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል ›› /ማቴ 21 ፤ 28 - 31/ ሲል አይሁድን በምሳሌ ያስተማረው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተሸክመው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስለሚቃወሙ ነበር፡፡ በጥቅሱ ከተገለጸው እንደምንረዳው የእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታ እንዳለው ቀራጮችና ጋለሞቶች ለጊዜው ባይቀበሉትም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ኅሊናቸው ይታዘዛል፤ ስለዚህም ቃሉን ከምናውቀውና በነገር ከምንራቀቀው ሁሉ ቀድመው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ይገባሉ፡፡ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም›› /ማቴ 7፤21/ ‹‹ ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም ›› /ማቴ 10 ፤ 29/ ‹‹ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ›› /ማቴ 12 ፤ 50/ የሚሉት ጥቅሶችም ጌታችንን ፈቃዱን አውቀን እየፈጸምን እንድንኖር የሚሻ መሆኑን ደጋግሞ ከገለጸባቸው ትምህርቶቹ ውስጥ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ታዲያ ፈቃዱን እንዴት ልንፈጽም እንችላለን?

1) ፍቅረ እግዚአብሔርን ገንዘብ ስናደርግ

የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመረዳት እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ በፍጹም ኃይልና በሁለንተና መውደድ ይጠይቃል፡፡  እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ደግሞ የእግዚአብሔር ለሆነው ሁሉ ክብርና ፍቅር ይሰጣል፡፡ ፍቅርም ማለት ፍቅሩ አለን በሚሉ አካላት መካከል የፈቃድ ስምምነት ላይ መድረስ ወይም የአንዱን ፈቃድ አንዱ መቀበል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ፈቃደ እግዚአብሔርን ወደ መረዳት ልደግ ካለ የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ እየፈጸመ መኖር የመጀመሪያው ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ ‹‹ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቅ›› ነው ያለው፡፡ ቃሉን ሲጠብቅ በፍቅርና በመታዘዝ ከሆነ የራሱን ፈቃድ መተው ይለምዳል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ ጠላታችሁን ውደዱ›› የሚለውን ቃል ቀርቶ ‹‹ ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ›› ከሚለውና በምስጢር ባይራራቁም ከዚህ ወዳጅን እንደ ራስ አድርጎ ከመውደድ እንጀምረው ብንል እንኳ ምን ያህል በውስጣችን ያሉ ፍላጎቶችን መተው እንዳለብን መረዳት እንችላለን፡፡ ቢያንስ በዚህ መንገድ የምንጓዝ ከሆነ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመረዳት መንገዱን ጀምረነዋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ፈቃደ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ  ጠንቋይ እንደሚያደርገው በዝርዝርና በየዕለቱ የሚነገረን ነገር አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው በጎውም ይሁን ክፉ የሚመስለን ነገር ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለን ለማመን የምንችለው በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን ለመፈጸም ሰንጣጣር ነው፡፡ ካልሆነ ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው ›› /ያዕ 1 ፤ 26/ ሲል እንደገለጸው አምልኮታችን ሁሉ የእልህና የጥላቻ ይሆንብናል፡፡ የፈለገ ያህል ለእግዚአብሔር ቀንተን ነው ብንል የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እየተላለፍንና በራሳችን መሻት መሠረት ብቻ የምናደርገውን ሁሉ እኛ አምልኮት ስላልነው እግዚአብሔር ይቀበለዋል ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር መጀመሪያ የሚፈልገው ትዕዛዙን እንድንጠብቅለት ነው፡፡ ሌሎቹን በጉልበታችን ልናስጠብቃቸው አንችልም፡፡ አሁን ችግር የሆነው እኛ የማንሽረውን የሻሩ የመሰሉንን ሰዎች አሻግረን እያየን በመበሳጨታችን ብቻ እግዚአብሔር ያን ጊዜ ያለንን ቅንዓታችንን አይቶ ለምን አይሰማንም ማለታችን ነው፡፡ አይሁድ ጌታችን በሚያሰተምርበት ጊዜ መጥተው እናትህና ወንድሞችህ በውጭ ቆመዋል ብለው በመናገራቸውም ለእርሱ የሚያስቡና የሚያስደስተውም ይመስላቸው እንደነበረው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ለእርሱ የሚያስቡ እንኳ ቢሆኑ ይህን የሚያውቀው እነርሱ ስለነገሩት አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ወዳጅና ባለሟል መሆን የሚቻለውም ቃሉን በመስማትና ትእዛዙን በመጠበቅ እንጂ ለእርሱ ያሰቡ መስሎ በመኖር አይደለም፡፡ ስለዚህ ከእኛ መጀመሪያ የሚጠበቀው ቃለ እግዚአብሔርን እየሰሙ በፍቅረ እግዚአብሔር መኖር ነው፡፡

2) ተነሣሒ መሆን

‹‹ እግዚአብሔርን የሚፈራ ፈቃዱንም የሚያደርግ ቢኖር ያንን እግዚአብሔር ይሰማዋል እንጂ ኃጢአተኞችን እንዳይሰማ እናውቃለን›› /ዮሐ 9 ፤ 31/ ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደተገለጸው እግዚአብሔር የኃጥአንን ጸሎት አይሰማም፡፡ ይህም የተባለው ኃጢአተኞችን ስለሚጠላ ሳይሆን ተነሳሒነትን ስለሚሻ ነው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ይበላል ተብሎ እስኪከሰስ ድረስ እነርሱን አይወድም ነበረ፡፡ ከእነርሱም ጋር የሆነው ግን በተነሣሒነታቸውና ትእዛዙን ለመጠበቅ ባሳዩት ፈቃድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይህ ነውና፡፡ ሳምራዊቷን ሴት ሲያስተምርና ሲፈውስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ከተማ ሔደው  ነበር፡፡ ሲመለሱ ምግብ ገዝተው ብላ ሲሉት አልበላም አላቸው ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነርሱ ሐሳብ የሚበላውን ሌላ ሰው አምጥቶለት ይሆናል ነበረ፡፡ እርሱም ይህን ሀሳባቸውን ባወቀ ጊዜ ‹‹ የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው ›› / ዮሐ 4 ፤ 34/ ሲል መለሰላቸው፡፡ እግዚአብሔር ፈቃዱን‹‹ ምግቤ›› ሲል የጠራው ፈቃዱ ተነሣሒነት ከዚያም በኋላ ድኅነታችን ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በዚህ ምድር የምንኖር ኃጥአን ፈቃዱን መረዳትና እንደ ፈቃዱ መኖር ከፈለግን የመጀመሪያው እርምጃ ሁሌም ተነሣሒ ሆኖ መኖር ነው፡፡ ከንስሐና ከመልካም ሥራ የተለየ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሊያውቅ የሚችልበት ምንም መንገድ የለውም ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ ›› / ሮሜ 12፤ 2/ የሚለው የእግዚአብሔር ፈቃዱ መለወጣችን ስለሆነና ባልተለወጠ ሰውነትም ፈቃደ እግዚአብሔርን መረዳት ስለማንችል ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ላይ ያለው ፈቃዱ ምንድን ነው የሚል ሰው ቢኖር በእውነት ንስሐ ይግባ፤ የእግዚአብሔር ትልቁና የመጀመሪያው ፈቃዱ ንስሐ መግባታችንና መዳናችን ነው፡፡ ይህ መሆን እስከቻለ ድረስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ያለውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ለመረዳትም ሆነ ለመቀበል አይቸግረንም፡፡
ለምሳሌ ያህል ብዙ ወጣቶችን በአሁኑ ጊዜ እያስጨነቀ የሚገኘው የማንን ላግባ ጥያቄ መልሱ የሚገኘው በምልክትና በራዕይ አይደለም፡፡ ብዙዎች በዚህ ጥያቄ የሚታወኩት ራሱ በተሳሳቱ አስተሳሰቦች ላይ ተመሥርተው ስለሚሔዱ ነው፡፡ ከእነዚህ የመጀመሪያው ራስን የእግዚአብሔር ሳያደርጉ የእግዚአብሔርን ሰው መሻት ነው፡፡ እግዚአብሔር በምሪት ያገኛኛቸውን የብሉይ ኪዳን አባቶች ታሪክ እንኳ ብናየው እግዚአብሔር እንዲያገናኛቸው ምክንያት የሆነው ሁለቱም የእግዚአብሔር በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ርብቃ ለይስሐቅ /ዘፍ 24/ ሣራ ወለተ ራጉኤል ለጦብያ ወልደ ጦቢት የተዘጋጁበትን መንገድ እግዚአብሔር የራሱን ሰዎች እንዴት በሁሉ ነገር እንደሚመራና እንደሚጠብቅ መመልከት እንችላለን፡፡ ራሱን በንስሐ ሕይወት ሳያኖርና እንደ ቃሉ መመላለስ የማይወድ ሰው ከእግዚአብሔር በመጠየቁ ብቻ ምን ሊያገኝ ይችላል? ራሱን በሌላ ዓለም የሚያኖር ሰው መልአክ የመሰሉ ሰዎችን በመሻቱ ብቻ እንዴት እግዚአብሔር ሊሰማው ይችላል? እግዚአብሔር መልአክ የመሰለ ሰው እንዲሰጠው የሚፈልግ ራሱን መልአክ ማድረግ እንኳ ባይችል ቢያንስ ራሱን ከመልአክ ጋር ለመኖር የሚችል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በአጭሩ የእግዚአብሔርን የሚሻ ሁሉ ራሱን የእግዚአብሔር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ የሚቻለው በንስሐ በመለወጥና እንደ ቃለ እግዚአብሔር በመኖር ብቻ ነው፡፡

3) ምልክት አለመሻት

የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም በሕይወታችን ለአንድ ወይም በጣም ለትንሽ ወሳኝ ጉዳዮች ብቻ የምንፈልገው አይደለም፡፡ አንዱና መሠረታዊ ስሕተታችንም ፈቃደ እግዚአብሔርን ለኑሮአችን ወይም ለሕይወታችን በየዕለቱ የምንፈልገው ሳይሆን ለአጽድቆተ ነገር ብቻ የምንሻው ምልክት መሆኑ ነው፡፡ ጌታ በወንጌል ‹‹ የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል ›› /ሉቃ 12 ፤47/ ሲል ያስተማረው ፈቃደ እግዚአብሔር በማንኛውም ሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔር ሲፈልገው ሊያገኘው የሚገባ ነገር ስለሆነ ነበር፡፡ የዘወትርና የማንኛውም ጸሎታችን ማሳረጊያ በሆነው የአባታችን ሆይ ጸሎት ውስጥ ‹‹ ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነ እንዲሁም በምድር ይሁን›› እያልን እንድንጸልይ ያሰማረን በየዕለቱ ፈቃዱን እየሻን በዚያ መሠረት እንድንጓዝ ነበረ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም ›› /ዮሐ 1 ፤13 / ሲል የገለጸው በእኛ ወይም በዚህ ዓለም ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ እንድንኖር መንፈሳዊ ልደት መወለዳችንን ለማሳየት ነበር፡፡ ምክንያቱም ፈቃዱን አንድ የምንፈልገው ነገር መደረጉን በሆነ መንገድ ወይም ምልክት ለማረጋግጥ የምንሻው ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በሕይወታችን የምንሻው ወይም ልንሻው የሚገባን ነገር በመሆኑ ነው፡፡ ያ ከሆነ ከመደበኛ ዕቅዳችን ውስጥ የገጠመንን ሥራ አለቃችን አውቆ እንዲያጸድቅልን የምንፈልግበትን ነገር ይመስልብናል፡፡ እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ለፈቃደ እግዚአብሔር ምንም የተለየ ምልክት አያስፈልገንም ማለት ነው፡፡ ራሱ ጌታችን ሁሉን እያወቀ ራሱን ስለሁላችን አሳልፎ ሊሰጥ በቀረበባት ሰዓት ‹‹ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ›› /ሉቃ 22 ፤ 42/ ሲል የጸለየው ምን እንደሚሆን ስለማያውቅ ወይም ሞቱን ፈርቶትና ተሰቅቆት ሳይሆን የታወቀ ነገር እንኳ ቢሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጸሎት እየጠየቁ መቀበል ተገቢ ነው ለማለት ወይም እኛ ምን ማድረግ እንዳለብን አብነት ለመሆን ነው፡፡ እንዲያውም ከዚህም አለፍ ብሎ ‹‹ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና ›› /ዮሐ 6 ፤38/ በማለት ያለ አብ በራሴ ( ማለትም በሦስትነት ያለ ቢሆንም ፈቃድ የአንድነት ነውና) አላደርግሁም ብሎ አርዓያነቱን ይገልጽልናል፡፡ እኛ እርሱን እንድንመስል የተጠራነው ደግሞ የራሳችን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ እንድንፈጽም ነው፡፡

በሕይወታችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየተለማመድንና እርሱንም ለማድረግ የምንሻ ከሆነ ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅም ሆነ ለመቀበል አንቸገርም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ነንና ፈቃዱን እየጠየቅን በቃሉም እየኖርን መልካም ይሆናል ብለን የምናስበውን ከሠራን በኋላ የሚሆነውን ሁሉ ለመቀበል አንቸገርም፡፡‹‹ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን›› /ሐዋ 21 ፤14/ የሚለውም ቃል የእግዚብሔርን ፈቃድ ቀድሞ በምልክት ማወቅ ሳይሆን እየጸለዩና በቃለ መጻሕፍት መሠረት እየኖሩ የሆነውን መቀበል ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በገሐድ ስሙን እየጠራ ያናገረው ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንኳ ‹‹ ምናልባት ብዙ ቆይቼ ወደ እናንተ አሁን እንድመጣ በእግዚአብሔር ፈቃድ መንገዴን እንዲያቀናልኝ እየለመንሁ ሁልጊዜ ስጸልይ ስለ እናንተ ሳላቋርጥ አሳስባለሁ ›› / ሮሜ 1 ፤ 10/ ሲል የጻፈላቸው እርሱ እንኳ ፈቃዱ እንዲሆን እየጠየቀ በየዕለቱ ከመጸለይ ውጭ የተለየ ምልክትን ይሻበት እንዳልነበር ያስረዳናል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ›› /ሮሜ 8 ፤5/ የሚለን ስለ ፈቃደ እግዚአብሔር በመንፈስ መረዳት የምንችለው መጀመሪያውኑ ኑሮአችን በመንፈስ ሲቃኝ እንደሆነ ለማስረገጥ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ‹‹ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ ›› / ኤፌ 5፤ 17/ ‹‹ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ ›› /ኤፌ 6 ፤ 6/ ሲል አጠንክሮ ይመክረናል፡፡ ስለዚህ በምልክትና በመሳሰሉት ነገሮች ሳንወሰን በሕይወታችን ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመለማመድና ለመኖር ያብቃን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡ ተፈጸመ፡፡

© ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ የምጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment