Tuesday, August 20, 2013

ሥጋ ሥጋት ሲኾን

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ከኢትዮጵያ ውጭ ለመኖር በኹኔታዎች ተገድዶ ወደ ጀርመን የሔደ አንድ ወንድማችን በሚኖርበት ሀገር እጅግ በሽተኛ ኾኖ ይቸገራል፡፡ ጾም አይጾም፤ ምግብ አይመርጥ የነበረው ሰው የፈለገውን ቢያደርግም ለጤናው ሽሎት ያጣል፡፡ በሚኖርበት ሀገር በሕክምና ዕውቀት በጣም ያደገ ስለነበር እጅግ ብዙ ሙከራዎችን ቢያደርግም ተስፋ ያጣል፡፡ በመጨረሻ በአመጋገብ ብቻ ሕክምና ወደምታደርግ ስፔሻሊስት ሐኪም ይላካል፡፡ ሐኪሟም የበሽተኛውን የሕማም ታሪክ ጊዜ ወስዳ በተደጋጋሚ ካጠናች በኋላ ሕክምናውን ለመጀመር ኹለት ዝርዝሮች አዘጋጅታ ጠበቀችው፡፡ ከዝርዝሮቹ አንደኛው ሊመገባቸው የሚገባውን የምግብ ዐይነቶች የያዘ ሲኾን ኹለተኛው ደግሞ ሊመገባቸው የማይገባውን የያዘ ነበር፡፡ ዝርዝሩን ይዞ ወደ ቤቱ በመሔድ በትእዛዙ መሠረት መዳኑን እየተጠባበቀ መመገብ ጀመረ፡፡ ለውጡን በመጠኑ እያየ ደስ እያለው ሳለ እንዲበላቸው የታዘዛቸው ምግቦች ቀደም ብሎ በብዛት ከሚመገባቸው የተለዩ ስለነበሩና ቀድሞ በብዛት ይመገባቸው የነበሩት ደግሞ ከተከለከላቸው ውስጥ ስለነበሩ ኹኔታዉን ደጋግሞ ሲመለከት አንድ ነገር ይከሰትለታል፡፡ የተከለከላቸው ምግቦች በሙሉ ሲያያቸው በሀገር ቤት በፍስክ የሚበሉት ሲኾኑ እንዲመገባቸው የታዘዙለት ደግሞ በሙሉ የጾም ምግብ ከሚባሉት ኾነው ያገኛቸዋል፡፡ በኹኔታው በጣም ከተገረመ በኋላ “የጾም ምግብ ለጤና ተስማሚ ከኾነ ለምን አልጾምም?” ይልና ፈጽሞ ረስቶት የነበረውን ጾም ድንገት በሰኔው የሐዋርያት ጾም ይጀምራል፡፡ ልክ አንድ ሳምንት ከጾመ በኋላ ኹል ጊዜም እንደሚያደርገው ለክትትል ወደ ሐኪሙ ያመራል፡፡ የላባራቶሪ ውጤቶቹ ሲመጡ በተለይ እነ ደም ግፊት፣ ስኳርና የመሳሰሉት በሽታዎች በከፍተኛ ኹኔታ ቀንሰዋል፡፡

 ሐኪሟ ከጠበቀችው በከፍተኛ ፍጥነት ቀንሰው በማግኘቷ ግራ ተጋብታ “የተለየ ነገር ያደረግከው አለ ወይ?” ስትል ጠየቀችው፡፡ በሽተኛውም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሥርዓት ጾም ምን እንደኾነ ከገለጸ በኋላ እንዲመገብ ያዘዘችለት ምግብ በሙሉ የጾም ምግብ ኾኖ ስላገኘው ጾም መጀመሩን ይነግራታል፡፡ ሐኪሟም ደንገጥ ትልና “እኔኮ ያዘዝኩህ እነዚህን ብቻ እንድትመገብ እንጂ እንድትጾም አይደለም” ትላለች፡፡ ይህ ወንድማችንም “ከዚህ አድርሰሽኛል፤ ከዚህ በኋላ ያለው እኔው አደርጋለሁ” ይላል፡፡ ሐኪሟ ጾሙ ሊጐዳው እንደሚችል ልታስረዳው ብትሞክርም በሽተኛው እምቢ ብሎ ጾሙን በአግባቡ ይቀጥላል፤ ከዚያም ተስፋ እንዳደረገው ደኅነቱ ይፋጠንለታል፡፡ ቆይቶ አሁንም ለክትትል ሲሔድ የበለጠ ተሸሎት ሲገኝ ሐኪሟም አትጹም የሚል ክርክሯን አቆመች፡፡ ሰውዬው በጾሙ ቀጠለና ሲሠራበት ከነበረ የሶሻሊዝም ጸረ ሃይማኖት አስተሳሰብ ተላቅቆ ወደ ሃይማኖቱ አጥር ይመለሳል፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ ሌሎቹን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችም መወጣት ይጀምራል፡፡ ይህ ታሪክ ሲናገር የሰማሁትም የዛሬ አራት ዓመት ከፍራንክፈርት ወደ ሙኒክ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በሚደረግ ሃይማኖታዊ ጉዞ ላይ ተሳትፎ ምስክርነት ሲሰጥ ነው፡፡ “እድናለሁ፤ እበረታለሁ” ብሎ ይበላ የነበረው ሰው የሚድነውና የሚበረታው ያበረቱኛል ያላቸውን ሥጋ ወለድ ምግቦች ሲያቆም ብቻ መኾኑን ከተረዳ በኋላ ሲበላበት በነበረው ዘመኑ እየተጸጸተ ብቻ ሳይኾን ለዚህ ያበቃው መኾኑን በመረዳት እየወቀሰም እንደገና ዕድሜ ልክ ጾም ተመለሰ፡፡
 አሁን አሁን በተለይ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች አንጻር እያከራከሩ ካሉት ጉዳዮች አንዱ የሚበሉና የማይበሉ እንስሳት ዝርዝር፤ በጾም ወቅት የዓሣ መብላትና አለመብላት፤… የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡ በአንድ ወቅት በአንድ ገዳም ተገኝተን በዚያ ከሚኖሩ ታላላቅ አባቶች አንዱን የተለያዩ ጥያቄዎችን በምንጠይቅበት ጊዜ “ዓሣ ደም የለውም ይባላል፤ እንደዚህ ከኾነ ለምን በጾም አይበላም?” ሲል ጓደኛችን ጠየቀ፡፡ አባም ረጋ ብለው “ዓሣን ምን ትሉታላችሁ?” አሉት፡፡ ግራ ተጋባና “አልገባኝም” አለ፡፡ “ዓሣ ምድቡ ከሥጋ? ከአትክልት? ወይስ ከጥራጥሬ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ ጓደኛችንም ፈጠን ብሎ “እርሱማ ሥጋ ነው” አለ፡፡ “ታድያ ሥጋማ በጾም ክልክል ነው ልጄ” አሉት፡፡ እርሱም ከተል አድርጎ ደግሞ “የሚራባ በደመና ነው ይባላል፤ ታድያ …” ብሎ ቆም ሲያደርግ እኛ አባትም ረጋ ብለው “ልጄ የሚበሉትና የማይበሉት በርቢ ምክንያት አይደለም፡፡ እንዳልከው በርቢ ምክንያት በኾንና ዓሣም እንዳልከው በሩካቤ የማይባዛ በመኾኑ የተከለከለ ቢኾን ኖሮ ገዴ የተባለችውም አሞራም ሩካቤ ስለማታደርግ ትበላ ነበር፡፡ ዓሣ የማይበላው ሥጋ ስለኾነ ብቻ ነው፡፡ አንተ ግን መብላት የምትፈልገው ጾም ስለምትፈራ ይመስለኛል እንጂ የዓሣ ሥጋነት ጠፍቶህ አይመስለኝም” አሉትና ዝም አሉ፡፡ በርግጥም ዓሣ የሚበላ ከኾነ በግና ፍየል ወይም ዶሮና ከብት በጾም እንዳይበሉ የሚያደርግ ኀጢአት አድርገዋል ወይ የሚያሰኝ ነው፡፡
 በተለይ ብዙዎቻችን ለጾም ካለን ፍርሐት ይኾን ወይም ስለኾኑ ምግቦች በተለይ ስለ ሥጋ ምግቦች ካለን ፍቅር የተነሣ ሥጋ እንኳ ብናጣ ሥጋ መሰል ነገር ለመብላት የማናደርገው ጥረት የለም፡፡ (ፍቅር ያልኩት ስለተለመደ ነው እንጂ መባል የሚገባው ስስት ነበር፤ ምክንያቱም ፍቅሩ ለምግቡ ሳይኾን ለራሳችን ስለኾነ፡፡ የምንበላውም ለሥጋውስ ማን አለው ብለን አዝነንለት ሳይኾን ለእኛው ብለን ስለኾነ አፈቀርናቸው ሊያሰኝ ስለማይችል መባል ያለበት ለምግቡ ያለን መጐምጀት ወይም ስስት ነው፡፡ ነገር ግን አዳሜ ብልጥ ነው “ፍቅር” እያለ የሳሳለትን ኹሉ ከሽ ማድረጉን ሠልጥኖበታልና ምን ይደረግ?)፡፡ ትንሽ ቀደም ብሎ ከተዋወቅናቸው የጾም ቅቤዎችና የጾም ማኪያቶ አሁን በምግብ ደረጃም የጾም ዱለት፣ የጾም ክትፎ የሚባሉትና ተመሳሳይ ምግቦች በተመሳሳይ መልክና ጣዕም ተዘጋጅተው እስኪቀርቡልን ድረስ የሥጋ አምሮታችን አድጓል፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ምግቦች የሚዘጋጁት ከአኩሪ አተርና ከመሳሰለው እንደኾነ ብናውቅም በክክ ወጥ፣ በእልበትና በስልጆ በመሳሰሉት የጾም ምግቦች መለክ ከመብላት ይልቅ በዱለትና በክትፎ መልክ እንድንበላቸው የፈቀድነው ለተከለከለ ነገር ያለን ፍላጎት ከፍተኛ መኾኑን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ እነዚህን ፍላጎቶቻችን የሚደግፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ወይም መከራከሪያ ሐሳቦች ካገኘን ደግሞ መብላታችንን ተጨማሪ ጽድቅ ልናደርገውም እንሯሯጣለን፡፡ ይህነ አውቆ ነበር ጌታችን ለጽድቃችን ይኾነን ዘንድ ሥጋውንና ደሙን በመብል መልክ የሰጠን፤ ነገር ግን እርሱን የሚያጸድቅ ስለኾነ ልንበላው ብዙም ባንፈልግም ሌላውን ሥጋ ግን እንደ ጽድቅ ምግብ እንዲቆጠርልን እንጣጣራለን፡፡
 ይሔው ከፍተኛ የኾነ የሥጋ ፍላጎታችን ሌሎቹን እንስሳትና አራዊትም ለመብላት እያስከጀለን ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሌላ ጽሑፍ እንደገለጽኩት የማይበሉት እንስሳት ተብለው በመጽሐፍ ቅዱስ የተዘረዘሩትንም እንዳንበላቸው የተከለከልነው ንጹሐን ስላልኾኑ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚደረጉ ሙከራዎችም እያረጋገጡት የመጡት ነገር የእነዚህን እንስሳዎችና አራዊት ሥጋ መብላት ምን ያህል ለጤና አደገኛ መኾኑን ነው፡፡ በተለይ እንደ አሳማና ጥንቸል ያሉት ሥጋቸው በከፍተኛ ደረጃ በሽታ አምጭ ሕዋሳትን በቀላሉና በፍጥነት ለማራባት አመቺ ከመኾናቸውም በላይ ለውጫዊ ተሐዋስያን በተለይም ለባክቴሪያዎች ከፍተኛ ተጋላጭና ለጤና አደገኞች እንደኾኑ በምርምሩም እየታወቀ ነው፡፡ እንደ ካንሠርና የመሳሰሉት አደገኛ ቫይረስ ወለድ በሽታዎችም የእነኝህን እንስሳትና አራዊት ሥጋዎች በሚበሉት ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚከሠቱ እሙን እየኾነ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችንም ንጹሐን ያልኾኑ መኾናቸውን ነግሮ የከለከለው የፈጠራቸው እርሱ ስለኾነና ከእርሱም በላይ ጥቅማቸውንም ኾነ ጉዳታቸውን የሚያውቅ ስለሌለ በርግጥም ልንበላቸው የሚገባን ኾኖ ሳለ እግዚአብሔር የከለከለን አድርገን መረዳት አይገባንም፡፡ እግዚአብሔር አትብልዋቸው ያለን በመከልከሉ ሊጠቀም ሳይኾን እኛ ባለመብላታችን ስለምንጠቀም ነውና፡፡ እንኳን ንጹሐን ያልኾኑትን የኾኑትም መበላት የጀመሩት ከኖኅ ዘመን ጥፋት በኋላ ነው፤ ከዚያው ጊዜም ጀምሮ የሰው ልጅ ዕድሜ በመቶዎች ከመቆጠር ጣራው ፻፳ ብቻ ኾነ፤ አጠረ፤ የሥጋ ውጤት፡፡
 አሁን አሁን መብል እየፈተነን እያከራከረንም ያለው ስለምንጓጓለት እንጂ ለጤናችን ያን ያህል አስበንና ገብቶን አይመስለኝም፡፡ እውነቱን ለመናገር አንዳንድ የምሥራቁ ዓለም ሰዎች እንደሚሉንም ትሉንም ሌላውንም ስለበላን ከረሀብ የምንድን ከችጋርም የምንወጣ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ቢሆን ኖሮ ጥንቱን እነርሱም መቸገር አልነበረባቸውም፡፡ ኾኖም በምግብ መልክ የማንበላቸውን ነገሮች ስላልበላናቸው አልጠቀሙንም ለማለት አንችልም፡፡ የምንኖርባትን ዓለም የተፈጥሮ ሚዛኗን ጠብቃና ለሰዎች ተስማሚ ኾና እንድትቀጥል ለማድረግ የኹሉም ፍጥረት ህልውና አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ፍጥረት ባለው ተፈጥሮአዊ መስተጋብርና መመጋገብ በተዘዋዋሪ እንመገባቸዋለን ማለት ይቻላል፡፡ ቀጥታ ካልተመገብናቸው ማለት ግን ተፈጥሮን ከተፈጥሮአዊ ሥርዓቱ ውጭ ለመጠቀምና ጦሱንም ለመቀበል መጣደፍ ሊኾን ይችላል፡፡ እንኳን ንጹሐን ያልኾኑት ተጨምረዉበት ቀርቶ ንጹሐን የኾኑትንም አዘውትሮ መመገብ ዕዳው ሥጋት ኾኗል፡፡ በልቶ ከመበላ ሳይበሉ መሰንበት ሳይሻል አይቀርምና እንወቅበት፡፡
© ምንጭ፡- አዲስ ጉዳይ መጽሔት፣ ቅጽ 7፣ ቁጥር 173፣ ሐምሌ 2005 ዓ.ም.    

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount