(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- እንኳን ለእመቤታችን በዓለ ዕርገት አደረሳችሁ፡፡
ዘሰ ይብል አፈቅረከኪ ወኢያፈቅር ተአምርኪ [ትንሣኤኪ ወዕርገትኪ] ክርስቲያናዊ፤
ኢክርስቱን ውእቱ አይሁዳዊ ወሠርፀ እስጢፋ ሐሳዊ፤
አንሰ እቤ በማኅሌተ ሰሎሞን ሰንቃዊ፤
አፈቅሮ ለፍግዕኪ ወለተ ይሁዳ ወሌዊ፤
ከመ መርዓቶ ያፈቅር ጽጌኪ መርዓዊ፡፡
እንደ ይሁዳ ስሙን የሚቃረን ግብር ሁልጊዜም የሚሠራውና ራሱን ‹‹ አባ ሰላማ ›› ብሎ የሚጠራው የተሐድሶዎች ብሎግ አንድ የሚያስደንቅ ጽሑፍ ሰሞኑን አስነብቦናል፡፡ የሚያስደንቅ ያልኩት ራሴን ባስደነቁኝ ሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ለርእስነትና ሐሳቡን ለማስተላለፍ መሪ አድርጎ የተጠቀመው ጥቅስ መልእክቱ ከነገረ ጉዳዩ ያለውን ርቀትና አንድ ሰው ከካደ በኋላ ጥቅሶችን እስከምን ድረስ ሊያጣምም እንደሚችል ሳስብ አሁንም እደነቃለሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ክርስትና ከተመሠረተበትና በይፋ በብዙዎች ተቀባይነት እያገኘ ከመጣበት ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ብዙ የዓይን ምስክሮች አይተው ያስተላለፏቸውን ትውፊቶች ሁሉ ምን ያህል እንደሚጠሉ ሳስብ በዚያ ዘመን የነበሩ አይሁድ በአካለ ሥጋ የመመለስ እድል ገጥሟቸው ቢጠየቁ እንኳ ‹‹ እንዴት ከእኛ በላይ ጠላችኋቸው›› ብለው የሚገረሙባቸው ስለሚመስለኝ እደነቃለሁ፡፡ ሦስተኛውና ሁልጊዜም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ተሐድሶዎች የምደነቀው ደግሞ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብና ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ባላቸው ጥላቻ ነው ፡፡ አስተውሎ ለሚያይ ሰው ጽሑፍ ነክ ነገር ላይ ከተነሡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን ወቅታዊ ነገር ላይ ከተነሡ ማኅበረ ቅዱሳንን አንዳንድ ጊዜ ሁለቱንም አንድ ላይ ካላመቼም የሚጽፉበትን ሰው ማኅበረ ቅዱሳን ወይም ዘርዐ ያዕቆብ ነክ አድርገው ካላቀረቡ መንፈሳቸው የሚቀጣቸው ይመስለኛል፡፡ ዓለም አቀፍና ልዩነት የሌለበት የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ነባር ትውፊቶች መካከል አንዱ የሆነውን የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት ለዘርዓ ያዕቆብ መስጠት ማለት ምን ያህል ድፍን ቅልነት ይሆን? እንዲህ የምለውና የምደነቀውም ብዙ ጊዜ የስሕተትና የክህደት ጽሑፍ ቢጽፉም እውነቱ የያዙትና በዚያም እንጸድቃለን ብለው የሚያስቡና ለዚያም ለመሰላቸው የሚተጉ ይመስለኝ ስለነበረ ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ሳየው ግን ‹‹ ኦርቶዶክስን እንዴት እናስጠላለን፤ ሰውንስ ከእምነት እንዴት እንለያለን?›› በሚል መንፈስ ብቻ እንደሚሠሩ ስለተረዳሁ ነው፡፡ አሁን አሁንማ እንደ መሸታ ቤት በየሥርቻው በከፈቷቸው ብሎጎቻቸው ዓይን ያወጣ ስድብና ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው የስም ማጥፋት ቅርሻቶቻቸውን በመትፋት ላይ መሆናቸውን ሳይ አውሬው ብስጭቱ እየጨመረ የመጣው ወደፊት ሰማዕትነትን አይቶ እየፈራ ይመስላል ፡፡
በርግጥ ይህ ብሎግ በመኖሩ ‹‹ ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው›› /ራእ 13፤ 5/ ተብሎ የተነገረለት አውሬው ሥራውን እያበረታ መሆኑን እናያለን፡፡ በማያቋርጠው የሐሰትና የጠብ ፤ የስድብና የስም ማጥፋት እንዲሁም የኑፋቄና የክህደት ጽሑፎቻችሁም ‹‹ እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ ›› /ራእ 12 ፤ 15/ የተባለውን አውሬው በገቢር የሚያሳይባችሁ የክሕደትና የኑፋቄ የአውሬው የትፋት ወንዞች መሆናችሁን ታረጋግጡልናላችሁ፡፡ ነገር ግን ‹‹ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው ›› /ራእ 12 ፤16/ ተብሎ እንደተጻፈው ምድር ቤተ ክርስቲያን የእናንተን የክህደት መርዝ ታሰርገዋለች ፡፡ አሁንም እንደተለመደው ሁሉ ስሕተቶቻችሁን ከማሳየት እንጀምር፡፡
አውሬ ያበከተውን አትብሉ
በመጽሐፍ ‹‹በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ›› /ዘሌ 22 ፤ 8/ ተብሎ እንደተጻፈ አውሬ ያቆሰለው ደሙን መጥጦ ያበከተው የጫረው ሁሉ እንዳይበላ በኦሪቱ ታዝዟል፡፡ በላይኛው አንቀጽ ላይ ደግሞ አውሬው ማን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ነግሮናል፡፡ አንድ ሰው በጉ ወይም በሬው የእርሱ ቢሆንም አውሬ ሊበላው ጭሮ ካቆሰለው ደሙን መጥጦ ከገደለው እንዳይበላው እንደተከለከለው ሁሉ ለሕይወታችን ምግብ በአምልኮታችንም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገን ከምናቀረበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱን ለይተው ልክ አውሬ በጉን ከመንጋው ለይቶ እንደሚበላው ወይም እንደሚያቆስለው አውሬ የተባለ መናፍቅም ወይም ከሐዲ ከእናቱ ወይም ከመንጋው ለይቶ በተሳሳተ ትርጉም ያቆሰለውን ወይም የጫረውን ወይም በክህደት አስተምህሮ የገደለውን መብላት ለእኛ የተከለከለ ነው፡፡ በኦሪቱ ትእዛዝ እንዳየነው በጉ ንብረትነቱ የሰው ቢሆንም አውሬ ስለነካው ብቻ እንደተከለከሉት ጥቅሱ የእኛውና ከእኛው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ቢሆንም አውሬ መናፍቅ በጥርጥርና በክህደቱ መርዙ የወጋውን በልተን እንዳንጎዳ የተከለከለ ነው፡፡ ስለዚህም ጥቅስን እኛ ለነፍሳችን የምንመገበው በአውሬ መናፍቃን ትምህርት ያልተጫረና ያልረከሰ ሲሆን ብቻ መሆኑን ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ መናፍቃን በተሳሳተ መንገድ ያጣመሙትን ሁሉ ለነፍሳችን ማቅረብ ራስን መቅጣት መሆኑን ማወቅና መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡
ለምሳሌ እመቤታችን አልተነሣችም አላረገችም ብሎ ለመካድ የግድ ጥቅስም የሚያስፈልገው አልነበረም፡፡ ‹‹ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም ›› / ዮሐ 3 ፤13/ የሚለውን ጠቅሶ እጂግ በተዛባ መንገድ እመቤታችን አላረገችም ለማለት መጥቀስ ልክ በበጎቹ አውሬ እንደሚያደርገው የበጉን ደሙን ( የጥቅሱን ነፍሱን ምስጢሩን ወይም ዋና መልእክቱን ) መጥጦ ገድሎ አበክቶ መስጠት ነው፡፡ ቀጥታ በዚህ መንገድ እንተርጉመው ካልንማ መጀመሪያውኑ የሚለው ወደ ሰማይ የወጣው ከሰማይ የወረደው ከሆነ ክርስቶስ ያረገው በተዋሐደው ሥጋ ነውና በውኑ ሥጋውን ከሰማይ ይዞ ወርዷልን? እንዲህማ ከሆነ የሰው ልጅ ተብሎስ እንዴት ሊጠራ ይችላል? እንዲህማ ከሆነ የራሱ ትምህርትና ንግግርም ሆነ ስለ እርሱ ሐዋርያትና ሊቃውንት ያስተማሩት ሁሉ ከንቱ ሆነ፡፡ ከሰማይ በውረድማ ከሆነ መላእክቱን እንኳ ብንተዋቸው ቅዱስ ጳውሎስ እስከ ሦስተኛ ሰማይ የተነጠቀው ጥንቱን ከዚያ ቢመጣ ነውን? ወይስ ሔኖክና ኤልያስ ያረጉት ድሮውንም ከሰማይ የወረዱ በመሆናቸው ነው? ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ወርደው ያልተመለሱም አሉ፡፡ ለይስሐቅም ምትክ ሆኖ የተሰዋው ከሰማይ የወረደ ነበር፡፡ ለኤልያስም እንጎቻ በመሶብ ውኃም በማሠሮ ወርዶለት ነበረ፡፡ ጥቅሶችን የምትተረጉሙት እንደዚህ ከሆነ ‹‹ እኔ ስለ እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር ምስክሬ እውነት አይደለም ›› / ዮሐ 5 ፤ 31/ የሚለውንስ ምን ትሉለታላችሁ? በእውነት ጥቅስን እንዲህ ያለ ቦታውና ያለመልእክቱ መጠቀም በገዳመ ቆሮንቶስ ለጌታም ጥቅስ እየጠቀሰ ለመፈታተን ያላፈረውንና አሁንም ይህን ከማድረግ የማያፍረውን የማይሰለቸውንም ዲያብሎስን ያስመስላችሁ ወይም በእርሱ መንፈስ የምትሠሩ ፈታኞች መሆናችሁን ታረጋግጡ ካልሆነ በቀር የምትፈጥሩት ነገር የለም፡፡ ልክ ክፉ አውሬ በጉን ከመንጋው ለይቶ አድክሞ ይዞ ደሙን መጥጦ እንደሚገድለው ጥቅስንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ከመንጋውና ከመልእክቱ ለይቶ ምሥጢር ደሙን መጥጦ በማብከት ተሐድሶዎችን የሚተካከል ያለ አይመስለኝም፡፡
ይህ ጥቅስ የተጠቀሰለት ዳግም የመወለድ ምስጢር ረቅቆበት አልገባው ላለው የአይሁድ መምህር ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ከጥቅሱ ጌታችን ኒቆዲሞስን ከነበረበትም ዕውቀትና እምነት ከፍ እንዲልና ታላቁን ምሥጢረ ሃይማኖት እንዲረዳ እያደረገው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ በፊቱ ቆሞ የሚያነጋግረው ጌታ ዕሩቅ ብእሲ ሳይሆን ከሰማይ አካላዊ ቃል መጥቶ በተዋሕዶተ ትስብእት የተገለጠ መሆኑንና በሚያየው ትስብእት ውስጥ የማያየው መለኮት ተዋሕዶ መኖሩን ትስብእትም ለዚህ የበቃው በተዋሕዶ እንጂ እንደ ቀደሙት ነቢያት በጸጋ አለመሆኑንና የባሕርይ አምላክ መሆኑን ነበር ያስረዳው፡፡ በርግጥም ወልደ እጓለመሕያው ጌታ ራሱን አምላክ ያደረገ ፍጡር አይደለም፡፡ አምላክነት ከጥንት ገንዘቡ ነው፤ ነገር ግን ይህን ሰማያዊነት፣ ቀዳማዊነትና፣ ፈጣሪነት፣ ሁሉን ማወቅና ከመወሰን ሳይወጡ መምላት፣ ከመግዘፍ ሳይወጡ መርቀቅ ( ቀድሞ በሰማይ የነበረውን) ትስብእት ወይ ሥጋ የወረሰው በተዋሕዶ ከቃል ነውና ‹‹ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም›› ሲል እውነተኛ ተዋሕዶውን አረጋገጠልን፡፡ ጥቅሱ ራሱ የሚፈጸመው ‹‹ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው ›› በሚል ሐረግ ነው፡፡ ጌታ ራሱ በኒቆዲሞስ ፊት ሆኖ እያነጋገረው እያለ ራሱን ‹‹ በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው›› ሲል የጠቀሰው በዚያው ቅጽበት ወይም ቃል ሥጋን ከተዋሐደበት ቅጽበት ጀምሮ ሥጋ ቅድመ እርገትም በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ በክብር ያለና ፍጹም አምላክ መሆኑን ሲያስረዳው ነው፡፡ ምክንያቱም ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ቢየየው በሰማይ የሌለ እንዳይመስለው ተዋሕዶውንና አምላክነቱን ለማስረዳት የተናገረው መሆኑን በዚህ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ እንደዚህማ ባይሆንና ጥቅሱ ለጌታ ለዕርገቱ የተነገረ ቢሆን ኖሮ ‹‹ አሁን በሰማይ የሚኖረው›› ለምን ይለዋል፡፡ ገና አላረገም ነበርና፡፡ ስለዚህ ጥቅሱ ከእመቤታችን ዕርገት ቀርቶ ከጌታም ዕርገት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ፡፡
ለመሆኑ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገትን ያስተማሩና የሰበኩ እነማን ናቸው? በግእዙ ያለው ታሪካችን ከሆነ ያስጠላችሁ እስኪ በሦስተኛ ክፍለ ዘመን ስለ እመቤታችን ድንቅ ድንቅ ስብከቶች የሰበከውን ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራትን ዘርዓ ያዕቆብ አስተማረህ ትሉታላችሁን? ወይስ የእመቤታችን በዓለ ዕረፍቷ ከበዓለ ዕርገቷ ጋር በአንድ ላይ በጁሊያን አቆጣጠር ኦገስት 15 አንድ ላይ ይከበር ይል ለነበረው ለቁስጥንጥንያው ንጉሥ ለዮስጥንያኖስ ከጥንት ጀምሮ ከኢየሩሳሌም መጥቶ በመንበረ ማርቆስ ካቴድራል ቤተ መጻሕፍት ተቀምጦ የኖረውን የእመቤታችንን የዕረፍቷንና የዕርገቷን ዜና መጽሐፍ ተርጉሞ በመስጠት ዕረፍቷ ጥር 21 ዕርገቷ ነሐሴ 16 መሆኑን በመግለጽ ቢያንስ በዚያ ዘመን ሁለቱም በዓላት በየራሳቸው እንዲከበሩ እንጂ አንድ ላይ መከበሩ እንዳይታወጅ ያደረገው የ33ኛው የእስክንድርያ ፓትርያርክ የቴዎዶስዮስን (535 - 566) ሥራ ምን ልታደርጉት ነው? አትደብቁት በብዙ የዓለም ቋንቋዎች የተተረጎመ ነው፡፡ እንግዲህ እናስተውል ፤ ይህ ቴዎዶስዮስ በጽርእ (ግሪክ) ቋንቋ ተርጉሞ ለንጉሡ የሰጠው መጽሐፍ በዓሉ ከእርሱ ዘመን በፊት ተለያይቶ ይከበር እንደነበርና ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ያሉት የምስራቁ ክፍል አባቶች በዚህ ትውፊት ጸንተው ይጠቀሙበት እንደነበር አሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ምርምር ለሚያደርጉ ማስረጃ ሆኖ ያገልግላል፡፡ በቅርብ ጊዜ አሜሪካን ሀገር ያለው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ከፍተኛ ትምህርት ቤት የሆነው የቅዱስ ቭላድሚር ሴሚናሪ ከሚያሳትማቸው እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ አባቶች ስብከቶች (Patristic
writings) መካከል አንዱ የእመቤታችንን ዕረፍትና ዕርገት (Dormition and Assumption) በተመለከተ በዚያ በጥንቱ ዘመን የተሰበኩ ስብከተ ሊቃውንትን አሰባስቦ የያዘ ነው፡፡ ይህ በዓል በጥንታውያኑ አበው ሲያከብሩት የመጣና እመቤታችን ዕረፍቷም ሆነ ዕርገቷ ከሐዋርያት ጀምሮ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበሩ እጂግ ብዙ ደናግል ሴቶች በአካል በነበሩበት የተፈጸመ እንደሆነ ትውፊቱን የመዘገቡ መጻሕፍት ሁሉ የሚያረጋግጡት እውነታ ነው፡፡ በዚያ የነበሩ ሁሉ አይተው እንዳረጋገጡት ጌታ በሚያስደንቅ ግርማ የእመቤታችንን ነፍስ ሊቀበል በተገለጸ ጊዜ በአንድነት የሰገዱት ሐዋርያትና ደናግል ፍርሐት ርቆላቸው ቀና ሲሉ ሙሴ ከፊት ሆኖ ሌሎች ነቢያትና ጻድቃን ጌታን ከብበው ዳዊት በበገናው ‹‹ ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ፤ አንተ ወታቦተ መቅደስከ›› የሚለውን መዝሙሩን ሲዘምር ሁሉም በአንድነት አይተዋል፤ ሰምተዋል፡፡ ይህ የተረጋገጠ ታሪክ ነው፡፡ የነበሩት ሁሉ መስክረውታልና፡፡ እንግዲህ ሐዋርያትና ከእነርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ ነበርን አይተናል ብለው አውርሰውት ከሔዱና ሁሉም እየተቀባበለ ለእኛ ካደረሰው በኋላ እናንተ አንቀበልም በማለታችሁ ከሐዋርያት መንገድ መውጣታችሁን ታረጋግጡልናላችሁ እንጂ እኛ የምንጠራጠር ይመስላችኋልን?የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት ትውፊት ወይም የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት የማትቀበሉ ከሆነ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ከየት አገኛችሁት? ማን ሰጣችሁ? ምዕራፍና ቁጥሩንስ ከየት ተቀበላችሁት? ነቢያት ሐዋርያት እንደጻፉትስ በምን ታረጋግጣላችሁ? በእነማንስ በኩል ተጠብቆ ደረሳችሁ? ለመሆኑ ተነሣች ዐረገችን ለመቀበል ከቸገራችሁ አልተነሣችም አላረገችምን ለምን አመናችሁት? የተነገረውንና ሲተላለፍ የኖረውን ለማመን የምትቸገሩ እናንተ ልብወላዳሁን ለማመን የሚያፋጥናችሁ ማን ነው? መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ወይም የዕረፍቷንና የአቀባበሯ ሌላ ትውፊት እንኳ ሳትይዙ የነበረውን ለማቃለል ብቻ የሚያጣድፋችሁ እንዴት ያለ ክፉ መንፈስ ነው? እናንተ የተረጋገጠ ጽሑፍ ብቻ ነው የምንቀበልስ ካላችሁ ትንሣኤና ዕርገቷ የተመለከተውን ጽሑፍ ማን እንደጀመረው፣ እንዴት እንደተሸጋገረና እንዴት ስሕተት እንደሆነስ ለምን አልመረመራችሁም? ጥላቻ ጊዜ አይሰጥማ፤ ክህደት የእውነተኛ ዐውቀት ጭላንጭል የለውማ፡፡ እንግዲህ እናነተን በምን መርዳት ይቻል ይሆን? ሐዋርያትን ካልተቀበላችኋቸው እኛንማ እንዴታ!በክህደት ትምህርታችሁና በስም ማጥፋታችሁ የምንደነግጥ ይመስላችኋልን? ይህንማ ሥራችሁ እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እናንተም ሥራችሁን እኛም ሥራችንን እንሠራለን፡፡ በኋላ ዘመን ዋጋችን እንደ ሥራችን እንዲመዘን እናውቃለንና፡፡ ወይስ እንደ ዲያብሎስ ተስፋ ድኅነት የለንም ብላችሁ ተስፋ ቆረጣችሁ?
ትንሣኤዋና ዕርገቷ ለክርስቲያኖች ሊቀበሉት የማያስቸገረው ግን የተረጋገጠ ትውፊት በመኖሩ ብቻም አይደለም፡፡ ትልቁና ዋናው ምሥጢር ያለው ደግሞ እመቤታችን ‹‹ ልዩ ›› መሆኗ ላይ ነው፡፡ ዕድገቷና ሕይወቷ ልዩ ነበር፡፡ በእርሷ የተደረገው የአካላዊ ቃል ጽንስና ወሊድም እስካሁን ሊገልጹት ቀርቶ ሲያስቡትም ይከብዳል፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩን ጥልቅነት ሊዋኝ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሰወሪያው ማዕበልም ያማታዋል፡፡ ... አሁንም ገናንቱን አንመርምር፤ ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ፤ የገናንቱን መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው›› እንዳለው ለማንም የሚቻል አይደለም፡፡ ለዚህ የታደለችው ነገሩን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው የነበረችው እራሷ ድንግል እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ገብርኤልም ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹ ልዩ›› መሆኗን አስቀድመው ምስጋናቸውን ያስከትሉላት፡፡ ታዲያ እመቤታችን ልዩ በሆነ መንገድ ከጸነሰችና ከወለደች ልዩ በሆነ መንገድስ የማትነሣው የማታርገው ለምንድን ነው? መነሣቷና ማረጓ አድሎ ያስመስላል የሚባለው በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷንስ ለምን አድሎ ነው አይባልም? ጽንሱ ልደቱ ሰለ እርሱ ነው የምትሉ ከሆነስ ትንሣኤውና ዕርገቷ ምን የሚያረጋግጥ ይመስላችኋል? የእርሱን ትንሣኤና ዕርገት ተሰርቆ ነው ሲሉ የነበሩ አይሁድ በእርሷ ትንሣኤና ዕርገት ሲያፍሩ ብዙዎቹም ከእነርሱ ወደ ክርስትና ሲመለሱ እናንተ ይህን ከማለት የማትመለሱ የክርስቶስን ትንሣኤም ሳታውቁ ታቃልላላችሁን? የእናንተ ክሳደ ልቡና በእውነቱ እንደምን ከዚያ ዘመን አይሁድ ይልቅ ጸና? በውኑ አድሎን ለእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት የምትጠቅሱት በደብረታቦር በዓል ሙሴን ከሙታን ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን ብቻ ይዞ መውጣቱንስ አድሎ ትሉታላችሁን? በእውነቱ ስንቱን ተመሳሳይ ታሪክ ልንጠቅስ ስንቱንስ ልናስታውሳችሁ እንችላለን? በእውነት የቀደሙትን አበው ትምህርትና ትውፊት እንዳትቀበሉ የእግዚአብሔርንስ የማይታወቅ መንገድ የደረሳችሁበት አስመስሎ ያሞኛችሁ ወይንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? የእመቤታችን ልዩ መሆን ካልገባችሁ በትንሣኤዋና በዕርገቷም ልዩ መሆኗን እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ማስተዋላችሁን የጋረደውን የስድብና የስም ማጥፋት ግብር ያሰደረባችሁን ከፉን መንፈስ ትቃወሙትና ከዚህም ነጻ ትወጡ ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ይርዳችሁ ከማለት በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች ዐርጋለችም፤ ክብር ምስጋና ለተወደደ ልጇ ይሁን፤ አሜን፤ በረከቷም ይደረብን፡፡
አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እም አንክሮ፤
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ፤
ገነትኪ ትጽጊ ሰላመ ወተፋቅሮ፤
እለያማስኑ ለዓጸደ ወይንነ ወፍሮ፤
ቆናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ፡፡
© ከዲ/ን ብርሃኑ አድማስ መጽሐፈ
ገጽ በቀጥታ የተወሰደ!!!
አቤት! እንዴት ያለ የጣፈጠ የነፍስ ምግብ ነው ጃል! ለአውሬው ደግሞ ጥሩ ተግሣጽ ነው! ለአስተላላፊውስ ቃለ ቃለህይወት ያሰማል……ን ብለናል፡፡
ReplyDeleteታላቅ ምግበ ነፍስ ነው...::ቃለ ህይወት ያሰማልን ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ::
ReplyDeleteTrash
ReplyDeleteሉተራዊ መልስ የለውም።የሱስ ጌታ ነው ፣ሃሌ ሉባ።that is all. አልቦ እውቀት ።
Deleteአንተም እንደ ክፉ አባቶችህ ትርጉም ታጣማለህ እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ ማርያም እንኲን ያላረገችውን ብታርግ እንኲን አንድ ነገርን አውቃለሁ የእግዚአብሔር አሳብ በሰማይ በምድር ያለሁን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።ኤፌ.1፥10 እግዚአብሔር ቃሉን ያብራልህ እስካሁን ድረስ የአባ ሰላማን ብሎግ አላቀውም ነበር ግን ስለ አስተዋወከኝ አመሰግናለው።
ReplyDeleteየናንተ በሬ ሁሌ ነዉ የሚወልደዉ?
Deleteቃለ ሕይወት ያሰማልን ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
ReplyDeleteተሀድሶ መናፍቃን እና አሸዋ አንድ ናቸዉ፤ አሸዋ ምንም እነኩአን በዉሃ ዉስጥ ቢቀመጥ፣ ርሶ አየቅም፤ እኒህ መናፍቃንም ምንም እነኩአን የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ ቢደረድሩ፣ ቢነገራቸዉም፣ እዉነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ሊገባቸዉ አየችልም፡፡ እነርሱ አዉሬዉ የቆመባቸዉ የበባህር አሸወዋዎች ናቸዉ፤ ከዚህም የተነሳ እርሱአን እና ዘሩአን ሲያሳድዱ ይኖራሉ፡፡ ደ/ን ብርሃኑ፣ የአገልግሎት ዘመንህን ያብዛልን፡፡
ewnet new wendm! :- ...በክህደት ትምህርታችሁና በስም ማጥፋታችሁ የምንደነግጥ ይመስላችኋልን? ይህንማ ሥራችሁ እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እናንተም ሥራችሁን እኛም ሥራችንን እንሠራለን፡፡ በኋላ ዘመን ዋጋችን እንደ ሥራችን እንዲመዘን እናውቃለንና፡፡ ወይስ እንደ ዲያብሎስ ተስፋ ድኅነት የለንም ብላችሁ ተስፋ ቆረጣችሁ? ...
ReplyDelete