Pages

Sunday, August 11, 2013

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው ማን ነው ?

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም)፡- ሰኮናቸው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳት (የዘመናችን ተሐድሶዎች)(የመጨረሻ ክፍል)

“ታዲያ ሠለስቱ ደቂቅን ያወጣቸው ማን ነው?” ለሚለው የተሐድሶዎች ጥያቄ የቀረበ መልስ፡፡ 

መጀመሪውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ገብርኤል ነው አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹ የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ አማካሪዎቹንም፤ ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፦ እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ ›› /ዳን 3 24 -25/ ፡፡ በዚህ ገለጻ መሠረት አራተኛውን ያየው ንጉሡ ናቡከደነጾር ነው፡፡ እርሱም አየሁ ያለው አራተኛ ሰው ነው፡፡ የጨመረበት ቢኖር አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል የሚለውን ነው፡፡ ለመሆኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየ ? ሌሎቹ ለምን አላዩም ? አንደኛው የጥያቄው ቁልፍ ምስጢር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሣት የጣለው ራሱን ምስል አቁሞ ለምስሉ ሕዝቡን በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አምላክ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ የሚያየውን አራተኛውን  ሰው ‹‹ የእኛን ልጅ ይመስላል ወይም እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹ የአማልክትን ልጅ›› ይመስላል ያለበት ምስጢር ምንድን ነው ? ይህን ያለበት ምክንያቱ ያየው ነገር አራተኛው አካል ከህልውና ያለው በዘር በሩካቤ የተወለደ ሰው እነርሱ ሳያዩት እሳቱ ውስጥ ገብቶ ሳይሆን ነገሩ መገለጥ ስለሆነ ነው፡፡


 በብሉይ ኪዳን ከተገለጹት ታላላቅ ሦስት የእግዚአብሔር መገለጦች ውስጥ አንዱ ይህ የሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ነው፡፡ አንደኛው በመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር እግዚአብሔር ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል የተገለጠው መገለጥ ነው / ዘፍ 18/ ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አሁንም እግዚአብሔር ለአባታችን ለያዕቆብ በጎልማሳ አምሳል ተገልጾ ሲታገለው ያደረበት ታሪክና ያዕቆብንም መጀመሪያ ‹‹ ካልባረከኝ አልለቅህም ›› ከተባረከ በኋላም ‹‹ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው ›› /ዘፍ 32 25 - 32/ ያሰኘው መገለጥ ነው፡፡ ሦስተኛው ይህ ለባቢሎኑ አላዊ ንጉሥ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እቶን እሳት በጣለበት ወቅት ያደረገው መገለጥ ነው፡፡ ሦስቱም መገለጦች የሚያመሳስሏቸው ሁለት ጠባያት አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው በሦስቱም ጊዜ እግዚአብሔር በሰው መልክና አምሳል መገለጡ ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ደግሞ ቃለ እግዚአብሔር በሥጋዌ ( ሰው በመሆን) ተገልጦ ለሰው ፍጹም ድኅነት የሚሰጥ መሆኑን አስቀድሞ በምሳሌ መግለጽ ነው፡፡ መሠረታዊ መልእክቱ ደግሞ አምላክ ሰው ከሆነ በኋላ የሚያድነው የተስፋውን ዘር እሥራኤልን ብቻ ሳይሆን አሕዛብንም ጭምር መሆኑን ለማሳየትና አሕዛብም የሥጋዌው ነገር ቀድሞ የተገለጸው ለእሥራኤል ብቻ ስለሆነ እኛ ልናምንበት አይባም እንዳይሉ ለዚህ ደንዳናና ጫካኝ ናቡከደነጾርም ጭምር ገለጸለት፡፡ የእነ ነነዌ ታሪክም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሆኖ የተቀመጠውና እግዚአብሔር ለአሕዛብም ድኅነት ይፈጽም እንደነበር የተዘገበው እግዚአብሔር የእሥራኤል ብቻ ሳይሆን የሁሉም አምላክ የነበረ መሆኑን ራሱ ብሉይ ኪዳንም ምስክር እንዲሆን ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ታሪኮችና ምሳሌዎችም በብዛት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ፡፡ ስለዚህ የዚህ በሠለስቱ ደቂቅ ድኅነት ውስጥ የታየው መገለጥ ዋናው ምስጢሩና መልእክቱም የአካላዊ ቃልን ሰው ሆኖ መገለጥና አዳኝ መሆኑንን በሐዲስ ኪዳንም እንደ ሠለስቱ ደቂቅ እሳትና ስለት፣ ሰይፍና ጎራዴ፤ እስራትና ግርፋት የሚቀበሉትን ሰማዕታት ሁሉ የሚያድናቸው እርሱ መሆኑን መግለጽ ነው፡፡  ታዲያ ዋናው መልእክቱና ምስጢሩ ይህ ከሆነ ገብርኤልም ሆነ ሌሎቹ መላእክት ለምን አዳኑ ይባላሉ?

በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት መሠረት ለሰዎች ከጊዜያዊና ምድራዊ አደጋና ሰዎች ከሚያመጡባቸው መከራ ድኅነት ሲደረግላቸው ድኅነታቸውን የሚፈጽሙላቸው ቅዱሳን መላእክት ማለትም ጠባቂ መላእክቶቻቸው ናቸው፡፡ ምንም አንኳ ይህ መሆኑን አንዳንድ ጊዜ በግልጽ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምስጢር ቢገለጽም የእግዚአብሔር መላእክት ከሚጠብቋቸው ሰዎች ተለይተው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ያዕቆብን ያስገደለው ሔሮድስ ቅዱስ ጴጥሮስንም ለመግደል ባሰረው ጊዜ በዚያ ወቅት ሊሞት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ መልአኩ እንዲያድነው አድርጓል፡፡ ‹‹  እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም። ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ። ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ / ሐዋ 12 7 - 11/ ተብሎ እንደተጻፈ ሙት ላነሣውና ስንት ተአምራት ላደረገው ቅዱስ ጴጥሮስ አሁን ግን ይህን ሁሉ የሚያደርግለት መልአኩ ነው፡፡ ይህ መልአክ የቅዱስ ጴጥሮስ ጠባቂ መልአክ እንደሆነ ብዙ ሊቃውንት በትርጓሜያቸው አስተምረዋል፡፡ በዚሁ ታሪክ ላይ  ‹‹ ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤  የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም፦ አብደሻል አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እርሱም፦ መልአኩ ነው አሉ ›› / 13-15 / ተብሎ  እንደተጻፈው  ውስጥ የነበሩት ጴጥሮስ አይሆንም ‹‹ መልአኩ›› ነው ያሏት እርሱን ሊመስልሽ የሚችለው ጠባቂ መልአኩ ነው ለማለት ነበር፡፡ ይህም የሆነው በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ የጠባቂ መላእክት ጥበቃና መገለጥ በሰፊው ይታወቅ ስለነበረ ነው፡፡ በመጽሐፈ ጦቢትም ላይ ቅዱስ ሩፋኤል ሰው መስሎ ለጦብያና ለቤተሰበው እንዲሁም ለራጉኤልና ለቤተሰቡ ቀድሞ ጸሎታቸውን በማሳረግ በኋላም ከፈተናቸው በማዳንና ሕይወታቸውን በመባረክ ተገልጾ አይተነዋል፡፡ እነዚህ ሁለት ታሪኮች የሚያሰረዱን ጠባቂ መላእክት በድሕነታችን ውስጥ ትልቅ ስፋራ የሚሰጣቸውና በርግጥም እነርሱ የሌሉበት ድኅነት የሌለ መሆኑን ነው፤ ልዩነቱ በአንዳንዶቹ ታሪኮች ላይ መገለጣቸው በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ተገልጠው ለሰው አለመታየታቸው ብቻ ነው፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና ›› /ማቴ 18 10/ ያለው ስለጠባቂ መላእክቶቻችን ነው፡፡ በእያንዳንዱ ነገራችንና ፈተናችን ላይ ወደ እግዚአብሔር እያመለከቱ የሚጠብቁን የሚያድኑን የሚያስፈርዱልን ወይም የሚያስፈርዱብንም እነርሱ ናቸውና፡፡ እንደናቡከደነጾር ያለውን አስፈርደውበት አውሬ አድርገው ሣር ያስግጡታል፤ እርሱም ራሱ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ ብሎ አሁንም አረጋግጧል / ዳን 4 13/ ፡፡ እንደ ሔሮድስ ያለውን  ደግሞ  ‹‹ ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ ›› / ሐዋ 12 23/ ተብሎ እንደተጻፈው  አስፈርደው ይቀስፉታል፡፡ እንደ ዳንኤል፤ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ዮሴፍ፣ ሠለስቱ ደቂቅ ያሉትን ደግሞ ያድኗቸዋል፡፡ ‹‹ ...  እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። ... ›› /መዝ 90 / ተብሎ ተጽፏልና፡፡

ጠባቂ መላእክቶቻቸው የሚያድኗቸው ቢሆንም በራእዩ የታየው አንድ ሆኖ ሳለ ሦስቱ ተደርገው በሦስት ድርሳናት ለምን ተገለጸ የሚል ጥያቄም ልናነሣ እንችላለን፡፡

እንዲህ ያሉትን ምስጢራት መረዳት የምንችለው በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉትን ተመሳሳይ ታሪኮችና ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ስናውቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የጌታችንን ትንሣኤ አስመልክቶ አራቱም ወንጌላውያን መዝግበውልናል፡፡ አራቱም የመዘገቡበት መንገድ ግን ተቃርኖ ባይኖረውም ልዩነት አለው፡፡ አበይት ልዩነቶቹ ሦስት ነገሮች ላይ ናቸው፡፡ የተገለጹት መላእክት ቁጥር ላይ፤ የመጡት ሴቶች ማንነት ሴቶቹ የመጡበትን ሰዓት በተመለከተ የአዘጋገብ ልዩነት አለ፡፡ ለዛሬው ለጉዳያችን ቅርበት ያለው የመላእክቱ ብዛት ላይ እናተኩር፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹  እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው /ማቴ 28 2-7/ ሲል ይገልጻል፡፡ ማርቆስ ደግሞ ‹‹ ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ፤ ... ›› /ማር 16 5/ ይላል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ ›› /ሉቃ 24 4/ ይለናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ብዙ ነገር ስለ ትንሣኤው ካተተ በኋላ ‹‹ ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች / ዮሐ 20 11 - 12/ ሲል መዝግቦልናል፡፡ እነዚህን አገላለጾች ስናያቸው የአዘጋገብ ልዩነት ቢታይባቸውም ቅራኔና የእውነታ ልዩነት ግን የላቸውም፡፡ ማቴዎስና ማርቆስ ስለ አንድ መልአክ ማነጋገር ቢገልጹም ሌላ መልአክ እንዳልነበረ ግን አላመለከቱም፡፡ እንዲያውም ማቴዎስና ማርቆስ የመዘገቡልን ስለ አንድ መልአክ ይሁን እንጂ ሁለቱም የመዘገቡት ግን ስለተለያዩ መላእክት ነው፡፡ ማቴዎስ ከመቃብሩ ወጭ ድንጋዩን አንከባሎ ስለተቀመጠው ዘግቦ ከመቃብሩ ውስጥ በቀኝ በኩል (በራስጌ ወይም በግርጌ) ስላለው አልመዘገበም፡፡ ማርቆስ ደግሞ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስላለው መዝግቦ በውጭ በኩል ስላለው ወይም የመቃብሩ ድንጋይ ላይ ስላለው አልመዘገበም፡፡ ሁለቱም ግን ሌላውን መልአክ አልነበረም አላሉም፤ ‹‹የለም›› በሚያሰኝ መንገድም አልገለጹም፡፡ ሉቃስና ዮሐንስ ደግሞ ሁለቱንም መኖራቸውንና በግርጌና በራስጌ መሆናቸውን ገለጹልን፡፡ ስለዚህ ሁሉም ትክክል ናቸው፡፡ የተለያዩና የማይቃረኑ የተባለው ለዚህ ነው፡፡  ይህም ቢሆን በተዘገበው መንገድ ስለተገለጹት መላእክት ይናገራል እንጂ በትንሣኤው ዕለት ስለነበሩት መላእክት አጠቃልሎና ዘግቶ አይናገርም፡፡ የነበሩትን መላእክትም ሁለት ብቻ ነበሩ ማለት ፍጹም ስሕተት ላይ ይጥላል፡፡

ወንጌላውያኑ በዚህ በመላእክቱም ቁጥር ሆነ በሌሎቹ ጉዳዮች የተለያዩትስ ለምንድን ነው ስንል ደግሞ አንድ መሠረታዊ መልእክት እናገኛለን፡፡ ይኸውም ስለመላእክቱ የተለያየ ዓይነት መገለጥ የገለጹት ለተለያዩ ሰዎች በትንንሽ የጊዜ ልዩነት የታየውን መገለጥና ለአንዳንዶችም በተቀራራቢ ግን በተለያየ ጊዜ የተገለጠውን ስለመዘገቡ ነው፡፡ለምሳሌ  ቅዱስ ዮሐንስ መግደላዊት ማርያም መመላለሷ ከማሳየቱም በላይ ለእርሷ የተደረገውን የአንድ ጊዜ መገለጥ ብቻ ነው የነገረን፡፡ ሉቃስ ደግሞ ለሌሎች ሴቶች የተደረገውን ( ምክንያቱም ተመላልሰው ያዩም አንድ ጊዜም ያዩ አሉ፤ ብዙ ታሪኮች በውስጡ አሉና) እያሉ ከነጊዜው ስለመዘገቡ እንጂ አንዱን ነጠላ ድርጊት ለያይተውና አሳሰተው መዝግበው አይደለም፡፡ በዚህ መሠረት ቀስ ብሎና በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ክፍል ላይ እንዳየነው ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ተሰጥቷቸውና በጊዜው የነበረውን እውነተኛውን ትውፊት ከሐዋርያትና ከነበሩት ሰምተው ከተረጎሙት ሳይረዳ ልክ እንደዚያ ርኩሳን እንደተባሉት እንስሳት ሳያመሰኳ ወይም እውነታውን ሳይቆነጥጥ ወይም እንደ አሳዎቹ ሐዋርያት የእምነት መከላከያ ጋሸ(ቅርፊት) እና ምስጢራትን የሚረዳበት ክንፈ ጸጋ ሳይኖረው በአመክንዮ (ሎጂክ) ብቻ እረዳለሁም አስረዳለሁም ቢል ይሳሳታል፡፡

ስለዚህ የሠለስቱ ደቂቅ ድኅነትን በተመለከተ በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል ተብሎ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል ተብሎና በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ሩፋኤል ተብሎ መገለጹ ከላይ በወንጌል እንዳየነው ያለ ትውፊቱን ለያይቶ መዘገብ እንጂ ተቃራኒ ነገር አይደለም፡፡በዚሁ መሠረት ሦስቱን ሕጻናት አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልንም ያዳኗቸው ጠባቂ መላአክቶቻቸው ናቸው፡፡ እነዚህም ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ልክ ሥላሴ ለአብርሃም በተገለጹለት መንገድ ሦስት ሆነው ከሦስቱ ጀርባ ቆመው መታየት ነበረባቸው ካላልን በቀር ከጥንት ጀምሮ በተላለፈው ትውፊት ሦስቱ መላእክት የሦስቱ ሕጻናት ጠባቂ መላእክት ነበሩ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ሦስት ሆነው ይቅርና አንድም ሰው ቢሆን ሦስትና ከዚያ በላይ መላእክት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ዮናታን ወልደ ሳዖል ‹‹ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና›› /1ሳሙ 14 6/ እንዳለው በአንድም በብዙ ማዳንም የእግዚአብሔር ፈቃድና ምስጢር እንጂ የማነስና የመብዛት ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንኳን በመላእክት ቃል ኪዳን ተቀብለው በሚያማልዱና በሚያድኑ ሰማዕታትና ቅዱሳንም ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸ መሆኑን ከተለያዩ ገድላት መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ አሣ አስጋሪ ሰው  መርምህናም ( ማር ምህናም፤ ቅዱስ ምህናም ማለት ነው) እርዳኝ እያለ ሲጠራ  ‹‹ ወበጊዜሃ መጽአ ኅቡረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅዱስ መርምሕናም ተፅኢኖሙ ዲበ አፍራሲሆሙ ....›› ተብሎ እንደተገለጸው ቅዱስ ጊዮርጊስም አብሮ ተገልጾ እንደረዱት የሚነግር ተአምር በገድለ ጊዮርጊስ ተአምሩ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በዋናነት ሊገለጽ የሚችለው በገድለ መርምሕናም እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡  ስለዚህ በቅዱሳን ዘንድ አንዱ ብቻ ነው እንጂ ሌሎቹ የሉም የሚያስብል ታሪክም ድርጊትም የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ልዩነት ያለ የሚመስለን መገለጦችን የምንረዳበት ሒደት አነስተኛ ሲሆን ብቻ ነው፡፡


 ይህ ከሆነ ታዲያ በሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ገብርኤል ጎልቶ ለምን ይወጣል? በዓል ሆኖ የሚከበረው ለቅዱስ ገብርኤል፤ በሥዕልም ላይ አራተኛው ተብሎ በናቡከደነጾር የተገለጸው ሰው የቅዱስ ገብርኤል ሥዕል ሆኖ የሚሣለው ለምንድን ነው? የሚለው የሰሞኑ ጥያቄ መልስ የመጨረሻው ክፍል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ዝም ብሎ ወይም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥጋዌውን አስቀድሞ የገለጸው መላእክትንም  በሰው አምሳል እንዲገለጹ በማድረግም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ለሙሴ መጀመሪያ የተገለጠለት በዚሁ መንገድ ነበረ፡፡  ‹‹ የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ ›› /ዘጸ 32/ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ ይህም ግን ነገረ ተዋሕዶን የሚስረዳ የምስጢረ ሥጋዌ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመላእክት አምሳል ሲገልጥ ደግሞ ቅድሚያውን ስፍራ የሚይዘው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ምክንያቱም ገብርኤል ማለት ቃለ እግዚአብሔር እንዲሁም ሰውና አምላክ ማለት ስለሆነ ነው፡፡ እመቤታችንን ሊያበስር የተላከውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለናቡከደነጾር ሥጋዌውን ‹‹ አራተኛ ሰው አያለሁ›› እስኪል ድረስ ሰውነቱን በመገለጥ ያሳየው ከሦስቱ ሊቃነ መላእክት ይህን ምስጢር በስሙም በተልእኮም ቅዱስ ገብርኤል የተሸከመው በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም ሦስቱም ሊቃነ መላእክት በጠባቂ መላእክትነታቸውና ረቂቃን ኃይላት በመሆናቸው ቢኖሩም እግዚአብሔር ሊገልጠው ለፈለገው ታላቅ ምስጢር ተስማሚ የሆነውን (ራሱ ገብርኤል መሆኑ ትርጉምና መልእክት ያለው ነውና) መልአክ በአምሳለ ወሬዛ ኀየል ወይም የነገሥታትን ልጅ በሚመስል መንገድ የንጉሠ ሰማይ ወምድር የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ምሳሌ ሆኖ እንዲገለጽለት አደረገ፡፡ በዓሉ ለእርሱ የተሠጠውና ሥዕሉ የእርሱ የሆነበት ምክንያትም ይኸው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ቅድሰት ተዋሕዶ ይህን ሁሉ ምስጢር እንዲህ ባለ ታላቅ ሥርዓተ በዓል እንዲከበር በሥዕልም እንዲታይ በማደረግ ነገረ ሠጋዌውንም የሕጻናቱን ተጋድሎም የመላእክቱንም ጠባቂነት ስትገልጽበትና ስታስረዳበት ትኖራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምልዓት መረዳት ያለው በእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት ትውፊትና ሥርዓተ አምልኮ ጸንታ በምትኖረው ቅድስት ተዋሕዶ ነው፡፡  የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ አማላጂነት የሊቃነ መላእክቱ ጥበቃና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃ አይለየን፤ አሜን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡


© ይህ ጽሑፍ በቀጥታ ከዲ/ን ብርሃነ አድማስ የመጽሐፈ ገጽ አድራሻ የተወሰደ ነው፡፡

4 comments:

  1. መነሻ ጥያቄው
    ድርሳነ ሚካኤል ድርሳነ ገብርኤል እና ድርሳነ ራጉኤል ላይ አለ የሚል ነው:: አሁን ደግሞ ድርሳነ ሩፋኤል ላይም አለ? ታዲያ 4 ከሆኑ 4 ጠባቂ መላክ ለ 3 ሰው አይሆንም ወይ?? ይህ የጽሁፍ ስህተት ነው ወይስ?? እባካችሁ መልስ ስጡበት??

    ReplyDelete
    Replies
    1. Dear Anonymous! Have u read this? Check it again. ...እንኳን ሰዎቹ ሦስት ሆነው ይቅርና አንድም ሰው ቢሆን ሦስትና ከዚያ በላይ መላእክት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ዮናታን ወልደ ሳዖል ‹‹ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና›› /1ሳሙ 14 ፤ 6/ እንዳለው በአንድም በብዙ ማዳንም የእግዚአብሔር ፈቃድና ምስጢር እንጂ የማነስና የመብዛት ጉዳይ አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንኳን በመላእክት ቃል ኪዳን ተቀብለው በሚያማልዱና በሚያድኑ ሰማዕታትና ቅዱሳንም ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸ መሆኑን ከተለያዩ ገድላት መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ አሣ አስጋሪ ሰው መርምህናም ( ማር ምህናም፤ ቅዱስ ምህናም ማለት ነው) እርዳኝ እያለ ሲጠራ ‹‹ ወበጊዜሃ መጽአ ኅቡረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅዱስ መርምሕናም ተፅኢኖሙ ዲበ አፍራሲሆሙ ....›› ተብሎ እንደተገለጸው ቅዱስ ጊዮርጊስም አብሮ ተገልጾ እንደረዱት የሚነግር ተአምር በገድለ ጊዮርጊስ ተአምሩ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በዋናነት ሊገለጽ የሚችለው በገድለ መርምሕናም እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በቅዱሳን ዘንድ አንዱ ብቻ ነው እንጂ ሌሎቹ የሉም የሚያስብል ታሪክም ድርጊትም የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡

      Delete
    2. Thanks. I have read it now and it makes sense.

      Delete
  2. Egezabere yestlen LEMENFEKAN TRU MELSE NEW.

    ReplyDelete