Pages

Tuesday, September 10, 2013

የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር - ክፍል 2

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ መስከረም 1 ቀን፥ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ዐውደ ዓመት
  ዐውደ ዓመት ማለት በፀሐይ 365¼ ዕለት፥ በጨረቃ 354 ዕለት ነው፡፡ ከፀሐይ ወሮች ዐጽፈ አውራኅ፥ ከጨረቃ ወሮች ደግሞ ሕጸጸ አውራኅ ይገኛል፡፡ ዐጽፈ (ድርብ፣ ዕጥፍ) አውራኅ ማለት በየወሩ 30 ቀን በሱባኤ ሲቀመር (ለሰባት ሲከፈል) የሚቀረው 2 ቀን በሌላው ወር ተደምሮ የሚቈጠር ስለሆነ ነው፡፡ ጨረቃ በዕለት፣ በ15 ቀን፣ በወርና በዓመት የምታጐድለው ቀንና ሰዓት ሕጸጽ ይባላል፡፡ ለምሳሌ በፀሐይ አቈጣጠር አንድ ወር 30 ቀን ሲሆን በጨረቃ ግን አንዳንዴ 29 ይሆናል፡፡ ይህ ጨረቃ ከፀሐይ የምታጐድለው አንድ ቀን ነው ሕጸጽ እያልነው ያለነው፡፡ ስለዚህ በፀሐይ አቈጣጠር ዐዲስ ዓመት መስከረም 1 ሲሆን በጨረቃ አቈጣጠር ግን ነሐሴ 24 ወይም ነሐሴ 25 ይሆናል ማለት ነው፡፡ [ጨረቃ ለ6 ወራት 29፣ 29 ትሆናለች፡፡ ስለዚህ 6 ቀን ታጐድላለች ማለት ነው፡፡ 5 የጳጉሜንን ዕለታትንም ጨምራ ስታጐድል በጠቅላላ 11፥ በየአራት ዓመት ደግሞ 12 ቀናት ታጐላለች፡፡ በዚህም ምክንያት በጨረቃ አቈጣጠር ዐዲስ ዓመት ነሐሴ 24 ወይም በየአራት ዓመት ነሐሴ 25 ይሆናል ማለት ነው፡፡]


ክፍላተ ዘመን
                                   
 
  ክፍላተ ዘመን ሲባል አንዱ ዓመት ተከፍሎ የሚያስገኛቸው ወቅታት እንደማለት ነው፡፡ ሊቃውንቱም ዓመቱን በአራት ከፍለዉት እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችጊዜ፣ወር፣ዘመን የተከፈሉ ናቸው፡፡ አንዱን ዓመት በአራት ክፍለ ዘመን በመክፈል ድርሰቱን ውሱን አድርጎታል፡፡ ዘመኑም እንዲሁ በድርሰቱ የተወሰነ ነው፡፡ እነዚህም ዘመናት ዘመነ መፀው፣ ዘመነ ሐጋይ፣ ዘመነ ጸደይ፣ ዘመነ ክረምት በመባል ይታወቃሉ፡፡ በዝርዝር ስናያቸው፡-

ሀ.
ዘመነ መፀው፡- በሌላ አነጋገር ጥቢ ይባላል፡፡ ጥቢ መባሉም እንደ ሌሊት ከብዶ የሚታየው ክረምት አልፎ መስከረም ከጠባ በኋላ 4ኛው ሳምንት ስለሚጀምር ነው፡፡ ዘመነ መፀው ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡ የዕለቱ ቊጥርም 90 ይሆናል፡፡ ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ በመሆኑ ዘመነ ክረምትን በማስቀደም ፅጌንና መፀውን በማስተባበር ቅዱስ ያሬድ የሚከተለውን ብሏል፡-ግሩም በሆነው ኃይልህ እንመካ ዘንድ አንተ ዘመናትን ሠራህ፤ ክረምትን ለዝናባት መፀውን ለአበቦች ሰጠህ” /ድጓ ዘጽጌ፣ ኩፋሌ 2፣ ኢዮ.2÷23፣ ኤር.524/፡፡ መፀው መሬት በክረምት የተሰጣትን ዘር አበርክታ፣ አብዝታ ለፍሬ የምታደርስበት የምርት ወቅት ነው፤ መፀው በአብዛኛው የአዝመራ መሰብሰቢያ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን በዋናነት ሦስት ወራት ያገኛሉ፡፡ እነርሱም ጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ ናቸው፡፡ ይህ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር አበቦች በየሜዳው በየሸንተረሩና በየተራራው ፈክተው የሚታዩበት አዝርእት የሚያሸቱበትና ለፍሬ የሚበቁበትን ወራት ይዞ ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ መዓልት እያጠረ ሌሊት እየረዘመ ይሔዳል፡፡ በመሆኑም ከዚህ 3 ሰዓተ ሌሊት ይገኛል፡፡

ለ.
ዘመነ ሐጋይ፡- ይህ የበጋ ወቅት ነው፡፡ሐጋይ”- በጋ ሆነ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ ይህም ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ የዕለቱ ቊጥርም 90 ነው፡፡ ሐጋይ (በጋ) የጥርን፣ የየካቲትንና የመጋቢትን ወር ይይዛል፡፡ ዘመነ ሐጋይ የቃሉ ትርጓሜ ዘመነ ፀሐይ ማለት ሲሆን ሥርወ ቃሉም ኃገየ ከሚለውግዕዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ የሐጋይ ፍቺ በጋ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም መፀውም ጸደይም በእርሱ ስም በጋ ይባላሉ፤ዘጠኝ ወር በጋእንዲሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍት ዓመቱን በሁለት ከፍለው ይናገራሉ፡፡ክረምትና በጋን አንተ ሠራህበበጋም በክረምትም እንዲህ ይሆናል” እንዲል /መዝ.7517 ዘካ.1410 ዘፍ.1022/፡፡ ኃጋይ ማለት መገኛ መክረሚያ በጋ፣ ፀደይ፣ ደረቅ ወቅት ማለት ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት በመፀው ያሸተውና ያፈራው መኸር የሚታጨድበት፣ የሚሰበሰብበትና በየማሳው ከተከመረ በኋላ የሚበራይበት፣ በጎተራ የሚከተትበት በመሆኑየካቲትየሚለውን ወር ይዞ እናገኘዋለን፡፡ የግብርናው ኅብረተሰብ እህሉን በጎተራው ከትቶ ለተወሰነ ጊዜ የሚያርፍበት በመሆኑ የዓመት በዓላት እንደ ልደት፣ ጥምቀት ያሉትና ዘመነ መርዓዊ የሚባለው የጋብቻ ዘመን በዚህ ወቅት የተካተቱ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ መዓልቱም ሌሊቱም ዕሩይ (ትክክል) ነው፡፡

ሐ.
ዘመነ ጸደይ፡- የቃሉ ትርጉም ዘመነ በልግ ማለት ነው፡፡ ይህም መጋቢት 26 ቀን እስከ ሰኔ 25 ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ የዕለቱ ቊጥርም 90 ይሆናል፡፡ ጸደይ በበጋና በክረምት መካከል የሚገኝ በውስጡ የሚያዝያን፣ የግንቦትንና የሰኔ ወራትን የያዘ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም ጸደይ የሌሎች ወቅቶችን ባሕርያት አሳምሮ የያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል የበልግ አዝመራ የሚታጨድበት፣ የሚወቃበትና የሚዘራበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለክረምት የሚዘራ ማሳ የሚታረስበት (ለዘር ዝግጁ የሚሆንበትን) ጊዜ ነው፡፡ በአብዛኛው ግን ዘመነ በልግ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓውይሁብ ዝናመ ተወን - የበልግ ዝናምን ይሰጣል” እንዳለው የበልግ ወቅት ነው፡፡ ይህም ወቅት በልግ አብቃይ በሆነው የሀገራችን ክፍል የበልግ አዝመራ የሚዘራበት፣ በልግ አብቃይ ባልሆነው ክፍል ደግሞ መሬት ለክረምቱ የዘር ጊዜ የሚያዘጋጅበት ነው፡፡አንድ ሰኔ የነቀለውን ሁለት ሰኔ አይተካውምእንደሚባለው የግብርናው ኅብረተሰብ ቀጣይ የግብርና ሥራውን በትጋት የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ክፍለ ዘመን መዓልት እየረዘመ ሌሊት እያጠረ ስለሚሔድ በጠቅላላ 3 ሰዓተ መዓልት ይገኛል፡፡

መ.
ዘመነ ክረምት፡- ማለት ዘመነ ውሃ ማለት ነውና በዚህ ዘመን ውኃ ይሰለጥናል፡፡ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለውን ጊዜ ይይዛል፡፡ የዕለቱ ቊጥርም 95 ይሆናል፡፡ ክረምት በውስጡ አራት ወራትን (ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ጳጉሜንና መስከረም) የያዘ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድያረሁ ክረምተ በበዓመት፣ ይሰምዑ ቃሎ ደመናት - በየዓመቱ ክረምትን ያገባል፤ ደመናትም ቃሉን ይሰሙታልሲል በድጓው እንደነገረን የዘመናት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር በየዓመቱ አዙሮ የሚያመጣልን ወቅት ነው፡፡ ደመናትም ለቃሉ ትእዛዝ ተገዢዎች በመሆን ዝናመ ምሕረቱን ጠለ በረከቱን የሚያወርዱበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ክፍለ ዘመን መዓልቱም ሌሊቱም እኩል ነው፡፡
 ከላይ እንደተመለከትነው በዓመት ሙሉ ያገኘናቸው 3 ሰዓተ ሌሊትና 3 ሰዓተ መዓልት ተደምረው በአራት ዓመት አንድ ዕለት ይሆናሉ፡፡ በየአራት ዓመቱ ጳጉሜን 6 የምትሆነውም ከዚሁ የተነሣ ነው፡፡

 
ዓመተ ወንጌላውያን

 ዓመተ ወንጌላውያን ማለት ዓመተ ዓለም ለአራት ክፍል ሲገደፍ (ሲከፈል) ትርፍ ሆኖ የሚገኘው ዓመት ነው፡፡ ክፍያው እኩል ሆኖ ምንም ባይተርፍ ያን ጊዜ ወንጌላዊው ዮሐንስ ጳጉሜንም 6 ትሆናለች፡፡ ከክፍያው አንድ ዓመት ቢተርፍ ግን ወንጌላዊው ማቴዎስ ነው፤ ጳጉሜንም 5 ትሆናለች፡፡ 2 ዓመት ቢተርፍ ወንጌላዊው ማርቆስ፣ ጳጉሜን 5 ትሆናለች፡፡ 3 ዓመት ቢተርፍ ወንጌላዊው ሉቃስ፣ ጳጉሜን 5 ትሆናለች፡፡ ለምሳሌ የ2006 ዓ.ም. በዘልማድ ወንጌላዊው ማርቆስ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በርግጥ ለማወቅ ግን አሠራሩ እንደሚከተለው ነው፡፡ ዓመተ ዓለም፡ 5500+2006=7506 ዓመታት ይሆናል፡፡ 7506 ለ4 ስንገድፈው (ስናካፍለው) 1876 ሲሆን ቀሪው 2 ዓመት ይሆናል፡፡ ስለዚህ 2 ዓመት ስለተረፈ ወንጌላዊው ማርቆስ ነው ማለት ነው፡፡ የሌሎች ዓመታትም የምናወጣው በዚሁ መንገድ ነው፡፡

የበዓላትና አጽዋማት አወጣጥ መንገድ

ይህ ዘዴ የምንፈልገውን ዓመት በዓላቱና አጽዋማቱ መቼ እንደሚገቡ የምናውቅበት ዘዴ ስለሆነ አስቀድመን ይህን ለመሥራት ምን ማወቅ እንዳለብን እንማማራለን፡፡ ቀጥለንም መንገዱን እናይና የ2006 ዓመተ ምሕረትን እንደ ምሳሌ በመውሰድ አጽዋማቱንና በዓላቱን እናውጃለን፡፡
 በዓላቱንና አጽዋማቱን ለመቀመር (ለማስላት) እነዚህን ማወቅ አለብን፡-
·        አዕዋዳቱን እናስታውሳቸው፡፡
·        አየዓርግንና ኢይወርድን ልናውቅ ይገባል፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በዓል/ፆም
ኢይወርድ (ታሕታይ ቀመር)
ኢየዓርግ (ላዕላይ ቀመር)
ፆመ ነነዌ
ጥር 17
የካቲት 21
ዐቢይ ፆም
የካቲት 1
መጋቢት 5
ደብረ ዘይት
የካቲት 28
ሚያዝያ 2
ሆሣዕና
መጋቢት 19
ሚያዝያ 23
ስቅለት
መጋቢት 24
ሚያዝያ 28
ርክበ ካህናት
ሚያዝያ 20
ግንቦት 24
ዕርገት
ግንቦት 5
ሰኔ 9
ጰራቅሊጦስ
ግንቦት 15
ሰኔ 19
ፆመ ሐዋርያት
ግንቦት 18
ሰኔ 22
ፆመ ድኅነት
ግንቦት 18
ሰኔ 22
መጥቅዕ
መስከረም 15
ጥቅምት 13
ፍስሕ (የአይሁድ ፋሲካ)
መጋቢት 25
ሚያዝያ 23

·        ሊቃውንት “ሠለስቱ ጥንታት ሀለዉ ውስተ ባሕር - ሦስቱ ጥንቶች በዘመን ውስጥ አሉ” እንዲሉ ሁልጊዜ ጥንታትን ልንረሳ አይገባም፡፡ እነርሱም ጥንተ ቀመር (ማግሰኞ)፣ ጥንተ ዮን፣ ጥንተ ዕለት (እሑድ) ናቸው፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው ነው፡-

ጥንተ ቀመር
ጥንተ ዮን
ጥንተ ዕለት
1
ማግሰኞ
ረቡዕ
እሑድ
2
ረቡዕ
ኀሙስ
ሰኞ
3
ኀሙስ
ዓርብ
ማግሰኞ
4
ዓርብ
ቅዳሜ
ረቡዕ
5
ቅዳሜ
እሑድ
ኀሙስ
6
እሑድ
ሰኞ
ዓርብ
7
ሰኞ
ማግሰኞ
ቅዳሜ

·        ትንሣኤ ከአይሁድ ፋሲካ ቀድሞ መዋል የለበትም፡፡ የአይሁድ ፋሲካ ጥላ ስለሆነ ቀድሞ መምጣት አለበት፡፡
·        ፆመ ነነዌ፣ ዐቢይ ፆምና ፆመ ሐዋርያት ሁልጊዜ ሰኞ ይገባሉ፡፡ ርክበ ካህናት ከረቡዕ፣ ዕርገት ከሐሙስ፣ ስቅለት ከዓርብ አይወጡም፡፡ እንዲሁም ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤና ጰራቅሊጦስ ከእሑድ ውጪ አይውሉም፡፡


አሁን ደግሞ በዓላቱንና አጽዋማቱን የምናወጣበት መንገድ እንመልከት፡፡
 ለጊዜው በዓላቱንና አጽዋማቱን የምናወጣበት መንገድ በጣም ቀላሉንና ሊቃውንቱ “የጭዋ ትምህርት” የሚሉትን እንጠቀማለን፡፡ ከባዱንና ውስብስቡን መንገድ ለማወቅ ፍላጐቱ ያላቸው አንባብያን ግን የባሕረ ሐሳብ መጻሕፍትን በማንበብና ከሊቃውንቱ እግር ሥር በመማር ማዳበር ይችላሉ፡፡
·        ዓመተ አበቅቴ = ዓመተ ዓለም ፥ ዐውደ ቀመር (532)
               = ቀሪው ቊጥር ፥ ዐውደ አበቅቴ
               = ቀሪው ቊጥር
·        ወንበር= ዓመተ አበቅቴ - 1
     ወንበር ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳት እኔ የተወለድኩት ሰኔ 29 ቀን 1976 ዓ.ም. ነው፡፡ 2006 ዓ.ም. ላይ 30 ዓመቴ ይሞላኛል፡፡ ይሔ ማለት ግን 29ኙን አጠናቀቅኩ (ሙሉ ለሙሉ እንደ ወንበር ተቀምጬበት) ለማለት እንጂ 30ኛውን ጨረስኩት ማለት አይደለም፡፡
·        አበቅቴ= [ጥንተ አበቅቴ x ወንበር] ፥ 30
·        ዓመተ ፀሐይ= ዓመተ ሥጋዌ ፥ ዐውደ ፀሐይ [28]
             = ቀሪው ቊጥር
·        ዕለተ ምርያ= ዓመተ ፀሐይ
·        ሠግረ ዮሐንስ= ዓመተ ፀሐይ ፥ 4 (በየ4 ዓመት ስለሚመጣ ነው)
              = ከቀሪው ቊጥር ውጪ ያለው ውጤት
·        ዕለተ ዮሐንስ= [ዕለተ ምርያ + ሠግረ ዮሐንስ] ፥ 7 (ሱባዔ)
             = ቀሪው ቊጥር ስንት እንደሆነ አውቆ ከጥንተ ዮን ጋር ማመሳከር ነው፡፡
·        አበቅቴ + መጥቅዕ= 30
·        ዕለተ መጥቅዕ + 190= ፍስሕ [ፍስሕ= መጥቅዕ + 10]
·        ትንሣኤ ከፍስሕ ቀጥሎ ያለው እሑድ ይውላል፡፡ ፍስሕ ማለት የአይሁድ ፋሲካ የሚውልበት ቀን ማለት ነው፡፡
ከዚህ በታች የምናያቸው ቀመሮች ትንሣኤ ሲደመር የበዓላቱ ወይም የአጽዋማቱ ላዕላይ ቀመር (ኢየዓርግ) ነው፡፡ “ላዕላይ ቀመር (ኢየዓርግን)” ደግሞ የምናመጣው ከላይ ካየነው ሰንጠረዥ ነው፡፡ ይኸውም፡-
·        ፆመ ነነዌን ለማግኘት= ትንሣኤ  + 21
·        ዐቢይ ፆም= ትንሣኤ + 5
·        ደብረ ዘይት= ትንሣኤ + 2
·        ሆሣዕና= ትንሣኤ + 23
·        ስቅለት= ትንሣኤ + 28
·        ርክበ ካህናት= ትንሣኤ + 24
·        ዕርገት= ትንሣኤ + 9
·        ጰራቅሊጦስ= ትንሣኤ + 19
·        ፆመ ሐዋርያት= ትንሣኤ + 20
·        ፆመ ድኅነት= ትንሣኤ + 22 ይሆናል ማለት ነው፡፡

2006 .. የባሕረ ሐሳብ ቀመር ከላይ ባየነው መንገድ ስንቀምረውም እንደሚከተለው ይሆናል ማለት ነው፡፡
·         ዓመተ አበቅቴ = 7506 ፥ 532 (ዐውደ ቀመር)
               = 14 ዐውድ ደርሶ 58 ዓመት ይቀራል
               = 58 ፥ 19 (ዐውደ አበቅቴ)
              = 3 ዐውድ ዞሮ 1 ዓመት ይቀራል
ስለዚህ ዓመተ አበቅቴ= 1 ነው ማለት ነው፡፡
·        ወንበር= ዓመተ አበቅቴ - 1 ነው፡፡ 1-1= 0 (አልቦ)
·        አበቅቴ= [11 x 0] ፥ 30= 0 (አልቦ) 
·        ዓመተ ፀሐይ= 2006 ፥ 28 (ዐውደ ፀሐይ)
            = 71 ዐውድ ደርሶ 18 ዓመት ይቀራል
ስለዚህ ዓመተ ፀሐይ= 18 ነው ማለት ነው          
·        ዕለተ ምርያ= ዓመተ ፀሐይ ስለሆነ ዕለተ ምርያ 18 ይሆናል፡፡
·        ሠግረ ዮሐንስ= 18 ፥ 4
              = 4 በሌላ አገላለጽ በ18 ዓመት ውስጥ 4 ጊዜ 6ኛ ጳጉሜን አለች ማለት ነው፡፡
·        ዕለተ ዮሐንስ= [18 + 4] ፥ 7
             = 3 ደርሶ 1 አበቅቴ ፀሐይ ይተርፋል፡፡ አበቅቴ ፀሐይ 1 ነው ማለት መስከረም አንድ ረቡዕ ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ጥንተ ዮን ረቡዕ 1 ብሎ ጀምሮ ኀሙስ 2፣ ዓርብ 3 እያለ ስለሚሔድ፡፡ ከላይ ያየነውን ሰንጠረዥ ይመልከቱ፡፡
·        አበቅቴ + መጥቅዕ= 30 ነው፡፡
መጥቅዕ= 30 – 0
        = 30 መስከረም 30 ሆነ ማለት ነው፡፡
·        ፍስሕ= መጥቅዕ + 190
      = 30 + 190
      = 220 ይህም ማለት ከመስከረም ጀምረን 220 ቀን (6 ወር ከ10 ቀን) እንቈጥራለን ማለት ነው፡፡ ይኸውም ሚያዝያ 10 ይሆናል፡፡
·        ትንሣኤ ከፍስሕ ቀጥሎ ያለው እሑድ ነው፡፡ የመስከረም መባቻ ከሚያዝያ መባቻ ጋር ትክክል ስለሆነ ሚያዝያ 1 ረቡዕ ነው ማለት ነው፡፡ ሚያዝያ 10 ደግሞ ዓርብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ቀጥሎ ያለው እሑድ ደግሞ ሚያዝያ 12 ይሆናል፡፡ ስለዚህ የ2006 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ሚያዝያ 12 ይውላል ማለት ነው፡፡     
·        ፆመ ነነዌን ለማግኘት= 12  + 21 = 33 ስለዚህ የካቲት 3 ይገባል፡፡ 3 እንዴት አድርገን ቈጠርነው ሲባል ከ30 በማለፉ ነው፡፡ 31 ብለን የምንቈረው ወር የለምና ወደ ቀጣዩ ወር ይሻገራል፡፡
·        ዐቢይ ፆም= 12 + 5 = 17 ስለዚህ የካቲት 17 ይገባል፡፡
·        ደብረ ዘይት= 12 + 2= 14 ስለዚህ መጋቢት 14 ይሆናል፡፡
·        ሆሣዕና= 12 + 23= 35 ስለዚህ ሚያዝያ 5 ይሆናል፡፡
·        ስቅለት= 12 + 28= 40 ስለዚህ ሚያዝያ 10 ይሆናል፡፡
·        ርክበ ካህናት= 12 + 24= 36 ስለዚህ ግንቦት 6 ይሆናል፡፡
·        ዕርገት= 12 + 9= 21 ስለዚህ ግንቦት 21 ይሆናል፡፡
·        ጰራቅሊጦስ= 12 + 19= 31 ስለዚህ ሰኔ 1 ይሆናል፡፡
·        ፆመ ሐዋርያት= 12 + 20= 32 ስለዚህ ሰኔ 2 ይሆናል፡፡
·        ፆመ ድኅነት= 12 + 22= 34 ስለዚህ ሰኔ 4 ይሆናል ማለት ነው፡፡

ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment