Pages

Saturday, November 23, 2013

ጾመ ነቢያት

ገ/እግዚአብሔር ኪደ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፥ ኅዳር ፲፬ ቀን፥ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡-   በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
  “ጾም” በፊደላዊ ትርጕሙ- “ጾመ”፣ “ተወ”፣ “ታቀበ”፣ “ታረመ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ነው፡፡ የቃሉ ፍቺ ምግብ መተው፣ መከልከል፣ መታቀብ፣ መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ቃሉ በዕብራይስጥና በሱርስት ቋንቋዎች “ጻም” ሲባል በዐረብኛ ደግሞ “ጻመ” ይባላል፡፡ ስለዚኽ ጾም ማለት ለክፉ ሥራ ከሚያነሣሱ የምግብ ዓይነቶች በቤተ ክርስቲያን የሥርዓት መጻሕፍት ከተወሰነው ጊዜ ሳያጓድሉ መከልከል ወይም ለተወሰነ ጊዜና ሰዓት ሰውነት ከሚያስፈልገው ነገሮች ሁሉ መወሰን (መታቀብ) ማለት ነው፡፡

    የቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገሥት ጾምን እንዲኽ በማለት ይተረጕሟል፡- “ጾምስ በታወቀው ዕለት፣ በታወቀው ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው፡፡ ይኽም ዋጋውን ለማብዛት እርሱ ወዶ ሕግን ለሠራለት የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ሥጋም ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው” /ፍት.ነገ.አንቀጽ.፲፭/፡፡
   ሶርያዊው ቅዱስ ይስሐቅ ደግሞ፡- “ጾም ቁስለ ነፍስን የምትፈውስ፣ ኃይለ ፍትወትን የምታደክም፣ የበጐ ምግባራት ኹሉ መጀመርያ፣ የጽሙዳን ክብራቸው፣ የድንግልና የንጽሕና ጌጣቸው፣ የንጽሕና መገለጫ፣ የጸሎት ምክንያት እናት፣ የእንባ መገኛ መፍለቂያዋ፣ አርምሞን የምታስተምር፣ ለበጐ ሥራ ኹሉ የምታነቃቃ፣ ሰውነትን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ የምትደረግ መድኃኒተ ነፍስ ናት” ይላታል /ማር.ይስሐቅ. አንቀጽ ፬፣ ምዕ.፮/፡፡
 ስለዚኽ ጾም ማለት አንድ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በቀር ለማንም ወይም ለምንም የበላይ ኃይል ባርያ፣ ተገዥ ወይም አገልጋይ አለመኾኑን የሚያረጋግጥበት፣ በውስጡ ያሉትን የክፉው ወገን የኾኑትን የኃጢአት ጠንቆች አዳክሞ የበጐው ወገን የኾኑትን ጸጋዎች የሚያሰፍንበት፣ ማንኛውንም ዓይነት የነፍስ ፈተናና የሥጋ መከራ ተቋቁሞ የሚያሸንፍበት፣ ሃይማኖቱንና ምግባሩን የሚያጠናክርበት፣ የፍጹም ትዕግሥትና ተስፋ ባለቤት ለመኾን የሚበቃበት፣ የሥጋና የነፍስ አካላቱን በእውነተኛው ጤንነት የሚጠብቅበት ፍቱንና ኃይለኛ መሣርያ ነው ማለት ነው፡፡
  በሕገ ልቡና ከነበሩ አበው አንሥቶ በዘመነ ኦሪት እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በተለያዩ ጊዜአት የነበሩት ቀደምት አበው፣ ነቢያት፣ ነገሥታት፣ ካህናት በጾምና በጸሎት ጽሙድ ኾነው እግዚአብሔር አምላካቸው በይቅርታ እንዲጐበኛቸው ኃይሉን እንዲያጐናጽፋቸው ተማጽነውታል፡፡ የመዳናቸውን ቀን በመጠባበቅ የአባታቸውን የአዳምን ርስት ይወርሱ ዘንድ ተስፋ በማድረግ በጾምና በጸሎት ያሳልፉ ነበር፡፡
  በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት የታነጸችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም መጾም የሚችል ኹሉም እንዲጾማቸው መጀመርያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የደነገገቻቸው ፯ የዋጅ አጽዋማት አሏት፡፡ ከእነዚኽም አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ይኽ ጾም ከጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት አስቀድሞ የሚጾም ጾም ሲኾን በቤተ ክርስቲያናችን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡ የተወሰኑትን ለመግለጽ ያኽልም፡-
፩ኛ፡- ጾመ አዳም
 ይኸውም ለአዳም የተነገረው ትንቢት የተፈጸመበት ጾም በመኾኑ ነው፡፡ አዳም የማይበላውን በልቶ አምላኩን ባሳዘነ ጊዜ በፈጸመው በደል ተጸጽቶ ይጾም ይጸልይ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ከልብ የኾነ ጸጸቱንና ዕንባውን በራሱ መፍረዱንም አይቶ “ከአምስት ቀን ተኵል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወለጄ አድንኀለሁ” የሚል ተስፋ ድኅነትን ሰጠው /መጽ.ቀሌምንጦስ/፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜም ከዘመኑ ዘመን፣ ከወሩ ወር፣ ከዕለታቱ ዕለት፣ ከሰዓታቱ ሰዓት ሳያጓድል የአዳም የልጅ ልጅ ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ /ገላ.፬፡፬/፡፡ በመኾኑም ጾሙ የተሰጠው ተስፋ የተቆጠረውም ሱባዔ ስለ ተፈጸመበት “ጾመ አዳም” ይባላል፡፡
፪ኛ፡-ጾመ ነቢያት
 ይኸውም ነቢያት የተናገሩት ትንቢት የተፈጸመበት ስለኾነ ነው፡፡ በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ በምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ ትንቢት ተናገሩ፤ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ጾሙ፤ ጸለዩ /ኢሳ.፶፰፡፩/፡፡ ለተናገሩት ትንቢት ፍጻሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑ /ማቴ.፲፫፡፲፯/፡፡ በየዘመናቸው “አንሥእ ኃይሌከ ፥ ፈኑ እዴከ” እያሉ ጮኹ /መዝ.፻፵፬፡፯/፡፡ በጾም በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራት፣ በዓመታት ቈጠሩ /ዳን.፱፡፳፮/፡፡ እነዚኽ ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ባይፈጸምም “እግዚአብሔር አያደርገው አይናገር፤ የተናገረውንም አያስቀር” ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ /ዕብ.፲፩፡፲፫/፡፡ በመኾኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት “ጾመ ነቢያት” ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔር ሰው መኾን ያስተማሩበት ስለኾነም “ጾመ ስብከት” ይባላል፡፡
፫ኛ፡- ጾመ ሐዋርያት
 ሐዋርያት “ትንሣኤን ዓቢይ ጾምን ጾመን እናከብራለን፤ ልደትንስ ምን ሥራ ሠርተን እናከብራለን?” ብለው ከልደተ ክርስቶስ በፊት ያሉትን ዕለታት ጾመውታል፡፡ በመኾኑም “ጾመ ሐዋርያት” ተብሎ ይጠራል፡፡ 
፬ኛ፡- ጾመ ፊልጶስ
 ሐዋርያው ፊልጶስ ወደ አፍራቂና አውራጃ ኹሉ ወጥቶ በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተማረ፡፡ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አደረገ፡፡ ብዙዎችን እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሰ፡፡ በብዙ ሀገሮች እየተዘዋወረም የከበረ ወንጌልን አስተማረ፡፡ ብዙዎች በትምህርቱ ሲያምኑ ያላመኑት ግን ከንጉሡ ዘንድ ተመካክረው መከራ አጸኑበት፡፡ እርሱ ግን “ከዘለዓለም ሕይወት ስለምን ትርቃላችሁ? የነፍሳችሁንስ ድኅነት ስለምን አታስቡም?” ይላቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን ልቡናቸው ደንድኗልና በብዙ መከራ አሰቃዩት፡፡ በመጨረሻም ኅዳር ፲፯ ቀን ዘቅዝቀው ሰቀሉት፡፡ ሥጋዉን በእሳት ሊያቃጥሉት በወደዱ ጊዜ ግን እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ሥጋዉን ከእጃቸው ነጠቃቸው፤ እያዩትም ወስዶ ሠወረው፡፡ ይኽንንም ተመልክተው ስለ ገደሉት ተጸጽተው ያዘኑና ያመኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሱባዔ ይዘው ሥጋዉን ይመልስላቸው ዘንድ ቢጾሙና ቢጸልዩ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀበለና በ፫ኛው ቀን መለሰላቸው፡፡ እነርሱም በፍጹም ደስታ አሳረፉት፡፡ ይኽን ያዩ ብዙዎችም ወደ እምነት ገቡ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን “ጾሙን ጀምረን አንተወውም” በማለት እስከ ልደት በዓል ጾሙት፡፡ ስለኾነም “ጾመ ፊልጶስ” ይባላል፡፡
፭ኛ፡- ጾመ ማርያም
 ይኸውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስለ ጾመችው ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ እንደምትወልደው ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ትሑት ናትና “ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልዷለሁ?” ስትል ጌታን ከመውለዷ በፊት ጸሟለችና “ጾመ ማርያም” ይባላል፡፡
   እንግዲኽ በጥቂቱም ቢኾን ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረ አባቶቻችን ነቢያት ሐዋርያትም ጾመዉት በረከት አግኝተውበታል፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ስለ ትሕትናዋ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም! በመኾኑም የቤተ ክርስቲያን አባቶች ምእመናን ጾመን እንድንጠቀምበት ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ይኽን ሥርዓት በመያዝ ባለፉት ዘመናት የነበሩት ምእመናን ጾመዉት በረከት አግኝተውበታል፡፡ ዛሬም እንጾመዋለን፡፡ ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይኹንና ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ መጥቶ ለእያንዳንዱ  እንደ ሥራው በሚያስረክብበት ጊዜ በቀኙ እንዲያቆመንና “እናንተ የአባቴ ብሩካን” ብሎ መንግሥቱን ከሚያወርሳቸው ቅዱሳኑ ጋር እንዲደምረን “አምላከ ነቢያት ወሐዋርያት፣ አምላከ ጻድቃን ወሰማዕታት ተለመነን” እያልን እንጾሟለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ጾማችን ጾመ ድኅነት ያድርግልን፡፡ አሜን!!!
ዋቢ መጻሕፍት
፩. ጾምና ምጽዋት፣ በዲ/ን ቃኘው ወልዴ፤
፪. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ታሪክ፣ በብጹዕ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ፡፡


2 comments:

  1. ቃለ ሂዎት ያሰማልን ተባረኩ !!!!!!

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወትን ያሰማልን

    ReplyDelete