Pages

Thursday, January 9, 2014

ለመላው ኦርቶዶክሳውያን ፦ ታላላቅ የአንድነት የስብከትና የዝማሬ ጉባኤያትን ስለማዘጋጀት - ጥቆማ



በታምራት ፍሰሓ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ጥር ፪ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- ኦርቶዶክሳዊት እምነታችን በብዙ መስክ (በቅዳሴ በማህሌት በሰአታት በሰርክ ጉባኤያት በበዓላት ዝግጅቶች) በልዩ ስርአት ወጥነት ሐዋርያዊ መሰረተ እምነቷን ለምእመናን ስታስተላልፍ ቆይታለች አሁንም በማስተላለፍ ላይ ትገኛለች፤ በቅዳሴው ለተካፈለ በማህሌቱም ለተሳተፈ በሰአታቱም ለተገኘ በሰርክ ጉባኤውም ላልቀረ ይህ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን በነዚህ ተገኘን? ካልተገኘንስ እንደምን እምነታችንን ልናውቅ በእምነታችንስ ልንፀና ይቻለናል?

ብዙወቻችን ደግሞ የቤተክርስቲያን ታላላቅ በዓላትን (ደመራ ጥምቀት) መሰረት በማድረግ ተገኝተን እናከብራለን ይህም በጣም ብዙ ኦርቶዶክሳዊ በአንድነት የሚገናኙባቸው ክስተቶች ቢሆኑም ነገር ግን እኒህ ልዩ በዓላት እንደመሆናቸው የራሳቸው የሆነ የአከባበር ስርአትና ይዘት ያላቸው በመሆኑ በዚህ ጊዜ ለሚገኙ ምእመናን የሚገባውን ያህል ትምህርት ሰጥተው የሚያልፉ አይደለም ይልቅስ በነዚህ በዓላት ጥቂት ከመዘመርና በዓሉን የመታዘብ ያክል ከተመለከትን በኅላ ወደቤታችንም ሆነ ወደሌሎች ጉዳዮች የምንመለስ ብዙወች ነን፡፡ ስለዚህም ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በአንድነት ተሰባስበን የቤተክርስቲያናችንን ስብከቷን ዝማሬዋንም ሆነ ልዩ ልዩ ሃሳቦቿን የምንረዳባቸው የምንሳተፍባቸውና የምንወያይባቸው መድረኮች የሉንም፡፡


ይህም ብቻ አይደለም በተለይ ራሳቸውን ኦርቶዶክሳውያን ብለው የሚጠሩ ነገር ግን ቤተክርስቲያን ቀርበው ለመማር ብዙ ጉዳዮችን ከፊት አኑረው ምክንያትን የሚያበዙ ባለፀጎች ታዋቂወችና ኩሩወች እየበዙ ሲመጡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን እኒህን ልታንፅበት ወደልቦናቸው ልትመልስበት ቃለ እግዚአብሄርን ልትመግብበት ዝማሬ መስዋእትን እንዲያቀርቡ ልታበረታታበት የሚያስችል ልዩ መድረክም ያስፈልጋታል በአለማዊ ፀጋቸው እግዚአብሄርን አክብረው እንዲያልፉ በአለማዊ ታዋቂነታቸው ክርስቶስን በህይወት እንዲሰብኩ በኩራታቸውም ትህትና እንዲሞላበት ሞግዚታቸው እናት ቤተክርስቲያን በእኒህ ላይ ሳትፈርድ (አትፈርድምና) እነሱ ባይመጡ እሷ ወደነሱ ሄዳ ልትስባቸው የሚገባ ነው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም በልዩ ልዩ ምክንያት ከኦርቶዶክሳዊነት ተለይተው በፕሮቴስታንቱም ሆነ በሌላው እምነት እያነከሱ ያሉ የቤተክርስቲያንን ጥሪ በእጅጉ እየናፈቁ አንድም ስብከቷን ትምህርቷን ዝማሬውን ሊያደምጡ የሚጓጉ በተረዳም እውቀት ወደቤታቸው ሊመለሱ የሚከጅሉ ብዙ ልጆቿን ሳያውቋት የሄዱባትን እምነት አውቀዋት እንዲመለሱላት የምትጠራበት የምታስተምርበት የምትመክርበት በጥበብም ልጆቿን የምትስብበት ልዩ መድረክ ያስፈልጋታል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰወች ወደቅፅረ ቤተክርስቲያን ለመግባት ቢያፍሩ ቢፈሩ አንድም ቢጠሉና ቢፀየፉ ስብከቷን ግን ባገኙት አጋጣሚ መስማትን ይናፍቃሉና እኒህን ሞግዚት እናት ቤተክርስቲያን ልታይ ይገባታል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም አንዳንድ ጊዜ ቤተክርስቲያን ፊቷን ወደልማት ስለምን አታዞርም? የሚሉ ሰወችን እሰማለሁ ለምን ድሆችን አሰባስባ አትረዳም ወላጅ አልባ ህፃናትን ሰብስባ ለምን አታሳድግም? አረጋውያንን ለምን አትጦርም? ጤና ኬላ ሰርታ ስለምን ለምስኪኖች የነፃ ህክምና አትሰጥም? ስግብግብ በሆነ ትውልድ መካከል ስለምን አታበራም? የሚሉ ስለቤተክርስቲያን አስበው ፊታቸውን ቅጭም የሚያደርጉ ኦርቶዶክሳውያንን አስተውያለሁ እኔም ብሆን ራቁቱን መሬት ላይ ወድቆ ያለውን ምስኪን ልብስ ሳታለብስ በወርቅ የተንቆጠቆጠ አብያተ ክርስቲያናትን ብታንፅ ይህ ለክርስቶስ ምኑ ነው? ስል በድፍረት እናገራለሁ የአብነት ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ ቤተክርስቲያናት ውስጥ ፋውንቴን ቢተከል ይህ በምን መስፈርት ክርስቲያናዊነት ነው? ብየ እጠይቃለሁ ነገር ግን ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንዲህ አይደለችም የተቀበለችው ያለችበትም መንፈስ ይህ አይደለም እንዲያውም የድሆች ቤት ናት እንጂ በአለማዊ ህክምና ገንዘባቸው ያለቀባቸውን ምእመናን ሰብስባ በነፃ ፀበሉ ፈውሳ ወደቤታቸው ትልካለች በትምህርት ቤት ውድነት የተማረሩ ወላጆችን ልጆቻቸውን ሰብስባ በነፃ ታስተምራለች ቤቷ ለሁሉ ክፍት ነው ድሆች ይረዱበታል ህሙማን ይፈወሱበታል አይብዛም እንጂ የህፃናት ማሳደጊያወች አሏት አይብዛ እንጂ የአረጋውያን መጦሪያወች አሏት አይብዛ እንጂ ጤና ኬላወች አሏት አይብዛ እንጂ ድሆችን መርጃወች አሏት ነገር ግን ሊሰራ ከሚገባው አንፃር ይህን ስንመረምር አሁን ያለውን እንደሌለ ልንቆጥር ይገባናል፡፡

ስለዚህ ለዚህም የሚሆን ገቢ ቤተክርስቲያኗ ያስፈልጋታል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም በሃገራችን ኢትዮጵያ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ህሊናቸው ተነቃቅቶ ሰናይ ምግባራትን በመከወን ላይ ያሉ ጥቂትም ቢሆኑ ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኞችን እያየን ነው እንደሜቄዶንያ ሜሪ ጆይ አበበች ጎበና ጌርጌሲዮን የወደቁትን እናንሳ ወዘተ እኒህ ሁሉ የክርስቶስን ፈቃድ የሚፈፅሙ የቤተክርስቲያናችን ፍሬወች ሲሆን ቤተክርስቲያን ደግሞ ከምእመናን ጋር በመሆን ልታግዛቸው ልታበረታቸው እንዲህም የመሳሰሉ ሌሎች ብዙ እንዲቋቋም ይፋዊ እውቅና ልትሰጣቸው የሚገባ ነው፡፡ ይህም ለምስኪኖች ታላቅ ደስታ ለክርስቶስም ውዳሴ ለክርስቲያኖችም መነቃቃት እጅግ ይጠቅማልና ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ባለራእዮችን ከባለፀጎች ጋር የቀረቡትን ከራቁት ጋር ደካሞችን ከብርቱወች ጋር የምታገናኝበት የምታዋድድበት መድረክ ያስፈልጋታል፡፡

ሌላስ ምን ቀረ? ብዙ ልትጨምሩበት ትችላላችሁ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ መሳካት ጥቂትም ቢሆን ገንዘብ ተከፍሎባቸው እጅግ ብዙ ምእመናን የሚሳተፍባቸው (እንደ ሚሊንየም አዳራሽ ባሉ ቦታወች) እንዲህ ያሉ ታላላቅ ስራወችንም የምንሰራባቸው መድረኮች ቤተክርስቲያናችን ያስፈልጓታል ይህንንም ወር በገባ በመጀመሪያው እሁድ ቢደረግ ማንንም የሚጎዳ አይመስለኝም ምእመናን በስብከት በመዝሙር ይታነፁበታል ለበጎነት ይነቃቁበታል አረጋውያን ይጦሩበታል ድሆች ይታሰቡበታል ህሙማን ይረዱበታል የጠፉት ይመለሱበታል ክርስትናም ትደምቃለች፡፡ ይህ ቢሆን የቤተክርስቲያናችን ወርቃማ ጊዜ እንደተመለሰ ብንናገር ስህተት እንሆን ይሆን?

ይህን ስል ግን ተያይዘው የሚመጡ አንዳንድ ተቃርኖወች ሊኖሩ እንደሚችሉ አልዘነጋሁም ነገር ግን ሁሉ በፍቅርና በስርአት በበጎነትና በታማኝነት እስከተከናወነ ድረስ ብፁአን አባቶቻንን ከፊት አስቀድመን በኦርቶዶክሳዊው ስርአት እየተመላለስን ታላቅ ስራን ልንፈፅም እንደምንችል አምናለሁ፡፡ ለዚህ መሳካት እንደማህበረ ቅዱሳን ደጆችሽ አይዘጉና የሰንበት ተማሪወች አንድነት ጉባኤ መሰል ማህበራት የቅድሚያ ሃላፊነቱን ቢወጡ መልካም ነው እላለሁ፡፡

ዘመኑን ዋጁ!!!

የክርስቶስ ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment