Pages

Wednesday, March 12, 2014

ምኩራብ ዘሐሙስ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 3 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ

 ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

 ከልዑላን ይልቅ ከፍ ከፍ በሚል፣ በቅዱሳን ዘንድ በሚቀደስ፣ በትጉሃንም በሚመሰገን፣ ከሀዲዎችን በዘለዐለማዊ ቀኝ ክንድ በሚገለባብጥ፣ አምኖ ስሙን ለሚጠራው የመትጋትን ኃይል በሚያደርግለት፣ አፍ ሁሉ አንደበትም ሁሉ በሚያመሰግነው፣ ጉልበትም ሁሉ በጊዜ እና በዘመናት ሁሉ በሚሰግድለት በእግዚአብሔር ስም ለዘለዓለሙ ሰላም ለእናንተ ይሁን (መጽሐፈ ምስጢር)፡፡

 አንትሙሰ ከመዝ ንቡ ውስተ ይእቲ ሃገር እለ ሥዩማን . . . እናንተስ በዚህች ሀገር የተሾማችሁ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እንደዚህ ተናገሩ፤ ለእግዚአብሔር ለጽዮን ምስጋና ይገባል፡፡ዛሬ ዜማውን ድርሰቱን የጀመረው ለሊቃውንቱ ትጋትን በማስተማር ነው፡፡ ዘወትር የምስጋናው ወተት ከሚፈስባት ቅድስት ጽዮን ቤተክርስቲያን ያለድካም ሆናችሁ ከዚህ ዓለም ተለይታችሁ ወደ ላይ ከፍ ብላችሁ አመስግኑ፡፡ እሷ ነገሥታት የሚገዙላት የንግስናቸው ጌጥ፣ የመንግስታቸው መድኃኒት፣ በወርቅ እና በዕንቁ በከረከዴን የተሸለመች ናትና፡፡

 ኃይለ ለጥበብ ክርስቶስ ጽንዕ ሃይማኖት . . . የጥበብ ኃይሉ ክርስቶስ፣ የሃይማኖት ጽናት ኢየሱስ የቤተክርስቲያን መሠረት መስቀል ነው፡፡

 ዜመኛው ይቀጥላል፤ይገብር ነግሀ ወያበርህ ለኩሉ በታሕተ ሰማይ . . . ከሰማይ በታች የልመናውን መልስ ይሰጠዋል፡፡የአእምሮአችንን ብርሃን እንደጠዋት ጎህ ብሩህ ያደርገዋል፡፡ በመልካምም ቀናችንን እንውል ዘንድ በመንገዳችን ሁሉ መሰናክልን አይሰጠንም፡፡ ሁሉ የእርሱ ነውና ያለመጠራጠር እንዲቀበል ሆኖ የለመነውን ሁሉ ከሰፊው እጁ ይሰጠዋል፡፡ በቤቱ የሚለመነውን ልመና ቸል አይልም፤ አይኖቹም ጆሮዎቹም በዚያ ናቸውና፡፡

 ኩሉ ዘጌሠ ወመጽአ ሃቤሃ ኢይጻሙ. . . ወደ እሷ የመጣ የገሠገሠ ሁሉ ዋጋውን አያጣም፡፡ይህ የእርሱ ቃል ነው፡፡ አንሽረውም፤ እንጠቀምበታለን፡፡ አንረሳውም፤ እንድንበታለን፡፡

 በከመ ይቤ ዕንባቆም አቅርንት ውስተ እደዊሁ . . . ዕንባቆም እንዳለ ጨረር ከእጁ ወጥቷል፤ ኃይሉም በዚያ ተሰውሯል፡፡ ጸዳሉም እንደ ብርሃን ነው፡፡ በኢየሩሳሌም በሰቀሉት ጊዜ በጨለማ ውስጥ ሳለን ብርሃን ሆነ፡፡ በመስቀሉም ሕይወታችን ሆነ፡፡ያን ጊዜ በሰቀሉትም ሰዓት ጨለማ ሆነ፡፡ ጨለማ ያለፈውን የጨለማ ዘመን እንዳንረሳ ምልክት ሆነን፡፡ ቀን ብርሃን ሲሆን ጨለማ ያሸነፈዋል፡፡ በመስቀሉ ግን የተሰጠን ብርሃን ማታ ጨለማ የለባትም፡፡ አይነጋም ለዘለዓለም ያበራል፡፡ ይህ ብርሃን የአብ ልጅ፣ የአብ ቀኝ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን ከእጁም ያበራልን የፍቅር ብርሃን ነውና፡፡ ልዩ የሆነ የፍቅር ስጦታ ነው፡፡

  በከመ በወንጌል አኃዝዎ ለኢየሱስ ወአስተብረኩ ቅድሜሁ . . . በወንጌል እንዳለ ኢየሱስን ያዙት፤ በፊቱ እጅ ነሱ (ሰገዱ)፡፡ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ ስምኦንን ግድ አሉት፤ ስሙ ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ሀገር አደረሱት፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው፡፡ መጠን የሌለው ቸርነት የኢየሱስ ትዕግስቱን መሬት መሸከም አልቻለችም፡፡ስለዚህ ነገር እኔ ልናገር እንዴት ይቻለኛል? ጽሑፌ ንግግሬ ምድራዊ የሚታይ ነው፡፡ ትዕግስት ትህትና ግን የማንሸከመው ነው፡፡ በቃ ከሊቁ ጋር ብቻ እናዚመው፡፡ ይህንን የጌታ ፍቅር ሊቁ ካሰበ በኋላ ራሱን እንደ ደካማ ይቆጥርና የወንድሞቹን መልካም ጸሎት እንዲህ ይጠይቃል፡፡አኃውየ ፍቁራንየ ሰላም ለክሙ ዝክሩኒ በጸሎትክሙ . . . የተወደዳችሁ ወንድሞቼ! ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ በጸሎታችሁ አስቡኝ፡፡ የጻድቅ ሰው ጸሎትና ልመና ብዙ ትረዳለች፡፡ በረከትን ትወርሱ ዘንድ በሃይማኖት ጸንታችሁ ቁሙ፡፡ቆመው ራሳቸውን ተኝተው እንዳገኙት ሳይሆን በዕምነት አንተን እንድንመስል አቤቱ ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው በጸሎትህ በምልጃህ አስበን፡፡

  አንተ እግዚኦ ተአምር ኩሎ ፈኑ ተፋቅሮ እስመይእቲ ትባልሕ . . . አቤቱ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፡፡ ከሞት የምታድነውን ፍቅር ላክልን፡፡ የምንሄድበትን ትክክለኛውን መንገድ ምራን፡፡

 በመጨሻምወሰላመ እግዚአብሔር እንተ ኩሉ ባቲ . . . ሁሉ ያለበት የእግዚአብሔር ሰላም ዘወትር ከእናንተ ጋር ትኑርአሜን፡፡
ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ፡፡ አሜን! በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment