Pages

Thursday, March 20, 2014

መጻጉዕ ዘዓርብ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 11 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 እስከሞት ድረስ በወደደን፤ ስለፍቅር በሞተልን፤ በዚያች ቀን በቀኙ ባለው በኩልዛሬ ከእኔ ጋር ናችሁ” ባለን፤ የእርሱን የምሕረት ቃል ከመስማት የበለጠ ደስታ በሌለን፤ 30 ዘመን ፍቅሩ የሺህ ዘመን ኃጢአታችንን በደመሰሰልን፤ የምሕረቱን ጥልቅነት በሰውኛ ቋንቋችን ልንገልጸው በማንችለው፤ በመስቀሉ ደም ቤዛችን በሆነን፤ ነፃነትና ሰላምን ባጎናጸፈን ሰላም ለእናንተ ይሁን::


  ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ለቤተክርስቲያን ርኢክዋ አዕመርክዋ አፍቀርክዋሮሜ ሀገር ሄጄ ቤተክርስቲያንን አየኋት፣ አወቅኋት፣ ወደድኳት፣ እህቴ እንደሆነች በጎ ነገር አሰብኩ:: ከረጅም ዘመን በኋላ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዳግመኛ አየኋት:: በጢግሮስ ወንዝ ትታጠባለችበማለት የእለቱን ዜማ ይጀምራል:: ቤተክርስቲያንን ሮሜ ሀገር ሄጄ አየኋት ስለአየኋትም ፍቅሯ ሳበኝ:: አሁን እርሷን እንደ እህቴ አልለያትም፤ እርሷን ያገባትንም ጌታ እንዲሁ::

  ገብረ ብርሃናተ አበይተ ባሕቲቱብቻውን ታላላቅ ብርሃናትን ፈጠረ (አደረገ) ለፀሐይ ቀንን አስገዛው፤ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና በሁሉ ዘንድ ንጉሥ ነው:: ይቅር ባይ እግዚአብሔር ይለምኑ ዘንድ ይወዳል::” የሚለምኑትን የሚሰማ፣ ብርሃናትን በሕይወታችን ያደረገ፣ እንደ ፀሐይ በርቶ ለትንሿ ጽድቃችን ድምቀትን የሰጠ ዛሬ እናመሰግነዋለን፤ እንደ መቋሚያዎቹ ግራ ቀኝ እያልን:: እንደ ካህናቱ ያለ እንቅልፍ በመሆን ሌሊቱን ሁሉ ከእርሱ ምሕረትን እንለምናለን::

 ብርሃን አንተ እግዚኦ ዘኢትጸልም ዘበሥላሴከ አመድካአንተ የማትጨልም ብርሃን ነህበሦስትነትህ ምድርን ለካሃት:: የነገሥታት ንጉሥ አሸናፊ ቀላዮችን የዘረጋህ የሚያስፈራውንም የወሰንህ ይኸውም በተመሰገነ ስምህ ነው::” ነገሥታትን አትመስላቸውም፤ አንተ ብቻህን የነገሥታቱ ንጉሥ ነህና:: አስፈሪውን ሁሉ በስምህ እናሸንፋለን:: ስምህን ስንጠራ የተናዳፊዎች መርዝ ውሃ፣ የጠላት ጦር ዕውር፣ የእኛ ፊት ብሩህ ይሆናል:: እንደ አባታችን ሙሴ በሰጠኸን በትር ሁሉን እናሸንፋለን:: ይኸውምነሲዐየ ማዕተበ ዘወልደ እግዚአብሔርየእግዚአብሔርን ልጅ ምልክት ይዤ በሥላሴ ስም አማትባለሁ:: ብወድቅም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱሥ ስም አማትቤ እነሳለሁ፤ በመስቀሉ ኃይል እመካለሁ::” በላዪዋ ላይ መስቀል ከበታቿም የመሥዋዕቱ መንበረ ታቦት ያለባት ቤተክርስቲያን ምንኛ ያማረች ናት::

 መፍቀሪተ ገዳም ሥነ ሕንፃሃድኅነትን የምትወድ ሕንፃዋ ያማረ በሮቿ በሥላሴ ስም የታተሙ በመለኮት ጨው ምግቧ የጣፈጠ ሰፊ አደባባዪዋ ሰላም የሞላበት ነው::” ምንኛ በጸጋ ላይ ጸጋ ያለባት ቤት ናት:: ጉልላት መስቀል የሐዲስ ኪዳን መስዋዕት በታች ታቦት መሠዊያ:: በዚህች እመቤት ፊትበጽባሕ ትብጻሕ ጸሎትየ ቅድሜከበጠዋት ጸሎቴ ወደ አንተ ትድረስ አምላኬ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ በምሕረትህ አስበኝ፤ የልመናዬን ድምጽ አቤቱ ስማ፤ የባሪያህን ጩኸት አትናቅ፤ ነፍሴ ለዘለዓለም ታመሰግንሃለች::”

  ወደተለመደው የጾም ነገራቸንም እንዳንወጣ:: “በገቢረ ምሕረት ቀድሱ ጾመምሕረትን በማድረግ ጾምን ቀድሱ፤ ከልቡናችሁ ቂምን አስወግዱ፤ አስቀድማችሁ የእርሱን መንግስት እሹ፤ በምሥጋና የተሰራ ልብሱን ትለብሱ ዘንድእያለ ያስታውሰናል:: “እናንተስ” ይላል በሚመስጥ፣ ይህንን ዓለም ለቀን ወደ አርያም በሚወስደን ዜማ!እናንተስ ስትጾሙ ራሳችሁን መርምሩ:: ከበሮ እንዲመታላችሁ፣ መለከት እንዲነፋላችሁ በአደባባይ ራሳችሁን አትግለጡ:: አብዝታችሁ አባታችሁ በሚያውቀው ብቻ ጹሙ፤ እርስ በእርሳችሁ ተፋቀሩ:: የጾም አላማው የክርስትናም ግቡ ይህ ነውና:: እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ:: ማንም ከወገኑ ጋር በቁጣና በሃሜት አይኑር፤ ጽድቁንና ሰላሙን ፈልጉ፤ ከምሥጋናም ፈጽሞ ራሳችሁን አትለዩ::”

 በመጨረሻም በዛሬዋ ዕለት መጋቢት 27 ቀን ጌታ ተሰቅሎ አዳነን፡፡ከመ ኪያነ ያድኅነነ እሞት ሰፍሐ እደዊሁ ቅዱሳተ ዲበ ዕፀ መስቀልእኛን ከሞት ያድነን ዘንድ ቅዱሳት የሆኑ እጆቹን በእንጨት መስቀል ዘረጋ፡፡ ከመ ይተሐፈር ጸላኢ ወይኅጣዕ ዘይነብብ ቃለ ኀሡ በላዕሌነ በመስቀሉ ቤዘወነ ትምህርተ ሰላምነ አልቦቱ ዘይክል አህድጎተነ ፍቅሮ ለክርስቶስጠላት እንዲያፍር በእኛ ላይ ክፉ ነገር የሚናገረው እንዲያጣ በመስቀሉ ዋጀን፡፡ መስቀል የሰላም ምልክታችን ነው፤ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን የለም፡፡ የመስቀሉን ፍቅር ያሳድርብን፡፡” አሜን!

No comments:

Post a Comment