Pages

Thursday, March 27, 2014

ደብረዘይት ዘዓርብ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 18 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ሹመት የእርሱ በሆነ፣ መላእክቱን ለምስጋና በሚያሰልፍ፣ የነፍስ ረቂቅነት ግዙፉ በሆነ፣ ልባችንና ኩላሊታችን በሚታወቅበት፣ ዳግም ለሰው ልጆች የንስሃ ጊዜን በሚሠጥ፣ በደረቀ ሕይወት ዝናሙን በሚያዘንም፣ እውነተኛ የጽድቅ ጎዳና በሆነው በክርስቶስ ስም ሰላም ይሁንልን::


 ይሴፎ ሰብእ ይርከብ ተስፋሁተስፋውን ያገኝ ዘንድ ሰው ተስፋ ያደርጋል (ይታመናል) በፈጣሪውም ተስፋ ያደርጋል፤ ዐይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ፤ አቤቱ ለሚታገሱት አንተ ኃይል ነህ::” ተስፋ ነገን የምናይባት የአምላክ ስጦታ ነች:: ሰው ሁሉ ለበጎ ይሆን ለክፉ በዚህ ዓለም ሥርዓት የሚመላለሰው ተስፋ ስላደረገው ነገር ነው:: ይልቁንም አምላክን ተስፋቸው ያደረጉ ተስፋቸውን አያጡትም:: በሥጋው ተስፋ የቆረጠ ሥጋውን ይገድላል፤ በነፍስም ተስፋችን እርሱ ካልሆነ ነፍሳችን ቀይ ምልክት ውስጥ ናት:: ቅዱስ ያሬድ ተስፋ እንዳላቸው ነፍሳት እንድንመላለስ ይነግረንና የጠዋት ምሥጋናውን ለቤተክርስቲያን ይሠጣል:: ብርሃን ቤተክርስቲያን የቅዱሳን መዓዛ፣ የሰማዕታት እናት፣ የሁሉ መድኃኒት ወደ አንቺ የመጣ ሁሉ አይደክምም፤ ዋጋውን ያገኛል እንጂ::

  በጼወ መለኮት ቀሰሙ አለምሃ ውስተ ቤተ መርዐበነገረ መለኮት ጨው ዓለምን አጣፈጡ፤ በሙሽራው ቤት ሰላምን አፈሰሱ፤ ሐዋርያት ርጉም ጠላትን ከሕዝብ አስወገዱ፤ ድንቅ የሆኑ ተዓምራትን አሳዩ:: ለጻድቃን ብርሃን ወጣ፤ ሞገስ አላቸውና፤ እንደ ድካማቸው ዓለምን ይዋረሳሉ፤ የግዮን የጤግሮስ የኤፍራጠስ ዘይት ወንዝ አዲስ ምድርን አወረሳቸው::” አሥራ ሁለት ሆነው አልጫውን ዓለም ጣዕም ሠጡት፤ በስሙ ዓለሙን ሁሉ የጽድቅ ቀለም ቀቡት፤ በመስቀል ስለተሠጠው ደስታ ዞረው የምሥራች ሰበኩ::

 ክርስቶስምአውሥአ ኢየሱስ በምሳሌ ወይቤሎሙበምሳሌ መልስ እንዲህ አላቸው እውነት እውነት እላችኋለሁ በትዕግስታችሁ ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጋላችሁ:: ለእናንተ ገነት ተከፈተ፤ የሕይወት እንጨት ተተከለ፤ መላእክት ነፍሶቻችሁን ይጠብቃሉ፤ ሥጋችሁንም በማይጠፋ አዲስ ምድር ይኖራል፤ እናም አይጠፋም::” ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ ደዌ እና ሕማም የሌለበትን ቅድስት ሃገር አወረሳቸው:: ትዕግስትን እንከተላት፤ ጾማችንን በትዕግስት እንጨርስ፤ ያን ጊዜ በክብር ከፍ ከፍ እንላለን::

 ያወጽኦሙ ለአኃው እንተ አንቅዕተ ማያትወንድሞችን ወደ ውሃ ምንጮች ይወስዳቸዋል፤ ቅዱሳን ምድርን ይወርሳሉ፤ ወደ ሕይወትም ይሄዳሉ::… የክርስቶስ መስቀልስ ለባሪያዎች ነፃነት ለሚያምኑት ሰላም ነው:: መስቀል የተቸገረን ይረዳል:: የመስቀሉን ሰላም ይስጠን:: አሜን!!!

No comments:

Post a Comment