Pages

Thursday, March 6, 2014

ቅድስት ዘዐርብ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ የካቲት 27 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ

ጸልዩ እምቅድመ ንባበ ዝንቱ ክርታስ

 በመስቀሉ ፍቅር ተስባችሁ፣ በሞተ ወልዱ ተቀድሳችሁ፣ በጎኑ ውሃ ፍሳሽነት ታጥባችሁ፣ ለእርሱ የተሰጣችሁ የቅዱሳን ወዳጆች የእናታችሁ ልጆች ሰላምና ፍቅር እናንተን ይክበባችሁ በማለትእለቱን ድርሰት ከአባታችን ጋር እነሆ፡፡


 አቤቱ የሰው ልጅ የህይወቱ ጅማሬ ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ነው፡፡ ዕድገቱ ሌሊት ከቀን ከእናቱ ጋር የእናቱን ጡት እየጠባ ነው፡፡ እንዲሁ ከሥላሴ የተወለደ ዕድገቱ ሌሊትም ቀንም ከእናቱ ከቤተክርሰቲያን ጋር ነው፡፡ ሳይጸልይ የሚወጣ የተሸነቆረ ጀልባን እንደሚቀዝፍ ሰው ነውና ቀናችንን በቤቱ በሌሊት በመገሥገሥ በጸሎት እንድንጀምር ሊቁ ይነግረናል፡፡ወአንተሰ ጊስ ሀበ እግዚአብሔር ጸሊ ወትረ ወኢትናፍቅ ለጸሎትአንተስ ወደ እግዚአብሔር ገስግስ፤ ሁልጊዜ ጸልይ፤ ጸሎትን አትጠራጠር፤ ታምነህ በሰማያት ያለህ አባታችን እያልክ ጸልይ፡፡ተሰናብቶን አልቀረም፤ በዐርብ ደግሞ እንዲሁ በጠዋት ተነስተን በቤተክርስቲያን በሚደረግ ጸሎት ቀናችንን ቀድሰን እንጀምር ዘንድ ይለናል ፡፡ እኛም በጸሎት ጀምረናል፤ አሁንም ቢሆን ከጸሎት አንለይ፡፡

 በብረሀንከ ንርአይ ብርሀነበብርሃንህ ብርሃንን እንይ፤ ሰውን ወዳጅ ክርስቶስ ሆይ! በእውነት ፊትህን እንይ፡፡ አቤቱ ፍርድህ እውነት እንደሆነ አወቅሁ፤ ከብዙ ወርቅ እና ብር የአፍህ ሕግ ይሻለኛል፡፡ ስምህ እውነት ነው፡፡” “ከእኔ በጎ ሥራ የአንተ ቸርነት እንዲበልጥ አሁን አውቄያለሁ፡፡ ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ከብዙ እውቀትና ክብር ከብዙ ውበትና ደም ግባት ከብዙ መልካም ሥራ ሁሉ የአንተ ቸርነት እንዲበልጥ አሁን አውቄያለሁ” እያለ በትህትና ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ያዜምልናል፡፡ እኛም ይህንን እንደግማለን፤ የተገባ መልካም ሥራ ነውና፡፡

 ከዚህ በኋላ እንደ ሌላው ቀን ድርሰቱ ቤተክርስቲያንን ሲያወድስ ቆይቶ ወደ ወድሶተ መስቀልመስቀል ብሂል…” ብሎ ይጀምራል፡፡መስቀል ብሂል ዕፀ ሕይወትመስቀል ማለት ዕፀ ሕይወት ማለት ነው፡፡ ዕፀ ሕይወት ማለት ክቡር ደሙ የነካው ዕፅ ክቡር አይደለምን? ከሁለቱ ዕፀ መስቀሎች በደሙ ቀድሶ አላከበረውንም? ከፍ ከፍ አላደረገውምን?” ብሎ ክብሩን ከገለጠልን በኋላ ይህ በደሙ የከበረ ዕፀ መስቀል ደግሞ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ፡-መስቀል ተስፋ ቅቡጻንመስቀል ተስፋ ለቆረጡ ተስፋ፣ የዓለም ሁሉ ህይወት ሆነ፡፡ ለምናምን ለእኛ ደስታችን፣ ለነገሥታት ውበትና ክብር፣ የቤተክርስቲያን መሠረት፣ የባህር ፀጥታዋ፣ የመርከብም ፀጥታ መስቀል ነውበማለት ለመስቀል ያለንን ክብር ሌሎች እንደሚሉት ድንገት በዘመን እኩሌታ ያልተጨመረ ትምህርተ አበው እንደሆነ ነገረን፡፡

 አሁንም ዕለቱ ዐርብ ነውና የጌታ ህማም የጌት ስቅለት እንዴት እንዲታሰብ ስለመስቀል እየነገረን ያነቃቃናል፡፡ወንድሞቼ” ይለናል፡፡ “መስቀል ብርሀን መያጢሆሙ ለሐጥአንመስቀል ብርሀን፣ ሐጥአንንም የሚመልሳችው፣ በገነት ውሰጥ ያለ፣ ምስጋናን የለበሰ፣ በሰማያት ያለ፣ አዳም የበላው ዕፅ ይሳለሙት ዘንድ ወረደ፡፡በእንጨት ያጣነውን ልጅነት በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መለሰልን፡፡ አሁን እንጨትን አንረግምም፤ እንሳለምዋልን እንጂ ፡፡


 ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው በዚህ ጾም ጊዜ መፋቀርን እንድናፀና አብዝቶ ይመክረናል፤ ይመርቀናል፡፡አሐውየ ሠናያን አሐውየ ፍቁራንየመልካም ወንድሞቼ! የምወዳችሁ ወንድሞቼ! ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር በጾምና በጸሎት ስትገዙ በመካከላችሁ ሰላምና ፍቅር ይብዛ፡፡ ወደ አምላካችን ሀይማኖታችንን እናጽና፡፡ ልባችንን እናንጻ፡፡ ወንድሞቼ በሙሉ ልባችሁ ተፋቀሩ፡፡ መፋቀር ሁሉን ይሸፍናልና፡፡ በሀይማኖት የጸናችሁ ሁኑ፡፡ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፡፡ ወንድሞቻችሁ የሚሏችሁን ተቀበሉ፡፡ አቤቱ እውነትን በሰላም ያጸናሀት ምራኝ በሰላምም በፊትህ ልቁምእያለ ራሳችንን በእምነት በፍቅር እንኖር ዘንድ ይመክረናል፡፡

 እኔም በአጭሩ ሳይገባኝ የጻፍኩላችሁን ቃሉን ዜማውን ትሰሙ ዘንድ እያልኳችሁ ያለ ቁጣና ክፉ ሀሳብ የተቀደሱ እጆቻችንን አንስተን እንጸልይ ብዬ በአባቴ ምርቃት እሰናበታችኋለሁ፡፡ጸውዖ ስሞ ለክርስቶስ ወበመስቀሉ ይቀድሰክሙ ክርስቶስ የሀሉ ምስሌክሙየክርስቶስን ስም ጥሩ፤ በመስቀሉ ይቀድሳችሁ፡፡ ክርስቶስ በመካከላችሁ ይኑር፡፡ ሰላምና ደኅንነት በመካከላችሁ ይሁን፡፡ ማኅበራችሁን ቀድሱ፡፡ የወንድማችሁን በደል ተዉለት፡፡ በመስቀሉ ኃይል ይጠብቃችሁ፡፡ የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን፡፡” አሜን፡፡

 ለእርሱ ልጅነት የማልበቃ ደካማ ስሆን የማይገባኝን ነገር ስለፃፍኩ ስለእኔ ፀልዩልኝ አሜን በጾሙ ሰላምን ይስጠን ጾሙን በሰላም ያስፈጽመን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ይጠብቀን፡፡

No comments:

Post a Comment