Sunday, March 16, 2014

መጻጉዕ ዘሠኑይ



በዲ/ን ስመኘው ጌትዬ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መጋቢት 7 ቀን፣ 2006 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

 ከባሕሪዩ በማይለወጥ በእግዚአብሔር አብ ስም፣ ከአባቱ በማይለይ በእግዚአብሔር ወልድ ስም፣ በአንደበቱ እስትንፋስ ነቢያትን እፍ ባለባቸው የጸጋውንም ወንጌል ይሰብኩ ዘንድ በተሰጠ ሰረገላዎችም ይሆኑት ዘንድ በእነርሱ ባደረ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስም ሰላም ለሁላችሁ ይሁን::


 በትረ ኃይል ይፌኑ ለከ እግዚአብሔር እምፅዮንየኃይል በትር እግዚአብሔር ከፅዮን ይልክልሃል፡፡ በጠላቶች መካከል ትገዛለህ (ትፈርዳለህ)፡፡ ከክፉ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ይጠብቅህ፡፡ እንደ ዳዊት ያለ ሞገስ በእግዚአብሔር ፊት ይስጥህ::” አሜን! በማለት ቅዱስ ያሬድ የዚህ ሳምንት የሰኞ ድርሰቱን እየመረቀን ያዜምልናል፡፡ እኛም ይህ የሚገባ ነውና አሜን ብለናል:: ከዚህ በኋላ እንደ ሌላው ጊዜ ቤተክርስቲያንን ሰላም ብሎ የዚህ ሳምንት ምስጋናውን ይጀምራል::

 አፍቅርዋ ተዐሥየከ ዑዳ ወታሌዕለከውደዳት፤ ዋጋህን ትሰጥሃለች፡፡ ዙራት፤ መድኃኒት ቤተክርስቲያን ከፍ ታደርግሃለች::” “አፍቅርዋ” አለን:: እኛ ያለፉትን ሳምንታት አብረን ስናወድሳት፣ በእርሷም ዘንድ ስንቆይ ሰንብተናል:: የሚያውቁትን ይልቁንም ያለ ቅድመ ሁኔታ የወደደንን ይበልጥ በቤቱ ስናውቀው ፍቅር በውስጣችን ያድጋል:: ከሩቅ ሆኖ የማያውቁትንእወዳለሁ” ማለት ራስን ማታለል ነውና:: ስለዚህ ቀርበን ቤተክርስቲያንን ስንሳለማት ስንዞራት ዕለት ዕለት አብረናት ስንሆን ፍቅሯ ያድርብናል::

 መሐሪ ወትረ ወመፍቀሬ ሰብእዘወትር ይቅር የምትል (ምሕረትህ የበዛ) ሰውን የምትወድ ክርስቶስ ስምህ ለዘለአለም የተመሰገነ ነው:: በትዕዛዝህ ንጋት ጠዋት ተሠርቷል…፡፡” “ስምህ ከስሞች ሁሉ ጣፋጭ የሆነ፣ በሚገድሉህ ፊት የዘለዓለም ይቅርታን ያደረግህ፣ ሳንወድህ የወደድከን፣ ስንርቅህ የቀረብከን፣ ጠፋን የለንም ስንል ያልተውከን ከታወቀውም ከተሰወረውም በደላችን ይቅር በለንእያልን ከሊቁ ጋር እናዜማለን:: ወገኖቼ ይህንን ዜማ እኮ እዛው ቤተክርስቲያን ብንሰማው ምንኛ ነፍሳችን በረካች! ምንኛ ወደ አምላክ ከፍ ከፍ ባልን ነበር::

 እንደ ፀሐይ ከሩቅ የምታበራዋን የእስራኤል ዘነፍስ እናት መንገድ የሆነችውን ቤተክርስቲያን አብዝቶ ያወድሳል:: የእርሷንም ራስ ክርስቶስ እንዲሁ:: “ብርሃነ ብርሃናት ፈጣሬ አዝማናት እስዕለከየብርሃኖች ብርሃን፣ ዘመናትን የፈጠርክ ጸሎቴን ትሰማ ዘንድ እምነቴንም ትቀበል ዘንድ እለምንሃለሁ::” የዐይናችንን ሳይሆን የልባችንን ብርሃን፣ የአካላችንን ሳይሆን የሕሊናችንን፣ የነፍሳችንን ብርሃን ከጨለማ ለይልን::

 ከመ በንጹሕ ንጹም ጾመበንጹሕ ጾምን እንጾም ዘንድ ጌታችን ስለ እኛ ጾመ:: ምሳሌነቱንም ይሠጠን ዘንድ ጾምን ስለ እኛ አከበራት::” ነቢያት የጾሙትን 40 ቀን ጾም ሳይሽር ለእኛ ጾሞ አስረከበን:: ስለዚህም ከታላላቅ ሐጣውእ እንድን ዘንድ በንጹሕ ጾምን መጾም ይገባናል::

  በወልታ ዚአከ ከለልከነ ሃሉ መዐልተ ምስሌነበአንተ ጋሻነት ከለልከን፡፡ ቀን ከእኛ ጋር ሌሊትም በመካከላችን ሁን፡፡ አቤቱ ከእኛ አትራቅ፡፡ በሁላችን አፍ እናመሰግንሃለን::” የምሕረቱን ጥልቅነት አንመረምረው፤ እንዲያው በቸርነቱ እንድንኖር እድሜ ሰጠን::

  ያበዝኅ ሣህሎ ዲበ እለ አበሱ ወለእመ ኢያብዝኃ ሣህሎበበደሉት ሰዎች ላይ ይቅርታውን ያበዛል፡፡ ይቅርታን ባያበዛ ኖሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነ ነበር::”

 በመጨረሻም መስቀሉን እንደተለመደው ካወደሰ በኋላ በሠላምታ ይሰናበተናል:: “ኖላዊነ ሔር ወመፍቀሬ ሰብእ ክርስቶስ ዘመርዔትሰውን የሚወድ ቸር ጠባቂያችን ክርስቶስ መንጋውን የሚረዳ በጎቹን የሚያድን ነው:: አምላካችን ሰላምን ስጠን እውነትን አስተምረን::” አሜን!

No comments:

Post a Comment

FeedBurner FeedCount