Pages

Tuesday, August 12, 2014

ማርያም ፊደል

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ ፯ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 እንኳን ለዓለም ኹሉ ደስታን ወዳመጣችው ዕለት አደረሳችኁ፤ አደረሰን፡፡ ነሐሴ ሰባት ቀን የባሕርያችን መመኪያ የምትኾን ንጽሕተ ንጹሐን፥ ቅድስተ ቅዱሳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችበት ዕለት ነው፡፡ ይኽቺን ዕለት ያልናፈቀ ትውልድ የለም፡፡ ጽድቃቸው እንደ መርገም ጨርቅ ለኾነባቸው ቅዱሳን አበው ወእማት ተስፋቸው የሚፈጸመው በዛሬው ዕለት በተጸነሰችው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ነውና፡፡ ቅድስትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችንም ከእግዚአብሔር ቀጥሎ እንደ እመቤታችን ከፍ ከፍ የምታደርገው ፍጥረት የሌለው ስለዚኹ ነው፡፡ ሊቃውንቱ፡- “ሐና አንቺን የጸነሰችበት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ቀን ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን  ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ቀን ናት፤” ብለው የሚዘምሩላትም ይኽን ምሥጢር በልቡናቸው ቋጥረው ነው /አባ ጽጌ ድንግል፤ ማኅሌተ ጽጌ ቁ.፵፬/፡፡

 አነሣሣችን ግን ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ጽንሰት ለመናገር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ቢወድና ቢፈቅድ ለዛሬ እንድንማማር የወደድኩት “ከእመቤታችን ሕይወት ምን እንማራለን? እመቤታችን “ታማልዳለች፤ አታማልድም” ከሚለው ክርክር በላይ ከሕይወቷ የምንማረው ነገር የለም ወይ?” የሚል መሠረተ ሐሳብን የያዘ ትምህርታዊ ስብከት ነው፡፡
 ተወዳጆች ሆይ! ክርስትና የሚኖሩት ሕይወት እንጂ የሚተርኩት ታሪክ አይደለም፡፡ ጌታችን በተራራው ስብከቱ ላይ፡- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” ያለን ስለዚኹ ምክንያት ነውና /ማቴ.፯፡፳፩/፡፡ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ለጊዜው በዛን ወቅት ለነበሩት ምዕመናን ለፍጻሜው ግን ለእኛ ለኹላችንም ከንግግሩና ከስብከቱ ጣዕም የተነሣ ሲያጨብጨቡለትና ሲያደንቁት ዐይቶ፡- “ልጆቼ! ስለምናገረው ንግግር ብታደንቁኝ ምን ያደርግልኛል? ስለ አሰባበኬስ ብታጨበጭቡልኝ ምን እጠቀማለኹ? እኔ የምጠቀመው ደግሞም የምማጸናችኁ በጽሞና እንድታደምጡኝና የምነግራችኁን ቃለ እግዚአብሔር ለማድረግ እንድትጣጣሩ ብቻ ነው፡፡ እንዲኽ ስታደርጉ ነፍሴ ስለ እናንተ ሐሴት ታደርጋለች፡፡ የምናገረውን ሳታደርጉ ስለ ንግግሬና ስለ አሰባበኬ ብቻ የምታደንቁ ከኾነ ግን ጥቅም የለውም” ነበር ያላቸው፡፡ ስለዚኽ ስለ እመቤታችን ከመናገር በላይ እመቤታችንን ለመምሰል እንደ ዓቅሚቲ መጣጣር የተሻለ ዋጋ አለው ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” እንዳለን ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ከመተረክ በላይ ቅዱስ ጳውሎስን ለመምሰል ልንተጋ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
 መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዐለማየኹ በአንድ ጕባኤ ላይ እንዲኽ ብለው ሲያስተምሩ አድምጫለኹ፡- “ቅዱሳን አባቶቻችን መጽሐፍ ቅዱሱን በአንድ ወገን፤ የትርጓሜ መጻሕፍትን በአንድ ወገን፤ የገድላትና የድርሳናት መጻሕፍትንም በሌላ ወገን አድርገው በብልት በብልት ከፋፍለው ያስቀመጡልን የድኅነት መንገድን ለማስረዘም አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን እንድናነበው፤ ቢጸንብን በትርጓሜአት እንድንረዳው፤ በገድላቱና በድርሳናቱ ደግሞ እንደምን ተግባራዊ እንደሚኾን እንድንገነዘበው እኛም በዚያ ሕይወት ለመመላለስ እንድንጣጣር ነው እንጂ፡፡” እውነት ነው!!! የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በአንድምታ ትርጓሜአትና በተለያዩ ድርሳናትና ተአምራት ተከፋፍሎ መቅረቡም ለዚኹ ዓላማ ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አንብበው የማይጨርሷት እጅግ ትልቅ መጽሐፍ ናት፡፡ ከአዕምሮ በላይ የኾነ፥ ግን ደግሞ የተፈጸመ ሕይወቷን ስናነበው የእኛንም ሕይወት ስናየው፥ “የእመቤታችን አምላክ ሌላ ነው እንዴ?” ያስብላል፡፡ እስኪ ለማንኛውም ምንም እንደ ርሷ ባንኾንም የዓቅማችንን ያኽል ክርስቲያን እንኾን ዘንድ እመቤታችንን እናንብባት፤ እንማርባትም፡፡
 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚያክል ንጹሕ ፍጥረት በሰማይም በምድርም ፈጽሞ የለም፡፡ እግዚአብሔር አብ በሰማያት ኾኖ ምሥራቁንና ምዕራቡን፣ ሰሜኑንና ደቡቡን ቢመለከት እንደ እመቤታችን ያለ ንጹሕ ፍጥረት አላገኘም፡፡ ንጽሕናዋ ልዩ ነው፡፡ “ወኢረኵሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በኅሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ - ከፈጠራት ዠምሮ በምንም በምንም ከድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አልተለወጠችም (አልበደለችም)” /ሃይ.አበ. ዘቴዎዶጦስ ፶፫፡፳፪/፡፡ ምንም ኀጢአት በሌለበት በሰማይ ለመላዕክት ያልተቻላቸውን ንጽሕናና ቅድስና፥ እመቤታችን እንደ ባሕር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት በደል በበዛበት ዓለም ኾና ኑሯለች፡፡ እመቤታችን በዚኽ ምድር በቆየችባቸው ፷፬ ዓመታት አንድም ቀን አልበደለችም፡፡ እኛ ከፈቀድን በኀጢአት ሥራ በተከበበ ቦታ፣ ክፋት በተንሰራፋበት መሥሪያ ቤት ወይም ትምህርት ቤት ብንኾንም ከእግዚአብሔር ጋር የማይቻል የለም ማለት ነው፡፡ እኛ የተቸገርነው ፈቃዳችንን እንደ እመቤታችን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው፡፡ መለወጥ እንፈልጋለን፤ ፈቃዳችን ግን ከእኛ ጋር ነው፡፡ እመቤታችን ግን ፈቃዷን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ያስረከበች ብጽዕት ናት፡፡
 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጸሎት፣ የዝማሬና የተመስጦ ሕይወት ነበራት፡፡ ዘመዷ ኤልሳቤጥን በጐበኘቻት ጊዜ ያመሰገነችውን ምስጋና ስንመለከት ይኽን እውነት ፍንተው አድርጐ ያሳየናል፡፡ ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል ወደ ዓለም ሲበተኑ የእመቤታችን ተግባር እነርሱን በጸሎቷ መርዳት ነበር፡፡ ክንፍ የሌላት ወፍና የጸሎት ሕይወት የሌለው ክርስቲያን አንድ ናቸው፡፡ ክንፍ የሌላት ወፍ መብረር አትችልም፡፡ ጠላት በቀላሉ ያጠቃታል፡፡ ክርስቲያንም ያለ ጾምና ጸሎት አምላኩን ማግኘት አይችልም፡፡ ርኵሳን መናፍስትንም ከሕይወቱ ማራቅ አይችልም፡፡ እስኪ እውነት እንነጋገር! ስንቶቻችን ነን ከጧት እስከ ማታ በመጽሐፈ ገጽ (በፌስ ቡክ) ተተክለን ስንውል የማይደክመን፤ የጸሎት ሕይወታችን ግን ምንም የኾነብን? መጽሐፈ ገጽ አያያዙን አልቻልንበትም ማለት አይደል? ጸሎትና እመቤታችን ግን ለቅጽበት ስንኳ ተለያይተው የማያውቁ ወዳጆች ናቸው፡፡      
 የእመቤታችንን የተመስጦ ሕይወት ስናነብ ደግሞ እጃችንን በአፋችን እንጭናለን፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ፣ ሰብአ ሰገል ከአሕዛብ አገር መጥተው በልጇ ፊት ሰግደው እጅ መንሻ ባቀረቡ ጊዜ፣ መላዕክት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ ሃሌ ሉያ - አምላክ ለኾነ ሥጋ ከሥላሴ ጋራ ባንድነት ምስጋና ይገባዋል፤ የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ፡፡ አንድም የሰው ፍቅር አገብሮት አምላክ ሰው ቢኾን ሰው አምላክ ኾነ” ብለው ባመሰገኑ ጊዜ፣ መላዕክት የነገሯቸው ኖሎት (እረኞች) ሰምተው በተደነቁ ጊዜ፣ ግዑዛኑ እንስሳት ጌታን በበረቱ ከብበው በትንፋሻቸው ባሞቁት ጊዜ “ማርያምሰ ተዓቅብ ዘንተ ኵሎ ነገረ ቀትወድዮ ውስተ ልባ - እመቤታችን ግን ይኽን ነገር ታስተውለው ነበር፤ በልቡናዋም ታኖረው ነበር” እንጂ ለሰው አታወራውም ነበር፡፡ የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፡- “የምትናገረው በጣም ጥቂት ሲኾን ርሱም ለማድረግ አስፈላጊ በሚኾንበት ብቻ ነበር” ይላል፡፡
 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃለ እግዚአብሔርን ዕለት ዕለት የምታነብ ነበረች፡፡ “ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ተብሎ እንደተጻፈ ቃለ እግዚአብሔር የዕለት ተዕለት ምግቧና መጠጧ ነበር፡፡ በሉቃ.፩፡፵፯-፶፭ በምናነበው ድንቅና ጥልቅ ምስጋናዋ ላይ የምናስተውለው ነገር ቢኖር ምን ያኽል ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደምታነብና እንደምታውቅ ነው፡፡ ማወቅ ብቻ አይደለም፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ትጠቀምበት ነበር፡፡ መልዐኩ መጥቶ “ትፀንሲ” ሲላት “እም አይቴ ረከብከ ዘከመዝ ብሥራት ዘእንበለ ምት እም ድንግል ፅንሰት ወዘእንበለ ዘርዕ እምድር እትወት - ምድር ያለ ዘር ታፈራ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ ትፀንስ ዘንድ እንዲኽ ያለ የምሥራች ከማን አገኘኸው?” ያለችው ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ስለኾነ ነው፡፡ አንድ እንግዳ ነገር በሕይወታችን ሲመጣ እውነትነቱን የምንመዝነው በቃሉ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ሲባል ከቃሉ ባለቤት ከእግዚአብሔር ጋር መጨዋወት መነጋገር ማለት ነውና፡፡ እግዚአብሔርም ለዚያ ቃሉን ለሚያነብ ሰው ፈቃዱ ምን እንደኾነ ይገልጥለታልና፡፡ ለዚኽም ነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲኽ በማለት የሚመክረን፡- “ዕለት ዕለት ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነብ ሰው ንዑድ ክቡር ነው፡፡ መጻሕፍትን የማያነቡ ብዙ ሰዎች ሕገ እግዚአብሔርን ካለማወቅ የተነሣ ክሕደት የተባለ ክፉ ልጅን ወልደዋልና፡፡ ኃጢአት የተባለ ክፉ ዛፍም ዳግም በተወለደው ሰውነታቸው ላይ አብቅለዋልና፡፡ ደጋግመው ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነቡ ግን ቢወድቁ እንኳ ተመልሰው ይነሣሉ፡፡ ልጆቼ! እናንተም ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማንበብ ቸል አትበሉ፡፡ በጣም ተቸግራችኁ ለተከታታይ ዐሥር ቀናት ብቻ ይኽን ብትለማመዱት ከዚያ በኋላ ልምድ ይኾንላችኋል፡፡ በርግጥ ይኽ ልምምድ ለንባብ ብቻ ሳይኾን ለሌላ መንፈሳዊ ሕይወታችኁም ብትጠቀሙበት መልካም ነው፡፡” ተንቀሳቃሽ ስልካችንን ከቤት ረስተነው ወደ ሥራ ቦታ ብንሔድ ምን ይሰማናል? ቃሉን ስንረሳውስ?
 እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጅግ ትሑት ነበረች፡፡ ትንቢተ ኢሳይያስን ስታነብና “ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች” በሚለው አንቀጽ ስትደርስ “ምነው እኔ በኾንኩኝ?” አላለችም፤ “ምነው በዘመኗ ደርሼ ይኽቺን ድንግል ባገለገልኳት?” አለች እንጂ፡፡ መልዐኩ “ተፈስሒ” ሲላት “ይገባኛል” አላለችም፤ “ነየ አመተ እግዚአብሔር - የእግዚአብሔር ገረዱ እነሆኝ” አለች እንጂ /ሉቃ.፩፡፴፰/፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ “የጌታዬ እናቱ እመቤቴ ወደኔ ትመጭ ዘንድ እኔ ምንድነኝ?” ስትላት “ልክ ነሽ፤ ይደልወኒ - ይገባኛል፤ አምላክን ፀንሻለኹና” አላለችም፤ “የባርያይቱን ውርደት ተመልክቷልና” አለች እንጂ፡፡ ብትል እኮ ያምርባታል፡፡ ነገር ግን አላለችም፡፡ ምንም ሳንሠራ “ይገባኛል” የምንል የማን ልጆች እንኾን?
 እመቤታችን ኤልሳቤጥ እንዳረገዘች ሰምታ ትጠይቃት ዘንድ መሔዷ የትሕትናዋን ጥልቀት ያሳያል፡፡ ለልማዱ ባርያ ወደ ጌታው ይሔዳል፡፡ አኹን የኾነው ግን እንዲኽ አይደለም፡፡ የመጣችው ኤልሳቤጥ አይደለችምና፤ ወላዲተ አምላክ እመቤታችን ሔደች እንጂ፤ ያውም በዚያ ተራራማው ስፍራ፡፡ የእመቤታችን ትሕትናዋ ግሩም ነው፡፡ ትሕትና ሰዎችን አማልክት ዘበጸጋ ታደርጋለች፤ ትዕቢት ደግሞ ቅዱሳን መላዕክትን ታዋርዳለች፡፡ ትዕቢት እጅግ ክፉ ነው፡፡ ትዕቢት ሰዎች ከተለመደው ባሕርያቸው አስወጥቶ ያደነዝዛቸዋል፤ የስንፍናን ካባ ያጐናጽፋቸዋል፡፡ ትዕቢት እንደ ዕብድ ያናግራል፡፡ አንድ ሰው ቁመቱ ሦስት ክንድ ከስንዝር ቢኾን እንኳን ትዕቢቱ ተራራን ያሳክሏል፤ ተራራን ባያክልም እንደዚያ እንደኾነ እንዲያስብ ያደርጓል፡፡ ትዕቢት ከዕብደት የከፋ በሽታ ነው፡፡ ምክንያቱም ትዕቢት በእኛ ፈቃድ የሚይዘን በሽታ ሲኾን ዕብደት ግን ሳናውቀው ሊይዘን የሚችል የጤና እክል ነውና፡፡ ወዮ! መቼ ይኾን ከዚኽ በሽታ የምንላቀቀው?
 መቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እጅግ የምታምንና ታዛዥ ነበረች፡፡ ሕይወቷ ኹሉ “ይኵነኒ በከመ ትቤለኒ - እንደ ቃልኽ ይደረግልኝ” በሚል የተመላ ነው፡፡ ወላጆቿ ለቤተ እግዚአብሔር ቢያስረክቧት “ይኵነኒ”፤ ካህናት “ቤተ መቅደሳችንን ታረክስብናለች” ብለው ቢያስወጧት “ይኵነኒ”፤ “በድንግልና ፀንሰሽ በድንግልና ትወልጃለሽ” ስትባል “ይኵነኒ”፤ “ከሦስቱ ቅዱስ አንዱን ቅዱስ በበረት ትወልጂዋለሽ” ስትባል “ይኵነኒ”፤ “የስዱዳን ተስፋቸውን አዝለሽ ትሰደጃለሽ” ስትባል “ይኵነኒ”፤ ሽፍቶች ቢያስደነግጧት “ይኵነኒ”፤ ማየ ሕይወትን አዝላ ውኃ ቢጠማት አንድም ልጇ ቢጠማው “ይኵነኒ”፤ አባቶቿ ፵ ዓመት የፈጀባቸውን መንገድ በልጅነት ዕድሜዋ “ልጅ አዝለሽ ትሔጃለሽ” ስትባል “ይኵነኒ”፤ “ሄሮድስ ሞቷልና ተመለሺ” ስትባል “ይኵነኒ”፤ አንዱን ልጇ ሲያሰቃዩባት ሲገርፉባትና ሲገድሉባት “ይኵነኒ”፡፡ ታዛዥነቷ ከአዕምሮ የሚያልፍ ነው፡፡ ሄሬኖዎስ የተባለው ቅዱስ አባት የእመቤታችንን ታዛዥነት ለምን እንደኾነ ሲያስተምር እንዲኽ አለ፡- “እነሆ ጌታ የራሱ ወደኾኑት በግልጥ (በለቢሰ ሥጋ) መጣ፡፡ ትዕዛዙን ተላልፎ በዕጽ የሞተውን አዳም በዕጽ ላይ ታዝዞና ካሣውን ከፍሎ፣ ወደ ጥንተ ተፈጥሮው ይመልሰው ዘንድ በራሱ ጥበብ ከፍጥረቱ ተወለደ፡፡ ለአንድ ወንድ የታጨችው ድንግል በምክረ ከይሲ ያመጣችውን ያለመታዘዝ ኃይል የእውነት መልዐክ ለአንድ ወንድ ለታጨችው ድንግል ባበሠራት ጊዜ ፈራረሰ፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን ከእግዚአብሔር እንድትርቅና ቃሉን እንድትቃወም ክፉ መልዐክ አታለላት፡፡ ዳግማይቱ ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ደጉ መልዐክ ይዞት የመጣው መልካሙን ዜና እንድትቀበለውና እግዚአብሔርን በከዊነ ቃሉ እንድትወልደው አመነች፡፡ ቀዳማይቱ ሔዋን እግዚአብሔርን እንዳትታዘዘው ክፉ መልዐክ አታለላት፤ ወደቀችም፡፡ ዳግማይቱ ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን እግዚአብሔርን እንድትታዘዝ ቅዱስ መልዐክ አሳመናት፤ ርሷም ሔዋንን ረዳቻት፡፡ ነገደ አዳም በአንዲት ድንግል አለመታዘዝ ምክንያት ሞት ተፈረደበት፣ ኾኖም በሌላይቱ ድንግል መታዘዝ ምክንያት ዳነ፡፡” በሕይወታችን “ይኵነኒ” ማለትን መልመድ ጸጋ እግዚአብሔርን በሕይወታችን ማትረፍረፍ ነው፡፡ እንላለን ወይ ነው ቁምነገሩ? እግዚአብሔርን የሚጋርዱብን ነገሮች (ለምሳሌ ሥራ፣ ውበት፣ ሥልጣን፣ ሀብት፣…) ከሕይወታችን ይወገዱ ብንባል “ይኵነኒ” ለማለት ምን ያኽል ዝግጁዎች ነን?
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ርኅሪኅተ ኅሊና ነበረች (ናት)፡፡ እጅግ አዛኝ እናት!!! ሊቃውንት እንደሚያስተምሩት ምኅረት (ምጽዋት) ሦስት ዓይነት ነው፡፡ ምኅረት ሥጋዊ፣ ምኅረት መንፈሳዊና ምኅረት ነፍሳዊ፡፡ ምኅረት ሥጋዊ የታረዘን ማልበስ፣ የተራበን ምጉረስ ነው፡፡ ምኅረት መንፈሳዊ የተጨነቀን ወይም ያዘነን ሰው መርዳት፣ ወይም ማጽናናት ነው፡፡ ምኅረት ነፍሳዊ ደግሞ ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኙ መርዳት ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰውስ ይቅርና ለተጠማ ውሻም ሳይቀር በወርቅ ጫማዋ ውኃን ያጠጣች ርኅርኅተ ኅሊና ናት፤ ምኅረት ሥጋዊ፡፡ እናቶቻችንን በምጥ ጊዜ እንዴት እንደምትረዳቸው መናገርም ለቀባሪ ማርዳት ነው፤ ምኅረት መንፈሳዊ፡፡ ክርስቲያን፥ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ኾኖ ከእመቤታችንን ርኅራኄ (ምልጃና ቃል ኪዳን) ያልቀመሰ የለም፤ ምኅረት ነፍሳዊ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በቅዳሜ ውዳሴው ላይ “የዚኽ ዓለም ሰዎች አማልዱኝ ቢሏቸው ነገር አጽንተው ይመለሳሉ፡፡ ርሷ ግን ማእምንት ሰአሊተ ምኅረት - የታመነች የምሕረት አማላጅ ናት” ያለውም ስለዚኹ ነው፡፡ እኛስ ምን ያኽል ርኅሩኀን እንኾን? ኧረ በወርቅ ጫማ ቀርቶብን በንጹሕ ሳህን ለመመጽወት ልቡናችን በራራ? ኧረ ለውሻው ቀርቶብን ለሰዉም ባዘንን?
 የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወት ገና ስንዠምር እንደተናገርነው በሕይወት ዘመን አንብበው የማይጨርሱት እጅግ ትልቅ መጽሐፍ ነውና አንድ ኹለት ብለን መቁጠር አይቻለንም፡፡ ማንበብ ከቻልን ሕይወቷ ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴአችን አስተማሪ ነው፡፡ “ማርያም ፊደል ናት ….” ብለን መዘመራችንም ስለዚኹ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እንኪያስ የምንዘምር ብቻ አንኹን፤ እናንብባትም ጭምር እንጂ፡፡ የምናነብ ብቻ አንኹን፤ እንለወጥም ጭምር እንጂ፡፡ ማንበቡንማ ዲያብሎስም ያነባል፡፡ እንኪያስ አንብበን እንለወጥና በእውነት የድንግል ልጆች እንኹን፡፡      
  ይኽን እንድናደርግ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን ወአሜን፡፡ 
   



1 comment: