Pages

Tuesday, September 23, 2014

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ኹለት)

 (መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 13፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

የሃይማኖት አዠማመርና ዕድገት

 የተለያዩ ሰብአ ዓለም (የዚኽ ዓለም ሰዎች) የሃይማኖት አመጣጥን በተመለከተ የተለያየ ዓይነት አመለካከት ቢኖራቸውም፥ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን ሃይማኖት ገና ከፍጥረት መዠመሪያ (ከዓለመ መላዕክት) ዠምሮ የነበረ መለኮታዊ ስጦታ ነው ብለን እናምናለን /ሐዋ.17፡26/፡፡ የመዠመሪያዎቹ ምእመናንም ቅዱሳን መላዕክት ናቸው፡፡ ይኽ እንዴት እንደኾነም በሥነ ፍጥረት ትምህርታችን የምንመለስበት ይኾናል፡፡
ከቅዱሳን መላዕክት በኋላ ይኽቺው ነቅዕ፣ ኑፋቄ የሌለባት ንጽሕት ሃይማኖት አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ በ40 እና በ80 ቀናቸው ተቀብለዋታል፡፡

 ምንም እንኳን አዳምና ሔዋን ከበደሉ በኋላ ከሃይማኖት መንገድ ቢወጡም እግዚአብሔር አዳምን ጠርቶ “ወዴት ነኽ?” ባለው ጊዜ መልሶታል፡፡ ከአቤል ዠምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ላይ በነበሩ ደጋግ ሰዎችም ቀጠለች፡፡ አቤልን ከቃየል፣ ኖኅን ከሰብአ ትካት፣ አብርሃምን ከሰብአ ዑር፣ ሙሴን ከሰብአ ግብጽ፣ ነቢያትን ከሐሰትና ከክሕደት የለየቻቸውም ይኽቺ ርትዕት ሃይማኖት ናት /ዕብ.11/፡፡ በመጨረሻ ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጉልቶና አብራርቶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣት /ዮሐ.17፡8/፡፡ ከእኛም ዘንድ ደረሰች /ይሁዳ ቁ.3/፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር የምታስተምረውም ይኽንኑን ነው፡፡ መዳን ከዚኽች እምነት ውጪ ኾኖ እንደማይገኝ፣ በቤቷ ብንመጣ በሕይወታችን ሰላምን እንደምናገኝ፣ በሚመጣውም ዓለም ከዚኽ የበለጠ ሰላምና ዕረፍት እንደሚጠብቀን ለኹላችንም ማስተማሯ ስለዚኹ ነው፡፡

ሃይማኖት ያላቸው ፍጥረታት

 ሃይማኖት ያላቸው ፍጥረታት ኹለት ሲኾኑ፥ እነርሱም መላዕክትና ሰዎች ናቸው፡፡ አጋንንትም ቢኾኑ ምድባቸው ከመላዕክት ወገን ስለኾነ ሃይማኖት እንዳላቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል /ያዕ.፪፡፲፱/፡፡ የአጋንንት ችግራቸው ከምግባር የተለየ ሃይማኖት ስላላቸው ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት 

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ ሃይማኖት” እንዳለ /ኤፌ.4፡5/ በዓለመ መላዕክት የነበረች፣ በሕገ ልቡና በሕገ ኦሪት የቀጠለች፣ በዘመነ ሐዲስም ያለች ሃይማኖት አንዲት ነች፡፡ ይኽቺ ሃይማኖት ተነጻጻሪ፣ ተፎካካሪ፣ እኩያ እኅት ወይም ወንድም፣ መንትያ ቅጥያ፣ ልዋጭ አማራጭ፣ ተቀዳሚ ተከታይ የላትም፡፡ ሃይማኖት አንድ የኾነችበት ምክንያትም እግዚአብሔር አንድ ስለኾነ ነው፡፡ ከዚኽች ሃይማኖት ውጪም ድኅነት የለም፡፡

የሃይማኖት አስፈላጊነት

 የሰው ልጅ የተፈጠረው የእግዚአብሔርን ክብር ወርሶ፣ ስሙንም ቀድሶ በዘለዓለማዊ ሕይወት ለመኖር ነው፡፡ በመኾኑም ሰው ያለ ሃይማኖት ልኑር ቢል በፍጹም አይችልም፡፡ የታሪክ ድርሳናትም ሰው ያለ ሃይማኖት የነበረበትን ዘመን አልጻፉልንም፡፡ ምናልባት በፍጡራን ወይም በኅሊናው በፈጠረውና ጭራሽ ህልውና በሌለው ምናብ ተይዞ የሚያመልከውን አምላክ በትክክል ላያውቀው ይችል እንደኾነ እንጂ ሰው ያለ ሃይማኖት መኖር አይችልም፡፡ ሃይማኖት የለኝም ብሎ የሚያስበው ሰው እንኳን “ሃይማኖት የለኝም” የሚለው አመለካከቱ ለርሱ ሃይማኖቱ ነው፡፡ ሰው ያለ ሃይማኖት መኖር እንደማይችል የበለጠ የሚታወቀው ደግሞ አስቸጋሪ ኹናቴ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ በዚያ የጭንቅ ሰዓት ሰው ረዳት ይፈልጋል፡፡
 ከላይ በገለጥናት አንዲት ሃይማኖት ስንኖር እጅግ ብዙ ጥቅሞችን እናገኛለን፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያኽልም፡-
·        በሕግ በአምልኮት ለሚሹት ሰዎች እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ዋጋ እንዳለ ዐውቀን በሃይማኖት ስንቀርብ እግዚአብሔርን ደስ እናሰኛለን /ዕብ.11፡6/፤
·        ምንም ዓይነት መከራ ቢገጥመንም እግዚአብሔር ያስችለኛል ብለን መንፈሰ ጠንካራ በመኾን ፈቃደ ሥጋን አንድም ፈቃደ ሰይጣንን እናሸንፋለን፤ በሃይማኖት /ፊልጵ.4፡13፣ 1ኛ ዮሐ.5፡4-5/፤
·        ባለመኖሩ አይታይ የነበረው ዓለም ካለ መኖር ወደ መኖር መጥቶ እንደታየ የምናውቀው በሃይማኖት ነው፡፡ በዚኽም የእነዚኽን ፍጥረታት አስገኚ እግዚአብሔርን እናውቅበታለን፤ በሃይማኖት /ዕብ.11፡3/፤
·        ሰው ቢሰጥ ኃላፊውንና ጠፊውን ነው፤ እግዚአብሔር ግን ዘለዓለማዊውን ይሰጣል፡፡ ሰው ቢሰጥ ግዙፉን ነው፤ እግዚአብሔር ግን ረቂቁን ነው፡፡ ሰው ቢሰጥ ማፍጀት፣ መሰልቸት፣ መጸጸት፣ መሰቀቅ  አለበት፤ እግዚአብሔር ሲሰጥ ግን ይኽ ኹሉ የለበትም፡፡ በመኾኑም በሃይማኖት ወደርሱ ስንቀርብ እውነተኛ ሰላምን እናገኛለን /ዮሐ.14፡27/፤
·        በየትኛውም ዓይነት ሥፍራና ኹናቴ ብንኾንም በሃይማኖት ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብ ከኾነ ከሚቃጣብን መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ እንድናለን /ዳን.6፡10-28/፤
·        አብን ወላዲ፣ ወልድን ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ ብለን ስናምን ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ እናገኝባታለን፤ ሃይማኖት /ዮሐ.3፡18/፤
·        እና የመሳሰሉት፡፡

ኦርቶዶክስ እና ተዋሕዶ የሚሉ ስሞችን የምንጠቀምበት ምክንያት

 ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል የጽርዕ (የግሪክ) ቋንቋ (ኦርቶ= የቀና፣ የተስተካከለ ፥ ዶክሳ= እምነት፣ አመለካከት) ሲኾን ትርጓሜውም ቀጥተኛ እምነት ማለት ነው፡፡ ይኽ ስም ለክርስትና እምነት የተሰጠው በ325 ዓ.ም. በጉባኤ ኒቅያ ነው፡፡ ሠለስቱ ምዕት ለክርስትና ሃይማኖት ይኽን ስያሜ ሲሰጡት አርዮስ “ወልድ ፍጡር በመለኮቱ” ብሎ ሲነሣ ከክርስቶስ የተቀበሏት ሃይማኖት እንዲኽ ዓይነት እንግዳ ትምህርት እንደሌላት ገልጠው ሃይማኖታቸው ርትዕት፣ የቀናች መኾኗንና ከአርዮስ ትምህርት የተለየች መኾኗን ለመግለጥ ነው፡፡
 ተዋሕዶ ማለት ከግእዝ የተወረሰ ቃል ሲኾን የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ለምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት መጠሪያ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ትርጓሜውም ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ ከኹለት አካል አንድ አካል፥ ከኹለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ እንደ ነፍስና ሥጋ አንድ መኾኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይኽ ስም ለኦርቶዶክስ ክርስትና የተሰጠው በ431 ዓ.ም. በጉባኤ ኤፌሶን ነው፡፡ ቅዱሳን አበው ይኽን ገላጭ ቃል ሲጠቀሙ ሥጋን ከመለኮት ነጥሎ አካልንና ባሕርይን ከፋፍሎ የሰበከ ንስጥሮስንና ተከታዮቹን ሲያወግዙ ነው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ ተዋሕዶ የሚለው አገላለጽ ሥጋን ከመለኮት ጋር ቀላቅሎና አጣፍጦ የተወገዘውን የአውጣኪን ትምህርት ያርቃል፡፡ በነገረ ክርስቶስ ትምህርታችን በስፋት እንመለስበታለን፡፡
 የኦርቶክስ ተዋሕዶን እምነት የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያናት 6 ሲኾኑ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ እስክንድርያ፣ የሕንድ ማላንካራ፣ ሶርያ እና አርመን ናቸው፡፡

ተወዳጆች ሆይ! እኛም በዚኽች አቤልን ከቃየል፣ ኖኅን ከሰብአ ትካት፣ አብርሃምን ከሰብአ ዑር፣ ሙሴን ከሰብአ ግብጽ፣ ነቢያትን ከሐሰትና ከክሕደት፣ ሐዋርያትን ከሰብአ ዓለም የለየቻቸውም ተነጻጻሪ፣ ተፎካካሪ፣ እኩያ እኅት ወይም ወንድም፣ መንትያ ቅጥያ፣ ልዋጭ አማራጭ፣ ተቀዳሚ ተከታይ የሌላት አንዲት ሃይማኖት ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ከዚኽች ሃይማኖት መውጣት ከሕይወት መውጣት ነውና፡፡ ከዚኽች ሃይማኖት መውጣት ሲባል ግን እምነቷን መካድ ብቻ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በልቡናቸው እግዚአብሔርን እንደሚያውቁት አድርገው እናምናለን ይላሉ፡፡ በሥራቸው ግን ይክዱታል” እንዳለ /ቲቶ.1፡16/ በተግባራዊ ምልልሳችንም በዚኽች ሃይማኖት ጸንተን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚኽም የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡


2 comments:

  1. በእውነት ቃለ ሕይወት ያሰማልን። ብዙ የሰው መብት የማይጠብቁ መምህራን ኣይተናል። እርሶት ግን ይእውነት መምህር ኖት።

    ReplyDelete