Pages

Tuesday, September 30, 2014

ለይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ የተሰጠ ምላሽ (ክፍል አንድ)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 21 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
  የይሖዋ ምስክሮች የተባለው ተቋም እ.ኤ.አ. በ1870 ላይ የተመሠረተ ሲኾን፥ መሥራቹም ፔንሳልቫንያ በምትባለው የአሜሪካ ግዛት እ.ኤ.አ. በ1854 ላይ የተወለደው ቻርለስ ራስል የተባለ ግለሰብ ነው፡፡ ይኽ ሰው ከጓደኞቹ ጋር በየጊዜው እየተገናኘ መጽሐፍ ቅዱስ ያጠና ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን በተለያዩ የክሕደት ትምህርቶች ውስጥ ወደቀ፡፡ ከክሕደቶቹ መካከልም “ነፍስ ትሞታለች፤ ሥላሴ የሚባል ትምህርት የለም፤ ወልድ ፍጡር በመለኮቱ፤ ክርስቶስ በሥጋ አልተነሣም፥ በፍጹም ሥጋም ወደ ሰማይ አላረገም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ነው፤ ዘለዓለማዊቷ ገነት ይኽቺ የምንኖርባት ምድር ነች፤ ኃጢአተኞች ፈጽመው ከመኖር ወዳለመኖር ይጠፋሉ እንጂ የዘለዓለም ስቃይ የሚባል አያገኛቸውም፥ ሰይጣንም ቢኾን ወደአለመኖር ይጠፋል እንጂ አይሰቃይም፤ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ኃይል እንጂ አካላዊ አይደለም” የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ለዚኹ ትምህርቱ ይረዳው ዘንድም መጽሐፍ ቅዱስን በማጣመም “የአዲሲቱ ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ” በማለት የራሱ የኾነ መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ በአኹኑ ሰዓትም ይኽን የክሕደት ትምህርታቸውን በተለያዩ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ብዙ ሰዎችን እያታለሉ ይገኛሉ፡፡ እኛም፥ እግዚአብሔር በፈቀደልን መጠን፥ እነዚኽ ተረፈ አርዮሳውያን በትምህርተ ሥላሴ ዠምረን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አንድ በአንድ መልስ እንሰጥበታለን፡፡ ለዚኽም እግዚአብሔር ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን፤ አሜን!!!


 ምስጢረ ሥላሴ

 ምስጢረ ሥላሴ የክርስትና እምነት መሠረታዊ ትምህርት ነው፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. አምስቱ አዕማደ ምስጢር (የምስጢራት ምሰሶዎች) ተብለው ከሚታወቁት መሠረታዊ የትምህርተ ሃይማኖት (የዶግማ) ትምህርትም ቀዳሚው ነው፡፡ የዚኹ መሠረቱም የዮሐንስ ወንጌልና የሠለስቱ ምዕት ትምህርት ነው፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ገና ሲዠምር የእግዚአብሔር የአንድነቱን የሦስትነቱን ምስጢር በመግለጥ ነው /ዮሐ.1፡1/፡፡ ጸሎተ ሃይማኖትም እንደዚኹ “ኹሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፤ … ከርሱ ጋር በነበረ አንድ የአብ ልጅ በሚኾን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፤ …በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን” በማለት ምስጢረ ሥላሴን ያስተምራል፡፡ ስለዚኽ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ቄርሎስ “አርማስ - መርከብ” በተባለ መጽሐፉ ላይ፡- “ንዑሰ ክርስቲያን ለጥምቀት የቀረቡ ናቸው እንጂ ወደ ፍጹምነት ባይደርሱ በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ ተብሎ በማመን ጸንቶ መኖርን ያስተምሯቸው፤ ያስረዷቸው፡፡ በሥላሴ ስም አምነው ይጠመቁ፡፡ … የሦስት አካላት መለኮት አንድ እንደ ኾነ ሐዋርያት ያስተማርዋት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸው፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ኹሉ ይመኑ” እንዳለው አንድ ሰው ከምንም በፊት ስለ ምስጢረ ሥላሴ መማር አለበት /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ 70፡12/፡፡ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ሳያምኑና ሳያውቁ ስለ እግዚአብሔር መናገር እውነተኛውንም አምላክ ማምለክ አይቻልምና፡፡
 ስለ ምስጢረ ሥላሴ የምንማረው ትምህርት ምስጢር የተባለበት ምክንያት የይሖዋ ምስክሮች እንደሚሉት የማይታወቅ ወይም ማንም እንዳያውቀው የተደበቀ ማለት ሳይኾን የሰው ልጅ ውሱን አዕምሮ ካለመቻል (ከመሳን) የተነሣ ሊደርስበት የማይችል ረቂቅ ትምህርት ስለኾነ ነው፡፡ “የእግዚአብሔር ጌትነቱን በነገር ትችት ብንመረምር ድፍረት ነው፡፡ የማይመረመር ጌትነቱን ከማወቅ ልቡናችን ይደክማልና፡፡ አይደርስበትምና፡፡ ኅሊና መርምሮ ሊያውቀው ያልቻለውንም ቃል ገልጦ ሊናገረው አይችልምና” /ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ቂሣርያ 33፡3/፡፡ የምንማረው እንኳን የተገለጠውን ያኽል፣ ከተገለጠውም የገባንን ያኽል ብቻ ነው፡፡ የተገለጠው ቢረቅብንም አምነን እንቀበሏለን እንጂ በመመርመር ልንደርስበት ስላልቻልን እውነት አይደለም አንልም፤ የእኛ አለማመን የእግዚአብሔርን እውነትነት አያስቀረውምና /ሮሜ.3፡3/፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ወንድ ዘር እንደተፀነሰ የታመነ ነው፡፡ ይኽ እንዴት ሊኾን እንደ ቻለ ግን እናምነዋለን እንጂ ሐተታ መስጠት አንችልም፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድንግልናዋን ሳይለውጥ እንደተወለደ እናውቃለን፡፡ ይኽ እንዴት ሊኾን እንደቻለ ግን በእምነት እንቀበለዋለን እንጂ እውነት አይደለም፤ አልተወለደም አንልም፡፡ ምስጢረ ሥላሴም እንደዚኹ ረቂቅ ነው፡፡ ስለዚኽ ከምንም በፊት ማመንን አስቀድመን ልቦናችን ወደ ቻለው መጠን ወደ ማወቅ እናስከትሏለን፡፡ ይኽም ፍኖተ አሚን ይባላል (ዕውቀትን ማስቀደም በሳይንሱ የተለመደ ሲኾን ፍኖተ አዕምሮ ይባላል)፡፡ በሌላ አገላለጥ ትምህርተ መለኮት አምነው የሚማሩት ነው ማለት ነው፡፡
ሥላሴ ማለት ልዩ ሦስት፣ ልዩ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ሦስትነታቸውም የአካል፣ የስም፣ የግብር፣ የኵነታት ነው፡፡ አንድ ሰው ከምንም በፊት ስለ አካላተ ሥላሴ መረዳት አለበት፡፡ የአካል ሦስትነትን የተረዳ ሰው የስም፣ የግብር፣ የኵነት ሦስትነትን ለመረዳት አይቸገርምና፡፡ ቤተ ክርስቲያን፥ በዘወትር ጸሎታችን “በአካል ሦስት ሲኾኑ” እንድንል ማድረጓም ስለዚኹ ነው፡

  ለመኾኑ አካል ምንድነው?

 አካል የሚለው ቃል “አኪል - መብቃት፣ ዐቅም፣ ማደግ” ከሚል የግእዝ ቃል የተገኘ ሲኾን ለሰውና ለእንስሳ እንዲኹም ለዕፅዋት ሲነገር ብቃትን፣ ማደግን ያመለክታል፡፡ በዓለመ መንፈስ ለሚገኙት ለመላዕክት ሲቀጸል (ሲነገር) ደግሞ ከዚኽ ከፍ ብሎ የማያድጉትን፥ ግን ደግሞ በምጣኔ ዓቅም እንዳሉ የሚገልጥ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ሲነገር ግን ሰማይም ምድርም አይበቃውምና መጠን፣ ወሰን የማያሳይን ትርጕም ይሰጣል /መሠረት ስብሃት ለአብ፣ ሥላሴ በተዋሕዶ፣ ገጽ 164-165/፡፡ አካል አኗኗር የሚታወቅበት ቁመት ማለት ነው /ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 167/፡፡ አካል “ፍጹም ምሉእና ቋሚ እኔ ነኝ ባይ ማለት ነው” /የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ64/፡፡

 የእነዚኽ አካላት ስም ማን ማን ይባላል? ቁጥራቸውስ?

 እነዚኽ እኔ ነኝ ባይ፣ ፍጹም፣ ምሉእና ቋሚ አካላት ስማቸው ማን እንደኾነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይነግረናል፡፡ “አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ” በማለት /ማቴ.28፡19-20/፡፡ ስም የሚወጣው በህልውና አለ ተብሎ ለሚታሰብ ኗሪ ነው፡፡ ለሌለ ስም አይወጣም /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ 869/፡፡ ከሌለ ምን ተብሎ ስም ይወጣለታል? ህልውና ላለው ስም እንደሚሰጠው ኹሉ ቁጥርም እንደዚኹ ይሰጧል፡፡ በህልውና የታወቀው አንድ ከኾነ፣ ኹለት ከኾነ፣ ሦስት ከኾነ ቁጥር ይሰጧል፡፡ የሌለ ከኾነ ግን የለምና ስምም ቁጥርም አይሰጠዉም፡፡ እንግዲኽ ከላይ እንዳየነው “አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ” የሚለው ስምም ቁጥርም በግልጥ ስለሚያሳይ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በግእዙ ሥላሴ ብላ ጠራችው፡፡  
 የይሖዋ ምስክሮች ግን በዚኹ መሠረታዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሃይማኖት ትምህርት አያምኑም፡፡ እንደነርሱ ሐሳብና አስተምህሮ አምላክ የሚባለው አብ ብቻ ነው፡፡

 ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment