Pages

Friday, October 10, 2014

ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (የመጨረሻው ክፍል)



በዲ/ ያረጋል አበጋዝ

 
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 30 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡


የቀጠለ…

4.4.
ማዕረረ ትንቢት ማርያም ዘመነ ጽጌ እንግዳ  
ወዘመነ ፍሬ ጽጋብ ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ
ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ
ያንጸፈጽፍ እምአድባሪሁ ወእም አውግሪሁ ለይሁዳ
ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወሃሊብ ፀዓዳ»
ትርጉም
«
በመከር ጊዜ አበባ በአበባ ጊዜ ደግሞ መከር አዝመራ ማጨድና መሰብሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም ጊዜያቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በመስከረም ወር የአበባ ጊዜ በመሆኑ አዝመራ መሰብሰብ የለም፡፡»


«
የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ. እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም ሆይ የኤልዳ ነቢዩ ኢዩኤል /ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል ብሎ/ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፤ ተፈጸመ፡፡» እመቤታችን ነቢያት የተናገሩት የትንቢት ዘር ተፈጸመባት፡፡ ማለትም ነቢያት የአምላክን ሰው የመሆን ነገር በተለያየ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ጌታችን ነቢያት የተናገሩት ትንቢት መፈጸሙንና ይህንን ፍጻሜ ለማየት የታደሉት ሐዋርያት መሆናቸውን «አንዱ ይዘራል አንዱም ያጭዳል የሚለው ቃል እውነት ሆኖአል፡፡ እኔም እናንተ ያልደከማችሁበትን ታጭዱ ዘንድ ሰደድኳችሁ፡፡ ሌሎች ደከሙ እናንተም በድካማቸው ገባችሁ» በማለት ተናግሮአል፡፡/ዮሐ.4.3738/፡፡ ይህም ነቢያት የዘሩት ትንቢት በሐዋርያት ዘመን ለአጨዳ /ለፍሬ/ መድረሱን መናገሩ ነው፡፡ ስለሆነም «ማዕረረ ትንቢት፤ የትንቢት መካተቻ» ማርያም አላት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፍሬ ክርስቶስን ያስገኘችና ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች» እየተባለ የተነገረላት በመሆንዋ በአበባ ትመሰላለች፡፡

ስለዚህ እመቤታችን በመከር ወራት የምትገኝ አበባ ናት፡፡ በመከር ጊዜ የአበባ መገኘት ያልተለመደ ስለሆነ «ወዘመነ ጽጌ እንግዳ፤ እንግዳ የሆነ አበባ» አላት፡፡

ከዚህ በኋላ
«
ብኪ ተአምረ ዘይቤ ነቢየ ኤልዳ፣
ያንጸፍጽፍ እም አድባሪሁ ወእም አውግሪሁ ለይሁዳ፣
ፀቃውዓ መዐር ጥዑም ወሀሊብ ፀዓዳ. . .» በማለት ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረውን ትንቢት አፈጻጸም ይናገራል፡፡
ነቢዩ ኢዩኤል በዘመኑ ጽኑ ረኀብ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት እንደሚጎበኛቸውና ረሀቡ እንደሚጠፋ ይነግራቸው ነበር፡፡ «ብዙ መብል ትበላላችሁ.ትጠግቡማላችሁ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች በተሃ ጠጅ ያንጠበጥባሉ.ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ.በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጎርፋሉ»/ኢዩ.3.18 2.26/፡፡
«ብኪ ተአምረ ዘይቤ ኢዩኤል ነቢየ ኤልዳ፤ያንጸፍጽፍ እምአድባሪሁ ወእምእግሪሁ ለይሁዳ ፀቃውዐ መዓር ወሀሊብ ፀዓዳ»፡፡ ይህም ማለት ነቢዩ ኢዩኤል ከይሁዳ ተራሮችና ኮረብቶች ጣፋጭ ሣርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል ይመነጫል ያለው በአንቺ ተፈጸመ ማለት ነው፡፡ ይህም እመቤታችን ክርስቶስን በወለደች ዕለት መሪሩ ጣፍጦ፣ ይቡሱ ለምልሞ ተገኝቷል፡፡ ይህ ለጊዜው ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ከእርሷ በነሣው ሥጋና ደም ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ ከልጅነት ተራቁቶ፣ በረሀበ ነፍስና በጽምዓ ነፍስ ተይዞ የነበረውን የሰው ልጅ ከጎኑ ውኃን ለጥምቀት፤ ሥጋውንና ደሙን ምግበ ነፍስ አድርጎ የአምስት ሺህ አምስት መቶውን ዘመነ ረሀብ እንዳስወገደልን ያስረዳል፡፡

4.5.
አርምሞትኪ ማርያም ኃለፈ እምአንክሮ
እስከ ንሬኢ ሕዝብኪ ለተአምርኪ ግብሮ
ገነትኪ ትፅጊ ሰላመ ወተፋቅሮ
ዕለ ያማስኑ ለዓፀደ ወይንነ ወፍሮ
 ቈናጽለ ንዑሳነ አፍጥኒ አሥግሮ

ትርጉም
«እመቤታችን ማርያም ሆይ አርምሞሽ ከማድነቅ በላይ ሆነ. በማድነቅ የማይፈጸም ሆነ፡፡ የወይን ቦታችንን የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች ለማጥመድ /ለመያዝ/ ፍጠኚ፡፡»

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወትወዲዮ ለኩሉ ውስተ ልባ፤ ነገሩን ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡»/ሉቃጠ2.51/ ሲል የእመቤታችንን አርምሞ እንዴት አስደናቂ እንደሆነ ገልጾአል፡፡ እመቤታችን ማንም ፍጡር ያልሰማውን ብሥራተ መልአክ የሰማች ለማንም ያልተደረገውን በድንግልና መፅነስና መውለድ የታደለች ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲመሰገንባት የመላእክትን ቅዳሴ የሰማች ፈጣሪዋን የመገበች ከሰው ወገን ይቅርና ከሱራፌልና ከክሩቤል የሚበልጥ ክብርና ጸጋ የታደለች ስትሆን እርሷ ግን በዚህ ዓለም ስትኖር ሁሉንም ነገር በልቧ ውስጥ ከማኖር በስተቀር ይህንን አየሁ ይህንን ሰማሁ አላለችም፡፡ ሔዋን ዕፀ በለስን ወደ መብላትና ጸጋዋን ወደማጣት ያደረሳት ለእርስዋና ለአዳም ብቻ የተነገረውን ምሥጢር አውጥታ ለዲያብሎስ በመናገርዋ ነበር፡፡ እመቤታችን ግን ሁሉን በልቧ መዝገብ በመያዟ የተመሰገነች ሆነች፡፡

ከክርስቶስም ሆነ ከእመቤታችን የተማርነው አርምሞን ነው፡፡ ክርስቶስን ጲላጦስና ሊቃነ ካህናቱ ከየት መጣህ? ማነህ? ትምህርትህስ ምንድነው? እያሉ ሲጠይቁት ዝመ ነው ያላቸው፡፡ ልሰቅልህ ሥልጣን አለኝ ሲለው ብቻ ነው መልስ የመለሰለት፡፡ ስለዚህ እኛም ከአባታችን ከክርስቶስና ከእናታችን ከድንግል ማርያም ያየነውን አብነት ማንሣት ይገባናል፡፡ /ዮሐጠ19.9 ማተጠ27.14/፡፡

ደራሲው የእመቤታችንን አርምሞ ካደነቀ በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞን «አሥግሩ ለነ ቈናጽለ ንዑሳነ እለያማሰኑ ዓፀደ ወይንነ፤ የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን» /መኃጠ2.15/ እንዳለ የወይን ቦታ የተባለ የሕግ መጠበቂያ ልባችንን ሊያበላሹ ውር ውር የሚሉትን በቀበሮ የተመሰሉ መናፍቃንንና አጋንንትን እንድታስታግስልንና እንድታስወግድልን ይጸልያሉ፡፡

«
ትመስል እምኪ ማርያም ዕለተ ሣልስተ ወራብዕተ ዘወለደት ጽጌ ወፀሐየ ዓለም ብርህተ ካዕበ ትመስል ሳብእተ ዕለተ እስመ ፈረየት ኪያኪ ተአምረ ግዕዛን ሰንበተ ለዕለ በሰማይ ወምድር ዘኮንኪ ዕረፍተ፡፡»

«
ማርያም ሆይ እናትሽ /ሐና/ ጽጌያት የተፈጠሩባትን ሦስተኛዋን ቀን ፀሐይ የተፈጠረችበትን አራተኛውን ቀን /ረቡዕ/ እንዲሁም እግዚአብሔር ሥራውን የፈጸመባትንና ያረፈባትን ሰባተኛዋን ቀን ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም በሰማይና በምድር ላሉ ሁሉ ዕረፍት የሆንሻቸውን አንቺን ወልዳለችና፡፡»

እግዚአብሔር በዕለተ ሠሉስ /3ኛው ቀን/ ዕጸዋትን ፈጠረ፡፡ /ዘፍጠ1.1113/፡፡ ከእነዚህ ዕጸዋት ጽጌያት /አበቦች/ ከጽጌያት ደግሞ ፍሬ ይገኛል፡፡ ቅድስት ሐናን ጽጌያት በተፈጠሩበት በዕለተ ሠሉስ እመቤታችንን በጽጌ ጌታን ደግሞ ከጽጌው በተገኘ ፍሬ መስሏቸዋል፡፡ በአራተኛው ቀን /በዕለተ ረቡዕ ፀሐይንና ጨረቃን፣ከዋክብትን ፈጠረ፡፡ ሐናን በዕለቱ፣ እመቤታችንን በፀሐይ መሰላቸው፡፡ በሰባተኛው ቀን /በሰንበት/ ለሰው ሁሉ ዕረፍት እንዲሆን ለአብነት እግዚአብሔር አረፈ ተባለ፡፡ በዚህች ዕለት ሰው ሁሉ ከሥጋዊ ድካምና ውጣ ውረድ አርፎ ፈጣሪውን እያመሰገነ ይውላል፡፡ በእመቤታችንም ሰው ሁሉ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ አርፎ ተግባረ ነፍስ እየሠራ ፈጣሪውን «ወሠርዓ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ፤ ሰንበትን ለሰው ዕረፍት ሠራ» እያለ ሲያመሰግን ይውላል፡፡

4.6. «
በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕፀተ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ ወበጸዳሉ አብርሀ ጽልመተ»

ትርጉም
በአንቺ ላይ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ለሰው የአካሉን ሦስትነት ገለጸ አስረዳ፡፡ ድንግል ሆይ ጽጌሽ ተኣምራቱን ገለጸ በብርሃኑም ጨለማን አራቀ፡፡

እግዚአብሔር አንድነቱንና ሦስትነቱን በግልጽ ያሳየው በእመቤታችን በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ነው፡፡

/ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበሥራት እንዲህ አላት «መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ፡፡»
መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጸልለሻል»/ሉቃጠ1.35/፡፡

መንፈሰ እግዚአብሔር ብሎ መንፈስ ቅዱስን፣ የልዑል ኃይል ብሎ ወልድን ልዑል ብሎ አብን በማንሣት ሦስትነታቸውን አስረዳ፡፡ እመቤታችን ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋ ሊዋሐድ፤ አብ ለአጽንዖ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ የአምላክ እናት ለመሆን እንድትበቃ ለማድረግ ሦስቱም ተሳትፈዋል፡፡

/ በዮርዳኖስ «ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ. የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው» አለ፡፡/ማቴ.3.1617/፡፡

ወልድ በተጠማቂነት. አብ በደመና ሆኖ ልጄ ነው እያለ ሲመሰክር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል ሲወርድ በአንድ ጊዜ ታይተዋል፡፡ አንድ ገጽ የሚሉ ሰባልዮሳውያን ላይጠገኑ ተሰበሩ፡፡ አንድ ራሱ በተለያየ ስም ተጠራ እንዳይሉ በአንድ ጊዜ ሦስቱም በየራሳቸው መገለጫ ወልድ በተዋሐደው ሥጋ አብ በደመና መንፈስ ቅዱስ በርግብ ተገለጡ፡፡

/ በደብረ ታቦርም አብ በደመና ሆኖ «በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት» በማለት ተናግሮአል፡፡ /ማቴ.1.1719/፡፡

4.7. «
ዕፀ ደንጐላ ዘቆላ ወአኮ ዘደደክ ዘጸገይኪ ጽጌ በማዕከለ አይሁድ አስዋክ ተአምረ ድኂን ማርያም ዘልማድኪ ምሒክ መሐክኒ ለምእመንኪ እምፃዕረ ኩነኔ ድሩክ ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ፡፡»
እሾህ በሆኑ አይሁድ መካከል ያለሽ የደጋ ያይደለሸ የቆላ የሱፍ አበባ ማርያም በአንቺ መታመን በከንቱ እንዳይሆንብኝ እኔን ምእመንሽን /የታመንኩብሽን/ ከክፉ ኩነኔ አድኝኝ አንቺ ምሕረት ልማድሽ ነውና፡፡» በመኃልየ መጽሐፉ ሰሎሞን «ወከመ ጽጌ ደንጉላት በማዕከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኅቤየ በማዕከለ አዋልድ፤ በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ እንዲሁ አንቺ ነሽ» ይላል፡፡ /መኃ.2.2/፡፡

የቆላ ሱፍ ዙሪያውን እሾህ ቢከበውም ከማበብና ከማፍራት ወደኋላ አይልም፡፡ እመቤታችንም ብዙ ተአምር እያዩ በማያምኑና ሁልጊዜ ምልክትን በሚፈልጉ በክፉዎች አይሁድ መካከል መሆኗ በሃይማኖት ከማበብና ፍሬ ትሩፋት ከመሥራት አልከለከላትም፡፡ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግልም የሰሎሞን የትንቢት ቃል እመቤታችን በአይሁድ መካከል ፍሬ ክርስቶስን በማስገኘቷ መፈፀሙን የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህን ትንቢቱንና ፍጻሜውን ካስረዳ በኋላ «መሐክኒ ለምዕመንኪ እምፃዕረ ኩነኔ ድሩክ ተአምኖትየ ብኪ ኢይኩን በበክ» ይላል፡፡ ማለትም «በአንቺ እናትነትና ቃል ኪዳን የምታመን እኔን ከክፉ ፍርድ አድኝኝ፣ በአንቺ መታመኔና አንቺን ተስፋ ማድረጌ ለከንቱ አይደለምና በማለት ጸሎቱን ያቀርባል፡፡

እስከ አሁን በመጠኑ ለማየት እንደሞከርነው የማኅሌተ ጽጌ ድርሰት እጅግ በጣም በምሥጢርና በኃይለ ቃል የታጀበና ልዩ የሆነ ውበትና ጣዕም ያለው ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት የሚቻለው እንዳለ ግእዙን ማንበብ፣ መረዳት ሲቻል ነው፡፡ እንኳን በግጥም መልክ የተደረሰ ድርሰት ይቅርና ተራ ንባብና ድርሰት እንኳ ሲተረጉሙት መንፈሱን መልቀቁ የማይቀር ነው፡፡ በተለይም ይህ የቅኔ ዓይነት አካሄድ ያለው ድርሰት ሲተረጎም እየተፍረከረከ ትክክለኛ መልእክቱን ለማስተላለፍ ፍዝ ይሆናል፡፡

መልክዐ መልክዖችን መተርጎም ችግሩ ይህ ነው፡፡ አማርኛው ትርጉም መልእክቱን አልችል ይላል፡፡ ሆኖም የማኅሌተ ጽጌን ምንነት መጠነኛ ግንዛቤ ሊያስገኝ በሚችል መልኩ ለመግለጽ ተሞክሮአል፡፡

ይህም የእግዚአብሔርን ጸጋ ሁላችንም በመቅረብ እንድናውቅና ማኅሌተ ጽጌን በመጸለይና ማኅሌቱን በመቆም የእመቤታችንን በረከትና ረድኤት የል የክርስቶስን ምሕረት ለማግኘት ያበቃናል፡፡ ለዚህም እመአምላክ ድንግል ማርያም በረድኤቷና በበረከቷ አትለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት፣ መስከረም 2005 .ም.
 

No comments:

Post a Comment