Pages

Friday, October 3, 2014

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል ሦስት)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 23 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ከኹሉም በፊት አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ማወቅ ያለበት
 አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከኹሉም በፊት ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ቅዱስ ትውፊት፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት የአተረጓጐም ስልት፣ ስለ ዶግማ እና ስለ ቀኖና በጥቂቱም ቢኾን ማወቅ አለበት፡፡ አስቀድሞ ከእነዚኽ መሠረታውያን ትምህርቶች ጋር የተዋወቀ ክርስቲያን በትምህርተ ሃይማኖት (ዶግማ) ውስጥ ለሚኖረው ትምህርት መሠረትን ይይዛል፡፡ የእነዚኽን ጽንሰ ሐሳብ ያልተረዳ እንደኾነ ግን ጭራሽኑ የክርስትናን ጽንሰ ሐሳብም ሊስተው ይችላል፡፡ የብዙዎች ከቤተ ክርስቲያን መጥፋትም በአንድም ይኹን በሌላ መልኩ የእነዚኽ ኦርቶዶክሳዊ ጽንሰ ሐሳቦች የዕውቀት ማነስ ነው፡፡ ኹሉንም አንድ በአንድ የምንመለከታቸው ሲኾን ለዛሬ ከነገረ ቤተ ክርስቲያን እንዠምራለን፡፡

ሀ) ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ (Orthodox Teaching of Ecclessiology)

ትርጕም

 ነገረ ቤተ ክርስቲያን ስንል ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ምን እንደኾነ የምንማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን ትምህርቱ እጅግ ጥልቅና ራሱን የቻለ ሰፊ መጽሐፍ የሚወጣው ቢኾንም በዚኽ ክፍል ግን በነገረ ሃይማኖት ትምህርታችን ውስጥ አስቀድመን ልናውቀው ስለሚገባው ነገር ብቻ ለማንሣት እንሞክራለን፡፡
 ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ዓይነት ሰዋስዋዊና ዘይቤአዊ ትርጕም አለው /አባ ጐርጐርዮስ (ሊቀ ጳጳስ)፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣ ገጽ 12-17/፡፡
·        የመዠመሪያው የተወሰነ ቦታን ያመለክታል፡፡ ይኸውም የክርስቲያኖች ቤት፣ መኖሪያ ማለት ነው /1ኛ ቆሮ.11፡18/፡፡ “ቤተ ክርስቲያን እንሒድ” /መዝ.121፡1/ ሲባልም ይኽን ፍቺ የያዘ ነው፡፡ በመጻሕፍትም ቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቤት ተብላለች /ዘፍ.18፡27፣ መዝ.5፡7፣ መዝ.26፡4፣ መዝ.83፡4፣ መዝ.92፡5፣ ሉቃ.2፡49፣ 1ኛ ጢሞ.3፡15፣ ዕብ.10፡21/፡፡
·        ኹለተኛው ደግሞ ክርስቲያኖች ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ /1ኛ ቆሮ.3፡16፣ 1ኛ ቆሮ.6፡19/፡፡ ይኸውም በመንፈሳዊና በምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ፥ ርሱ አድሮባቸው የሚኖሩ፥ ከቅዱሱ ቅባት /1ኛ ዮሐ.2፡20/ እና ከሥጋ ወደሙ የተካፈሉ ምእመናንን ለማመልከት ነው፡፡
·        ሦስተኛው ትርጕሙ ደግሞ የክርስቲያኖችን ኅብረት (ጉባኤን) የሚያመለክት ነው /1ኛ ጴጥ.5፡13/፡፡ እኛም በዚኹ ክፍል ትኵረት የምናደርገው በዚኹ በሦስተኛው ትርጓሜ ላይ ነው፡፡

 እኛ በግእዝ ቤተ ክርስቲያን የምንለው ጽርዓውያን (ግሪካውያን) “ኤክሊሲያ” ይሉታል፡፡ ትርጓሜውም “ለአንድነትና ለአንድ ልዩ ዓላማ የተጠሩማለት ነው፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችኁ እግዚአብሔር የታመነ ነውብሎ ከገለጸው ጋር የተስማማ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር አንድነትና ልዩ (ሰማያዊ) ዓላማ በሃይማኖት መጥራት ነውና /1ኛ ቆሮ.19/፡፡
 ጽርዓውያን ኤክሊሲያ የሚለውን ቃል መዠመሪያ አንድን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይም አስተዳደራዊ ችግርን ለመፍታት ለተሰበሰቡ ሽማግሌዎች መጥሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በ284 ከክርስቶስ ልደት በፊት ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ የተረጐሙት ሰብዓ ሊቃናት ግን፥ “ካሃል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ኤክሊሲያ ብለው ተርጕሞዉታል፡፡ ትርጕሙም የእስራኤልን ጉባኤ የሚገልጽ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም የሚከተሉትን ኀይለ ቃላት እንመልከት፡፡ “ማኅበሩንም ኹሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው” /ዘሌ.8፡3/፡፡ እዚኽ ጋር ማኅበሩ ተብሎ የተገለጠው በምስጢር ስለዚኽች ጉባኤ ነው፡፡ በዚኽች ጉባኤም አሮን ሊቀ ካህን ኾኖ ተሾሟል /ዕብ.5፡4/፡፡ በኦሪት ዘዳግምም እግዚአብሔር ሙሴን ሲያናግረው፡- “ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፤ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ኹሉ እኔን መፍራት ይማሩ ዘንድ” ብሎታል /ዘዳ.4፡9/፡፡ በሌላ አንቀጽም፡- “ስብሰባ ተደርጐ በነበረበትም ቀን እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ኾኖ የነገራችኁ ቃል ኹሉ ተጽፎባቸው ነበር” ይላል /ዘዳ.9፡10/፡፡ በዚኽ አንቀጽ እግዚአብሔር በመካከላቸው ኾኖ ታላቅ ጉባኤ እንደ ነበራቸው ይናገራል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም እንዳስተማረው፥ ይኽ የአይሁድ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን አምሳል፣ መርገፍ፣ ወይም ጥላ ነበር / THE CATECHETICAL LECTURES OF S. CYRIL, ARCHBISHOP OF JERUSALEM, pp 335/፡፡ እንደ ሊቁ አስተምህሮ አብዛኞቹ አይሁዳውያን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ባለማመናቸው ምክንያት ከዚኹ ጉባኤ ቢወጡም ጉባኤው ግን አልተበታተነም፤ ሊበታተንም አይችልም፡፡ ይልቁንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “በዚኽም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን (ጉባኤዬን) እሠራለኹ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም” በማለት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ጉባኤ አጸናት እንጂ /ማቴ.16፡18/፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም በሰዎች አመለካከት የተለያየ ዓይነት ስያሜ (እንደ አይሁዳውያኑና አኹን እንደምንሰማው ብዙ ስም) ቢሰጠውም ይኽ የሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ የባሕርይ አምላክነቱን፣ የባሕርይና የአካል አንድነቱን ሊከፋፍለው ወይም ሊሸራርፈው አይችልም፡፡ “ቤተ ክርስቲያን የገሃንም ደጆች አይችሏትም” የሚለው ኃይለ ቃልም ይኽን ጥልቅ ነገረ ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳብን በውስጡ የቋጠረ ነው፡፡

  በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መሠረት ይኽቺ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) በቅድስት ሥላሴ ባለው እምነቷ ህልውናዋን የዠመረችው በዓለመ መላእክት ማለትም ሰው ከመፈጠሩ በፊት ነው፡፡ ከዚያም ከአቤል ዠምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ በነበረው የደጋግ ሰዎች አንድነት ቀጠለች፡፡ በመጨረሻ ግን ከላይ እንደገለጥነው በክርስቶስ ደም ጸናች፡፡ አኹንም ይኽ ጉባኤ ከሥላሴ ጋር ያለው ግንኙነት ዘወትር በእድገትና በምንድግና ያለ ሲኾን መጨረሻ ያለው አይደለም፤ እግዚአብሔርን መምሰል የሚደረስ አይደለምና፡፡  
 ይኽቺ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የክርስቶስ ብልት /ኤፌ.1፡23፣ ቈላስ.1፡18/፤ የክርስቶስ ሙሽሪት /ዮሐ.3፡28፣ ኤፌ.5፡25፣ ራዕ.19፡7/ ተብላ ተጠርታለች፡፡ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ሕያው ቤተ መቅደስ /ኤፌ.2፡21/፣ የእውነት ዓምድና መሠረት /1ኛ ጢሞ.3፡15/ ተብላ ተጠርታለች፡፡
 ቤተ ክርስቲያን አራት መገለጫዎች አሏት፡፡ እነዚኽ መገለጫዎቿ እንዲኹ የተጠራችባቸው ሳይኾኑ እጅግ ጥልቅ የኾነ የነገረ ሃይማኖትን ትምህርት የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ከኹሉም በፊት አንድ ኦርቶዶክሳዊ ይኽን ማወቅ አለበት የምንልበትም ስለዚኹ ነው፡፡ ይኽም በጸሎተ ሃይማኖታችን ኹልጊዜ የምንለው ነው “… ከኹሉ በላይ (ኵላዊት) በምትኾን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፡፡”
v ቤተ ክርስቲያን አንዲት ነች፡፡
 እግዚአብሔር አንድ ነው፤ የክርስቶስ ማዳን አንድ ነው፤ ተስፋ የምናደርገው መንግሥተ ሰማያት አንድ ነው፤ የምንካፈለው ማዕድ (ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ) አንድ ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የተገለጠው እውነት ከነማብራሪያው አንድ ነው፡፡ ይኽን የምታስተምር ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ነች፡፡ የክርስቶስ አካል ነችና አንድ ናት፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልምና ቤተ ክርስቲያን አንዲት እንጂ ብዙ አይደለችም፡፡ ይኽቺ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተአምኖዋ በአንድ እግዚአብሔር ስለኾነ ኹለትነት፣ አራትነት፣ በአጭሩ መለያየት አይስማማትም፡፡ ሰዎች ወይም መላዕክት ከርሷ ውጪ ወጥተው በክሕደት በኀጢአት ሊሔዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሌላ ቤተ ክርስቲያን ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ እንመሥርት ቢሉም የመሠረቱት ስብስብ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ አይችልም፡፡ እነዚኽ ሰዎች ወይም መላዕክት በተለያየ መንገድ ከአንዲቷ ማኅበር ቢወጡም ቤተ ክርስቲያን ተከፋፈለች አይባልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አትከፈልም፤ አንዱ እንግዚአብሔር አይከፈልምና፡፡ አንዳንድ ወገኖች ለራሳቸው በየሰፈሩ “ቤተ ክርስቲያን” ብለው ይመሠርታሉ፡፡ ነገር ግን ይኽ ስብስባቸው ፈጽሞ ቤተ ክርስቲያን ሊኾን አይችልም፡፡ ለምን? ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናትና፡፡
 በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የቤተ ክርስቲያን አንድነት፥ ክርስቲያኖች በእውነት አምነው በፍቅር ተመላልሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚፈጥሩት አንድነት የሚመዘን ነው፡፡ ይኽ አንድነት ሰዎች በጠረጴዛ ዙርያ ተሰብስበው ወይም በፍርድ ቤት ትእዛዝ ሊመሠርቱት አይችሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሠርታት ደግሞም የመሠረታት እግዚአብሔርና እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የቤተ ክርስቲያን አባል ነው ወይም ክርስቲያን ነው የሚባለውም በዚኽች ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የአንድነታችን መሠረቱም በሥጋ ወደሙ ያገኘነው የክርስቶስ አካልነታችን ነው፤ ጌታ እንዲኽ እንዳለ፡- “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በርሱ እኖራለኹ” /ዮሐ.6፡56/፡፡
 ክርስቲያኖች በዚኽች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስንኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት እያደገ እየጠበቀ ይሔዳል፡፡ ይኽ አንድነትም በጊዜ ሒደት፣ ወይም በተለያየ ቦታ በመኾን የሚቋረጥ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ቅዱሳን መላዕክትን እንዲኹም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብጹዓን፣ በገነት በአጸደ ሥጋና በአጸደ ነፍስ ያሉትን ምእመናን ኹሉ የምትይዝ አንዲት ኅብረት ናት ማለታችንም ስለዚኹ ነው/ዕብ.1222-24/፡፡ በአጸደ ነፍስ ያሉት ምእመናን በንስሐ የተመላለሱ፣ ሩጫቸውን የጨረሱና ድል ያደረጉ ሲኾኑ፥ በአጸደ ሥጋ ያለን ደግሞ ሩጫችንን ገና ያልጨረስንና በተጋድሎ ውስጥ ያለን ነን፡፡ ሐዋርያው እንዲኽ እንዳለ፡- “እንዲኹ ብዙዎች ስንኾን በክርስቶስ አንድ አካል ነን” /ሮሜ.12፡5/፡፡
 ይኽ ትምህርት የነገረ ሃይማኖት መሠረት ነው የምንልበት ምክንያትም ኹለት ምሳሌዎችን በማንሣት እናስረዳ፡፡
1.     በካቶሊካውያን ዘንድ አንድ ሰው የፖፑን እንደራሴነት ካልተቀበለ የካቶሊክ ቤተ እምነት አባል አይደለም፡፡ ይኽም ማለት የእነርሱ አንድነት በሰው የተመሠረተ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ግን ቅዱሳን መላዕክት እንዲኹም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብጹዓን፣ በገነት በአጸደ ሥጋና በአጸደ ነፍስ ያለን ምእመናን አንድ የምንኾነው በክርስቶስ ኢየሱስ አካልነት (ብልትነት) ነው፡፡ ይኽም በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የምናገኘው ጸጋ ነው፡፡
2.    በፕሮቴስታንቱ ዓለም ያለውን ስንመለከት ደግሞ በአጸደ ሥጋ ያሉትና በአጸደ ነፍስ ያሉት ክርስቲያኖች የተለያዩ ናቸው፤ ርስ በርሳቸው አይተዋወቁም፡፡ በሌላ አገላለጥ እንደነርሱ አባባል “ቤተ ክርስቲያን ማለት የሚታዩት አባላት ብቻ ያሏት ተቋም ናት፡፡” የቅዱሳንን ምልጃ የማይቀበሉትም ስለዚኹ ነው፡፡ ይኽም ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ ከነገረን /ዕብ.12፡22-24/ የእውነት መሠረት የተለየ ትምህርት ነው፡፡ ዳግመኛም ይኽ የፕሮቴስታንቶቹ አስተምህሮ (አይቻልም እንጂ)፥ ስሙ ይክበር ይመስገንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ያደረገንን መለያየት ነው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ እያንዳንዱ ሰው ቤተ ክርስቲያን መባሉን አግኖ የጕባኤውን አንድነት የሚበታትን ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ግን ይኽ ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ከሚታየው የቤተ ክርስቲያን አካልም የማይታየው ይበልጣል፡፡
 ስለዚኽ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለኹ” እንዳለ /1ኛ ጢሞ.3፡15/፥ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከምንም በፊት ይኽን ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ማወቅና መረዳት አለበት፡፡ 
v ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡

 መሥራቿ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለኾነ ቤተ ክርስቲያንም ቅድስት ናት፡፡ የቤተ ክርስቲያን የቅድስና ምንጭ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ማለት የተለየ ማለት እንደኾነ፥ ቤተ ክርስቲያንም ከዓለም ተለይታ የእግዚአብሔርን ማዳን የምትመሰክር ናትና ቅድስት ናት፡፡ በሌላ አገባብ ደግሞ “እስመ ኢይትረከብ ነኪር በማዕከሌሃ - ባዕድ በመካከሏ አይገኝምና” እንዲል /መጽሐፈ ቅዳሴ 2፡6/ በሃይማኖት በምግባር የጸኑ ቅዱሳን መሰብሰቢያ ናትና (መኾንም ይገባታልና) ቅድስት ናት፡፡
 እግዚአብሔር እጅግ ቸር ከመኾኑ የተነሣ፥ ሩጫችንን ያልጨረስን ክርስቲያኖች ኃጢአት ብንሠራ እንኳን በንስሐ እየተመላለስን ከምሥጢራቱ እንድንካፈል በማድረግ የድኅነት መንገዱን አስፍቶልናል፡፡ ከበደላችን ተመልሰን ከምሥጢራቱ ስንካፈልም ከእግዚአብሔር ቅድስና እንሳተፋለን፡፡ ለዚኽም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “የርሱን በጐነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሡ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችኁ” ያለን /1ኛ ጴጥ.2፡9/፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ቅዱሳን ልትኾኑ ለተጠራችኁ” ያለንም ስለዚኹ ነው /ሮሜ.1፡7/፡፡ ስለዚኽ ከዚኽ ቅድስና የሚያርቀን ክሕደትና ኀጢአት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡


v ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት፡፡
  በብዙዎቻችን ልቡና የሚመጣው ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ሲባል “በኹሉም ቦታ፣ በኹሉም ሥፍራ፣ ለኹሉም ሰው ያለች” የሚል ትርጓሜው ነው፡፡ ርግጥ ነው ቤተ ክርስቲያን በኹሉም ቦታ፣ በኹሉም ሥፍራ፣ ለኹሉም ሰው አለች፡፡ ነገር ግን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ሲባል ከዚኹ ያለፈ (የላቀ) ትርጓሜ አለው፡፡ ኵላዊት የሚለው ቃል ከብዛት ይልቅ ርቱዕነትን፣ እውነተኛነትን፥ ፍጹምነትን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ስለዚኽ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ስንል ፍጽምት ናት፤ ኹሉንም የምትይዝ ናት፤ ምንም የሚጐድላት ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡
 ቤተ ክርስቲያን እንደ አኹኑ በዓለም ኹሉ ከመስፋፋቷ በፊት እንኳን ኵላዊት ትባል ነበር፡፡ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን፣ እንዲኹም የጥንቶቹ የአንጾክያ፣ የኤፌሶን፣ የቆሮንቶስ፣ የሮም ከተሞች አብያተ ክርስቲያናት ኵላዊት ይባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት መባሏ ከቦታ ወይም ከጊዜ አንጻር ሳይኾን ምንም የሚጐድለው የሌለው የክርስቶስ በመኾኗ ነው፡፡ ዳግመኛም ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት የምትባለው ከእግዚአብሔር የተገኘች የሐዋርያት ትምህርታቸው፣ የክህነት ውርሳቸው (ቅብብሎሽ) ስላላት ነው፡፡ ፍጽምት ናት፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ልውረስ ብሎ ወደ ርሷ ለተጠጋ ርስቱን መንግሥቱን ያለ እንከን ታሰጧለች፡፡  
 ይኽ ኵላዊት (ካቶሊክ፣ Universal) የሚለው አገላለጽ በምዕራባውያን (በካቶሊካውያን) አስተሳሰብ የተለየ ትርጕም አለው፡፡ ይኸውም ፖፑን ፍጹም የማይሳሳት ለማድረግ የተዘረጋ መዋቅራዊ (Structural) አካሔድ ነው፡፡ ይኽ ግን ፈጽሞ ስሕተት ነው፡፡ ክርስትና በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት (በተለይም በቅዱስ ቁርባን) እንጂ በፖፕ አንድ መኾን አይደለምና፡፡
  ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ወደ ስምርናስ በላከው መልዕክቱ እንደተናገረው፥ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት (ፍጽምት፣ ርትዕት፥ ኹሉንም የምትይዝ) የምትባለው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ እስከ ፈተተች ድረስ ብቻ ነው (ኵላዊት የሚለውን ቃል ለቤተ ክርስቲያን መገለጫነት የተጠቀመ የመዠመሪያው አባትም ይኸው አባት ነው)፡፡ በዚኹ ቅዱስ ምስጢር አማካኝነት በየትኛውም ስፍራ ያለን ክርስቲያኖች (በግብጽም፣ ኢትዮጵያም፣ በሰማይም፣…) አንድ ወደ መኾን፣ ወደ ፍጽምና፣ ወደ እውነት እንመጣለን፡፡ በመኾኑም ያለዚኹ ምስጢር ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት አትባልም /letter to Smyrnaens 8:2/፡፡ በዚኹ የሐዋርያነ አበው ትምህርት መሠረት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን “አማናዊ አይደለም፤ አምሳል ነው” የሚሉ ሰዎች ስብስባቸው ቤተ ክርስቲያን እንዳልኾነ እንረዳለን፡፡
v ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡
ይኽ ሐዋርያዊት የሚለው ቃል በውስጡ ሦስት መሠረታዊ መልዕክታትን የያዘ ነው፡፡
1.     አንደኛው ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያት እምነት መኾኗን ያስረዳል፡፡ በዚኽም ከመናፍቃንና ከአረማውያን እምነት የተለየች መኾኗን መግለጽ ነው፡፡  
2.    ኹለተኛው ሐዋርያዊ ውርርስ (ቅብብሎሽ) እንዳላት የሚያስረዳ ነው፡፡ ይኽም ማለት አኹን ያለው እውነት ወደኋላ በሔድን ቁጥር ሳይዛነፍ፣ ሳይሸራረፍ፣ በመኻልም የሚቋረጥ መስመር ሳይኖረው ከሐዋርያት ጋር እንደሚያደርሰን ያሳያል፡፡ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. ይኽን እምነት በጃንደረባው /ሐዋ.8፡26-28/፥ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ደግሞ በአኀት አብያተ ክርስቲያናት በኵል ተቀብሏለች፡፡
3.    ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ተልዕኮዋን መናገር ነው፡፡ ይኽም ማለት ቤተ ክርስቲያን “ሒዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” እንዲል /ማቴ.28፡19/ ሰውን ኹሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለማፍለስ፣ ለመማረክ የተላከች ነች ማለት ነው፡፡
 አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ዓለም የመጣበት አንዱ ዓላማ ሰዎችን ወደራሱ መንግሥት ለማፍለስ ነው፡፡ ይኽን ግብር ስለፈጸመም የሃይማኖታችን ሐዋርያ ተብሏል /ዕብ.3፡1/፡፡
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ተልኮ ወደዚኽ ዓለም እንደመጣ ኹሉ፥ ርሱም ሐዋርያትን ወደ ዓለም ልኳቸዋል፡፡ ሐዋርያው “አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለኁ አላቸው፡፡ ይኽንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” ያለንም ስለዚኹ ነው /ዮሐ.20፡21-22/፡፡ ሐዋርያት ወደ ዓለም ኹሉ በመሔድም የቤተ ክርስቲያንን መሠረት አስቀምጠዋል፡፡
  ዳግመኛም በዚኽ ምድራዊ አጥብያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰማያት ላለው የእግዚአብሔር መንግሥት በቃልና በገቢር ምስክር ትኾን ዘንድ ስለተላከች ሐዋርያዊት ትባላለች፡፡
 …ተመስጦ…
ቸር፣ ቅዱስ እና ገናናው እግዚአብሔር ሆይ! ቤተ ክርስቲያንን ገና በዓለመ መላዕክትን የመሠረትካት አንተ ነኽ፡፡ ይኽቺ ጕባኤ፥ ሳጥናኤል ከርሷ ተለይቶ ስለወጣ አልተበተነችም፡፡ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ሰዎች ከርሷ ቢወጡም አልተከፋፈለችም፡፡ አንተ ኹል ጊዜ አንተ ነኽና ቤተ ክርስቲያንም ኹል ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የገሃነም ደጆች አይችሏትም፡፡
 ቅዱስ አባት ሆይ! ይልቁንም እኛው ራሳችን በገዛ ክሕደታችንና ኀጢአታችን ከዚኽ አንዲት፣ ቅድስት፣ ኵላዊትና ሐዋርያዊት ጕባኤ እንዳንለይ ትጠብቀን ዘንድ ፈቃድኽ ይኹን፡፡ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት “አቤቱ በታላቁ ጕባኤ ውስጥ እገዛልሃለኹ፤ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለኹ” /መዝ.35፡18/፤ “ሃሌ ሉያ! ለእግዚአብሔር አዲሱን ቅኔ ተቀኙለት፤ ምስጋናው በቅዱሳኑ ጕባኤ ነው” /መዝ.149፡1/ እንዳለ በዚኽች የእውነት ዓምድ፣ ሕያዊት ቤተ መቅደስ እንኖር ዘንድ ፈቃድኅ ይኹንልን /መዝ.27፡4/፡፡
 ቸር ሰው ወዳጅ ሆይ! ክቡር ዳዊት “የክፉዎችን ማኅበር ጠላኁ” እንዳለ /መዝ.26፡5/ በጠረጴዛ ዙርያ ሰዎች ተሰብስበው ከመሠረቱትና፥ ሕይወት አንተ በሌለኽበት ጉባኤ ከመገኘት ጠብቀን፡፡ ዘወትር በኀጢአት ብንወድቅም በቸርነትኅ እያነሣኸን ቅድስናኅን ታሳትፈን ዘንድ ፈቃድኅ ይኹን፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን!!!  


3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሠማልን

    ReplyDelete
  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete