Pages

Thursday, December 4, 2014

ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ (ደረጃ ሁለት)



በዲ/ን ሳምሶን ወርቁ
(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ኅዳር 25 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ከዓለማዊ መሻት መለየት
 የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዴት ሰነበታችሁ? ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ በሚለው ጽሁፍ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ  በያዕቆብ ምናባዊ መሰላል ደረጃ ለዓለም ጀርባ መስጠት የመጀመሪያ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ በዚህ ያዕቆብ በራዕይ በተመለከተው ምናባዊ መሰላል ላይ እግራችን መውጣት ጀምሯል፡፡ አሁን ለዓለም ጀርባ ስለሰጠን አይኖቻቸን ወደ እግዚአብሔር የሚመለከቱ ጆሮዎቻችን ድምጹን ለመስማት የሚቀኑ መሆን ይጀምራሉ፡፡ ምንያቱም ለዓለም ጀርባ ስለሰጠን ኃጢአትን መጥላት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅሩንና ቸርነቱን መረዳት ጀምረናል፡፡ አሁን በእውነት እኛ ወደ እግዚአብሔር በማደርገው ጉዞ እንደርስ ይሆን የሚል ስጋት አይገባንም ምክንያቱም እኛ እስከፈቀድን ድረስ ከድካማችን ሊያሳርፈን ከወደቅንበት የሚያነሳን አምላክ ሊረዳን እንደቀረበ አውቀን ተረድተናልና፡፡ አሁን ጥያቄው እንዴት በመንገዳችን ጸንተን እንጓዝ የሚል ነው?

በመንገዳችን ለመጽናት ነፍሳችን ወደምትናፍቀው ለመድረስ “ከዓለማዊ መሻት” መለየት ይገባል፡፡ የዘወትር በእኛ ውስጥ ያለው መሻት በመንገዳችን ላይ በአዎንታዊ ወይም በአሉታዊ ጎኑ ተጽእኖ አለው፡፡ የብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ህይወት ወደ ተሻለ መንፈሳዊ ደረጃ ያለመድረስ ምክንያቱ መንገዱ አለመጀምር አይደለም፡፡ ነገር ግን እለት እለት በልቦናቸው የሚመላለሰው የልቦናቸው መሻት አንድ ጊዜ ምድራዊ አንድ ጊዜ ሰማያዊ ሆኖ መደበላለቅ ነው፡፡ ስለዚህ ቆርጠው ወስነው ከዓለማዊ መሻት መለየት ይከብዳቸዋል፡፡                
 ቅዱስ ዮሐንስ ዘላዕላይ ሁለተኛውን የመንፈሳዊ ሕይወት መሠላል ደረጃ ሲገልጽ “በእውነት  እግዚአብሔርን የምንውድና የመንግስቱን መምጣት የምንጠባበቅ የምንናፍቅ ከሆነ በእውነት በኃጢአታችን የምናዝንና ከፊታችን የሚጠብቀንን ሰማያዊ ፍርድ የምናስብ ከሆነ፤ በእውነት ዘለዓለማዊ ሞትን የምንፈራ ከሆነ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ የምናደርገውን ጉዞ ከሚያዘገዩንም ሆነ ከሚያደናቅፉን ነገሮች እንራቅ፡፡ ከእግዚብሔር በፊት ካስቀደምናቸው ሀብት ንብረት ምድራዊ ክብር ሌላው ቀርቶ ከገዛ ዘመዶቻችን ከእናት ከአባቶቻችን እግዚአብሔርን እናስቀድም፡፡ ይህንን ስናደርግ ለማንኛውም ዓለማዊ ነገር ጉጉትም ሆነ መሻት አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ዕለት ዕለት ሀሳባችን አንድ ብቻ ነው፤ ነገረ እግዚአብሔር ብቻ፡፡ ሌላው ቀርቶ የገዛ ሥጋችን ጉዳይ እንኳ አያስጨንቀንም፡፡ ይልቅስ ሁሉን ትተን ወደ አምላካችን  እንመለከታለን፡፡
ይህን ከዓለማዊ  መሻት መለየታችንን መንግሥተ ሰማያትን መሻታችንን ቅዱስ ዮሐንስ “ምናኔ” ማለትም መናቅ፣ መተው ይለዋል፡፡ ምናኔ ማለትም ዓለማዊውን ነገር ሁሉ መናቅ፣ መተው፣ ለሁሉ ክርስቲያን የሚገባ አስፈላጊ የክርስቲያናዊ ህይወት መሠረት ነው፡፡ ሁሉ ክርስቲያን ሊመንን ይገባል፡፡ ነገር ግን ምናኔ ለገዳማውያንና ምናኔ በዓለም ለሚኖር ክርስቲያን ዘይቤው ይለያያል፡፡ ምናኔ ለገዳማውያን ከዓለማዊ መሻት መለየት ብቻ ሳይሆን በአካልም ጭምር ከሰው ርቆ ከቤተሰብ ተለይቶ ሀብት ንብረትን ሁሉን ስለ መንግስተ ሰማያት ሲል ንቆ መኖር ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ በዓለም ቤት ሰርቶ ቤተሰብ መስርቶ ለሚኖር ክርስቲያን ምናኔ ከሰው ርቆ ተለይቶ ባይኖርም በዓለም ሳሉ ከዓለማዊ መሻት መለየት ነው፡፡ ይህም ከሀብት ከንብረት ከባል ከሚስት ከአባት በእናት በፊት እግዚአብሔርን ማስቀደም መንግስቱን መሻት ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ሁኔታ ሁለቱም እያነፃጸሩ ይሄ ይከብዳል ይሄ ይቀላል የሚሉ ሰዎች ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ የመቅለል የመክበድ ሳይሆን ከዓለማዊ መሻት መለየት ነው፡፡ ሁለቱም ለተሰጠውና ወዶ ከተቀበለው መጽደቂያ መንግስተ ሰማያትን መውረሻ መንገዶች ናቸው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ “ሰው ምናኔን ገንዘብ ለማድረግ ከሦስት ነገሮች መለየት ይገባዋል” ይላል፡፡ እነዚህም፡-
1.     ከዓለማዊ ሀሳብ
2.    ከራስ ወዳድነት
3.    ከከንቱ ውዳሴ
ተለይቶ በመኖር ምናኔን ገንዘብ ያደርጋል፡፡ ከዓለማዊ ሀሳቦች ሀብት ሥልጣን ምድራዊ ዕውቀት በህሊናችን የሚመላለሱ ከሆነ ዓለምን ለመናቅ እንቸገራለን፡፡ ዘወትር የዓለምን አላፊ ጠፊ ነገርን እየተውን በክርስትና ህይወት ስንመላለስ አንዳንዴ ልባችን ሊተው ያልፈለገው ያልፈቀደው ከንቱ ነገር ካለ ልንመረምር ያስፈልጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዓለምን እንዳንንቅ ራስ ወዳድነታችን ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ ለምሳሌ የገዛ ንብረታችንን ሰዎች በማወቅ ባለማወቅ ቢያጠፉብን ይቅር ከማለት ይልቅ በነገሩ እኛ አብዝተን ከተናደድን ያልተረዳነው ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይህን ስንል እኛ ለንብረታችን የሰጠነው ቦታ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በዋነኝነት ከእግዚአብሔር የተሰጠን መሆኑን ዘንግተን የኛ ነው ብለን በማሰባችን ነው፡፡ ጻድቁ የእግዚአብሔር ሰው ኢዮብ ሀብቱ ንብረቱ ልጆቹ በጠፉበት ጊዜ “እግዚብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ” ብሎ እግዚአብሔርን አመስገነ እንጂ የኔ ልጆች የኔ ሀብት አላለም፡፡ ባል በሚስት፤ ሚስት በባል የሚቀናኑት አልፎ ተርፎ እስከ ፍቺ የሚደርሱት ባሌን የሰጠኝ ሚስቴን የሰጠኝ እግዚአብሔር ነው አለማለታቸው ነው፡፡ ስለዚህ የኔ ባል የኔ ሚስት ከሚለው ሀሳብ ተለይተን ባል የሚሰጠ ሚስት የሚሰጠ እግዚአብሔር ነው ብሎ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ሰው ሀብት ኖሮት ለደሀ ቀርቶ ለራሱ የሚያሰስተው ሀብቱን ከእግዚአብሔር በፊት ስላስቀደመና የሰጠውም እግዚአብሔር መሆኑን ስላልተገነዘበ ነው፡፡ ስለዚህ የኔ ከሚለው ሀብት ሊለይና ሀብት የሰጠኝ እግዚአብሔር ማለት ይገባዋል፡፡  ሌላው ቀርቶ ሰው ስጋዊ ሞትን የሚፈራው ሕይወቱን የኔ ብሎ ሕይወቱን  የሰጠውን ፈጣሪውን ስለሚረሳ ነው፡፡  ስለዚህ ከአላስፈላጊ አብዝቶ በሥጋ ከመኖር ፍላጎት መለየት ይገባዋል፡፡ በአጠቃላይ ከየትኛውም ለኛ ጊዜያዊ ደስታን ከሚሰጠን እኛ አብዝተን ከምንሻው ነገር መለየት ይገባናል፡፡
ሌላው ምናኔን ገንዘብ ለማድረግ ከውዳሴ ከንቱ ልንለይ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ “በአለም ብዙ በጎ ነገሮች በከንቱ ወዳሴ ላይ ተተክለው በምስጋና ማዳበሪያነት አድገው በታይታ አብበው ተመልከትሁ” ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የፈሪሳውያን ጠባይ ነው፡፡ እነርሱ በሚፈጽሙት ህግ በሚሰሩት በጎ ስራ ሁሉ ለከንቱ ውዳሴ ለታይታ ነበርና ከዓለማዊ መሻት መለየት አልቻሉም፡፡ ቅዱስ መርቆሪዎስ በአንድ ወቅት ወደ ገዳሙ ሊሳለም የመጣ አንድ ሰው አንድ ጥያቄ ጠየቀው፡፡ “ሰው እንዴት ከዓለማዊ መሻት ሊለይ ይችላል?” ሲል፡፡ ቅዱስ መርቆሪዎስ “ሂደህ በመቃብር ያሉትን ሰዎች ስደባቸው” አለው፡፡ እርሱም ሄዶ ሰደባቸውና ዳግመኛ ወደ ቅዱስ መርቆሪዎስ መጣ፡፡ “አሁን ደግሞ አመስግናቸው” አለው፡፡ ሂዶ አመስግኗቸው ተመልሶ መጣ፡፡ ቅዱስ መርቆሪዎስ ያን ሰው “ስትሰድባቸው ስታመሰግናቸው ምን አሉህ?” አለው፡፡ እርሱም “ምንም አላሉኝም” አለው፡፡ “እንግዲህ ከዓለማዊ መሻት ለመለየት እነርሱ ያደረጉትን አድርግ ያን ጊዜ ትድናለህ” አለው፡፡ “ለሰዎች ርግማንም ሆነ ምርቃት የሞትህ ከሆንህ ያን ጊዜ ከዓለማዊ መሻት ትወጣለህ” አለው፡፡ ይህ ምክር ከዓለማዊ መሻት ነፃ የሚያወጣ ጠቃሚ ምክር ነው፡፡ ከዓለማዊ መሻት ተለይቶ ከእግዚአብሔር ሀሳብ ጋር አንድ መሆን ምን ያህም ታላቅ ነገር ነው፡፡ እንደሎጥ ከዓለማዊ ግብር መለየት የቱን ያህል ደስ ያሰኛል እንደሚስቱ ግን ወደኋላ እንዳንመለከት፡፡  እንግዲህ ከዓለማዊ ሀሳብ ከራስ ወዳድነትና ከውዳሴ ከንቱ እንለይ፡፡ ይህ ደረጃ ሁለት ነው፤ ለደረጃ ሶስትም የልቡናችንን እግር እናንሳ፡፡
ይቆየን!!!      

No comments:

Post a Comment